ግንቦት 06/2007 ዓ.ም

በግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አሊ ረዲ ምክትሉንደግሞ ፋሲል ተካልኝ አድርጓል ፌዴሬሽኑ እንዳሳወቀው፡፡ ተያያዥ ጉዳዮችንም እንደሚከተለው አስቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ.ም በሆቴል ይሰባሰባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም ጋቦን ለምታስተናግደው 31ኛው የአፍሪካ እግር ዋንጫ እንዲሁም ለቻን 2ዐ16 ሻምፒዮና የማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት ለመጀመር ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ.ም በሆቴል ይሰባሰባሉ፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና በዋሊያዎቹ ቡድን መሪ አቶ ዮሴፍ; ተስፋዬ ሰብሳቢነት የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ጨምሮ ከተለያዩ የፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ በብሔራዊ ቡድኑ አጠቃላይ ዝግጅት እና በሰብሳቢው አማካኝነት በቀረበው መነሻ: ሃሳብ እንዲሁም በዝግጅት እቅድ ዙሪያ ባተኮረው ስብሰባ ላይ እንደተገለፀው ለመጀመሪያ ዙሪያ ምርጫ 44 ተጫዋቾች ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ.ም በሆቴል ይሰባሰባሉ፡፡ የተጫዎቾቹ ዝርዝር ልምምድ ከመጀመሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ የሚደረግ ሲሆን፤ከጥቂት ቀናት ልምምድ በኋላ የሚለዩት 25 ተጫዋቾች ከውጭ ሀገር ክለቦች የሚጠሩትን 4 ወይም 5 ተጫዋቾች ጨምሮ ለወዳጅነት እና ከሌሴቶ ጋር ለሚካሄደው ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ ልምምዳቸውን እንደሚቀጥሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችና በሌሎች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች የተገኘውን ልምድና ያጋጠሙ የአሠራር ችግሮችን በማጤን እና የስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴው በሰጠው መመሪያ መሰረት ከወዲሁ የተጀመረው አጠቃላይ ዝግጅት ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነትና ተወዳዳሪነት ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው የቡድን መሪው አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የትጥቅ ፣ የሆቴል፣ የልምምድ ሜዳ፣ የመረጃ ልውውጥ፣ የአውሮኘላን ትኬትና የጉዞ ሰነዶችን አስቀድሞ የማዘጋጀትና እንዲሁም የወዳጅነት ጨዋታ ቅድመ ዝግጅት እና አጠቃላይ የጊዜ ሰሌዳ የመቅረፅና የማስፈፀም ሥራዎች በተጠና እና በተቀናጀ የአሠራር አግባብ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ ከውድድር ፣ ከዳኝነት፣ ከህክምና ፣ከሥልጠና ቡድን አባላት ጋር የሚኖረውን የሥራ ግንኙነትና ከፌዴሬሽኑ የሚጠበቀውን ሙያዊና አስተዳደራዊ ድጋፍ በተመለከተም ኃላፊነትና ተጠያቂነትን ባገናዘበ መልኩ የዝግጅት መርሀ ግብሩ እንደሚተገበር ታውቋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ በተሰጣቸው የሥራ ኃላፊነት መሠረት ለብሔራዊ ቡድን በረዳት አሠልጣኝነት እና በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት: የመረጧቸው ፋሲል ተካልኝ እና ዓሊ ረዲም አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንደተጠናቀቁ ሰሞኑን ሥራቸውን በይፋ ይጀምራሉ፡፡ የቅጥር ውል እንደተጠናቀቀም ዝርዝር መረጃዎች ይፋ ይደረጋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሰኔ ወር የሚያካሂዳቸው ጨዋታዎች የሚያስተናግዱባቸውን ስታዲየሞች በተመለከተም ከአየር ሁኔታ ትንበያና የተጋጣሚዎችን አጠቃላይ ሁኔታ መሠረት አድርጎ ሰሞኑን ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፡፡

ሚያዚያ 26/2007 ዓ.ም

የ21ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በክልል እና በአዲስ አበባ ስታድየም ተከናውነዋል:: ቅዳሜ በተከናወነ አንድ የክልል ጨዋታ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከነማን አስተናግዶ 1ለ0 አሸንፏል፡፡ በሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ደደቢት ጨዋታ ደደቢቶች 3 ለ 0 አሸንፈዋል ፡፡

የመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ያደረገ ጨዋታ በታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሳሙኤል ሳኑሜ ከእረፍት በፊት፤ እንዲሁም በረከት ይሳቅ እና ሽመክት ጉግሳ ተቀይሮ ገብቶ ለደደቢት ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ሳሙኤል ሳኖሚ ላስቆጠራት ጎል የንግድ ባንክ ተከላካዮች ስህተት እና የግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ድክመት በግልጽ የታየባት ነበር። ሳሙኤል ሳኑሚ ይሄን ተከትሎ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ከባንኩ ፊሊፕ ዳውዚ እኩል በ14 ግቦች መምራት ጀምሯል፡፡

በበርካታ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ታጅቦ 11፡30 ላይ በተከናወነው የመከላከያ ከወላይታ ድቻ ጨዋታ መከላከያዎች ከሶስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል። ጨዋታው እንደተጀመረ ለ20ደቂቃዎች በድቻዎች በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ ቢታይም አብዛኛው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግን ሀይል የተሞላበት የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ታይተዋል፡፡ የተቆጠሩት ግቦችም የተመዘገቡት በሁለተኛው 45 ሲሆን 57ተኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም ጥላሁን መከላከያን ቀዳሚ አደረገ፤ 76ተኛው ላይ አላዛር ፋሲካ ድቻን አቻ ሲያደርግ ተቀይሮ የገባው ሳሚኤል ሳሊሶ 88ተኛው ደቂቃ ላይ መከላከያን ቀደሚ የሚያደርገውን ግብ አስቆጥሮ ጫወታው 2 ለ 1 በመከላከያ አሸናፊነት ተጠናቋል ፡፡

ክልል ላይ በተካሄዱ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ በኤዶም ብቸኛ ጎል ወልድያ ከነማን አንድ ለባዶ በማሸነፍ በመጀመሪያው ዙር ደርሶበት የነበረውን የአንድ ለባዶ ሽንፈት አወራርዷል፡፡ ይርጋዓለም ላይ ሲዳማ ቡና  ከሃዋሳ ከነማ ጨዋታ ሀዋሳ ከነማ በተመስገን ተክሌ ብቸኛ ጎል አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። ሲዳማ ቡና የትናንቱን ጨምሮ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በመሸነፉ ከመሪው ቅ/ጊርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት በ 4 አስፍቶቷል፡፡ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ደደቢትም የሚበልጠው በሁለት ነጥብ ብቻ ነው። ለዋንጫው የሚያደርጉትን ግስጋሴ ያጠናከሩት ቅ/ጊርጊሶች ወደ አሰላ ተጉዘው ሙገር ሲሚንቶን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ተመልሰዋል። ሶስቱም ግቦች በ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ሲመዘገቡ ምንተስኖት አዳነ እና ብሪያን እሙኒ ለቡድናቸው ዘካሪያስ ቱጂ ደግሞ ለሙገር የተመዘገበችዋን ግብ በራሱ ላይ አስቆጥሯል፡፡

ቅ/ጊዮርጊስ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 42 በማድረስ ከተከታዩ ሲዳማ ቡና በአራት ነጥብ ከፍ ብሎ ሊጉን በብቸኝነት ይመራል። 

በወራጅ ቀጠናው ሙገር ሲሚንቶ በ19፣ ወልዲያ ከነማ በ12 ነጥብ፣ 13ተኛ እና 14ተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ዳሽን ቢራ፣ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከነማም በአንድ አንድ የነጥብ ልዩነት በወራጅ ቀጠናው በስጋት ውስጥ ናቸው፡፡

የሊጉን ኮከብ ጎል አስቆጣሪነት ሁለቱ ናይጄሪያውያን አጥቂዎች ይዘውታል፡፡ ፊሊፕ ዳውዝ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሳሙኤል ሳኖሚ ከደደቢት በእኩል 14 ጎል ይመሩታል። (አርያት ራያ)

ሚያዚያ 26/2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኢንስትራክተር ዮሀንስ ሳህሌን የቀጣይ የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ይታወሳል፡፡ እንደ ፌዴሬሽኑ ጥሪ ከሆነም ኢንስትራክተር ዮሀንስ ሳህሌ ከዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 26 /2007 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ይጀምራል ፡፡

