አገር አቀፍ ዜናዎች

ሚያዚያ 11/2008 ዓ.ም

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች ህይወታቸው ያለፈ ንፁሃን ዜጎችን ለማሰብ ከነገ ረቡዕ ጀምሮ የሁለት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን አውጇል፡፡

ምክር ቤቱ ከነገ ጀምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ፅ/ቤቶች ለሁለት ቀናት የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስኗል።

በተመሳሳይ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ የሆኑ መርከቦችም ከነገ ጀምሮ የኢፌዴሪ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ የሚያደርጉ ይሆናል።

ባሳለፍነው አርብ ምሽት በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች በደቡብ ሱዳን በኩል ድንበር ሰብሮ በመግባት በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው ከ208 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

እንዲሁም ቁጥራቸው 108 የሚደርስ ህጻናት በታጠቁት ሀይሎች ታፍነው ተወስደዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም ጥቃት ፈጻሚ ወንበዴዎችን ድንበር በመሻገር እርምጃ እየወሰደባቸው ሲሆን፥ ከ60 የሚበልጡ ጥቃት ፈጻሚዎች ተገድለው የጦር መሳሪያም ተይዟል።

በአሁኑ ጊዜም በታጣቂዎች ታፍነው የተያዙትን የማስለቀቁ ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ምንጭ - የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት

 

ሚያዚያ 03/2008 ዓ.ም

በየሁለት ሰከንድ ልዩነት ደም የሚፈልግ አንድ ሰው ያለ ሲሆን ከአገራችን ነባራዊ የህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አንድ ሚሊዮን ከረጢት ደም በአገራችን ይፈለጋል፡፡ ይሁን እንጂ 128ሺ ከረጢት ደም ብቻ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡

ይህም በተለያየ አደጋ፤ ከእርግዝና ጋር እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት የደም አቅርቦቱ ዝቅተኛ መሆኑን የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ዘለቀ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በየሶስት ወር ልዩነት ደም የሚለግሱ መደበኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ሊበረክት ይገባል፤ ይህም የደም አለጋገስ ሂደት የሰውን ህይወት ከማትረፍ ባሻገር ለጋሹን ጤነኛ የደም ባለቤት ያደርገዋል ተብሏል፡፡

የደም ለጋሾች ቁጥር አሁን ላይ ከ8 ሺ በታች በመሆኑ በአገራችን የደም ፈላጊው ቁጥርና አቅርቦት ላይ አለመመጣጠን በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን የገለፁት አቶ አብርሀም ዘለቀ፤ የህክምና እርዳታ የሚሰጡ ከ300 በላይ ተቋማትን ፍላጎት ማርካት ባለመቻሉ በደም እጥረት የሚሞተው ሰው ቁጥር ከፍ ብሏል ሲሉም ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

መጋቢት 27/2008 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ቫይበርና ዋትስአፕ ያሉ የጥሪ አገልግሎት የሚሰጡ አፕሊኬሽኖች ላይ ተጨማሪ ክፍያ ሊጠይቅ ነው የሚለው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነና ይሄን ጉዳይ ይፋ ያደረገው ጋዜጣም ማስተባበያ እንዲሰጥ መጠየቁን የኢትዮ-ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

መጋቢት 26/2008 ዓ.ም

ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከውንጌት ወደ 18 ማዞሪያ አየሄደ የነበረ ኮድ3 365515et የሆነ ከባድ መኪና በ6 መኪኖች ላይ ባደረሰው ጉዳት 3 ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ በ20 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ገልፀዋል፡፡ በአደጋው አንድ ሞባይል ቤትና አንድ ፋርማሲ ቤት ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን እና የአደጋው መንስኤም በመጣራት ላይ መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡

