ሰኔ 11/2008 ዓ.ም

የደቡብ ኮሪያ መንግስት በትናንትናው ዕለት 500,000 የአሜሪካን ዶላር የሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረጉ ተገልጧል፡፡ ይኸው ድጋፍ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ሲሆን የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ቲም ሙን ሀን እንዲሁም ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉነህ ወልደማሪያም በተገኙበት  በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጽ/ቤት ርክክቡ ተደርጓል፡፡

በአገራችን 2007/2008 ዓ.ም በኤልኒኖ ክስተት የመኸርና የበልግ ዝናብ እጥረት በማጋጠሙ በተከሰተው ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ህዝብ ለጉዳት መጋለጡን መሰረት በማድረግ በጃንዋሪ 2016 የወጣውን የሰብዓዊ ሰነድ መነሻ በማድረግ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል የተሰጠ የመጀመሪያ ድጋፍ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያና ደቡብ ኮርያ ካላቸው የቆየ ወዳጅነትና ትብብርም በተጨማሪ በቀጣይ አገሪቱ በምታደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎችም የደቡብ ኮርያ መንግስት የቅርብ ድጋፍ እንደማይለይ አምባሳደር ቲም ሙን ሀን ገልፀዋል፡፡

ይኸው ድጋፍ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ድርቁ በተከሰተባቸው የተለያዩ አካባቢዎች እየተደረገ ባለው ድጋፍ ተጨማሪ በመሆን ጥቅም ላይ እንደሚውል አቶ ሙሉነህ ወ/ማሪያም ገልፀዋል፡፡

ምንጭ- ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

ሰኔ 09/2008 ዓ.ም

የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብተማሪያም ደመወዝ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከመደበኛ እና ከበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ከ128 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የዓለም ደም ለጋሾች ቀን ዘመቻ በዋናነት የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች በለገሱት ደም ህይወታቸው የተረፉ ሰዎችን ታሪክ ማንፀባረቅና የመደበኛ በጎ ፍቃድ ደም ለጋሾች ህይወት አድን ስራን ቀጣይ እንዲያደርጉት ማነቃቃት፣ እንዲሁም ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ ጤንነቱ ተጠብቆ በበጎ ፍቃድ ደም እንዲለግስ ማነቃቃት ነው ብለዋል፡፡

አስተማማኝ የደም አቅርቦት የህመምተኞችን ህይወት በማራዘም የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ከማስቻሉም በላይ ውስብስብ የሆኑ የህክምና ስራዎችን፣ የእናቶችና የህፃናት ህይወት የማዳን ተግባርን በከፍተኛ ደረጃ ማቃለል ችሏል፡፡ በአለም ላይም በብዙ አገሮች በቂና ደህንነቱ የተጠበቀ ደም የማቅረብ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው የሚታወቅ ሲሆን በዋናነት በቂና አስተማማኝ የደም አቅርቦት ሊገኝ የሚችለው ያለማቋረጥ ከመደበኛ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች በሚገኝ የደም ልገሳ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ መከበር የጀመረው የበዓል ስነ-ሥርዓቱም እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ለ20 ሚሊዮን ህዝብ የፅሑፍ መልእክት የሚላክ፣ ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር የእግር ጉዞ የሚደረግ፣ ደም ለጋሾችን የማመስገንና እውቅና የመስጠት፣ ስለ ደም ባንክ አገልግሎት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን የመስራትና ከአዲስ አበባ ወጣት ፎረሞች ጋር በመሆን ደም የማስለገስ ተግባራት እንደሚከናወኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዘንድሮ የደም ለጋሾች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ መከበር የጀመረ ሲሆን በአሉም “ደም ያስተሳስረናል” በሚል መሪ ቃል እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ይቀጥላል፡፡

