ኢትዮ ቴሌኮም በ2009 በጀት ዓመት የደንበኞቹን ቁጥር ከ57 ሚሊዮን በላይ አደረሰ፤ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ኢትዮጲያ የሞባይል ተጠቃሚ ቁጥሯ ከፍ ይላል ተብሎ ተተንብዮላታል::
ከሰሀራ በታች የሚገኙ የሞባይል ተጠቃሚዎች በ2020 ከ500 ሚሊየን ሊበልጡ እንደሚችል አለም አቀፍ የሞባይል አገልግሎት ሰጪዎች ማህበር አስታውቋል፡፡ በ2016 መጨረሻ420 ሚሊየን የነበረው የሞባይል ስልክ በ2020 የተጠቃሚ ቁጥር 535 ሚሊየን ይደርሳል ተብሏል፡፡
አዲስ ከሚመጡ የሞባይል ተጠቃሚ ሀገራት ውስጥ 115 ሚሊየን የሚሆኑት ከኢትዮጲያ፣ከዲሞክራትክ ኮንጎ፣ ከናይጄሪያና ከታንዛኒያ እንደሚሆኑ በ2017 በወጣው ሪፖርት ተገልጾል፡፡
ኢትዮጲያ ከነዚህ ሀገራት መሀከል ተቀመጠች ሲሆን የሞባይል ስልክ አገልግሎት በሀገሪቱ ከ18 አመት በፊት በ36 ሺ ደንበኞች በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ ወደ 57 ሚሊየን አከባቢ እንደደረሰ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡በ2008 በጀት ዓመት የሞባይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር 45 ነጥብ 96 ሚሊዮን እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ደግሞ ሲነጻጸር ከፍተኛው የናይጄሪያ ሲሆን 216 ሚሊየን የሞባይል ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ እንደሚያሳው ከጥቂት አመታት በሆላ 103 ሚሊየን የሞባይል ተጠቃሚዎች እንደሚኖሩም አሳውቋል፡፡
የሞባይል ተጠቃሚ ቁጥር መጨመር ለአመታዊ ጥልቅ ምርት መጨመር፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው የማህበሩ የ2017 ሪፖርት ያመላክታል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም በያዝነው ዓመት አጠቃላይ የደንበኞችን ብዛት በሁሉም የአገልግሎት ዓይነቶች 57 ሚሊዮን ያደረሰ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ጋር ሲነፃፀር የ16 በመቶ እድገት ያሳያል፡፡
የገቢውን ሁኔታ በተመለከተም በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት15 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ መሆኑን አመልክቷል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲተያይም የ16 በመቶ እድገት አሳይቷል ተብሏል። ያልተጣራ የትርፉ መጠንም በዚሁ 6 ወራት ጊዜ ውስጥ 11 ነጥብ 91 ቢሊዮን መሆኑን መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል። ከዚህ አጠቃላይ ገቢውም ውስጥ ከሞባይል አገልግሎት የተገኘው የገቢ መጠን 74 ነጥብ 5 በመቶውን ይሸፍናል፡፡

