የበሻሌ አካባቢ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች መንግስት ቃል የገባላቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አላሟላልንም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ በሻሌ ትምህርት ቤት አካባቢ ለልማት ቦታው ይፈለጋል በሚል ምክንያት መንግስት ለዓመታት ከኖርንበት መሬታችን ቢያስነሳንም ቃል የተገባልን የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቆዎቻችን አልተመለሱም ለከፋ ችግርም ተጋልጠናል ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለዛሚ ቅሬታቸውን አቅርበዋል ፡፡
ስሜ አይገለፅ ያሉት የሰባ ዓመት አዛውንት በወቅቱ መንግስት መሬቱን ለልማት እፈልጋለው ሲለኝ 40.000 ካሬ ሜትር የሆነ የእርሻና የመኖሪያ መሬቴን መንግስት ወስዶ አሁን እኔንና መላ ቤተሰቤን ዞር ብሎ አላየም ችግር ላይ ነኝ ብለዋል፡፡
የአካባቢው ኗሪ የሆኑት አርሶ አደር አሰፋ አርሶ አደሩ አርሶ እንዳይበላ እዚህ ግባ በማይባል ካሳ መሬቱን መወሰዱ ሳያንሰው ቃል የተገባልን የመንገድ የመብራት ስራ ባለመሰራቱ ችግር ላይ ወድቀናል ሲሉ ስሜ እንዳይገለፅ ያለው ወጣት እኛ ወጣቶች በመንግስት አካላት ተደራጅታችሁ ስራ ትጀምራላችሁ ተብለን ነበረ አሁን ግን ተታለናል ይላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና መህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የልማት ተነሺ አርሶ አደር የልማት መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኩርኩራ ሙሉ ስማቸው እንዲገለፅ ፈቃደኛ ባይሆኑም ዛሚ ስለጉዳዮ አነጋግሮ ቢሮአችን ከተቋቋመ አንድ ዓመቱ ነው ይህን መረጃም ለመስጠት አንችልም ብለውናል፡፡
የቢሮ አላፊው ይህን ቢሉንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2009 እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ አቅጣጫ ሪፖርቱ ላይ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ከ22 ሺህ በላይ የልማት ተነሺ አርሶ አሰደሮች እና ቤተሰቦች መረጃ መደረጀቱንና ለ396 የአርሶ አደር ልጆች በማዕድን ስራ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ይላል፡፡
ምትኬ ቶሌራ

Wednesday, 19 July 2017 07:22

የሶማሌ መንግስት ለቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ ወርሃዊ የአርባ ሺህ የአሜሪካን ዶላር የጡረታ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው አፀደቀ፡፡

የሶማሌ መንግስት ለቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ ወርሃዊ የአርባ ሺህ የአሜሪካን ዶላር የጡረታ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው አፀደቀ፡፡
በአሁኑ ወቅት ኑሮዋቸውን በታንዛኒያ ያደረጉት የቀድሞ የሶማሌ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ የአገራቸው ካቢኔ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ስብሰባ ለጡረታዎ በሚል በየወሩ የአርባ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ክፍያ እንዲያገኙ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ክፍያው የፀጥታ፣ የመኖሪያ እና የጉዞ ወጪዎችን ያካተተ እንደሆነ ተገልፆዋል፡፡ ይህንን ውሳኔ ያሳወቁት የአገሪቱ የመረጃ ሚኒስትር አብዲርሃማን ኦስማን ናቸው፡፡ የካቢኔው ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኃላ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሉት ለቀድሞው ፕሬዝደንት ከተወሰነው የጡረታ ክፍያ ባሻገር የተሻሻለውን የሚዲያ ሕግ እና አዲሱን የፀረ ሽብር ሕግ ማፅደቃቸውን ተናግረዋል፡፡ በካቢኔው የፀደቀው የቀድሞ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ የጡረታ ክፍያ የአገሪቱ ፓርላማ እንዲያፀድቀው ይጠበቃል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ እ.ኤ.አ በጥቅምት 8ቱ ምርጫ ሳይቀናቸው ቀርቶ ከሥልጣን መውረዳቸው የሚታወስ ነው፡፡ በአገሪቱ የሚኖሩ ከ 43 በመቶ በላይ ዜጎች በቀን ከአንድ ዶላር በታች ነው የሚያገኙት፡፡ ከዚህም በበለጠ አገሪቱ የሽብርተኛው አል ሸባብ መናኽሪያ ሆናለች፡፡
ዘገባው የአፍሪካ ኒውስ ነው፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

