አገር አቀፍ ዜናዎች

በየደረጃው የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ቅንጅታዊ ጥረት  ሴቶችን በተለያዩ መስኮች በማሰልጠን ብቃታቸውን በተግባር ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ይህንንም ጥረት ከግብ ለማድረስ ከተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ በማላቀቅ በራሳቸው አምራች ዜጋ ለማድረግ በየዘርፉ አስፈላጊው እርዳታና ስልጠናን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህን ለሴቶቹ የሚደረገውን ስልጠና እና ድጋፍ ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶች ጋር በመሆን እያስፋፋ የሚገኝ ሲሆን የአውሮፓ ህብረትም ለዚሁ እንዲሆን 6.5 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዳደረገ በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር የህዝብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብይ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

ይህንን ድጋፍ ተግባራዊ በማድረግና በማስተባበሩ ረገድ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሚናውን የሚወጣ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ፕሮግራሙ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን የሚያሳትፍ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ከአውሮፓ በተገኘው ድጋፍ ሌሎች ሴቶችን መድረስ የሚያስችል አቅም እንደተፈጠረ አቶ አብይ ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

ታህሳስ 20/2006 ዓ.ም በልደታ ክ/ከ ቀበሌ 09/10 ክልል ልዩ ቦታው ቀበሌ 30 መዝናኛ ክበብ አካባቢ በግምት ከምሽቱ 3 ሰዓት ሲሆን በቦታው ጫት በመቃም ላይ ለነበሩት ደንበኞቿ ሻይ ለመቅዳት ባጎነበሰችበት ወቅት ተከሳሽ ሀምዱ ሽኩር መሀመድ በኋላዋ በመምጣት ቀደም ብሎ ከመርካቶ በገዛው ቆንጨራ ጀርባዋን ይመታታል፡፡ በዚህ የተነሳ ስትወድቅም እዛው በተኛችበት ሁለት ጊዜ ጭንቅላቷን በመምታት ከ10-12 ሴንቲ ሜትር የሆነ ጥልቅ ስንጥቅ ያለው ጉዳት ያደርስባታል፡፡ በዚህ ጊዜ በተፈጠረው ግርግር የተደናገጠው ተከሳሽም በአካባቢው በነበሩ ፖሊሶችና የህብረተሰቡ ድጋፍ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡

ድርጊቱን ለምን እንደፈፀመ ተከሳሹ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ከዚህ ቀደም በአፍንጫዬ መጥፎ ጠረን ይሸተኝ ነበር ለጠንቋይ ሄጄ ስጠይቅም አፍንጫህ እንዲሸት ያደረገችው እሷ ናት እሷንም ጀነት አስገባታለሁ የሚል ምላሽ በማግኘቴ ተናድጄ ነው ሲል ተናግሯል፡፡

ጉዳዩ ተጣርቶ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎትም አስፈላጊውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ከተመለከተ በኋላ ተከሳሹ በፈፀመው ከባድ ሰው የመግደል ሙከራ ወንጀል በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡ (ቴድሮስ ብርሀኑ)

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የደንበኞች ህገ-ወጥ የኤሌክትሪክ ሃይል አጠቃቀምን ለመከላከል የሚያስችል ነው በማለት ገልጧል፡፡ ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በቅርቡ ስራውን እንደሚጀምር የገለፁት የኮርፖሬሽኑ የከፍተኛ ሃይል ስርጭት የኮንስትራክሽንና የግንባታ ቁጥጥር ስራ አስፈፃሚ አቶ ቢትወደድ ገብረዋህድ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ደንበኞች በጥሪ ማዕከል የሚያቀርቡትን ጥቆማ አቀባበሉን የሚያፋጥን አዲስ የመልእክት መቀበያ ሶፍትዌር ስራ ላይ እንደሚያውል ተናግረዋል፡፡ አዳዲስ የሚገቡት መሳሪያዎች እና ሶፍትዌር ኮርፖሬሽኑ አገልግሎቱን የተፋጠነ እንዲያደርግ ይረዳዋል ሲሉ አቶ ቢትወደድ ገብረዋህድ ገልፀዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

ከተገልጋዩ ዘወትር የሚሰማውን የሞባይል ኔትወርክ ችግር በመቅረፍ ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክትን ለቻይናው ዜድ ቲ ኢ እና ሁዋዌ ኩባንያዎች መስጠቱ ይታወሳል፡፡ 1.6 ቢሊዮን ዶላር በሚደርስ እንደሚገነባ የተነገረለት ፕሮጀክት በ3 ምዕራፎች ሲከፋፈል ሁለቱ ቀድመው ተጠናቀዋል፡፡

