የካቲት 21/2008 ዓ.ም

የፌዴራል የስነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን 61 የሚደርሱ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር ሃላፊዎችን እና ባለሞያዎችን በሙስና ወንጀል በመጠርጠሩ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡

ከአስሩም ክፍለ ከተሞች በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎቹ የነበራቸውን የመሬት አስተዳደር ሃላፊነት እና የስራ ድርሻ በመጠቀም የመንግስትን መሬት በህገ-ወጥ መንገድ ካርታ አዘጋጅቶ በመስጠት፣ ለልማት ጥቅም ሊውሉ የሚችሉ ቦታዎችን በግለሰብ ይዞታ በማካተት፣ በፍርድ ቤት እግድ የወጣባቸውን መሬቶች ያልታገዱ አድርጎ መረጃ በመስጠት፣ በሀሰተኛ ህብረት ስራ ማህበራት ስም ቦታ እንዲያዝ በማድረግና በመሳሰሉት ወንጀሎች በመጠርጠራቸው በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት ከአዲስ አበባ መስተዳደር እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በጋራ በተከናወነ ኦፕሬሽን ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በዛሬው ዕለት (21/06/2008 ዓ.ም) በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ለተጨማሪ ምርመራ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሏል፡፡

-    ምንጭ- የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን

የካቲት 13/2008 ዓ.ም

በስነ-ስረዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ኘሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ኘሬዝዳንት አቶ ሙክታር ከድር ተገኝተዋል።

74ተኛው የጉጂ ገዳ ስርአት በዓል የሀርሙፋ 15ተኛው የስልጣን ዘመን ስነ-ስርዓት ላለፉት 5 ቀናት በጉጂ ዞን አዶላ ወረዳ በሜኤ ቦኩ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ በባህላዊ የአከባበር ስነ-ስርዓት የስልጣን ርክክቡ ተከናውኗል።

በኘሮግራሙ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ በርካታ የስርዓቱ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ በባህላዊ አልባሳትም ስርዓቱን አድምቀውታል።

የካቲት 08/2008 ዓ.ም

የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አንድ የገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለስልጣን ኦዲተር ከአንድ ድርጅት 100 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበል የካቲት 4፣ 2008 ዓ.ም በቁጥጥር ስር አውሎታል፡፡

ተጠርጣሪው አንድ የግል ድርጅትን በሕግ በማያስጠይቃችሁ መንገድ የታክስ መጠን ቀንሼ የኦዲት ሪፖርት ላዘጋጅላችሁ፤ ለዚህም 150 ሺህ ብር ለእኔ እና ለግብረ አበሮቼ ያስፈልገናል በሚል 100 ሺህ ብር ቅድሚያ ክፍያ ሲቀበል ኮሚሽኑ በደረሰው ጥቆማ መሰረት እጅ ከፍንጅ ሊይዘው ችሏል፡፡

ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሉን በመመርመር ላይ ሲሆን ምርመራው እንደተጠናቀቀ በተጠርጣሪው ላይ ክስ የሚመሰርት ይሆናል፡፡

- ምንጭ- የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን

የካቲት 07/2008 ዓ.ም

እነዚህ በምስል የሚታዩት ተጣብቀው የተወለዱት ህፃናት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በደሀና ወረዳ ቀበሌ 020 አዚላ ሽቫቫኖች ጎጥ ሲሆን በ06/05/2008 ዓም በተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል እናትም በጤና ህፃናትም በጤና ተጣብቀው ተወልደዋል። በፆታቸውም ሁለቱም ሴት ናቸው። የተጣበቁትን ለማለያየት ወደ መቀሌ አይደር ሆስፒታል ተልከው ህክምናው ባለመሳካቱ ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልከዋል።