Wednesday, 19 July 2017 07:19

ደቡብ ሱዳን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አወጀች፡፡

ደቡብ ሱዳን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አወጀች፡፡
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ለሶስት ወራት የሚቆይ ነው ያሉትን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል አውጀዋል፡፡ በትላንትናው ዕለት ምሽት በአገሪቱ ኤስ. ኤስ. ቢ. ሲ. የቴሌቭዥን ጣብያ ላይ በተላለፈው ድንጋጌ መሰረት በሰሜን ምዕራብ በሚገኙት ጎጅሪያል ከተማ፣ በቶንጂ አንዳድ አካባቢዎች፣ ዋሁ እና አዊል ከተሞች ላይ ነው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታወጀው፡፡
በደቡብ ሱዳን የዕርስ በርስ ጦርነት ብዙዎች ለህልፈት እና ለስደት እየተዳረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ በብሄሮች መካከል የተፈጠረው የዕርስ በዕርስ ጦርነት በታላቋ ባኅር ኤል ጋህዜል ክልልም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
ከሱዳን እ.ኤ.አ በ 2011 ነፃነቷን ያገኘችው ደቡብ ሱዳን ከሁለት አመታት በኃላ እ.ኤ.አ በ 2013 ወደ እርስ በዕርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ለእርስ በእርስ ጦርነቱ እንደ መነሾ ተደርጎ የሚወሰደው አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ምክትላቸው የነበሩትን ሪክ ማቻርን መፈንቅለ መንግስት ሊፈፅምብኝ አሲረዋል በሚል ምክንያት ከስልጣናቸው ካነሱ በኃላ ነው፡፡
አሁን በአገሪቱ ያለው ቀውስ ከነዳጅ የምታገኘው ገቢ ክፉኛ እየጎዳውና የግብርና ዘርፉንም እያሽመደመደው ነው ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

Tuesday, 18 July 2017 10:43

ኢራን ሲሰልለኝ ነበር ያለችውንና አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው ላይ የእስር ቅጣት አስተላለፈች፡፡

ኢራን ሲሰልለኝ ነበር ያለችውንና አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው ላይ የእስር ቅጣት አስተላለፈች፡፡
ኢራን ዢዊ ዋንግ የተሰኘውና ቻይና-አሜሪካዊ የፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የ 37 ዓመት ግለሰብ ላይ ነው የ10 ዓመት እስር ውሳኔ ያስተላለፈችው፡፡ እንደ ኢራን ፍርድ ቤት ዳኞች ገለፃ ዋንግ የተያዘው አገሪቱን ባለፍው ሚያዝያ ወር ላይ ለቆ ለመውጣት በሞከረበት ወቅት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በዋንግ ላይ ውሳኔ እንዳስተላለፈው ፍርድ ቤት ገለፃ ከሆነ ሰውየው የኢራንን ጥብቅ መረጃዎች ከአሜሪካ እና እንግሊዝ የተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ሲሰልል ነበር ብሏል፡፡ ከመያዙ በፊትም የተለያዩ የአገሪቱ 4500 ገፅ መረጃዎችን ዲጂታል በሆነ መንገድ አጠናክሮ መያዙ እንደተደረሰበት ተገልፆዋል፡፡
ቴህራን ከሰባ የሚልቁ ሰዎች አገሬን እየሰለሉ ነበር በሚል ፍርድ ተሰጥቶዋቸው እስር ቤት ይገኛሉ፡፡ አሁን በዢዊ ዋንግ ላይ የተላለፈውን የ 10 ዓመት የእስር ፍርድ ተከትሎ አሜሪካ ውሳኔውን በመቃዎም ዜጋዋ እንዲለቀቅና ክሱም የተፈበረከ ወሬ እንደሆነ እየተናገረች ነው፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