መጋቢት 23/2008 ዓ.ም

በቅርቡ የወጣውን ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል አዋጅና በውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን የሚደነግግ አዋጅ በተግባር ላይ ከማዋል ጎን ለጎን ከሰራተኛ ተቀባይ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ አስገዳጅነት ስምምነት እየተፈፀመ ነው ያሉት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ዳመና ደሮታ ናቸው፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ከኩዌትና ኳታር መንግስታት ጋር የተፈረመ ሰነድ መኖሩን ጠቅሰው ከሳውዲ አረቢያ ጋርም ሀገራቱ የየራሳቸውን ሰነዶች ተለዋውጠው እያጠኑ ሲሆን በአብዛኛው ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም በጥቂት ነጠቦች ላይ አሁንም የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ድርድር እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ሲጠናቀቁ ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው ከመኖር ባሻገር የግድ ወደ ውጭ መሄድ አለብን ብለው ካመኑ በሰላማዊና መብቶቻቸው ተጠብቀው እንዲሰሩ ለማስቻል በፌዴራልና በክልሎች ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዲሱን አዋጅ መሰረት ያደረገ የመዋቅር ለውጥ እየተሰራ መሆኑንና የተያዘው ዓመት እስኪጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አልቀው በቀጣይ ዜጎችን በህጋዊ መንገድ የመላክ ስራው እንደሚጀመር ሚኒስትር ድኤታው አስታውቀዋል፡፡

በአዲሱ አዋጅ የተለያዩ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚደነግግ ሲሆን ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎችንም እንዴት መዳኘት እደሚቻል አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው ተብሏል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

መጋቢት 23/2008 ዓ.ም

ያለፈው ክረምት ዘግይቶ በመጀመሩ እና ክረምቱ ግድቡ አንድ ሜትር እየቀረው በመውጣቱ ከ5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሀ ሳይጠራቀም ቀርቷል፡፡ በተመሳሳይ ክስተት የተነሳ የድሬ ግድብ ውሀም ቀንሷል፡፡ ይህም በለገዳዲ ማጣሪያ ጣቢያ ውሀ የማምረት አቅም ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ነው የተባለው፡፡ 
በመሆኑም ቀጣዩ ክረምት እስኪገባ ግድቡ የያዘውን ውሀ አብቃቅቶ መጠቀም አስፈልጎኛል ያለው ባለስልጣኑ የለገዳዲ ማጣሪያ ጣቢያ ዕለታዊ የውሀ ምርት በ30 ሺህ ሜትር ኪዩብ እንዲቀንስ ተደርጓልም ብሏል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከለገዳዲ ሲስተም የሚጠቀሙ አካባቢዎች የውሀ ስርጭት በፈረቃ ሊሆን ይችላልም ተብሏል፡፡

አሁን በሙከራ ስርጭት ላይ የሚገኘው የአቃቂ ከርሰ ምድር ውሀ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ወደ ሲስተም ሲገባ በለገዳዲ ማጣሪያ ጣቢያ ላይ የተፈጠረውን የአቅርቦት ክፍተት በመጠኑ እንደሚደፍነው ይጠበቃል መባሉን ከባለስልጣኑ ሰምተናል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

መጋቢት 22/2008 ዓ.ም

የኤልኒኖ አየር ለውጥ ክስተት ያስከተለው የውሀ እጦትና የግድቦች ድርቀት ጉዳዩን አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም መኖር ይገባው የነበረው የውሀ መጠን በግድቦቹ ውስጥ አልተገኘም፡፡ ይህ ደግሞ ከተለያዩ ግድቦች ይመነጭ የነበረው ሀይል በእጅጉ ዝቅ ያለ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡

ጊቤ 3 ግድብ ታዲያ አሁን ላይ ውሀ ማመንጨት የጀመረ ሲሆን ከ500 ሜጋ ዋት በላይ ውሀንም የማመንጨት አቅም ላይ መድረሱንና ለስጋቱ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ መስጠቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ተናግረዋል፡፡

ይህ ግድብ አምስት ያህል ዪኒቶችን ማንቀሳቀስ የሚችል ሲሆን እነዚህ ዪኒቶች ግን በውሀው መጠን ላይ ጥገኛ ስለሆኑ ሙሉ አቅማቸውን ለመጠቀም ይቸገራሉ 187 ሜጋ ዋት ያህል ሀይልን ማመንጨት ቢጠበቅባቸውም አሁን ላይ ግን 150 እና ከዚህ በታች የሆነ ሀይልን እያመነጩም ይገኛሉ ሲሉ ኢንጂነር አዜብ ተናግረዋል፡፡

