Thursday, 06 July 2017 09:51

ደቡብ ሱዳን የስዋሂሊ ቋንቋ የአገሪቱ ይፋዊ መግባቢያ እንዲሆን ልታደርግ ነው፡፡

ደቡብ ሱዳን የስዋሂሊ ቋንቋ የአገሪቱ ይፋዊ መግባቢያ እንዲሆን ልታደርግ ነው፡፡
የስዋሂሊ ቋንቋ በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (EAC) አባል በሆኑ አገራት ይተገበራል:: ደቡብ ሱዳንም የዚህ ማህበረሰብ አባል ለመሆን ከሚጠበቅባት ነገሮች መካከል አንዱ ቋንቋውን መጠቀም ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብን መስራች ከሆኑት አገራት መካከል ኬንያ፣ ዩንጋዳ እና ታንዛኒያ ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ጎን ለጎን የስዋሂሊ ቋንቋን ይፋዊ ቋንቋቸው አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
ሩዋንዳ ከብሔራዊ መግባቢያዋ ኪንያሩዋንዳ፣ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዘኛ ቀጥሎ በአራተኝነት መግባቢያዋ እንዲሆን ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ነች፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት የስዋሂሊ ቋንቋን እንዲያስተምሩለት በማሰብ ከታንዛኒያ መምህሮች እንዲመጡ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ጥያቄውን ያቀረቡት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝደንት ታባን ዴንግ ሲሆኑ ጥያቄውንም ያቀረቡት የአፍሪካ ሕብረት ከተጠናቀቀ በኃላ እንደሆነ የታንዛኒያው ምክትል ፕሬዝደንት ሳሚያ ሃሰን ለሲቲዝን ለተባለው የዜና አውታር ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የጤና፣ የግብርና እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ታባን ዴንግ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
ዘገባው የአፍሪካ ኒውስ ነው፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ በሚፈለገው መጠን ብድርን የሚደፍር ትውልድ መገንባት አልተቻለም ሲል በሌላ በኩል ከአጠቃላይ ተጠቃሚዎቹ 80 በመቶ ለመበደር አላማ የሚመጡ ሆነዋል፡፡
የዜጎች ቀጣይ እድገት ሊመዘገብበት የሚችለው ቅደመ ቁጠባን በማዳበር ለሚፈልጉት ዓላማ ማስፈፀሚያ ብድር መወሰድ ነው ሲሉ የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ስሩር ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በቅድሚያ ቆጥቦ መበደርን ይፈራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት የህብረት ስራ ማህበራት መካከል አዋጭ የገንዘብ እና ብድር ተቋም አንዱ ሲሆን ተቋሙ እስከ መጋቢት 30/ 2009 ዓ.ም ድረስ 4893 አባላትን ማሰባሰብ ችሎአል፡፡ከዚህም ውስጥ 457 አባላት ለቤት መግዣ እና 338 ያህሉ ደግሞ ተሸከርካሪ ለመግዛት የተበደሩ ናቸው፡፡ የቁጠባ ባህሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይፋ ቢደረግም የተናጠል ቁጠባው አሁንም እድገት ማሳየት አለመቻሉን የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የፋይናንስ ህብረት ስራ ማህበራት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሀኑ ዱፌራ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
የተበዳሪውን ማህበረሰብ ስጋት እና ፍራቻ ለመቀነስ አዳዲስ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው የሚሉት አቶ ዑስማን ስሩር በርካታ ገንዘብን ሰብስቦ በባንክ ማስቀመጥ ሳይሆን ለብድር አቅርቦት በማቅረብ ላይ ችግር በመኖሩ በሌላ በኩል የተበዳሪውን ፍላጎት ማርካት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመሰረታዊና ዩኒየን የገንዘብ ቁጠባና ህብረት ስራ ማህበራት እስከ አሁን 8.8 ቢሊዩን ብር ሲሰበሰብ 3.2 ቢሊዩን ብር ደግሞ ካፒታል ያስመዘገቡት ተቋማቱ አጠቃላይ ድምር 12 ቢሊዩን ብር በነዚህ የህብረት ስራ ተቋማት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የብድር አገልግሎት ለማግኘት ግለሰቦች በቅድሚያ የሚፈልጉትን የብድር መጠን 25 በመቶ ለተከታታይ 6 ወራት መቆጠብ እንዳለባቸው ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የተበዳሪዎችን መጠን በተመለከተ ከሚቆጥብት በላይ ለብድር የሚጠይቁት ገንዘብ ይልቃል የሚሉት ሀላፊው የብድር መጠኑ ከቆጣቢው ጋር ሲነፃፀር ተበዳሪው እንደሚልቅ ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ዘመናዊ የህብረት ስራ ከተጀመረ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን የህግ ድጋፍ አግኝቶ የተጀመረውም በንጉሱ ዘመን ነው፡፡ለመጀመሪያ ጊዜ የገበሬዎች የእርሻ ኅብረት ስራ ድንጋጌ ቁጥር 44/1953 ወጥቶ ስራ ላይ ውሏል፡፡ ለዚህ ድንጋጌ መውጣት ምክንያት የሆነው በከተማና በገጠር የነበረው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ሲሆን በከተማ የነበረውን ስራ አጥነትን ለመቅረፍ፣ከገጠር ወደ ከተማ የነበረውን ፍልሰት ለማስቀረት፣ በወቅቱ በመሬት ይዞታ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ለመፍታት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