ይህንን ተከትሎ ነው ክለቡ ደደቢት ዛሬ ረፋዱ ላይ ቦሌ አከባቢ በሚገኘው ደሳለኝ ሆቴል ለብሄራዊ ቡድን የተመረጠውን የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዮሀንስ ሳህሌን በክብር የሸኘው፡፡

በስፍራው የተገኙት የቡድኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል አምደመስቀል በነበረን ጊዜ ደስተኛ የሆንበት ብቻ ሳይሆን የምንኮራበት አሰልጣኝ ነበር፤ በጣም በስራ የሚያምን እና ጥሩ ነገርንም አስተምሮናል፤ ሊጉ ወሳኝ ሰዓት ላይ ያለ እና እኛም ጥሩ አቋም ላይ ያለን ቢሆንም እንደ ቡድን ለሀገራዊ ሀላፊነት ስንል ያለምንም የካሳ ጥያቄ አሰልጣኙን ለቀናል፤ መልካም እድልም እንዲገጥመው እንመኛለን ብለዋል ፡፡

አዲሱ የብሄራዊ ቡድን ኢንስትራክተር ዮሀንስ ሳህሌ በበኩላቸው ለነበረኝ ጊዜ አመሰግናለሁ፤ አሰልጣኝ የፈለገ አቅም ቢኖረውም መጀመሪያ ደደቢትን ስረከብ ጥያቄዬ ሙሉ አቅሜን አውጥቼ እንድጠቀም ይመቻችልኝ የሚል ነበር፤ ምንም ሳይጎድልብኝ ሁሉ ተሟልቶልኝ ስራዬን ሰርቻለሁ፤ ለዛም የተሳካ ጊዜን አሳልፌአለሁ፤ በነበረኝ ጊዜ የክለቡ አመራሮች፣ ረዳት አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ሁሉ ከጎኔ ነበሩ ሲል ሁሉንም አመስግኗል፡፡

ቀጣይ የውድድር አመቱ እስኪያልቅ ደደቢት በምክትል አሰልጣኙ ዳንኤል ጸሀዬ ዋና  አሰልጣኝነት እንዲሁም በተስፋ ቡድኑ አሰልጣኝ ኤሊያስ ኢብራሂም ረዳትነት ይመራል እንደ ቴክኒክ ዳይሬክተሩ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ገለጻ፡፡ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ለኢንስትራክተር ዮሀንስ ሳህሌ ከክለቡ የቡድኑ ሙሉ አባላት ያሉበት ፎቶግራፍ በስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ደደቢትን ከተረከቡ በኋላ በሊጉ 14 ጨዋታዎችን አድርገው፤ በሰባቱ አሸንፈው፤ በአራቱ አቻ ሲለያዩ በሶስቱ ተሸንፈዋል። (አርያት ራያ) 

ሚያዚያ 19/2007 ዓ.ም

በሊቢያ በግፍ የተሰው ወገኖች በአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት አስቦ የዋለው የ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎችን አስተናግዷል፡፡ በሳምንቱ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የቅ/ጊዮርጊስ ኢትጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ በ 1 ለ 1 የአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ለባንክ ግቡን ጨዋታው እንደተጀመረ ፊሊፕ ዳውዝ ሲያስቆጥር ቅ/ጊዮርጊሶች አቻ የምታደርጋቸውን ግብ ደግሞ ምንተስኖት አዳነ አስገኝቷል፡፡ 

ሌላው ተጠባቂ የነበረው የአዳማ ከነማ ከ ሲዳማ ቡና ጨዋታ በአዳማ ከነማ 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አዳማ ከነማ በውድድር አመቱ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጥንካሬው ቀጥሏል፡፡ በደረጃ ሰንጠረጁ ግር የሚገኘው ወልዲያ ከነማ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 1 ለ 0 በማሸነፍ ሶስተኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡ 