ሌሎቹ የጊቤ 3 ግድብ ውሀ ተጋሪ ዩኒቶች ቀስ በቀስ ውሀ እያገኙና ወደ ስራ እየገቡ ሲሆን የውሀ አቅሙ እያደገ ሲመጣ የስራ ሁኔታቸውም ከፍ የማለት እድልን ያገኛል ተብሏል፡፡ ይህ የአሁኑ ጊዜ ለጊቤ 3 የፍተሻ ጊዜው ሲሆን እንደ ሌሎቹ ነባር ጣቢያዎች በሙሉ አቅሙ ይሰራል ተብሎም አይጠበቅም እንደ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ገለፃ፡፡

እናም አሁን ላይ ውሀ አጥተው ደርቀው ስራ ለማቆም ጫፍ የደረሱ የውሀ ዩኒቶች በጊቤ 3 አማካኝነት ቀስ በቀስ ውሀን እያገኙ ወደ ቀደመ ስራቸው የመመለስ ተስፋ እንዳላቸው ተሰምቷል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

መጋቢት 21/2008 ዓ.ም

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በስልጤ ዞን ከሚገኙ 8 ወረዳዎች ውስጥ 5ቱ በድርቁ ተጎጂ ሆነዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ችግር ለገጠማቸው አርሶ አደሮች መንግስት ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ በዞኑ በተከሰተው ድርቅ 15 ሺ ሄክታር የእርሻ መሬት ሙሉ በሙሉ ሲወድም 30 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የምርት መቀነስ አጋጥሟል፡፡ 40 ሺ ተረጂዎችም በፌዴራል እና በክልሉ መንግስት የምግብ፣ የውሃና የእንስሳት መኖ ድፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

ችግሩን ለመከላከል የውሃ እቀባ፣ የአዳዲስ ኩሬዎች ቁፋሮ የመስኖና የተፋሰስ ስራ በአካባቢዎቹ እየተሰራ ሲሆን የማካካሻ ዘርም በመንግስት እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ስራው በዚህ አይነት መልኩ ይከናወን እንጂ የሚፈታተኑት አንዳንድ ችግሮች አልታጡም፡፡

በእርዳታ ሂደት ላይ ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት የቀበሌ አመራሮች በፖሊስ ክትትል ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሲገኝ የስልጤ ወረዳ የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ሃላፊ ከአካባቢው በመሰወሩ በፖሊስ እየተፈለገ እንደሚገኝ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅ/ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ወሲላ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

መጋቢት 20/2008 ዓ.ም

መምህር ግርማ ወንድሙ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ከወንጌል ተማሪዎቻቸው ያሰባሰቡትን 420 ሺህ ብር የሚገመቱ ምግብ፣ አልባሳት፣ የመማሪያ ቁሳቁስ እና የመሳሰሉትን ለሙዳይ በጎ አድራጎትና የወደቁትን አንሱ የአረጋውያን መርጃ ማህበር አስረከቡ፡፡

በቀጣይም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖችና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

መጋቢት 19/2008 ዓ.ም

መንግስት በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ ሰባት ክልሎችና ለድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር 1,087,000 ብር ለአስቸኳይ የምገባ ፕሮግራም መድቦ በትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎችን እየመገበ ይገኛል፡፡

በየካቲት ወር የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም በድርቅ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው የነበሩ ተማሪዎች እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ ድርቁ ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አንዱ ነው፡፡ በክልሉ በከንባታ ጠንባሮ ዞን በቀዲዳ ጋሚላ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የሆለገባ ዛቶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት 902 ተማሪዎች ሲኖሩት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 57 የሚደርሱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የምገባ ፕሮግራም በመጀመሩ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የተማሪዎች ራሳቸውን ስተው መውደቅ፣ ሙሉ ክፍለ ጊዜ አለመማር፣ መድከም፣ ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት መቀነስ፣ መቅረት እና ማቋረጥ በስፋት የታየ ችግር መሆኑን የትምህርት ቤቱ መምህር ተስፋነሽ ወልደኪዳን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት በቀጣይ ለተጨማሪ እርዳታ ለክልሎቹ 338 ሚሊየን ብር መድቧል፡፡ ይህም 1.5 ሚሊየን የሚሆኑ ተማሪዎችን ለመመገብ ይውላል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