ኢትዮጲያ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን ጥሩ መንገዶችን ተከትላለች ተብሏል፡፡
ኢትዮጲያ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን የተለያዩ የግብርና ጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ስነ ምህዳሩ እና ዘመናዊ ተክኖሎጂዎችን መጠቀሟ ሴክተሩን ለማዘመን ያግዛል ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጲያን ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ለማዘመን የኤክስቴንሽን ሰራተኞች መሳተፋቸው የጥናትና ምርምር ተቋማት በባለሙያ የታገዘው ግብርናዋ እንዲዘምን አግዞታል ተብሏል፡፡
የግብርና እና የተፈጥሮ አብት ሚኒስተር በ2016-2017 የምርት ዘመን ከአገሪቱ አጠቃላይ ዕድገት ኢትዮጲያ 13.8 ሚሊዮን ኤክታር መሬት በተለያዩ አዝእርቶች እንዲሸፈኑ በማድረግ ከ348 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በሚመጣው የመኧር ወቅት ታገኛለች ብለዋል፡፡
10.7 ሚሊዮን ኤክታር የሚሆነው መሬት እየለማ መሆኑንና ከዛ ውስጥ ደግሞ 3.5 ሚሊየን የሚሆነው ሄክታር መሬት ዘር ተዘርቶባቸዋል ከዚህም 14 ሚሊየን ኤክታር ምርት ይገኛል ተብሏል፡፡
ባሁኑ ወቅት ገበያ ተኮር የሆነ ግብርናን ለመምራት በአገሪቱ በተመረጡ 239 ወረዳዎች በምርጥ ዘር የታገዙ የአትክልትና ፍራፍሬ የእንስሳት ማርባት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአማራ እና ኦረሚያ ክልሎች የሚገኙ ገበሬዎች በኤክታር ከ66 እስከ 70 ኩንታል የሚደርስ ምርት እያገኙ ነው ተብለዋል፡፡
ምርቱን ከዚህ የላቀ እንዳይሆን በሴክተሩ ላይ ያለው የአቅም ውስንነት የገበያ ትስስሩ የላላ መሆን ተፅህኖ አሳድሮብናል ብሏል፡፡
ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጅማሮ ላይ ምርታማ የሚያደርጉ እና የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ ምርቶች ላይ ትኩረት አድረገን ለመስራት የያዝንውን አቅጣጫ እንቀጥልበታል ብለዋል፡፡
All African.com ጥቅሳ ምትኬ ቶሌራ ዘግባዋለች፡፡