- ምንጭ- ደሀና ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽ.ቤት

የካቲት 05/2008 ዓ.ም

የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስቴር በቀን ጥር 10፣ 2008 ዓም በቁጥር 030/2/3/5432/16415 በፃፈው ደብደቤ የንግድ ህግ አዋጅ 686 አንቀፅ 37ን በመጣሳቸው ምክንያት የ ቲያንስ ኢትዮጵን ንግድ ፍቃድ ማገዱን አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ ባንክም የንግድ ሚኒስቴርን ደብዳቤ አባሪ አድርጎ በቀን ጥር 18፣ 2008 ቁጥር 01/131/16 ለሁሉም ባንኮች በፃፈው ደብዳቤ የቲያንስ ኢትዮጵያ ንግድ ፍቃድ መታገዱን ጠቅሶ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

Wednesday, 10 February 2016 16:14

ቻይና ከካናዳ ንፁህ አየር መግዛት መጀመሯ ተሰማ፡፡

የካቲት 02/2008 ዓ.ም

የአለማችን የግዙፍ ኢንዱስትሪዎች መገኛ የሆነችው ቻይና ከኢንዱስትሪዎቿ በሚለቀቅ በካይ ጋዝ ምክንያት ነዋሪዎቿ እርስ በእርሳቸው መተያየት እስኪያቅታቸው መድረሳቸው፣ ለመተንፈሻ አካላት ህመም ሲጋለጡ፣ የትምህርትና የስራ ሁኔታዎቻቸው ሲስተጓጎሉባቸው ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ቢቢሲ ይዞት በወጣው መረጃ ደግሞ ቻይናዊያን የንፁህ አየር ያለህ፤ ንፁህ አየር ለሚሸጥልን የተፈለገውን ብር እንከፍላለን እያሉ ነው፡፡ ከወደ ካናዳም ለጥያቄያቸው ምላሽ የሰጠ አልጠፋም፡፡ አንድ የካናዳ ኩባንያ ከሮኪ ተራራ (Rocky Mountain) የጨለፈውን ንፁህ አየር በጠርሙስ እያሸገ ለቻይና ገበያ አቅርቧል፡፡

በእርግጥ ይሄን ንፁህ አየር ከባለፈው ዓመት ወዲህ በምዕራቡ የካናዳ ክፍል ማምረት ቢጀመርም ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያ ላይ የዋለው ግን በቻይና ሆኗል፡፡

ከቴሌግራፍ ጋር ቆይታ ያደረገው የድርጅቱ ተባባሪ መስራች Moses Lam በቻይና ገበያ እንደቀናቸው ተናግሯል፡፡ ለዚህም ደግሞ በአራት ቀን ውስጥ ብቻ 500 ንፁህ አየር የተሞሉ ጠርሙሶችን መሸጥ ችለናል ሲል ተደምጧል፡፡

4 ሺህ ሳጥን ንፁህ አየር ጭኖ ወደ ቻይና እየተጓዘ ቢሆንም አብዛኛው ሳጥን ገና ሳይደርስ ገዥዎች ከፍለውበታል ተብሏል፡፡

ይሄው ታሽጎ የሚሸጠው ንፁህ አየር አንዱ ጠርሙስ 7.7 ሊትር መያዝ የሚችል ሲሆን የአንዱ ዋጋ 100 የን (10 ፓውንድ) መሆኑ ታውቋል፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ በቻይና የታሸገ ንፁህ ውሃ ከሚሸጥበት ዋጋ በ50 እጥፍ ይበልጣል፡፡

በቅርቡ በተካሄደው የፓሪሱ የአየር ንብረት ጉባኤ የቻይናው ፕሬዝደንት ዢን ፒንግ ቻይና ወደ ከባቢ አየር የምትለቀውን በካይ ጋዝ ትቀንሳለች ብለው ቃል ቢገቡም ዛሬም ድረስ ግን ቻይናውያን የችግሩ ሰለባ መሆናቸው እንደቀጠለ ነው፡፡ (ቢቢሲ እና ቴሌግራፍ)