አገር አቀፍ ዜናዎች

ግንቦት 23/2008 ዓ.ም

የኮድ ቁጥሩ 12 የሆነውና ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወሳጆች ቀርቦ የነበረው የእንግሊዘኛ ፈተና ተሰርቆ መውጣቱ በመታወቁ ፈተናው እንዲሰረዝ መደረጉና ሌሎች ፈተናዎችም ላለመሰረቃቸው ማረጋገጫ ባለመኖሩ አጠቃላይ የፈተና ሂደቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ዛሚ ከትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ምስጋና ፀጋዬ እንደሰማው እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም እንደ አማራጭ የሚቀርቡና ለመጠባበቂያ ተብለው ተዘጋጅተው የነበሩ ፈተናዎች በመኖራቸው ፈተናው ከአንድ ወር በኋላ ማለትም ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ድረስ በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች ዳግም ይሰጣል ብለዋል፡፡ አቶ ምስጋና ፀጋዬ አክለውም የፈተና ዝግጅቱና አሰጣጡ በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ የሚከናወን ይሆናል ያሉ ሲሆን የህትመትና የስርጭት ስራውም በተመሳሳይ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበታል ብለዋል፤ ተፈታኞችም ተገቢውን ዝግጅት አድርገው ከአንድ ወር በኋላ ዳግም ለፈተና ለመቀመጥ ይዘጋጁ ሲሉ ለዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 23/2008 ዓ.ም

ለመላው ህዝብ እና ተፈታኞች ይቅርታ የጠየቁት የ12ኛ ክል ፈተና ተሰርቆ መውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡ ትናንት ሌሊት 8፡00 ሰዓት ላይ በማህበራዊ ድረ-ገፅ የተለቀቀው ፈተና ለተማሪዎች ከሚታደለውና በፊታቸው ከሚከፈተው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በዚህም ተሰርቆ መውጣቱ መረጋገጡን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ምስጋናው ፀጋዬ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ተሰርቆ መውጣቱ የተረጋገጠው ኮድ 12፤ የእንግሊዝኛ ፈተና ሲሆን ለ4 ተከታታይ ቀናት የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና ተቋርጧል፤ ላልተወሰነ ጊዜም ተራዝሟል መባሉ ተሰምቷል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ግንቦት 17/2008 ዓ.ም

ዶክተር ቴዎድሮስ በጀኔቫ እየተካሄደ ባለው የአለም ጤና ጉባኤ ላይ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በይፋ ጀምረዋል፡፡ ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት ከአፍሪካ ብቸኛው እጩ በመሆን እየተወዳሩ ያሉት የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እስካሁን በግላቸውም ሆነ እንደተቋም ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ለማሸነፍ የሚያስችሉ ናቸው ተብለዋል፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከ1998 እስከ 2004 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ በመሪነት ያሳኳቸው ስኬቶች አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ካሁን በፊትም የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትንም በቦርድ ሰብሳቢነት የመምራት ልምድ አላቸው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙልጌታ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን አፍሪካ የአለም የጤና ድርጅት አመራርነትን አግኝታ አታውቅም ያሉት ቃል አቀባዩ ይህንኑ ለማሳካት የመላ አፍሪካ አገራት ድጋፋቸውን ለዶ/ር ቴዎድሮስ በመስጠት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዶክተር ቴዎድሮስ በጀኔቫ እየተካሄደ ባለው የአለም ጤና ጉባኤ ላይ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ለመመረጥ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በይፋ ጀምረዋል፡፡ ዶክተር ቴዎድሮስ በጄኔቫ ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ በዓለም ዙሪያ በጤናው ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችሉ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ለሁሉም ዜጋ መሰረታዊ የጤና ጥበቃ አገልግሎቶችን ማረጋገጥ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና ዝግጁነትን ማሳደግ እና የሴቶችን ኑሮ እና ጤና የሚያሳድጉ ፖሊሲዎችን ማጎልበት የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ቢመረጡ የሚያከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት። በ26ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ዕጩ ተወዳዳሪ አድርጋ አቅርባ ተቀባይነት ካገኝች በኋላ በቅርቡም ከ30 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች ዶክተር ቴድሮስ ለአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ምርጫ እጩ ሆነው መቅረባቸውን መደገፋቸው ይታወቃል። አሁን የአለም የጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ያሉትን ቻይናዊቷን ዶክተር ማርጋሬት ቻንን ለመተካት ምርጫው በሚያዝያ 2009 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ይካሄዳል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ግንቦት 17/2008 ዓ.ም

ከመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ የቆየው የማስተማርና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን ግንቦት 30 ህጉ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ የምግብ፣የመድሀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ እንደተናገሩት ሲጋራን ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ማጨስን የሚከለክለው መመሪያ የመውጣቱ አስፈላጊነት አጫስ ያልሆኑ ሰዎች በሚያጨሱ ሰዎች አማካኝነት ከሚደርስባቸው የሲጋራ ጭስ ጉዳት መጠበቅ አንዱ ሲሆን የሲጋራ ሱሰኞችን ከጉዳቱ መታደግ የሚለው ሌላኛው አላማው ነው ብለዋል አዳዲስ የሲጋራ አጫሾች እንዳይፈጠሩ ማድረግንም እንዳካተተ ተናግረዋል፡፡

ህዝብ በሚሰበሰብበት ይሁን በሚገለገልበት ማንኛውም ቦታ ትንባሆ ማጨስ፣ ማጨስ በህግ በተከለከለባቸው ቦታዎች የሚገልፅ ምልክት ወይም ፅሁፍ በመግቢያና በመውጫ ቦታዎች እና ሌሎች አስፈላጊ ቦታዎች ላይ አለመለጠፍ፣ በተከለከሉ ቦታዎች ወይም መጨስ በሌለባቸው ቦታዎች ተረፈ ምርት ትንባሆ ማጠራቀሚያ ማስቀመጥ ከብር 2,000 የማያንስ እና ከብር 3,000 የማይበልጥ ገንዘብን ያስቀጣል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 15/2008 ዓ.ም

በተያዘው የመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን እንስራ ብለው ከቡራዩ አስተዳደር የኢንቨስትመንት መሬት የተቀበሉና ለረጅም ዓመታት አንዳችም ስራ ያልሰሩ ባለሀብቶች መሬት ከዚህ በኋላ ይነጠቃል ሲሉ የቡራዩ ከንቲባ ዳባ ጅንፌሳ ተናግረዋል፡፡ 

በኢንዱስትሪና በኮሜርሺያል በሚል የተለዩትን መሬቶች የወሰዱት ባለሀብቶች ቁጥርና የወሰዱት የመሬት ልኬታም የተለየ ሲሆን ከ3-5 ለሚደርሱ ዓመታት ልማት ያልታየባቸው 17 ሄክታር መሬቶችም እስካሁን ተለይተዋል፤ ለ10 ዓመታት ያህል ለመጋዘን አገልግሎት ብቻ ያዋሉ 12 ባለሀብቶችም ታውቀዋል፡፡

ከንቲባው እንዳሉት እስካሁን ድረስ በሶስት ደረጃዎች ባለሀብቶቹ ተለይተው ተገቢው እርምጃ እየተወሰደባቸው ሲሆን ለፋብሪካ ግንባታ በሚል መሬት ወስደው መጋዘን ያደረጉ 12 ባለሀብቶች የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፤ ሌሎች ልዩ ልዩ ችግር ገጥሞናል በሚል ሰበብ መሬቱን በከፍተኛ ገንዘብ ለመሸጥ የተዘጋጁና የተደረሰባቸው 18 ባለሀብቶችም የታወቁ ሲሆን አጠቃላይ የያዙት የመሬት ስፋትም 20 ሄክታር መሆኑ ታውቋል፡፡ እስካሁን የተጣራው መረጃ ለካቢኔ ቀርቧል ያሉት ከንቲባው በተያዘው ሳምንት የማሰናበቻ ደብዳቤ ይደርሳቸዋልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 15/2008 ዓ.ም

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቢሮውን መክፈቱን አስመልክቶ ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ ላይ የዓለም የሜትሪዎሎጂ ድርጅት (WMO) ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ፒተሪ ታላስ ተገኝተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የዓለም የሜትሪዎሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቢሮውን ወደ አዲስ አበባ ሲያዛውር ስራውን በቅርበት እና በተሻለ መልኩ ለማከናወን እንዲረዳው በማሰብ ነው ብለዋል፡፡  