በሌሎች የክልል ጨዋታዎ ዳሽን ቢራ ኤሌክትሪክን ሃዋሳ ከነማ መከላከያን በተመሳሳይ 2 ለ 1 ሲረቱ አርባምንጭ ከነማ ሙገር ሲሚንቶን 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡ ሊጉን ቅ/ጊዮርጊስ በ 39 ይመራል፤ ሲዳማ ቡና በ38 ሁለተኛ ኢት/ንግድ ባንክ በ33 ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ በወራጅ ቀጠናው ደግሞ ዳሽን ቢራ፤ ኤሌክትሪክ፤ ሀዋሳ ከነማ፤ ሙገር ሲሚንቶ እና ወልዲያ ከነማ በ 22, 21, 20 ,19 እና 12 ነጥቦችን ይዘው ከ10ኛ ደረጃ እስከ 14ኛ ደረጃን ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን የኢት/ንግድ ባንኩ ፊሊፕ ዳውዝ በ 14 ይመራል ኢት/ቡናው ቢኒያም አሰፋ በ13 ግቦች ይከተለዋል፡፡ (አርያት ራያ)

ሚያዚያ 18/2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዮሐንስ ሳህሌን የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ እንዲሰራ ትናንት በአካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ መርጦታል፡፡

ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ በስምምነት ከሃላፊነት መነሳታቸውን ተከትሎ የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ በፍጥነት እንዲመደብ በተላላፈው ውሳኔ መሰረት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለዮሃንስ ሳህሌ የዋና አሰልጣኝነቱን ሃላፊነት ሰጥቶታል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ከጥቂት ወራት በኋላ በቻን 2016 እና በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ለሚጠብቁትና በፌዴሬሽኑ ልዩ ትኩረት ለተሰጣቸው ወሳኝ አህጉራዊ የማጣሪያ ጨዋታዎች አዲስ ዋና አሰልጣኝ ለመምረጥ የተከተለው አቅጣጫ ከብሄራዊ ከቴክኒክና ልማት እንዲሁም ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተውጣጣ ኮሚቴ በማቋቋም ምርጫውን በፍጥነት ማከናወን ነው፡፡ የዋና አሰልጣኝ ምርጫው ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋና አሰልጣኞች የመምረጫ መስፈርት በማዘጋጀትና የሁሉንም ብቃትና ደረጃ በዝርዝር በማየት አራት ተወዳዳሪዎችን በኮሚቴው አማካኝነት ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለይቶ የማቅረቡ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ የሐንስ ሳህሌ በተዘጋጀው መመዘኛ መሰረት በቀዳሚነት ሊመረጥ ችሏል፡፡ በማወዳዳሪያው መስፈርት መሰረትም ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም እና ፋሲል ተካልኝ የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ እንዳገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲሱ የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አስፈላጊውን የቅጥር ስርዓት በፍጥነት በማጠናቀቅ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁኔይዲ ባሻ ጋር የምርጫው ውጤት እንደታወቀ የተዋያዩ ሲሆን ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ያገኙት ምላሽ አዎንታዊ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ውይይታቸው በዛሬው እለትም እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ደግሞ በእግር ኳስ ቤተሰቦች እና ከመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ላይ ለሚገኙት ወቅታዊና በተለይም ደግሞ ከዋና አሰልጣኝ ቅጥርና ስንብት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ፌዴሬሽኑ ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣል፡፡

-ምንጭ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

መጋቢት 10/2007 ዓ.ም

ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች በክልል ተከናውነዋል፤ ወደ ሃዋሳ የተጓዘው ቅ/ጊዮርጊስ በ ሀዋሳ ከነማ 2 ለ 0 ተሸንፏል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሁለተኛው ዙር ሀዋሳን ከተረከበ በኋላ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ አርባ ምንጭን በሜዳው 2 ለ 0፤ በተመሳሳይ ዛሬም ቅ/ጊዮርጊስን 2 ለ 0 አሸንፎ 6 ነጥቦችን አግኝቷል፤ በዛሬው ጨዋታ ግቦቹን ታፈሰ ሰለሞን እና ተደስታ ዩሀንስ አስቆጥረዋል፡፡

