Monday, 02 May 2016 15:02

አሰልጣኝ ዮሀንስን ለመተካት አሰልጣኝ ውበቱ እና ቶም ሴንትፊት ግምት አግኝተዋል፡፡

Written by 

ሚያዚያ 24/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምስጢር የመጠበቅ ችግር በርካቶችን እያነጋገረ ነው፡፡

ካሉት 10 የስራ አስፈፃሚ አባላት መካከል 7ቱ በተገኙበት የተካሄደው መደበኛ ስብሰባ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ እና የቴክኒክ ኮሚቴውን ስንብት ሲያፀድቅ የነበረበት ሂደት አፈትልኮ መውጣቱ አስገራሚ ሆኗል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አቶ ጁነዲን ባሻህ፣ ምክትል ፕሬዝደንቱ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ፣ አቶ አሊሚራህ መሀመድ፣ ዶ/ር ነስረዲን እና ኢንጅነር ቾል ባደረጉት ስብሰባ አሰልጠኝ ዮሀንስ ሳህሌና ቴክኒክ ኮሚቴው መሰናበታቸውን በይፋ ሳይገልፁና ከስብሰባ ቦታው ሳይወጡ መረጃ መውጣቱ ግርምታን ፈጥሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሰልጣኙ ስንብት በይፋ ለአሰልጣኝ ዮሀንስ አለመድረሱና መረጃውን የሰሙት ከመገናኛ ብዙሀን መሆኑ አሁንም የፌዴሬሽኑ የአስተዳደር አካሄድ ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ሆኗል፡፡

በግል ስራቸው ምክንያት ቱርክ የሚገኙት አቶ ጁነዲን ባሻ ዛሬ አዲስ አበባ የሚገቡ ከሆነ በነገው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እያሉ ፕሬዝደንቱ ካልመጡ ጋዜጣዊ መግለጫ አይሰጥም፤ ለተሰናባቾቹም የስንብት ደብዳቤው አይደርስባቸውም መባሉ በአመራሮቹ ዘንድ ክፍተት ይኖር ይሆን? አስብሏል፡፡

በሌላ ዜና ዋሊያዎቹን ለቀጣዮቹ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች የመምራት ዕድል ቢያገኙ እንደማይቀበሉት የቴክኒክ ዳይሬክተሩ መኮንን ኩሩ ተናግረዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሀንስን ለመተካት ከሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ከውጪ ደግሞ ቶም ሴንትፊት የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

Read 454 times

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.