Wednesday, 05 July 2017 12:34

የአፍሪካ ሕብረት በጀት ከውጪ ሀገራት እና ህብረቶቻቸው ድጎማ መንተራሱን ማቆም ባልቻለበት ጊዜ የዙምባቤው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የውጪ ርዳታ የመቀበል በሽታ እንዲለቀን ሲሉ ለአፍሪካ ህብረት የአንድ ሚሊየን ዶላር ድጎማ አድርገዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት በጀት ከውጪ ሀገራት እና ህብረቶቻቸው ድጎማ መንተራሱን ማቆም ባልቻለበት ጊዜ የዙምባቤው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የውጪ ርዳታ የመቀበል በሽታ እንዲለቀን ሲሉ ለአፍሪካ ህብረት የአንድ ሚሊየን ዶላር ድጎማ አድርገዋል፡፡

እንደ አንድ በ54 ሀገራት እንደተቋቋመ አህጉር አቀፍ ድርጅት የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ በቋሚነት በሚባል ደረጃ አንዱ ሀገር ሲሻለው ሌላውን ከሚያመው የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመውጫ ቁልፍ የሆነው የገንዘብ በጀት ጥያቄ ቀውስ ከተመሰረተበት ከ16 አመት በፊት ጀምሮ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

ህብረቱ አማራጭ ተገቢ ቀጣይነታቸው የተረጋገጠ የገንዘብ ምንጮችን የሚያገኝበትን መንገድ እንደሚያፈላልግ በተለያዩ ስብሰባዎቹ ላይ ይመክራል፡፡
ከሁለት አመታት በፊት አዲስ የበጀት ሞዴል ሲያስተዋውቅ የታሰበውም ይህ ነበር፡፡ ነገር ግን ህብረቱ አሁንም በውጪ ሀገራት እና በህብረታቸው የፋይናንስ ድጋፍ ላይ አይኑን ጥሎ ተስፋ አድርጎ የተሰጠውን እየቃረመ ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት በ2009/10 የበጀት አመት የህብረቱ 66.3 በመቶ በጀት የተሸፈነው በአልጄሪያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ እነዚህ ሀገራት የተለያዩ የውስጥ እና የውጪ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል፡፡
እናም በ2010 ከነበረው ከውጪ አጋር ሀገራትይቀበል የነበረው የገንዘብ ርዳታ ከነበረው 45 በመቶ ባሳለፍነው አመት በጀቱ ወደ 70 በመቶ አድጓል፡፡

ለአብነት ያክልም ከአውሮፓ ኮሚሽን በ2010 91 ሚሊዩን ፓውንድ ተቀብሎ የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር ከአምስት አመታት በኋላ ወደ 300 ሚሊዩን ፓውንድ አድጓል፡፡ ከተሰጠው ድጎማም 90በመቶው ለሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ ስራ ነበር የተመደበው፡፡

አሜሪካ፣ የአለም ባንክ፣ ቻይና እና ቱርክም ለህብረቱ በጀት እርዳታ ከሚያደርጉት መካከል ናቸው፡፡

ለአፍሪካ ህብረት በጀት ከውጪ ሀገራት የሚደረገውን ድጋፍ ለማስቀረት በህብረቱ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ በተዘጋጀ የህብረቱ ከፍተኛ ደረጃ የፓኔል ውይይት ላይ ቀርቦ ነበር፡፡

ይህ አማራጭ ከእያንዳንዱ በየሀገራቱ በሚገኙ ሆቴሎች ከሚስተናገድ እንግዳ የ2 ዶላር ግብር፣ ከአፍሪካ ተነስተው ለሚደረጉ ወይም ወደ አፍሪካ መዳረሻቸውን አድርገው ለሚደረጉ ማንኛውም የአውሮፕላን በረራዎች ከእያንዳንዱ 10 ዶላር ግብር እንዲከፈል ተነጋግረው የነበረ ሲሆን በእነዚህ ሁለት አማራጮችም በ2017 ለህብረቱ 728 ዶላር ማሰባሰብ ይቻላል ተብሎ ነበር፡፡

በተጨማሪም ፓኔሉ በሀገራቱ ውስጥ ከሚላኩ አጭር የጽሁፍ መልእክቶች ከእያንዳንዳቸው 0.005 ዶላር በመሰበሰሰብ በአጠቃላይ በዚህ አመት 1.6 ቢሊየን ዶላር እንዲያሰባስብም ሀሳብ አቅርቦ ነበር፡፡
የአፍሪካ ህብረት ጉባኤው የአነዚህን ገንዘብ የማሰባሰቢያ አማራጮች እና ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ ከ4 አመታት በፊት አጽድቆ ነበር፡፡