የኢፌዴሪ ውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው የዓለም የሜትሪዎሎጂ ድርጅት ቢሮውን ከስዊዘርላንድ ጄኔቫ ወደ አዲስ አበባ በማዘዋወሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለቢሮው እንቅስቃሴ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ዛሬ ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው የብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኤጀንሲ ግቢ የአፍሪካ ቢሮውን በይፋ ከፍቷል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ግንቦት 09/2008 ዓ.ም

ቤተ-ክርስቲያኗ በልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮምሽን በኩል ባበረከተችው ድጋፍ በኤሊኖ ምክንያት የድርቅ አደጋ በደረሰባቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ከ 238,000 በላይ ዜጎችን መርዳት ችያለሁ ብላለች፡፡ ቤተ-ክርስቲያኗ ባዘጋጀቻቸው 230 ያህል ፕሮጀክቶች በዋናነት በትግራይ በአማራ ኦሮሚያ በደቡብና ሶማሊያ የሚገኙ ዜጎችን ረድታለች፡፡ የእርዳታ መርሃ ግብሩም የዘር አቅርቦት አልሚ ምግብ ማከፋፈል የፍየል እና ጊደር ልገሳ እንዲሁም የእርሻ መሳሪያዎችን መለገስን ያካተተ ነው ይላሉ የቤተክርስቲያኗ የልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ኮምሽን ኮምሽነሩ አቶ ግርማ ቦሪሼ፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

ግንቦት 09/2008 ዓ.ም

ታላቁ የኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውን የነፃነት ተምሳሌት በሆነው በአድዋ ድል ስያሜ የተሠጠው “አድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ” የተሰኘውን ግዙፍ የትምህርት እና የምርምር ተቋም በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የምስረታ ቻርተሩ ቀርቦ በምሁራን ምክክር ተደርጎበታል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምስረታ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ቢተው በላይ እንደተናገሩት የአድዋ ድል የድል ታሪክ ከመባል ባለፈ በወቅቱ ምን እንደተሰራ፣ ምን እንደተፈፀመ እና ድሉ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ፤ ብሎም ከድሉ ጀርባ እነማን እንደነበሩ ጭምር በስፋት ሊቃኝበት የሚችል የታሪካችን ማዕከል እንዲሁም የጥናትና ምርምር መከወኛ ቦታ እንዲሆን እቅድ ተይዞለታል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአፍሪካና ከመላው አለም ሀገራት የሚመጡ ምሁራን ስለ አድዋ የሚፈልጉትን አይነት መረጃ በቀላሉ የሚያገኙበት የምርምር ስራቸውንም የሚከውኑበት እንዲሆን ለማስቻል ታስቧል፡፡

ዶ/ር አየለ በክሪ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው መመስረት ዋነኛ አላማ የድሉን ታላቅነት ለትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ የ2063 የአፍሪካ የልማት አጀንዳን እውን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ታሪካዊና ባህላዊ ሁነት ላይም ትኩረቱን ያደርጋል፣ ሀገራችንም የአህጉሪቱ የታሪክ ዳራ ትሆናለች የሚል እምነትን ይዘናል ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት እና በልዩ ልዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ቅርሶችን በማስመለስ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው እና ለጎብኚዎችም ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ጋርም በጋራ እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲውን የማቋቋም እንቅስቃሴው አምና የተጀመረ ሲሆን የመመስረቻ ፅሁፍ ከማዘጋጀት አንስቶ የጋራ ውይይት በማድረግና ምሁራንንም በማሳተፍ ዘልቆ መሻሻል አለባቸው የተባሉ ጉዳዮች ላይም የሀሳብ ግብዓትን ሰብስቧል፡፡ ባለ ሶስት ነጥብ የአቋሙን ይፋ ያደረገው ኮሚቴው 25 አባላትንም መርጧል፤ ነሐሴ ላይም አለም አቀፍ ጉባኤ ለማከናወን ቀጠሮ ይዟል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 08/2008 ዓ.ም

አያሌ አትሌቶችን ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያበረከቱት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ በሰሜን ሸዋ ተጉለት እና ቡልጋ ጥር 1939 ዓ ም የተወለዱ ሲሆን ፤ በትምህርቱ አለምም ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ምስራቅ አውሮፓ ሀንጋሪ በማቅናት በባዮሎጂ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ ሰርተው ተመልሰዋል፡፡