ይርጋለም ላይ ኤሌክትሪን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና ደግሞ መብራትን 2 ለ 1 በማሸነፍ በድጋሚ መሪነቱን ከ ቅ/ጊርጊስ ተረክቧል፡፡ በጨዋታውም ግቦቹን ዕንዳለ ከበደ እና የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አሰግድ አክሊሉ በራሱ ላይ ሲስቆጥር ማናዮ ፋንቱ የኤሌክትሪክን ብጨኛ ግብ አስገኝቷል፡፡
በሌላ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ከ አርባምንጭ ተገናኝተው አርባምንጭ ከነማ 1 ለ 0 ድቻን በሜዳው አሸንፎታል፡፡ ግቧም በ ታሪኩ ጎጀሌ ተመዝግባለች፡፡

በትላንትናው እለት በተደረገ የ15ተኛው ሳምንት ብቸኛ የአዲስ አበባ ጨዋታ መከላከያ ዳሽን ቢራን ከጨዋታ ብልጫ ጋር በጎዶሎ ልጅ 3 ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ዛሬ የተከናወኑትን ጨዋታዎች ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ 31 ነጥብ መምራት ሲጀምር ቅ/ጊዮርጊስ በ28 ሁለተኛ ፤ ወላይታ ድቻ በ25 ሶስተኛ እንዲሁም መከላከያ እና አርባ ምንጭ ከነማ 22 ነጥብ ይዘው 4ተኛ እና 5ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ሃዋሳ ከነማ ደግሞ ነጥቡን ከ ዳሽን ቢራ እኩል 16 አድርጎት ከ ሙገር ሲሚንቶ ከፍ ብሎ እንዲቀመጥ ሆኗል፡፡

የሳምንቱ ጨዋታ በነገው እለት ይቀጥልና በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ከ ሙገር ሲሚንቶ እንዲሁም እሁድ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እየተሳተፈ የሚገኘው ደደቢት ወልዲያ ላይ ከወልዲ ከነማ ይጫወታሉ፡፡ (አርያት ራያ)

መጋቢት 07/2007 ዓ.ም

የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች አርብ ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ እና በክልል ሜዳዎች ተከናውነዋል፡፡በ14ተኛው ሳምንት የሊጉ የመጨረሻው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኘ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በባንክ 1 ለ 0 ተሸንፏል ፤ የባንክን ብቸኛ ግብ 72 ደቂቃላይ ሲሳይ ቶላ አስቆጥሯል፡፡

ባንኮች በዘንድሮው አመት ከቡና በተገናኘባቸው ጨዋታዎች የበላይነት ወስደዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በፍጻሜው በመለያ ምት እንዲሁም በመጀመሪው ዙር 2ለ0 አሸንፈዋል፡፡
የሳምንቱን ውጤቶች ለማስታወስ አርብ መከላከያ ኤሌክትሪክን 2ለ0፤ ዳሽን ቢራ በ ወላይታ ድቻ 1ለ0 ሲሸነፍ፤ ቅዳሜ ቅ/ጊዮርጊስ አዳማን ከነማን 2ለ0፤ ሀዋሳ ከነማ አርባ ምንጭን ከነማን በሜዳው 2ለ0 እንዲሁም ሙገር ሲሚንቶ
ከ ሲዳማ ቡና 0ለ0 የተመዘገቡ ውጤቶች ናቸው፡
የሊጉን መሪነት ቅ/ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ተረክቧል፤ በ13 ንጹ ግቦች በ 28 ነጥብ አንደኛ ሆኗል፡፡
አጠቃላይ ደረጃው፡-
1/ ቅ/ጊዮርጊስ --------14 +13 28
2/ሲዳማ ቡና ---------14 + 6 28
3/ወላይታ ድቻ -------14 + 4 25
4/ኢት/ ቡና------------14 + 4 21
5/ኢት/ ባንክ-----------14 + 3 19
6/መከላከያ ------------14 - 0 19
7/አዳማ ከነማ --------14 - 0- 19

8/አርባ ምንጭ -------14 - 1 19
9/ደደቢት -------------13 + 4 18
10/ኤሌክትሪክ----- ---14 - 3 17
11/ዳሽን ቢራ --------14 - 3 16
12/ ሙገር ሲሚንቶ--14 - 4 14
13/ ሃዋሳ ከነማ ------14 -3 13
14/ወልዲ ከነማ ------13 -20 5

ኮከብ ግብ አግቢነቱን ቢንያም አሰፋ ከኢትዮጵያ ቡና በ11 ግቦች ሲመራ ሳሙኤል ሳኑሚ ከደደቢት በ 8 ግቦች ይከተላል፡፡ (አርያት ራያ)

