ግንቦት 02/2008 ዓ.ም

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በአቶ ዘሪሁን ቀቀቦ የሚመራውን ቴክኒክ ኮሚቴ በይፋ ያፈረሰ ሲሆን የቴክኒክ ዲፓርትመንት አባላት ግን ራሳቸውን እያሸሹ ነው፡፡

በቴክኒክ ዲፓርትመንት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማርያም እና የዲፓርትመንቱ ውጤታማ ባለሙያ ታዬ ናኔቻ በተሻለ ክፍያ የተሻለ እምነት ጥለውብናል ላሏቸው ኢትዮጵያ ቡና እና ሰበታ ከተማ እጃቸውን ሳይሰጡ አንዳልቀረ እየተነገረ ነው፡፡

በኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ የሚመራው የቴክኒክ ዲፓርትመንት ከሁለቱ ባለሙያዎች ስንብት በኋላ መፃኢ ዕድሉ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

ግንቦት 02/2008 ዓ.ም

የከፍተኛ ሊግ የ1ኛ ዙር ፍልሚያ በወልዲያ ከነማ እና በጅማ አባቡና መሪነት ተጠናቋል፡፡

32 ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው ባደረጓቸው ጨዋታዎች ወልዲያ በ31 ነጥብ የምድብ ሀ ፍልሚያን ሲመራ ፋሲል ከነማ እና መቀሌ ከነማ በእኩል 29 ነጥቦች በጎል ተበላልጠው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡

በምድብ ለ ጅማ አባቡና ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ሽንፈት ሳይገጥመው በ39 ነጥብና 25 ጎል 1ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ይህን ውጤት ተከትሎ የክለቡ አመራሮች ለቡድኑ አባላት የገንዘብ ሽልማት ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ35 ነጥብና 12 ጎል 2ኛ፤ ሃላባ በ28 ነጥብና 8 ጎል 3ኛ ሆነው የምድቡን የመጀመሪያ ዙር አጠናቀዋል፡፡

የ1ኛ ዙር ግምገማና የ2ኛ ዙር ቀጣይ መርሃ ግብርን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ነገ ጠዋት 3፡00 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ሆቴል ቀጠሮ መያዙ ታውቋል፡፡ የፌዴሬሽኑ የውድድር ኮሚቴ ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁ 4 ክለቦች ለ2009 ፕሪሚየር ሊግ በቀጥታ የሚያልፍ ሲሆን አንደኞቹ ለዋንጫ ሁለተኞቹ ለደረጃ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

በ2009 በፕሪሚየር ሊጉ የሚካፈሉ ክለቦች 16 ሲሆኑ ዘንድሮ 2 ቡድኖች ይወርዱና የከፍተኛ ሊጉ አላፊ 4 ክለቦች ታክለው 16ቱ ውድድራቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

ግንቦት 01/2008 ዓ.ም

ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን የማጫወት መርሃ ግብር ተይዞለት የነበረው ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ ከኢትዮጵያ ቡና በተጻፈ የተቃውሞ ደብዳቤ በሌላ ዳኛ እንዲቀየር የተደረገበት መንገድ ፌዴሬሽኑ ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ የፊፋና የካፍ ህጎችን ወደጎን በማለት የሸገር ደርቢን ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሰ እንዲመራው ሲወስን፤ የደደቢትና ኤሌክትሪክ ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ታደሰ እንዲመራው ማድረጉ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች እንጂ በክለቦች ተቃውሞ አርቢትር የመቀየሩ ነገር ሌላ ጣጣ ሊያመጣ እንደሚችል የሚናገሩት ምንጮቻችን ቀሪዎቹ 13ቱ ክለቦች ይህን ዳኛ አንፈልግም ቢሉ የፌዴሬሽኑ ምላሽ ምን ይሆን? በማለትም ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የፍፁም ቅጣት ምት ከልክለሃል ተብሎ አንድ ዓመት የታገደው ኢንተርናሽናል አርቢተር ለሚ ንጉሴ ወደ ጨዋታ የተመለሰበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

አርቢትሩ አንድ ዓመት መታገዱ ለየሚዲያው በተገለፀበት ሂደት ሳይሆን ዓመት ሳይሞላው ዕገዳው ለምን እንደተነሳ ሳይገለፅ በደቡብ ደርቢ 0 ለ 0 የተጠናቀቀውን የወላይታ ዲቻና የሲዳማ ቡና ጨዋታ በመሃል ዳኝነት መምራቱ በርካቶችን አስገርሟል፡፡

የፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ በሁለቱ አርቢትሮች ዙሪያ የተፈጠረውን የተደበላለቀ ስሜት ለማጥራት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

