ጥር 12/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ምሽት 1:00 ሰዓት ከካሜሮን ጋር ያደርጋል። ብሔራዊ ቡድኑ በውድድር ለመቆየት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ በመጀመሪያው ጨዋታ የነበረውን ክፍተት እና ለዛሬው ጨዋታም ቡዱኑ ያደረገውን ዝግጅት ነግረውናል።

ቡድኑ ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ ግምገማ አድርጓል፤ ደካማ ጎኑንም ለይቷል ካሉ በኋላ ባለጋራ ቡድን አለማወቃቸው አንዱ ክፍተት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አስቀድመን ያሰብነው የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች ቡድኑን አይተን ከዛ ወጥተን ለመጫወት ነበር እቅዳች ግን አልተሳካም ያሉት አሰልጣኙ የመጀመሪያው 45 ሊጠናቀቅ ሲል የተቆጠረብን ግብ የስነልቦና ክፍተት ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡

በቪዲዮ ጨዋታውን ተመልክተን ተነጋግረንበታል፤ የጨዋታውንም መረጃዎች ለሁሉም ተጫዋቾች ሰጥተናቸው አይተውታል፤ እያንዳንዱ ተጫዋች ምን አይነት እንቅስቃሴ እንዳደረገም አይተዋል፤ እንዴት እንደሚነበብም እንዲያውቁ አድርገናል፤ ልምምዳችንን መስራት የጀመርነውም ከዚህ በመነሳት ነው ብለዋል፡፡

ከምድቡ ካሜሮን እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሶስት ሶስት ነጥብ አላቸው፤ ነጥቡ ያስፈልገናል፤ ይሄ ሌላ ቡድን ነው ያለን አማራጭ ማሸነፍ ብቻ ነው ወጥተን ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት እንጫወታለንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ (አርያት ራያ)

ጥር 12/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ዝግጅቶች ከጥር 24-29 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ሊያከብር መሆኑን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡

ኤግዚቢሽን፣ የፓናል ውይይት፣ የጥያቄና መልስ ውድድር እና የኢቢሲ ማህበረሰብን የሚያሳትፍ የሰብአዊ አገልግሎት (ለ6 ተቋማት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ) 50ኛ ዓመቱን አስመልክቶ የሚካሄዱ ስነ-ስርዓቶች ናቸው፡፡ (ሱራፈል ዘላለም)

ጥር 12/2008 ዓ.ም

ይህ ሩዋንዳ ኪጋሊ ውስጥ የሚገኝ የኢትዬጵያ ሬስቶራንት ነው፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ የባህል ምግቦች አሉት፤ በባህላዊ ምስሎችም አጊጧል ፣በሬስቶራንቱ የሚከፈተው ሙዚቃም የአማርኛ ነው ነገር ግን አንድም አማርኛ ተናጋሪ ሰው በቤቱ የለም፡፡

ሩዋንዳውያን አብዛኛው ነገራቸው በመልክ ለሀበሻ ስለሚቀርብ አስተናጋጆቹን አማርኛ ተናጋሪ አስመስሏቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባለቤቱን ጨምሮ ሁሉም ሩዋንዳውያን ናቸው፤ ምግብ አብሳዮቹም እንደዛው፡፡

ቤቱ ስራውን ሲጀምር አንድ መስፍን የተባለ ኢትዮጵያዊ ምግብ አብሳይ እንደነበር እና ከአራት ወር በፊት ህይወቱ እንዳለፈ አሁን ላሉት ምግብ አብሳዮች ደግሞ የሀበሻን ምግብ አሰራር እንዳስተማራቸው ሰምተናል፡፡ የምግብ መምረጫው ፅሁፍ ላይም አንድ የምግብ አይነት በስሙ ሰፍሯል "መስፍን የአዋዜ ጥብስ" የሚል…………. ሀገር ማስተዋወቅ እንዲህ ነው።

 

ጥር 04/2008 ዓ.ም

ባለፈው ታህሳስ 26 ቀን 2008 ዓ.ም በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዛን ከተማ በአንድ መኖሪያ ቤት በተዘጋጀው የሰርግ ስነ-ስርዓት ላይ ሙሽሮችን ጨምሮ ከ 120 በላይ ዜጎቻችን የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸውና በሀገሪቱ ህግ የተከለከለውን መጠጥ ይዞ በመገኘታቸው በሳዑዲ የፀጥታ ሀይሎች ተይዘው መታሰራቸው የሚታወስ ነው፡፡ በጂዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ፅ/ቤት ከጂዛን ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጋር በመሆን ከሳዑዲ መንግስት ጋር ባደረገው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እና ድርድር ኢቃማ (መኖሪያ ፈቃድ ) ያላቸውና ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች ከእስር ማስለቀቅ የተቻለ ሲሆን የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሰርግ ስነ ስርዓቱ ላይ የተያዙ ዜጎቻችን በተደረገው መግባባት በወንጀል ሳይጠየቁ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሸኙ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ስለሆነም ዜጎቻችን ለወደፊት በሚያደርጉት የማህበራዊ ግንኙነት ላይ የሀገሪቱን ህግና ስርዓት እንዲያከብሩ እናሳስባለን፡፡

ምንጭ- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ጥር 03/2008 ዓ.ም

የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤ ዛሬ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮምሽን አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን የምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎችም አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡

  1. አቶ አማረ አረጋዊ - ፕሬዝዳንት
  2. ወ/ሮ መአዛ ብሩ - ም/ፕሬዝዳንት
  3. አቶ አብርሀም ገ/መድህን - ዋና ፀሐፊ
  4. አቶ መሰረት አታላይ - አባል
  5. አቶ ታምራት ሃይሌ - አባል

(ሱራፌል ዘላለም)

ጥር 03/2008 ዓ.ም

የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ አዳነች አበበ እንዳስታወቁት በድርቁ ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ ሰዎችንና እንስሳቶችን ለመታደግ የኦሮሚያ ልማት ማህበር የራሱን ድርሻ ለመወጣት በማስብ 10 ሚሊዮን ብር ለግሷል፡፡

ማህበሩ ከአባላቱ መዋጮ ያገኘውን ገንዘብ ተጠቅሞ እርዳታ ማድረጉንና ችግሩ የመቀጥል አዝማሚያ ስላለው በተለይ ታች ድረስ ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ያለመ ድጋፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በድርቁ ምክንያት ትምህርታቸውን ለመከታተል የተቸገሩ ተማሪዎችን ለማገዝ ኦልማ ከሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተማሪዎች የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራም እንዲኖራቸው መደረጉን በተለይ በሀረርጌ ያለውን ምሳሌ በማንሳት ወይዘሮ አዳነች አብራርተዋል፡፡

የኦሮሚያ ልማት ማህበር ላለፉት 15 አመታት በክልሉ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ስራ የሰራ ሲሆን ለዚህም ከ115 ሚሊየን ብር የሚበልጥ ገንዘብ አውጥቷል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)