የአትሌቲክስ አሰልጣኝነትን የጀመሩት በኮተቤ ኮሌጅ አስተማሪ እያሉ በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን በ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ በሚሳተፈው ቡድን ውስጥ ዋና አሰልጣኝ ለነበሩት ንጉሴ ሮባ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ነበር፡፡

ዶክተር ወልደመስቀል በ1982 የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡

1992 ዓ.ም የአትሌቲክስ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ የነበሩትን ንጉሴ ሮባን ኅልፈተ ህይወት ተከትሎ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የያዙት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ዛሬም ድረስ በአለም የአትሌቲክስ ታሪክ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚጠራ አያሌ አትሌቶችን ለሀገር ማበርከት ችለዋል፡፡
በዚህ የአሰልጣኝነት ጊዜያቸውም ከባርሴሎና ኦሎምፒክ እስከ ቤጂንግ የ2008 ኦሎምፒክ  ውድድር ድረስ ለ16 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ የ5000 እና የ10,000 ሜትር አትሌቶችንም ማብቃት ተችሎዋቸዋል፡፡

ዶ/ር ወልደመስቀል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ በተሳተፉባቸው አምስት ኦሎምፒኮች ላይ 13 የወርቅ፣ 5 የብር እና 10 የነሐስ፤ በጥቅሉ 28 ሜዳሊያዎችን ለሀገራቸው አስገኝተዋል ፡፡

እ.ኤ.አ በ2006 ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቲክሱ ዓለም ለአሰልጣኞች የሚሸለመውን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ሽልማትን ተቀብለዋል፡፡ ዶ/ር ወልደመስቀል በስፖርት ዘርፍ የ2007ዓ.ም የበጎ ሠው ሽልማትንም ተቀብለዋል።

አምና የጭንቅላት ቀዶ ጥገና ህክምና አድረገው የነበረ ሲሆን ከዛ ጊዜ ጀምሮ በአልጋ ውለዋል፡፡ ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም በ69 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ የቀብ ስነ-ስርዓታቸውም በነገው ዕለት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን ይፈፀማል፡፡

ግንቦት 05/2008 ዓ.ም

መቀመጫውን ኒውዚላንድ ያደረገውና ላለፉት 130 አመታት በአለም ገበያ ላይ ሲሰራ የቆየው አንከር ወተት ወደ ሀገራችን ገብቶ ጥናትና ዝግጅት ካጠናቀቀ በኋላ ምርቱን ማቅረብ ከጀመረ ዘጠኝ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ድርጅቱ ከገበያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለውን የአመጋገብ ስርአት ለማሻሻል የሚረዱ ጥናቶችን በመላ ሀገሪቱ አጠናቆ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ እንደሚገኝም በኒውዚላንድ ወተት የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ዚኮ ቃሲም ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም በትምህርት ቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ያካሂዳል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ የአንከርን ወተት የሚገዙ ደንበኞቹ በሚደርሳቸው ኩፖን ላይ በእጣ የተለያዩ ሽልማቶችን አዘጋጅቷል፡፡ ሽልማቶቹ ለ100 ሰዎች ባለ 10 ሺህ ብር የተማሪዎች የቁጠባ ሂሳብ ያላቸው የባንክ ደብተሮች፤ 500 የህፃናት ሳይክሎች፤ 500 የተማሪ ቦርሳዎች፣ 1,000 የምሳ እቃዎች፣ 500 ኳሶችን እና 12,000 የአንክር ወተት መጠጫ ኩባያዎችን ያጠቃልላል፡፡ በጥቅሉ 26,000 ስጦታዎችን አዘጋጅቷል፡፡ ደንበኞች በኩፖናቸው ላይ ፍቀው የሚያገኙትን ማንኛውም ሽልማት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሄድ ሽልማታቸውን መቀበል ይችላሉም ተብሏል፡፡ 

(እንደገና ደሳለኝ)