በመጀመሪያው ፕሮጀክት በአዲስ አበባ በተለምዶ የኖኪያ አካባቢ የሚባለው ብስራተ ገብርኤል፣ መካኒሳ፣ አየር ጤና፣ ዓለም ባንክ እና አካባቢው እንዲሁም በሁለተኛው ምዕራፍ 239 አካባቢዎች ላይ ኔትወርኩን በአዲስ የመተካት ስራ የተሰራ ቢሆንም ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቀረፍ አልተቻለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዘላቂነት ችግሩን ይፈታል የተባለው የ3ኛው ምዕራፍ 410 ሳይቶች አዳዲስ ለሞባይል አገልግሎት ማስፋፊያ የሚውሉ የአንቴናና የአገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች ተከላ ስራዎች ተከናውነው የ4ጂ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዕቅድ መሰረት በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ነባሩን የቴሌኮም ኔትወርክ መሰረተ ልማት የመተካትና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተከላ እና ተጨማሪ አዲስ ኔትወርክ ሽፋን መዘርጋት የሚያስችል የሰርቬይ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡

ፓርቲው በሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ነው ይህን ያስታወቀው፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ግንባር ፓርቲ ተብሎ ይጠራ ነበረ፤ ይህ ስያሜው ማስተካከያ ተደርጎበት የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲ ብሄራዊ ግንባር ሆኗል፡፡

ፓርቲው በ2007 ለሚደረገው ምርጫ ዝግጅት አያደረገ መሆኑንም ገልጧል፡፡

ዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ከህብረተሰቡ የሚደርሱትን ጥቆማ እና ቅሬታዎች በስልክ እንዲሁም በአካል ቢሮ ድረስ የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች እያስተናገደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአካል እና በስልክ መስመሮቻችን ከሚደርሱን ቅሬታ እና ጥቆማዎች በተጨማሪ በ8089 አጭር የፁሁፍ መልእክት መቀበያ ማስተናገድን ጨምሮ አድማጮች ካሉበት ሆነው በ8089 ቅሬታ እና ጥቆማችሁን በመላክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጣቢያው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በአገራችን የወላድና የሞት ቁጥር የተመጣጠነ መሆን ለዚህ እንደ ትልቅ ምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችል በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ አሰፋ ኃ/ማሪያም ናቸው፡፡

እንደርሳቸው ገለፃ ከሆነ የቁጥሩ ከፍተኛ መሆን ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር ተመጣጣኝ ባይሆንም በሰው ሃይል ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ይህን ጥናታቸውን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የጥናት፣ እቅድና በጀት ዋና የስራ ሂደት የሥነ-ህዝብ ጉዳዮች ማስተባበር ንዑስ የስራ ሂደት የስነ-ህዝብ ቀን በትላንትናው ዕለት ባከበረበት ወቅት ነው፡፡

ፕሮፌሰሩ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ 17 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ስራ እንደማይሰራና ከሚሰራውም 25 በመቶ የሚሆነው በቀን ለ2 እና ለ3 ሰዓታት ብቻ የሚሰሩ ስራዎች ላይ የተሰማራ እንደሆነ በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ይህንን ሃይል ወደ ስራ በማስገባት ቢሰራ ካፒታላቸውን የሰው ሃይል በማድረግ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንዳደጉት ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥም ፈጣን ለውጥ  ማምጣት እንደሚቻል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ በቂ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ለአርሷደሮች ማከፋፈሉን ገልጧል፡፡ በዘንድሮ የምርት ዘመን 304 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ይሰበሰባል ሲልም የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ለአዝእርት ዝግጁ የሆኑና ይታረሳል ተብሎ የሚጠበቀው መሬት 12.6 ሚሊዮን ሄክታር ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ የአቅርቦት ችግር እንደሌለ የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አስራት ገበረ ፃድቅ ተናግረዋል፡፡ በወረዳ ደረጃ ችግሩ ካለ እናጣራለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በ2005 -2006 ዓ.ም የተገኘው አጠቃላይ ምርት 254 ሚሊዮን ኩንታል ነው፡፡ ሚኒስቴሩ 30ሺ በሰው የሚጎተት የዘር መዝሪያ ቴክኖሎጂና 1,255 በእንስሳት የሚጎተቱ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ ማከፋፈሉን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ወደ ተግባር ስራ የተገባው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት በጥር ወር የሙከራ ስራውን እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

የግንባታ ስራውን በጥር ወር 2007 ዓ.ም በማጠናቀቅ ወደ ሙከራ ፕሮጀክት ስራው ይገባል የተባለው፤ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታው በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን የገለፁት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ናቸው፡፡

የሙከራ ስራው የሁሉንም የፕሮጀክቶችን ሳይት የሚያጠቃልል መሆኑን እና ከሙከራ ስራው በመቀጠል መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ በሚጠበቀው የባቡር ፕሮጀክት 41 የባቡር ፉርጎዎች በቻይና ሀገር ተመርተው የመጀመሪያዎቹ ፉርጎዎች በመጪው መስከረም ወር ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ተገልጧል፡፡

ባቡሩ ስራ ሲጀምር ለተወሰኑ ጊዜያት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለሚያስተዳድሩ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ኮንትራክተሮች እንደሚሆኑ አቶ ደረጀ ተፈራ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