ሚያዚያ 28/2008 ዓ.ም

ማርቲን በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ጉብኝት ካደርጉ የአርሰናል የቀድሞ ተጫዋቾች ሁለተኛው ነው፡፡ በጎንደር ቆይታው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ይጎበኛል፣ ከዳሽን ቢራ ሰራተኞች እና ደንበኞች ጋር ቆይታ ይኖረዋል፣ በከተማው የተለያዩ ስጦታዎችና ሽልማቶችንም ያበረከታል፡፡

በዳሽን ቢራ ወጪ በጎንደር ከተማ ለሚካሄዱ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ ልማት የመሰረት ድንጋይ ያኖራል፡፡ የአነስተኛ ወጪ ቤቶች ግንባታ የድጋፍ ማረጋገጫም ለከተማ አስተዳደሩ የሚሰጥ ሲሆን በአዲስ አበባ የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት ከታዳጊዎች ጋር ቆይታ ያደርጋል፡፡ 

ሚያዚያ 24/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምስጢር የመጠበቅ ችግር በርካቶችን እያነጋገረ ነው፡፡

ካሉት 10 የስራ አስፈፃሚ አባላት መካከል 7ቱ በተገኙበት የተካሄደው መደበኛ ስብሰባ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ እና የቴክኒክ ኮሚቴውን ስንብት ሲያፀድቅ የነበረበት ሂደት አፈትልኮ መውጣቱ አስገራሚ ሆኗል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አቶ ጁነዲን ባሻህ፣ ምክትል ፕሬዝደንቱ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ፣ አቶ አሊሚራህ መሀመድ፣ ዶ/ር ነስረዲን እና ኢንጅነር ቾል ባደረጉት ስብሰባ አሰልጠኝ ዮሀንስ ሳህሌና ቴክኒክ ኮሚቴው መሰናበታቸውን በይፋ ሳይገልፁና ከስብሰባ ቦታው ሳይወጡ መረጃ መውጣቱ ግርምታን ፈጥሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሰልጣኙ ስንብት በይፋ ለአሰልጣኝ ዮሀንስ አለመድረሱና መረጃውን የሰሙት ከመገናኛ ብዙሀን መሆኑ አሁንም የፌዴሬሽኑ የአስተዳደር አካሄድ ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ሆኗል፡፡

በግል ስራቸው ምክንያት ቱርክ የሚገኙት አቶ ጁነዲን ባሻ ዛሬ አዲስ አበባ የሚገቡ ከሆነ በነገው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እያሉ ፕሬዝደንቱ ካልመጡ ጋዜጣዊ መግለጫ አይሰጥም፤ ለተሰናባቾቹም የስንብት ደብዳቤው አይደርስባቸውም መባሉ በአመራሮቹ ዘንድ ክፍተት ይኖር ይሆን? አስብሏል፡፡

በሌላ ዜና ዋሊያዎቹን ለቀጣዮቹ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች የመምራት ዕድል ቢያገኙ እንደማይቀበሉት የቴክኒክ ዳይሬክተሩ መኮንን ኩሩ ተናግረዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሀንስን ለመተካት ከሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ከውጪ ደግሞ ቶም ሴንትፊት የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

ሚያዚያ 06/2008 ዓ.ም

ጊዮርጊስ ከመከላከያ ባደረጉት ተስተካካይ ጨዋታ ላይ አምቡላንስና ቃሬዛ ባለመገኘቱ ጠብታ አምቡላንስ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

የጠብታ አምቡላንስ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አንስቴቲስት ክብረት አበበ “ለተፈጠረው ችግር በይፋ ይቅርታ እንጠይቃለን፤ ፌዴሬሽኑ ተገቢውን መረጃ ቢሰጠንም በጊዜው ለመገኘት ሳንችል ቀርተናል፡፡ መዘግየታችን ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርስ መቅረቱ ግን አስደስቶናል” ሲሉ ለሃገሬ ስፖርት ተናግረዋል፡፡

የስፖርት ቤተሰቡ ግን ከጠብታ አምቡላንስ ውጪ የውድድርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ እና የጨዋታው ኮሚሽነርን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

“የተሟላ መሳሪያ ሳይኖር ጨዋታው መጀመር አልነበረበትም፤ ኮሚሽነሩ እና የውድድሩ አዘጋጆች ተመሳሳይ ስህተት ከመስራት ሊታረሙ ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

መከላከያ እና ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ የጊዮርጊሱ አሉላ ግርማ በደረሰበት ጉዳት ወደ ሜዳ ገብቶ ድጋፍ የሚያደርግለት አምቡላንስ እና ቃሬዛ ባለመኖሩ በክለቡ ተጫዋቾች እርዳታ ከሜዳ እንዲወጣ መደረጉ ይታወቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