ግንቦት 04/2008 ዓ.ም

በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ቡድኑ ኢትዮጵያውያንን ገድያለው ስለማለቱ ተጨማሪ መረጃ የለንም ሲል የመንግስት ኮሚዬኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ መንግስት አልባ በሆኑ ሀገራትና ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አከባቢዎች ጉዞ ማድረግ ለዚህ አይነቱ ጉዳት ያጋልጣል ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዬች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ አይ.ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ በትክክል ድርጊቱን ባይፈጽም እንኳን ቡድኑ ይህን ይፋ ማድረጉ ብቻ የኢትዮጵያውያንን ልብ የሚሰብር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከትናንት ምሽት ጀምሮ የኢራን ቴሌቪዢን 16 ኢትዮጵያውያን በአይ.ኤስ መገደላቸውን ሲዘግብ አምሽቷል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

ግንቦት 04/2008 ዓ.ም

ለጋዜጣው መዘጋት መንግስት በመገናኛ ብዙሀን ላይ የሚከተለው አሰራር አንዱ ምክንያት መሆኑን የሳምሶን አድቨርታይዚንግ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ማሞ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ ጋዜጣውን ለመደጎም ድርጅቱ በየወሩ እስከ 100 ሺህ ብር በማውጣት ባለፉት አመታት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ ማድረጉንና ይህም ለኪሳራ ዳርጎናል ያሉት አቶ ሳምሶን ከዚህ በላይ መቀጠል ባለመቻላችን ጋዜጣውን ለመዝጋት ተገደናል ብለዋል፡፡ ኢትዮ-ቻናል ጋዜጣ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ 20 ያህል ሰራተኞች የነበሩትና በማህበራዊ ጉዳይ በኪነ-ጥበባት በስፖርትና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሲሰራ የቆየ ጋዜጣ ነው፡፡ ወደፊት በምን አግባብ እንደምንቀጥል አልወሰንም ያሉት አቶ ሳምሶን ወደ መፅሄት የመዞር እቅድም እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ሚያዚያ 28/2008 ዓ.ም

ትናንት ምሽት 12 ሰዓት ገደማ ቦሌ አካባቢ በግንባታ ላይ በሚገኘው አዲሱ ብሔራዊ ስታዲየም ፕሮጀክት የቁፋሮ ስራ ይሰሩ በነበሩ ሰራተኞች ላይ አፈር ተደርምሶ ሁለት ወጣቶች ህይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች 11 ሰራተኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈው የ25 እና የ27 አመት ወንዶች ናቸው፡፡ ሰራተኞቹ በስራ ቦታቸው ላይ ምንም አይነት የደህንት አልባሳትን አለማድረጋቸውንም መረጃውን የነገሩን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ገልፀውልናል፡፡

ሚያዚያ 25/2008 ዓ.ም

እሁድ እለት በተከበረው የትንሳኤ በዓል ዋዜማ በተለያዩ ቦታዎች የሞትና የከባድ ጉዳት አደጋዎች ተመዝግበዋል፡፡ በእለተ ቅዳሜ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ ሶስት ወጣቶች በኤሌክትሪክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዚሁ ክ/ከተማ ሃና ማርያም በሚባለው አካባቢ በእያቄም ትምህርት ቤት የእሳት አደጋ ደርሶ 10,000 ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ ለገጣፎ አካባቢም በጎርፍ አደጋ የአንዲት ሴት ህይወት አልፏል፡፡

የበዓሉ እለት ደግሞ 43 የትራፊክ አደጋዎች ተመዝግበዋል፡፡ ሁለቱ የሞት እና ሁለቱ ከባድ ጉዳት መሆናቸውን ሰምተናል፡፡ ከተመዘገቡት የሞት አደጋዎች መካከል አንዱ በየካ ክፍለ ከተማ ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ የደረሰ ሲሆን ተጎጂው በኮሪያ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት አምሽቶ ሌሊት ሰባት ሰአት ህይወቱ አልፏል፡፡ ሌላኛው የሞት አደጋ ደግሞ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አካባቢ የደረሰ ሲሆን ተጎጅው ወዲያው ህይወቱን አጥቷል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማም እንዲሁ በከሰል ጭስ ምክንያት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ሰምተናል፡፡ መረጃውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ም/ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ እና ከአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ አግኝተነዋል፡፡