በዘንድሮው ክረምት ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ከባድ ጉዳት ለመቀነስ ከ1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የመጠባበቂያ ምግብ ተከማችቶ ተዘጋጅቷል::
የትሮፒካ ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከ5ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ የሚሞቅ ከሆነ ኤልኒኖ ፤ ከ0.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች የሚቀዘቅዝ ከሆነ ደግሞ ላሊና ይባላል ሲሉ የዘርፏ ባለሙያዎች ስለ ተፈጥሮ ክስተቶቹ ኤልኒኖና ላሊና ይናገራሉ፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወቅት አብዛኛው የላኒናን ክስተት ተከትሎ ከባድ ጎርፍ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ሊከሰት እንደሚችልም የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የትንበያ ሪፖርት ያመለክታል። ይህም በሰዎች፣ በንብረትና በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያሰከተላል፡፡ ከመደበኛው መጠን በላይ ይዘንባል ተብሎ በሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ምክንያት የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ለችግር ሲል ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሰራው መረጃ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ 700 ወረዳዎች አሉ ከነዚህ መካከል ለአደጋ ተጋላጭ ተብለው 300 ወረዳዎች ላይ በተካሄደ ጥናት በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሚከሰቱት አደጋዎች ጎርፍና ድርቅ መሆናቸው ተለይቷል፡፡
ታዲያ በዚህ ጉዳይ ላይ በሀገሪቱ በባለፈው አመት በአየር መዛባት (ኤልኒኖ) ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቶ ከ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተረጂ እንደሆኑ ይታወሳል፡፡ በኤልኒኖ ምክንያት በተፈጠረው ድርቅ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህል ከኤጀንሲው ወጪ ተደርጓል። ለሴፍቲኔት ፕሮግራም 130 ሺ ሜትሪክ ቶን ፣ ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ 270 ሺ ሜትሪክ ቶን ተሰጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት አስተዳደር ሊከሰት የሚችለውን ከባድ ጉዳት ለመቀነስ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምግብ ክምችት ማዘጋጀቱን ገልïል፡፡
በ2008 በጀት ዓመት 20 ሺ ሜትሪክ ቶን ታዝዞ በጥራት ጉድለት 7 ሺ 500 ሜትሪክ ቶን ተመላሽ መደረጉን ይታወሳል፡፡ በኤጀንሲው መስፈርት መሠረት ከባዕድ ነገር ንጹሕ መሆኑን፣የእርጥበት መጠኑ፣ አቧራማነቱ፣ ጠጠራማነቱ፣ በተባይ አለመያዙና አለመበላቱ እንዲሁም የተሰባበረና የተጨማደደ አለመሆኑ ይረጋገጣል፡፡
ጥራቱን የጠበቀ እህል ማከማቸት ካልተቻለ ለረጅም ጊዜያት በተቀመጠ ቁጥር እህሉን ለማከም የሚወጣው ወጪ እየጨመረ፣ ንጥረ ነገሩን እያጣ ስለሚሄድ ለሰው ልጅ ምግብነት ወደማይውልበት ደረጃ በመድረስ ኪሳራ ሊያስከትል ስለሚችል በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ይመዘናል፡፡
ከ89 ነጥብ5 በላይ ንጹሕ ከሆነ በሁለተኛ ደረጃነት፣ ከ94 በመቶ በላይ አንደኛ ደረጃ ንጹሕ ሆኖ ገቢ እንደሚደረግም ኤጀንሲው በመስፈርትነት አስቀምጧል፡፡
የላኒናን ክስተት ተከትሎ በሚከሰት ከባድ ዝናብ ብቻ ሳይሆን የክረምት ዝናብ በጨመረ ቁጥር አብዛኞቹ የሀገሪቱ ክፍሎች በስጋት ላይ ያሉ መሆናቸው ይታወቃል።በክረምት ወቅት ይዘንባል ተብሎ በተተነበየው ከባድ ዝናብ 486ሺ 10 ሰዎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የበሻሌ አካባቢ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች መንግስት ቃል የገባላቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አላሟላልንም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ በሻሌ ትምህርት ቤት አካባቢ ለልማት ቦታው ይፈለጋል በሚል ምክንያት መንግስት ለዓመታት ከኖርንበት መሬታችን ቢያስነሳንም ቃል የተገባልን የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቆዎቻችን አልተመለሱም ለከፋ ችግርም ተጋልጠናል ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለዛሚ ቅሬታቸውን አቅርበዋል ፡፡
ስሜ አይገለፅ ያሉት የሰባ ዓመት አዛውንት በወቅቱ መንግስት መሬቱን ለልማት እፈልጋለው ሲለኝ 40.000 ካሬ ሜትር የሆነ የእርሻና የመኖሪያ መሬቴን መንግስት ወስዶ አሁን እኔንና መላ ቤተሰቤን ዞር ብሎ አላየም ችግር ላይ ነኝ ብለዋል፡፡
የአካባቢው ኗሪ የሆኑት አርሶ አደር አሰፋ አርሶ አደሩ አርሶ እንዳይበላ እዚህ ግባ በማይባል ካሳ መሬቱን መወሰዱ ሳያንሰው ቃል የተገባልን የመንገድ የመብራት ስራ ባለመሰራቱ ችግር ላይ ወድቀናል ሲሉ ስሜ እንዳይገለፅ ያለው ወጣት እኛ ወጣቶች በመንግስት አካላት ተደራጅታችሁ ስራ ትጀምራላችሁ ተብለን ነበረ አሁን ግን ተታለናል ይላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና መህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የልማት ተነሺ አርሶ አደር የልማት መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኩርኩራ ሙሉ ስማቸው እንዲገለፅ ፈቃደኛ ባይሆኑም ዛሚ ስለጉዳዮ አነጋግሮ ቢሮአችን ከተቋቋመ አንድ ዓመቱ ነው ይህን መረጃም ለመስጠት አንችልም ብለውናል፡፡
የቢሮ አላፊው ይህን ቢሉንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2009 እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ አቅጣጫ ሪፖርቱ ላይ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ከ22 ሺህ በላይ የልማት ተነሺ አርሶ አሰደሮች እና ቤተሰቦች መረጃ መደረጀቱንና ለ396 የአርሶ አደር ልጆች በማዕድን ስራ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ይላል፡፡
ምትኬ ቶሌራ

Wednesday, 19 July 2017 07:22

የሶማሌ መንግስት ለቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ ወርሃዊ የአርባ ሺህ የአሜሪካን ዶላር የጡረታ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው አፀደቀ፡፡