መጋቢት 28/2008 ዓ.ም

ዓለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (ዋዳ) አምስት አገራትን አስጠንቅቋል፡፡

ኤጀንሲው ይፋ ባደረገው መረጃ ምርመራውን ሰፋ አድርገው እንዲጀምሩ፣ የየሀገራቸውን የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ እንዲያጠናክሩ እና ሌሎች ከልካይ ህጎችን እንዲያወጡ እስከ ህዳር 2009 ድረስ ቀነ ገደብ የሰጣቸው አምስት አገራት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሮኮ፣ ዩክሬን እና ቤላሩስ ናቸው፡፡

አምስቱም ሃገራት ይህን ካላደረጉ ከህዳር 2009 በኋላ እንደሚያግዳቸው ያስጠነቀቀው ዋዳ የታዘዙትን ተግባራዊ ያደርጋሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ተስፋውን ገልጧል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

መጋቢት 28/2008 ዓ.ም

የ6ቱ ኢንስትራክተሮች ጉዳይ ተቃውሞ እና ድጋፍ እያስተናገደ ባለበት በአሁኑ ወቅት የቴክኒክ ክፍሉ አባል የሆነው ዳንኤል ገ/ማርያም 7ኛው ኢንስትራክተር ሊሆን ከጫፍ ደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ልማት ክፍል የአሰልጣኞች ስልጠና ዴስክ ሃላፊ የሆነው አቶ ዳንኤል በካሜሩን ያውንዴ ለ5 ቀናት የተሰጠውን የኢንስትራክተርነት ስልጠና ወስዶ ተመልሷል፡፡

ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገሮች የመጡ 24 ባለሙያዎች ስልጠናውን የወሰዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡

6ቱ የካፍ ኢንስትራክተሮች አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ ዶ/ር ጌታቸው አበበ፣ አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ሃይማኖት እና አብርሃም መብራቱ፣ አቶ አንተነህ እሸቴ እና አቶ መኮንን ኩሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት) 

መጋቢት 26/2008 ዓ.ም

ኢትዮጲያዊያን አትሌቶችን ለዶፒንግ ተጠቃሚነት የሚዳረጉ ናቸው የተባሉ ምክንያቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡ ስለ ዶፒንግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መረሀ ግብር ላይ ለመገናኛ ብዙሀኑ መረጃውን የሰጡት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የህክምና ማዕከል ሀላፊ ዶክተር አያሌው ጥላሁን “እናመልጣለን፤ ምንም አንሆንም ወይም አንያዝም” የሚሉ አትሌቶች በመኖራቸው እራሳቸውን ሊያርሙ ይገባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

በቂ እውቀት ሳይኖር ደፋር መሆናቸው፣ በወሬ ስለሚፈቱ፣ ስለማይጠራጠሩ፣ አጉል እምነት፣ ማማከር ነውር ስለሚመስላቸው እና ስለሚፈሩ እንዲሁም ነጭ አምላኪ መሆናቸው ለዶፒንግ ተጠቃሚነት አጋልጧቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የአትሌቶቹ ማህበር፣ ሚዲያው፣ የአሰልጣኞች ማህበር፣ አትሌቲክስ ፌደሬሽን፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር የቀድሞ ጀግኖች አትሌቶች የመፍትሄው አካል በመሆን የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉ ዶ/ር አያሌው ጠይቀዋል፡፡

ሰኔ 30/1999 በአዋጅ ቁጥር 554/1999 ህጉ ጻድቆ ዶፒንግ መውሰድ በወንጀል፣ በፍትሃ ብሄር እና በአስተዳደር ክስ የሚያስመሰርት መሆኑም ይታወቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

መጋቢት 26/2008 ዓ.ም

ላብራቶሪዎቹን ለመጎብኘት የሀገራቱ መሪዎች መፍቀድ እንዳለባቸውም ተገልጧል፡፡

በብሄራዊ ሆቴል በተካሄደው የሚዲያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን እንደተናገሩት በየአመቱ ከ12-17 ሚሊየን ዩሮ በጀት የሚያዝላቸው ላብራቶሪዎች 24 የነበሩ ሲሆን የደቡብ አፍካው በመዘጋቱ አሁን 23 ብቻ ቀርተዋል፡፡

“የላብራቶሪዎቹ መሳሪያዎች በየአመቱ ይቀየራሉ፤ ቦታዎቹንም ሆነ ባለሞያዎቹን ሰው አያውቃቸውም” ያሉት ዶ/ር አያሌው ላብራቶሪዎቹን ለመጎብኘት የየሀገራቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ወይም ፕሬዝዳንቶች ፍቃድ የግድ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“የሲድኒ ኦሎምፒክ የሃይሌ ገ/ስላሴ የሽንት ናሙና አሁንም አለ፤ የሽንትና የደም ናሙናዎች ደግሞ እስከ 8 ዓመት ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ” ያሉት ዶ/ር አያሌው ጥላሁን “በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ተወስደው የተቀመጡ የሽንት ናሙናዎች እንደገና እንዲመረመሩ ተወስኗል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
(የሃገሬ ስፖርት)