ሚያዚያ 21/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ሰራተኞችን በማህበር የማደራጀት እና የመደገፍ አላማ ያለው ሲሆን መብታችውን እና ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲችሉ በማደራጀቱ በኩል የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡ ሰራተኞች በማህበር ካልተደራጁ ለሚፈጠሩ ችግሮች ብሎም የመብት ጥያቄን በተገቢው መንገድ ለማስከበርም ይሁን ለመጠየቅ እንደማይችል ኮንፌደሬሽኑ አስታዉቋል፡፡ ሰራተኞች የመደራጀት መብት እንዳላቸው ግንዛቤ የመፍጠር እና ሰራተኞችም በምን አይነት መልኩ ተደራጅተው መብታቸውን ማስከበር እንዳለባቸው ማሳወቅ ሌላኛው የአሰሪዎች ተግባር መሆኑን የኢትዮጲያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሌ ተናግረዋል፡፡ በማህበር ላልተደራጁ ሰራተኞች ምንም አይነት እርዳታ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነና በማህበር ቢታቀፉ ዘርፈ ብዙ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚያገኙም ተገልጧል፡፡ የመንግስት ሰራተኞችም በማህበር የመደራጀት መብት እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን ለኮንፌዴሬሽኑም መጠናከር የሚኖረው ጠቀሜታ ላቅ ያለ መሆኑን የኢትዮጲያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሌ ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

ሚያዚያ 20/2008 ዓ.ም

ኤጀንሲው የ2008 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና መውሰጃ የጊዜ ሰሌዳን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ 10ኛ ክፍል ፈተና ከግንቦት 17-19/2008 ዓ.ም ይሰጣል። በተመሳሳይም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከግንቦት 22-25/2008 ዓ.ም እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ሚያዚያ 17/2008 ዓ.ም

1998 ዓ.ም ላይ ከባድ የጎርፍ አደጋን አስተናግዳ የነበረችው የድሬዳዋ ከተማ ከ10 አመታት በኋላ ዳግም ይህን መሰል አደጋ ማስተናገዷ ነው የተሰማው፡፡

ሚያዚያ 17 ማለዳ 12፡30 ላይ የተከሰተው ይህ የጎርፍ አደጋ 4 ሰዎችን በጎርፉ እንዲወሰዱ ያደረገ ሲሆን “የ23 ዓመት ወጣት የሆነው ግለሰብ ከቀፊራ ማረሚያ ቤት እስከሚባለው አካባቢ በጎርፏ ከተወሰደ በኋላ ማረሚያ ቤት የሚባለው አካባቢ ላይ ሲደርስ ጎርፉ ተፋው፤ ህይወቱም በተዓምር ተረፈች፤ 3 ያህሉ ሰዎች ግን ህይወታቸው አለፈ” ሲሉ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ሃላፊው ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡

በጎርፉ ከድሬዳዋ ወደ መልካ ጀብዱ የሚወስደው ድልድይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፣ ከ12 በላይ በጎችና 2 ዩዲ ትራክ መኪኖችም በጎርፉ ተወስደዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ነግረውናል፡፡

ሚያዚያ 17/2008 ዓ.ም

የፋሺስት ኢጣልያ ወራሪ ሰራዊት ድል የተመታበትን 75ተኛ አመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በአሉን ለማክበር ዝግጅቱን ያጠናቀቀው የጀግኖች አርበኞች ማህበር በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አርበኞችን በማሰባሰብና በያሉበትም በመድረስ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፏን እያደረገ ይገኛል፡፡

የወቅቱ ድል እንዲገኝ አብይ ምክንያት የሆኑት አርበኞች ገሚሶቹ ህይወታቸው ሲያልፍ የተቀሩት ደግሞ በህይወት ይገኛሉ፤ በህይወት የሚገኙት አርበኞች ቁጥር ግን በማበሩ በውል እንደማይታወቅ ነው ከማህበሩ ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የሰማነው፤
በማህበሩ ሰንድ ውስጥ የሚገኘው በህይወት ያሉ አርበኞች ቁጥር ከ42-45 ሺህ ይገመታል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ግን ግምታዊ ቁጥር ነው እንጂ እርግጠኛ ቁጥር አይደለምም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ትክክለኛውን በህይወት ያሉ አርበኞችን ቁጥር ለማወቅ አሁን ላይ በየዞኑና በየወረዳው አርበኞችን ፍለጋና ምዝገባ እየተደረገ ነው ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