ቆይታ ከሚሚ ስብሃቱ ጋር – ፕሬዚደንት አብዲ መሃመድ ኡመር  

Written by on December 6, 2017

(ከቃለ ምልልሱ የተወሰዱ አናቅጽ – የሙሉውን ቃለ ምልልስ የድምፅ ፋይል ከታች ያገኛሉ)

**********

አወዳይ ላይ የተፈጠረው ከእኛ ቀድሞ በፌስቡክ ሲሰማ ጅግጅጋ የሚኖር የኦሮሞ ህዝብ በመፍራት ለመውጣት ተነሳ፡፡ አወዳይ ላይ ድርጊቱን የፈፀሙት የኦሮሞን ህዝብ እንደማይወክሉ የሚያሳየው ድርጊቱን ፈፅመው በፌስቡክ የለቀቁት ጅግጅጋ ላይ ብቀላ እንዲፈፀም በመፈለጋቸው መሆኑ ነው፡፡

በክልሉ ነዋሪ ከሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ከቀብሪደሃር አልተፈናቀሉም፣ ከጎዴ አልተፈናቀሉም፤ በክልሉ ባሉት 93 ወረዳዎችና 13 ዞኖችም ይኖራሉ፤ የተፈናቀሉት ከጅግጅጋ አካባቢ ነው፡፡

በግጭቱ ምክንያት ከክልላችን የተፈናቀሉትን በፌዴራሉ መንግስትም በክልሎችም እንደተስማማነው ባሉበት ሄደንና ለምነን እንደምንመልስና ትተውት የሄዱትን እቃቸውና ቤታቸውን ሳይነካ እንዳለ እንደሚረከቡ የኢትዮጲያ ህዝብ እንዲያውቅ እንፈልጋለን፡፡ እስከአሁን መጥተው ንብረታቸውን ያልወሰዱትን እንደምናስረክባቸው የተጎዱትን ድሆችም እንደ አቅማችን እንደምናግዝ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

**********

ከአቶ ለማ ጋር ግንኙነት የላችሁም ወይ ለሚለው ጥያቄ

ግንኙነት አለን ተደዋውለንም በችግሩ ዙርያ እንወያያለን፣ ለምሳሌ ከትላንት ወድያ በስልክ ተነጋግረናል ባለፈው ሳምንት ሰኞም በስብሰባ ተገናኝተናል፡፡ እሱም እኔም ህዝብ ነው እየመራን ያለነው፣ ወንድማማች የሆነ ህዝብ፤ ህዝብ እየመራን ልንኮራረፍ አንችልም፡፡

ከበፊት ጀምሮ ኢህአዴግ ለአጋር ድርጅቶች (በእድገት ወደ ኋላ ለቀሩ ክልሎች) እገዛ ይሰጣል የሚል አቅጣጫ አለው፡፡ ህወሓት ለአብዴፓ (አፋር) ነው እገዛ የሚሰጠው፣ ብአዴን ለቤንሻንጉል፣ ደኢህዴን ለጋምቤላ፣ ኦህዴድ ደግሞ ለኢሶዴፓ እገዛ ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ ስለዚህ ግንኙነታችን የግድ ነው የድርጅቱን እገዛም እንፈልጋለን፡፡ ይሄ ደግሞ የኢህአዴግ አቅጣጫ ነው፡፡

**********

ህገወጥ ዶላር የሚጓዘው ከአዲስ አበባ ነው ወደ ውጫሌ ነው እንጂ ከዚህ ወደ አዲስ አበባ አይደለም፡፡ ሰው ኤል.ሲ. ለመክፈት ዶላር ባንክ ሲያስገባ ከየት እንደተገኘ ይጠየቃል፤ ውጫሌ ላይ ሲሆን ግ ከውጭ እንደገባ ነው የሚሆነው፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ አዲስ ባንክ ሲከፈት የመጀመርያ ቅርንጫፉ አዲስ አበባ ላይ ሲሆን ሁለተኛው የሚከፈተው ውጫሌ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጲያን ዶላር ከውጭ የገባ በሚል መሰብሰብ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ዶላር ከመሃል አገር ነው እንጂ የሚመጣው ከዚህ አይሄድም፡፡ ይሄ መቆም አለበት፤ ለዚህም የበኩላችንን እያደረግን ነው፡፡ በየቀኑ ነው የምንይዘው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ኦሮሚያ ከተያዘው ግማሽ ሚልየን ዶላር በኋላ በሳምንቱ 1.5 ሚልየን ዶላር ውጫሌ ላይ ተይዟል፡፡ ሙሉ በሙሉ ለማስቆም የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል፡፡