የካቲት 24/2008 ዓ.ም

ምክር ቤቱ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከ80 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት 19 የግልና የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን አባላት የምክር ቤቱን የመተዳደሪያ የስነምግባር ደንብ በመቀበልና ፊርማቸውን በማኖር ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ ማእከል መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ምክር ቤቱ አሁን ላይ በመስራችነት ከተገኙት 19 አባላቱ በተጨማሪ በዛሬው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ 10 ተጨማሪ አባላት መገኘታቸውም ታውቋል፡፡ የምክር ቤቱን የስራ ሪፖርት ለምልአተ ጉባኤው ያቀረቡት አቶ አማረ አረጋዊ የመተዳደሪያ ደንቡን ሰነድ ስለማስተካከል፣ የምክር ቤቱን አግባብ ባለው የመንግስት አካል የማስመዝገብ ስራ ፣ ጽህፈት ቤት ለማደራጀት ስለሚያስፈልገው በጀት እና አመታዊ የአባላትን መዋጮ መጠን ለጉባኤው አቅርበዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

የካቲት 21/2008 ዓ.ም

የፌዴራል የስነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን 61 የሚደርሱ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር ሃላፊዎችን እና ባለሞያዎችን በሙስና ወንጀል በመጠርጠሩ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡

ከአስሩም ክፍለ ከተሞች በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎቹ የነበራቸውን የመሬት አስተዳደር ሃላፊነት እና የስራ ድርሻ በመጠቀም የመንግስትን መሬት በህገ-ወጥ መንገድ ካርታ አዘጋጅቶ በመስጠት፣ ለልማት ጥቅም ሊውሉ የሚችሉ ቦታዎችን በግለሰብ ይዞታ በማካተት፣ በፍርድ ቤት እግድ የወጣባቸውን መሬቶች ያልታገዱ አድርጎ መረጃ በመስጠት፣ በሀሰተኛ ህብረት ስራ ማህበራት ስም ቦታ እንዲያዝ በማድረግና በመሳሰሉት ወንጀሎች በመጠርጠራቸው በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት ከአዲስ አበባ መስተዳደር እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በጋራ በተከናወነ ኦፕሬሽን ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በዛሬው ዕለት (21/06/2008 ዓ.ም) በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ለተጨማሪ ምርመራ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሏል፡፡

-    ምንጭ- የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን

የካቲት 13/2008 ዓ.ም

በስነ-ስረዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ኘሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ኘሬዝዳንት አቶ ሙክታር ከድር ተገኝተዋል።

74ተኛው የጉጂ ገዳ ስርአት በዓል የሀርሙፋ 15ተኛው የስልጣን ዘመን ስነ-ስርዓት ላለፉት 5 ቀናት በጉጂ ዞን አዶላ ወረዳ በሜኤ ቦኩ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ በባህላዊ የአከባበር ስነ-ስርዓት የስልጣን ርክክቡ ተከናውኗል።

በኘሮግራሙ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ በርካታ የስርዓቱ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ በባህላዊ አልባሳትም ስርዓቱን አድምቀውታል።

የካቲት 08/2008 ዓ.ም

የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አንድ የገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለስልጣን ኦዲተር ከአንድ ድርጅት 100 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበል የካቲት 4፣ 2008 ዓ.ም በቁጥጥር ስር አውሎታል፡፡

ተጠርጣሪው አንድ የግል ድርጅትን በሕግ በማያስጠይቃችሁ መንገድ የታክስ መጠን ቀንሼ የኦዲት ሪፖርት ላዘጋጅላችሁ፤ ለዚህም 150 ሺህ ብር ለእኔ እና ለግብረ አበሮቼ ያስፈልገናል በሚል 100 ሺህ ብር ቅድሚያ ክፍያ ሲቀበል ኮሚሽኑ በደረሰው ጥቆማ መሰረት እጅ ከፍንጅ ሊይዘው ችሏል፡፡

ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሉን በመመርመር ላይ ሲሆን ምርመራው እንደተጠናቀቀ በተጠርጣሪው ላይ ክስ የሚመሰርት ይሆናል፡፡

- ምንጭ- የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን

የካቲት 07/2008 ዓ.ም

እነዚህ በምስል የሚታዩት ተጣብቀው የተወለዱት ህፃናት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በደሀና ወረዳ ቀበሌ 020 አዚላ ሽቫቫኖች ጎጥ ሲሆን በ06/05/2008 ዓም በተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል እናትም በጤና ህፃናትም በጤና ተጣብቀው ተወልደዋል። በፆታቸውም ሁለቱም ሴት ናቸው። የተጣበቁትን ለማለያየት ወደ መቀሌ አይደር ሆስፒታል ተልከው ህክምናው ባለመሳካቱ ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልከዋል።

- ምንጭ- ደሀና ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽ.ቤት

የካቲት 05/2008 ዓ.ም

የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስቴር በቀን ጥር 10፣ 2008 ዓም በቁጥር 030/2/3/5432/16415 በፃፈው ደብደቤ የንግድ ህግ አዋጅ 686 አንቀፅ 37ን በመጣሳቸው ምክንያት የ ቲያንስ ኢትዮጵን ንግድ ፍቃድ ማገዱን አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ ባንክም የንግድ ሚኒስቴርን ደብዳቤ አባሪ አድርጎ በቀን ጥር 18፣ 2008 ቁጥር 01/131/16 ለሁሉም ባንኮች በፃፈው ደብዳቤ የቲያንስ ኢትዮጵያ ንግድ ፍቃድ መታገዱን ጠቅሶ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

የካቲት 02/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ዘንድሮ 6ኛውን ሃገር አቀፍ የባህል ሳምንት ፌስቲቫል “ህብረ ብሄራዊ ኩራታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 15 - 23/2008 ዓ.ም ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በጅግጅጋ ከተማ ያከብራል፡፡

ማዕከሉ 3ኛውን ሃገር አቀፍ የባህል ሳምንት ፌስቲቫል በ2005 ዓ.ም በማዕከሉ ቅጥር ግቢ፤ 4ኛውን በ2006 ዓ.ም በአማራ ብ/ክ/መ/በጎንደር ከተማ እንዲሁም 5ኛውን በአፋር ክልል በስመራ ከተማ ማክበሩ ይታወሳል፡፡

የካቲት 01/2008 ዓ.ም

ሰኞ ዕለት ከቀኑ 10፡30 አካባቢ ተሳፋሪ የጫነ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ከጎለልቻ ወረዳ ወደ ጮሌ ወረዳ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ልዩ ስሙ ጭሊና ተራራ በተባለ አካባቢ ሲደርስ ባጋጠመው የመንሸራተት ችግር ምክንያት ወደ ገደሉ መገልበጡን ነው የሰማነው፡፡

የጮሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጋሻው ደጀኔ ለዛሚ እንደተናገሩት ተሽከርካሪው ከተፈቀደለት ሰው በላይ ጭኖ ሲጓዝ ነበር፣ ተራራው አካባቢ ሲደርስም የመንሸራተት አደጋ ገጥሞት ወደ ተራራው ተገልብጧል ብለውናል፡፡

በአደጋው 18 ያህል ተሳፋሪዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 25 የሚደርሱ ሌሎች ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በአዳማ እና አቦምሳ ሆስፒታሎች የህክምና እርዳታ እያገኙ እንደሆነ ተነግሯል፤ አሽከርካሪውም የከፋ ጉዳት እንደደረሰበትና ከአዳማ ሆስፒታል ለተጨማሪ ህክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መላኩን አቶ ጋሻው ደጀኔ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡

ተራራው ረጅም ቢሆንም ይህን መሰል ከባድ አደጋ አጋጥሞ አያውቅም ያሉት አስተዳዳሪው አሽከርካሪዎች የመንገዱን ጠመዝማዛነትና አስቸጋሪነት ተረድተው ጥንቃቄ ያድርጉ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