የአባል ሀገራቱን መዋጮ መጨመርን በተመለከተም ለመወያየት እቅድ ይዘው ነበር የተለያዩት፡፡
ግና ምንም እንኳን ሀሳቡ ታላቅ እና የሚደገፍ ቢመስልም አባል ሀገራቱ በዜጎቻችን ላይ የግብር ጫና ይበረታባቸዋል አሉ፡፡ በቱሪዝም ልማት ላይ ገቢያቸውን የመሰረቱት ሀገራትም የበረራ ግብሩ በኢንዱስትሪው ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ጫና ያሳስበናል ብለው ገለጹ፡፡ የሞባይል ባለአክሲዩኖች ደግሞ በሚሊዩን የሚቆጠሪ ደንበኞቻችን ላይ ተጨማሪ ገንዘብ ለአጭር መልእክት ጽሁፍ መጠየቅ ንግዳችን ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡
እናም በ2014 የህብረቱ ፋይናንስ ሚኒስትሮች የከፍተኛ ደረጃ ፓኔሉን ውሳኔ ተቃወሙ የታለመው ሳይፈታ የስብሰባ አጀንዳ ሆኖ ቀረ፡፡

የአፍሪካ ህብረት በአሁን ወቅት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዩች ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ አጀንዳ 2063 እና ቀጣይነት ያለው ልማት ጎሎች እና በዚሁ ስር Sustainable Development Goals SDGን፡፡ ኤስ ዲ ጂ የልማት እቅድ ብቻ በአመት እስከ 613 ቢሊየን ዶላር ገቢ ከአባላቱ ማስገባት ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ለሰላም እና ደህንነት ሌላ በጀት ያስፈልጋል፡፡
አባል ሀገራቱ ለህብረቱ ፈንድ የሚያዋጡት ገንዘብም በአመታዊ የኢኮሚ እድገታቸው ተወስኗል፡፡
በዚህ የአከፋፈል መንገድ ሀገራቱ በሶስት ተከፍለዋል፡፡

ህብረቱ በዚህ አመት አዲስ ለበጀቱ ፈንድ እነዲሆነው አባል ሀገራቱ በዋናነት በሚያስመጧቸው እቃዎች ከእያንዳንዱ ላይ 0.2 በመቶ ግብር ለማሰባሰብ ተግባራዊ እንዲደረግ የታለመ ፈንድ ማድረጊያ ሞዴል አቅርቧል፡፡
ነገር ግን አሁንም ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት እቅዱ የተለያዩ ችግች እንዳሉበት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ይህ እቅድ ሁሉም አባል ሀገራት በየክልላቸው እንዲያዋጡ ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሰረትም ግብሩን በተመለከተ ሀገራቱ የራሳቸው የሆነ የገንዘብ ተቋም አልያም የጉሙሩክ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት መርጠው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያዛል፡፡ ሀገራቱ ያለቸው የጉሙሩክ አገልግሎት ሞዴሉ ስኬታማ እንዳይሆን ሊያግደው እንደሚችልም ተገልጾል፡፡
ራሷን ችሎ በጀቱን ማግኘት በዚህ ሲሉት በዚያ እያለ የውሀ ቅዳ የውሀ መልስ ስራ የሆነበት የአፍሪካ ህብረት ይህን አዲስ ሞዴል እስካሁን ተግባራዊ ያደረጉት ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቻድ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ እና ኢትዩጲያ ብቻ ናቸው፡፡
የዚህ ሞዴል ተገባራዊነትም በአባል አገራቱ ምላሻቸውን ለመስጠት በሚወስድባቸው ጊዜ ይወሰናል፡፡
ይህን የተረዱ የሚመስሉት የዙምባቤው ፕሬዚዳንት ሙጋቤም ሀገራቱን ለአዎንታ ተነሱ ቶሎ እንጀምር በሚል አስተያየት የውጪ ርዳታ የመቀበል በሽታችን እንዲለቀን ብለው ሀገራቸው የቁም ከብት አጫርታ 1 ሚሊዩን ዶላር ለህብረቱ እንድታበረክት አድርገዋል፡፡
ኢኮኖሚስቶች ግን የፕሬዚዳንቱን ስራ የገንዘብ እና የምግብ ቀውስ ባለበት ወቅት እርዳታ መስጠታቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
ህብረቱ ግን ከአባል ሀገራት ሆነ ከውጪ የእርደታ ገንዘቡን ከመቀበል አላፈገፈገም፡፡
ከቢቢሲ፤ ከኢንስቲቲውት ፎር ሴኪውሪቲ ስተዲስ፣ ከኢሲዲፒኤም እና ሌሎች ምንጮች የተገኙትን መረጃዎች ለተጠናከረው
ዘገባ ናርዶስ ዩሴፍ፡፡