የሶማሌ መንግስት ለቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ ወርሃዊ የአርባ ሺህ የአሜሪካን ዶላር የጡረታ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው አፀደቀ፡፡
በአሁኑ ወቅት ኑሮዋቸውን በታንዛኒያ ያደረጉት የቀድሞ የሶማሌ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ የአገራቸው ካቢኔ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ስብሰባ ለጡረታዎ በሚል በየወሩ የአርባ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ክፍያ እንዲያገኙ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ክፍያው የፀጥታ፣ የመኖሪያ እና የጉዞ ወጪዎችን ያካተተ እንደሆነ ተገልፆዋል፡፡ ይህንን ውሳኔ ያሳወቁት የአገሪቱ የመረጃ ሚኒስትር አብዲርሃማን ኦስማን ናቸው፡፡ የካቢኔው ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኃላ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሉት ለቀድሞው ፕሬዝደንት ከተወሰነው የጡረታ ክፍያ ባሻገር የተሻሻለውን የሚዲያ ሕግ እና አዲሱን የፀረ ሽብር ሕግ ማፅደቃቸውን ተናግረዋል፡፡ በካቢኔው የፀደቀው የቀድሞ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ የጡረታ ክፍያ የአገሪቱ ፓርላማ እንዲያፀድቀው ይጠበቃል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ እ.ኤ.አ በጥቅምት 8ቱ ምርጫ ሳይቀናቸው ቀርቶ ከሥልጣን መውረዳቸው የሚታወስ ነው፡፡ በአገሪቱ የሚኖሩ ከ 43 በመቶ በላይ ዜጎች በቀን ከአንድ ዶላር በታች ነው የሚያገኙት፡፡ ከዚህም በበለጠ አገሪቱ የሽብርተኛው አል ሸባብ መናኽሪያ ሆናለች፡፡
ዘገባው የአፍሪካ ኒውስ ነው፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

Wednesday, 19 July 2017 07:19

ደቡብ ሱዳን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አወጀች፡፡

ደቡብ ሱዳን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አወጀች፡፡
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ለሶስት ወራት የሚቆይ ነው ያሉትን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል አውጀዋል፡፡ በትላንትናው ዕለት ምሽት በአገሪቱ ኤስ. ኤስ. ቢ. ሲ. የቴሌቭዥን ጣብያ ላይ በተላለፈው ድንጋጌ መሰረት በሰሜን ምዕራብ በሚገኙት ጎጅሪያል ከተማ፣ በቶንጂ አንዳድ አካባቢዎች፣ ዋሁ እና አዊል ከተሞች ላይ ነው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታወጀው፡፡
በደቡብ ሱዳን የዕርስ በርስ ጦርነት ብዙዎች ለህልፈት እና ለስደት እየተዳረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ በብሄሮች መካከል የተፈጠረው የዕርስ በዕርስ ጦርነት በታላቋ ባኅር ኤል ጋህዜል ክልልም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
ከሱዳን እ.ኤ.አ በ 2011 ነፃነቷን ያገኘችው ደቡብ ሱዳን ከሁለት አመታት በኃላ እ.ኤ.አ በ 2013 ወደ እርስ በዕርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ለእርስ በእርስ ጦርነቱ እንደ መነሾ ተደርጎ የሚወሰደው አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ምክትላቸው የነበሩትን ሪክ ማቻርን መፈንቅለ መንግስት ሊፈፅምብኝ አሲረዋል በሚል ምክንያት ከስልጣናቸው ካነሱ በኃላ ነው፡፡
አሁን በአገሪቱ ያለው ቀውስ ከነዳጅ የምታገኘው ገቢ ክፉኛ እየጎዳውና የግብርና ዘርፉንም እያሽመደመደው ነው ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

Tuesday, 18 July 2017 10:43

ኢራን ሲሰልለኝ ነበር ያለችውንና አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው ላይ የእስር ቅጣት አስተላለፈች፡፡

ኢራን ሲሰልለኝ ነበር ያለችውንና አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው ላይ የእስር ቅጣት አስተላለፈች፡፡
ኢራን ዢዊ ዋንግ የተሰኘውና ቻይና-አሜሪካዊ የፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የ 37 ዓመት ግለሰብ ላይ ነው የ10 ዓመት እስር ውሳኔ ያስተላለፈችው፡፡ እንደ ኢራን ፍርድ ቤት ዳኞች ገለፃ ዋንግ የተያዘው አገሪቱን ባለፍው ሚያዝያ ወር ላይ ለቆ ለመውጣት በሞከረበት ወቅት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በዋንግ ላይ ውሳኔ እንዳስተላለፈው ፍርድ ቤት ገለፃ ከሆነ ሰውየው የኢራንን ጥብቅ መረጃዎች ከአሜሪካ እና እንግሊዝ የተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ሲሰልል ነበር ብሏል፡፡ ከመያዙ በፊትም የተለያዩ የአገሪቱ 4500 ገፅ መረጃዎችን ዲጂታል በሆነ መንገድ አጠናክሮ መያዙ እንደተደረሰበት ተገልፆዋል፡፡
ቴህራን ከሰባ የሚልቁ ሰዎች አገሬን እየሰለሉ ነበር በሚል ፍርድ ተሰጥቶዋቸው እስር ቤት ይገኛሉ፡፡ አሁን በዢዊ ዋንግ ላይ የተላለፈውን የ 10 ዓመት የእስር ፍርድ ተከትሎ አሜሪካ ውሳኔውን በመቃዎም ዜጋዋ እንዲለቀቅና ክሱም የተፈበረከ ወሬ እንደሆነ እየተናገረች ነው፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