ምንጭ - የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

ግንቦት 29/2008 ዓ.ም

ከቀኑ 9፡30 ሰዓት በአዲስ አበባ የጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢን፣ ሜትሮሎጂ እና ተክለሀይማኖት አካባቢዎችን በጎርፍ ያጥለቀለቀ ሲሆን በሰው ላይ ምንም ጉዳት አላደረሰም ተብሏል፡፡ ጎርፏ ስድስት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የገባ ሲሆን ሶስት መቶ አስር ሺ ብር የሚገመት የንብረት ውድመትንም አስከትሏል፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ሰራተኞች በየመኖሪያ ቤቶቹ የገባውን ውሀ ለማውጣት ስድስት ሰዓታትን የፈጀ እርዳታንም ሲሰጡ እንደነበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 29/2008 ዓ.ም

እሁድ ምሽት 2፡30 ሰዓት በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪዎች የመኝታ ፍራሽ ማከማቻ በሆነ ክፍል ውስጥ የተነሳው እሳት አራት ተማሪዎች በጭስ እንዲታፈኑ ያደረገ ሲሆን አንድ መቶ ሺ ብር የሚገመት የንብረት ውድመትም አስከትሏል ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡

አደጋ የደረሰባቸው ሁለት ተማሪዎች በሚኒሊክ ሆስፒታል ሁለቱ ደግሞ በየካ ጤና ጣቢያ የህክምና እርዳታን እያገኙ እንደሆነ የተናገሩት ሀላፊው የእሳቱ ትክክለኛ መንስኤም በፖሊስ እየተጣራ እንደሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡

እሳቱን ለማጥፋት 12 ሺ ሊትር ውሀ፣ 14 ባለሙያዎች እና 2 አምቡላንስ እንዲሁም ሁለት የአደጋ መከላከያ መኪናዎች ተሰማርተው እንደነበርም ተገልጧል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 23/2008 ዓ.ም

የኮድ ቁጥሩ 12 የሆነውና ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወሳጆች ቀርቦ የነበረው የእንግሊዘኛ ፈተና ተሰርቆ መውጣቱ በመታወቁ ፈተናው እንዲሰረዝ መደረጉና ሌሎች ፈተናዎችም ላለመሰረቃቸው ማረጋገጫ ባለመኖሩ አጠቃላይ የፈተና ሂደቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ዛሚ ከትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ምስጋና ፀጋዬ እንደሰማው እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም እንደ አማራጭ የሚቀርቡና ለመጠባበቂያ ተብለው ተዘጋጅተው የነበሩ ፈተናዎች በመኖራቸው ፈተናው ከአንድ ወር በኋላ ማለትም ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ድረስ በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች ዳግም ይሰጣል ብለዋል፡፡ አቶ ምስጋና ፀጋዬ አክለውም የፈተና ዝግጅቱና አሰጣጡ በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ የሚከናወን ይሆናል ያሉ ሲሆን የህትመትና የስርጭት ስራውም በተመሳሳይ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበታል ብለዋል፤ ተፈታኞችም ተገቢውን ዝግጅት አድርገው ከአንድ ወር በኋላ ዳግም ለፈተና ለመቀመጥ ይዘጋጁ ሲሉ ለዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 23/2008 ዓ.ም

ለመላው ህዝብ እና ተፈታኞች ይቅርታ የጠየቁት የ12ኛ ክል ፈተና ተሰርቆ መውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡ ትናንት ሌሊት 8፡00 ሰዓት ላይ በማህበራዊ ድረ-ገፅ የተለቀቀው ፈተና ለተማሪዎች ከሚታደለውና በፊታቸው ከሚከፈተው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በዚህም ተሰርቆ መውጣቱ መረጋገጡን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ምስጋናው ፀጋዬ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ተሰርቆ መውጣቱ የተረጋገጠው ኮድ 12፤ የእንግሊዝኛ ፈተና ሲሆን ለ4 ተከታታይ ቀናት የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና ተቋርጧል፤ ላልተወሰነ ጊዜም ተራዝሟል መባሉ ተሰምቷል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)