Tuesday, 18 July 2017 10:41

የፈረንሳይ አዲሱ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን የአሜሪካ አቻቸውን ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንዲመለሱ አሳምኜያቸኃለሁ ብለው እንደሚያስቡ ተናገሩ፡፡

የፈረንሳይ አዲሱ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን የአሜሪካ አቻቸውን ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንዲመለሱ አሳምኜያቸኃለሁ ብለው እንደሚያስቡ ተናገሩ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራፕ አገራቸው እ.ኤ.አ በ 2015 በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ከተደረሰው የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አገራቸውን ማስወጣታቸውን ተከትሎ ከተለያዩ አገራት እና ግለሰቦች ውሳኔያቸው ትክክል እነዳልሆነ የሚገልፁ መልዕክቶች ሲተላለፉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ፕሬዝደንት ትራፕ ፈረንሳይን በጎበኙበት ወቅት ከፈረንሳዩ አቻቸው ማክሮን ባደረጉት ንግግር ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አገራቸውን በሚመልሱበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡ በዚህም ማርኮን እንዳሉት ዶናልድ ትራፕ ጉዳዩን በድጋሚ ለማጤንና መፍትሄ ለመፈለግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀውልኛል ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይም ጥልቅ ንግግር ማድረጋቸውን ማክሮን አክለው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራፕ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መውጣታቸውን ባሳወቁበት ሰሞን ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣልያን በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት አገሪቱ ያሳለፈችው ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነና ውሳኔውም ሊቀየር የሚችል እንደሆነ መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡ አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት በመውጣቷ ምክንያት ለአለም የ 1.3 ዲግሪ ሴልሺየስ ሙቀት እንዲጨምር ታደርጋለች ሲል ኢንዲፔንደንት እና ቢቢሲ ዘግበዋል፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

Tuesday, 18 July 2017 10:40

ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ወታደራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ንግግር ለማድረግ ጥያቄዋን አቀረበች፡፡

ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ወታደራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ንግግር ለማድረግ ጥያቄዋን አቀረበች፡፡
ፒዮንግያንግ ከሳምንታት በፊት የሞከረችውን የርጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ሙከራ ተከትሎ በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ውጥረቱ ከፍ ካለ በኃላ ነው ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ንግግር እንዲደረግ ጥሪውን ያስተላለፋችው፡፡
የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣን እንዳሉት ንግግሩ በዋነኝነት አላማውን ማድረግ ያለበት በሁለቱ አገራት ድንበር መካከል ያለውን ውጥረት ከሚያንሩ ጉዳዮች ስለሚታቀቡበት ሁኔታ መሆን መቻል አለበት፡፡ ፕሬዝደንት ሙን ጃ ኢን በበርሊን ቆይታቸው ወቅት እንዳሉት ደግሞ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክቶ ከምን ግዜውም በበለጠ አሁን ላይ ንግግር መድረግና የሰላም ስምምነትም መፈፀም እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ አክለውም ሰሜን ኮሪያ የኒውክለር ልማቷን እንድታቆም ለሚፈልጉ ሁሉ በአገራቸውና በሰሜን ኮሪያ መካከል የሚደረገው ንግግር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከደቡብ ኮሪያ የቀረበውን ይህንን የእንነጋገር ጥሪ አስመልክቶ እንካሁን ድረስ ከሰሜን ኮሪያ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡ ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የአህጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ባለቤት ለመሆን ያላትን ውጥን እውን ለማድረግ ሙከራዋን አጠናክራ መቀጠሏ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም የአህጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓና ሙከራውም የተሳካ ነበር ማለቷ ይታወሳል ሲል ሚካኤል ጌታሠጠኝ ቢቢሲ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል፡፡