በነገራችን ላይ ሶማሊ ክልል ከአስር አመታት በፊት አንድ ህጋዊ የመኪና ታርጋ አልነበረም፣ የሶማልያ ሽልንግ ነበር ገበያ ላይ የሚሰራው፡፡ ዛሬ መሃል ሃገር እንዳለ ክልል ሁሉም ህጋዊ ሆኖ እያለ ነው ይሄ ነገር እየተፈጠረ ያለው፡፡

**********

ጥፋተኞችን በመያዝ ላይ ክልሉ ዳተኝነት አሳይቷል ወይ ለሚለው ጥያቄ

አወዳይ ላይ ለተፈፀመው ምንድነው ምክንያት ሲባል የኦሮሚያ ክልል ጉርሱም ላይ ድሮ አስተዳደር የነበረ ሰው ተገድሏል የገደለውም ሶማሊ ነው ብሎ በፌዴራል መንግስትም በጠ/ሚኒስትርም በፀጥታ ም/ቤትም ያ ሰው መያዝ አለበት ተብሎ መጀመርያ የያዘው የሶማሊ ክልል ነው፡፡ የሶማሊ ክልል ፖሊስ ዋና ችግር ነው ይያዝ ተብሎ አነጋጋሪ የነበረውን ሰው ይዞ ለፌዴራል መንግስት አስረክቧል፣ ይሄን ባለፈው ነገሪ ሌንጮ በመግለጫው አልተናገረውም፡፡

እኛ ወንጀለኛን ሶማሊ ስለሆነ ብለን የምንከላከልለት አይነት ሰወች አይደለንም፤ የክልሉም ባህሪ አይደለም፡፡ ከአመታት በፊት የፀረ ሰላም ሃይሎች መፈንጫ የነበረና ሰው ከወረዳ ወደ ወረዳ በሰላም መጓዝ የማይችልበት የነበረውን እና ለሰላሙ የኢትዮጲያ ህዝብ ሁሉ መስዋእትነት የከፈለበት ክልል ነው፡፡ ወንጀለኛ የነበሩት ከእኛ አልፎ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ሊያፈነዱ የሞከሩ የኛው ዜጋ የኛው ጎሳ ተወላጅ አመራሮች የነበሩ ነበሩ እንጂ ከሌላ ብሄረሰብ አልነበሩም፡፡ የኛው የሆኑትን የተለየናቸው በአላማ ስለነበር የገቡበት ገብተን ይዘን ዛሬ በዝዋይና በሌላ ማረሚያ ቤቶች ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ክልሉ ወንጀለኛ አሳልፎ ላለመስጠት ይከራከራል የሚለው እውነት እንዳልሆነ ከዚህ በፊት የሆነውን በማየት መረዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡

**********

ኢትዮጲያ አሁን ገና ዲሞክራሲን እየተለማመደች ነው፤ በልምምዷ ወቅት ደግሞ የተጠራቀሙ የሁለት ሺህ አመት ችግሮቻችን ይወጣሉ ማለት ነው፡፡ ለግዜው ልዩነቶቻችን ጎልተው ይወጣሉ፤ ምክንያቱም ትላንት የተከለከለ ማንነቱን የሚፈቅድ ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ ያኔ ስላልተጠቀመ ኢትዮጲያን እንደ መጥፎ ያይ የነበረው የሶማሊ ህዝብ ዛሬ ስለተጠቀመ በሶማሊነቱ እንዲኮራ ስለተደረገ በየቦታው ባንዲራውን እንደ ልብስ ለብሶ የአገራችንን፣ የፌዴራሊዝሙን እና የህገ መንግስታችንን ጠላቶች የሚፋለመው ሶማሊ ሆኗል፡፡ we are proud to be Ethiopian.

እና የፌዴራል ስርአቱ ችግር ነው የሚሉት አይገርመኝም፤ የነሱ አስተሳሰብ እይታ ነው፡፡ እኔ ከፌዴራል ስርአታችን ውጪ አማራጭ የለንም ነው የምለው፡፡

**********

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ለማ በተመሳሳይ አጭር ቃለምልልስ እንዲሰጡን ጥያቄ አቅርበን እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡ መልስ እንዳገኘን ለአድማጮቻችን ይዘን እንቀርባለን፡፡

********


Reader's opinions

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


[There are no radio stations in the database]