መጋቢት 5/2007 ዓ.ም

ግቦቹን በመጀመሪያው አጋማሽ ብሪያ ከእረፍት መልስ ደግሞ ምንተስኖት አዳነ አስቆጥረዋል። በክልል ሙገር ሲሚንቶ ከ ሲዳማ ቡና 0 ለ 0 ሲለያዮ ወደአርባ ምንጭ ያቀናው ሀዋሳ ከነማ ድል ቀንቶታል፡፡ 

2 ለ 0 አርባ ምንጭን በማሸነፍ ተመስገን ተክሌ እና መስቀሌ መንግስቱ ግብ አስቆጣሪዎቹ ናቸው ።
የሳምንቱ የመጨረሻው ጨዋታ ነገ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይደረጋል። (አርያት ራያ)

መጋቢት 05/2007 ዓ.ም

ደደቢት በመጀመሪያ ጨዋታ በደርሶ መልስ የሲሼልሱን ኮት ዲኦር በድምር 5ለ2 ውጤት አሸንፎ ለቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል፡፡ በሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውንም ለማድረግ ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ናይጄሪያ ሌጎስ ከትናንት በስቲያ አምርቷል፡፡

ደደቢቶች ባልተመቸ መልኩ ከሌጎስ ጨዋታውን ወደሚያደርጉበት ዋሪ ከተማ የአውሮፕላን በረራ ባለማግኘታቸው ከሌጎስ ወደጎረቤት ቤኒን በርረው 100 ኪሎ ሜትሮች ገደማ በመኪና ተጉዘው የሚቻጫወቱበት ከተማ ዋሪ ገብተዋል፡፡ ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሰረት ትላንት ቀለል ያለ ልምምድም ሰርተዋል፡፡

ደደቢቶች ዛሬ 12፡00 ላይ በሚያደርጉት ጨዋታ ሀሰን ሞሀመድ ሀጊ፣ ሀምዛ ሀጊ አብዲ፣ ባሺር አብዲ ሱሌይማን እና ባሺር ኦላድ አራብ ከሶማሊያ ጨዋታውን ሚመሩት አርቢትሮች ሲሆኑ የጨዋታው ኮሚሽነር አል-ሀጂ ጃዉሉ ከጋና ናቸው፡፡

ድል ለደደቢት የዝግጅት ክፍላችን ይመኛል፡፡

መጋቢት 5/2007 ዓ.ም

በጅማሮ በአበበ ቢቂላ ስቴዲየም በ14ኛው ሳምንት መርሀ-ግብር የተገናኙት መብራት ኃይል እና መከላከያ ነበሩ፡፡ በ10 ሰአት ላይ ባደረጉት ጨዋታም መከላከያዎች 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፡፡ ለመከላከያ ግቦቹን የእለቱ የቡድኑ አምበል ሲሳይ ደምሴ በፍጹም ቅጣት ምት እና የመብራት ኃይሉ  ተከላካይ አሳልፈው መኮንን በምንይሉ የተመታውን ኳስ በመንካት በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል፡፡

ሁለቱም ግቦች በሁለተኛው አጋማሽ ነበር የተቆጠሩት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪው ዙር ጨዋታ ማራኪ እንቅስቃሴ አሳይተው ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ነበር የተለያዩት፡፡

በክልል በተከናወነ አንድ ጨዋታ ወደ ጎንደር የተጓዘው ወላይታ ድቻ ድል ቀንቶታል፤ ዳሽን ቢራን በሜዳው በአጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በተገኘ ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል ፡፡ ዳሽን ቢራ  በመጀመሪያው ዙር ቦዲቲ ላይ በመዳኔ ታደሰ ግብ በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የ14ተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲደረጉ 10፡00 ላይ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ቅ/ጊርጊስ ከ አዳማ ከነማ፤ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ከ መሪው ሲዳማ ቡና እንዲሁም አርባ ምንጭ ላይ አርባ ምንጭ ከነማ ከ ሀዋሳ ከነማ ይጫወታሉ፡፡

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በነገው እለት ዕሁድ 10፡00 ላይ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚደርጉት ነው፡፡ (አርያት ራያ)