በወርልድ ባንክ ግሩፕ በየአመቱ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው ዱዊንግ ቢዝነስ (Doing Business) የተሰኘ ሪፖርት ኢትዮጵያን ከ 190 አገራት 159ኛ ደረጃ ላይ አስቀመጠ፡፡
ይህ ሪፖርት በዋነኝነት በአንድ አገር የንግድና ኢንቨስትመንት ተግባርን ለማከናወን የተቀመጡ ደንቦችና በንግድና ኢንቨስትመንት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን የሚቃኝ ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ በአንድ አገር የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥራ ለማከናወንና ሂደቱን ለመጀመር ወሳኝ ናቸው ተብለው የተቀመጡ አስራ አንድ ያህል መስፈርቶች አሉ፡፡ በእነዚህ መስፈርቶች መሰረት አገሪቱ ያገኘችውን ደረጃ ምክንያት በማድረግ ከሪፖርቱ ኢትዮጵያ ምን ልትማርና ልታሻሽል ትችላለች ብለን ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አምርተን ነበር፡፡
በኮሚሽኑ የኢንቨስትመንት ክላይሜት ማሻሻያ እና የኤክስፖርት ተወዳዳሪነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ለማ ፈይሳ በሰጡን ምላሽ የኢትዮጵያን ደረጃ የማሻሻል ሥራ ብቻ ሳይሆን በአለም ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ትልቅ ደረጃ ማድረስ አላማቸው እንደሆነና በዚህ ሪፖርት ግን ከኢትዮጵያ በላይ ካሉት ዩጋንዳና ኬኒያ ትምህርት መውሰድ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
ሚካኤል ጌታሠጠኝ

በአዲስ አበባ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ዘንቦ የኮቢል ነዳጅ ማደያን ከጥቅም ውጪ አድርጓል፡፡
አዲስ አበባ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የቤት ቁጥር 052 የተመዘገበ በተለምዶ እራስ መኮንን ድልድይ አለፍ ብሎ የሚገኝ የነዳጅ ማደያ እሁድ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ጣሪያው ተደርምሶ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርጎታል፡፡
ታድያ በቦታው ተገኝተን የነዳጅ ማደያውን ስራ አሰኪያጅ አነጋግረናቸው የሰጡን ምላሽ አደጋው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የነዳጅ መቅጃዎችን ጨምሮ ምንም አለመቅረፍን ተናግረዋል፡፡
ስራአስኪያጁም አክለው በሰው ህይወት ላይ ምንም የገጠመ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ይሄ የተፈጥሮ ጉዳይ ስለሆነ ማንም ተጠያቂ የሚሆንበት ጉዳይ እንዳልሆነም አስረግጠው ተናግረዋል፡
በሀገሪቱ የነዳጅ ጣቢያዎችን በተመለከተ ከወጡ ጥናቶች መካከል 700 ያህል የነዳጅ ጣቢያዎችን አሎት ነገር ግን በቂ አይደለም፡፡ 700የነዳጅ ማደያ ለ100 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ 103 የነዳጅ ማደያ ብቻ እንዳለ ተገልጾዋል፡፡
ዘገባው የፍሬህይወት ታደሰ ነው