አገር አቀፍ ዜናዎች

መስከረም 06/2007

በኢትዮጵያ ውስጥ ለታካሚዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ከ1250 በላይ አንቡላንሶች የሚገኙ ሲሆን ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ ነው የሚሰጡት፡፡

በዚህም ምክንያት አንድ ታካሚ ወደ ሆስፒታል ከመድረሱ በፊት ህይወቱ ሊያልፍ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካኝነት በአንቡላንስ ውስጥ የህክምና አገልግሎት ለመጀመር እንዲቻል ለህክምና ባለሞያዎች ስልጠና መስጠቱን ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር አሚር አማን ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

መስከረም 06/2007

ምህገ አዳነ የተባለው የ35 ዓመት ጎልማሳ ነው፡፡ ጳጉሜ 2/2006 ዓ.ም በአባይ ወንዝ ነው ከሌሊቱ 10 ሰዓት አደጋ የደረሰበት፤ ቦታው ጨለማ በመሆኑ ምክንያት ሳያስበው ወደ መሃል ገብቶ የተወሰደው ግለሰቡ በውሃ 25 ኪሎ ሜትሮች ከተጓዘ በኋላ ድንገት ያላሰበው ሽሚዙን በያዘው የዛፍ ቅርንጫፍ አማካኝነት ህየወቱ ሊተርፍ ችሏል፡፡ (ቴድሮስ ብርሀኑ)

መስከረም 05/2006

ከ11.3 በሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአዳማ ፍጥነት መንገድ ስራውን በይፋ የጀመረ ሲሆን ለስራው በአሁን ሰዓት አጠቃላይ ከ300 በላይ ሰራተኞች ተሰማርተዋል፡፡ ማንኛውም አሽከርካሪ ለሚጓጓዝበት ኪሎ ሜትር ደረሰኝ ይቆርጣሉ፡፡ ደረሰኙን እስከ መውጫ በር ድረስ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሂወት ሞሲሳ ገልፀዋል፡፡

የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ችግር ቢያጋጥማቸው ተሽከርካሪውን ሊያቆሙ የሚችሉበት 75 ሜትር የማቆሚያ ስፍራ እንዳለም ገልፀዋል፡፡ ተሽከርካሪዎች ጎን ለጎን በሚሄዱበት መንገድ 3.7 5 ሜትር (ሶስት ነጥብ ሰባት አምስት ሜትር)  ስፋት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

መስከረም 05/2006

ከለገዳዲ 30 ሜትር ኪውብ ከቃሊቲ ደግሞ 70 ሜትር ኪዊብ የውሃ አቅርቦት ለማሳካት ለህብረተሰቡ ቃል የገባው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በቃሉ መሰረት ለምን እንዳልተገበረ ላቀረብንለት ጥያቄ የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ሃ/ማርያም አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን እና መብራት ሃይል በተገቢው መንገድ አቅርቦቱን ባለመተግበሩ ቃላቸው አለመጠበቃቸውን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በበኩሉ አስፈላጊውን ስራ አጠናቀናል በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

መስከረም 05/2006

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ አፍሪካን በመወከል በዓለም መድረክ ስታንፀባርቃቸው ከነበሩት ሃሳቦች መካከል የአረንጓዴ ልማት ዋንኛ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በሀገራችን ከሚገኙ የደን ተክሎ መካከል አብዛኛውን የሽፋን መጠን የባህር ዛፍ ተክል በመያዝ የደን ሽፋኑን ያሳደገ ቢሆንም ጠቀሜታው ዝቅተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር አስታውቋል፡፡

በውጭ ሀገር እና በሀገር ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኞች የተቋቋመው ማህበሩ በ1986 ዓ.ም ከመንግሥት ፈቃድ አግኝቶ በ1988 ዓ.ም ቦታውን በመረከብ በእንጦጦ ተራራ ላይ ስራ እንደጀመረ የገለፁት የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር የተፈጥሮ ፓርክ አስተዳደር ክፍል ሃላፊ አቶ መሳይ ስንታየሁ ናቸው፡፡ 1300 ሄክታር በሚሸፍነው ቦታ ላይ የባህር ዛፍ ተክልን በማንሳት ሀገር በቀል ዛፎችን የመትከል ስራው ሲጀመር የተለያዩ ምሁራን የባህር ዛፍ ተክሉ መነሳት እንደሌለበት የገለፁ ቢሆንም አሁን በውጤቱ ደስተኛ መሆን ችለዋል ሲሉ የተናገሩት ሃላፊው የባህር ዛፍ ተክል በተፈጥሮ  የከርሰ ምድር ውሃን የሚሻማና በአካባቢው ሌሎች ተክሎች እንዳይበቀሉ የሚያደርግ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ሊጀመር ችሏል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

ጳጉሜ 05/2006

ሶፉመር ዋሻ መገኛ በሆነችው ባሌ ሮቤ እና የኢንደስትሪ ዞን ወደ ሆነችው ኮምቦልቻ የኢትዮጲያ አየር መንገድ በረራውን በአዲስ መልክ መጀመሩን ኢትዮጲያ አየር መንገድ ዋና  ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ተናግረዋል ፡፡

5800 ምእመናን ይሳተፉበታል  ተብሎ የሚጠበቀው የሀጂ መንፈሳዊ ጉዞ በዛሬው  እለት የተጀመረ ሲሆን ለመጀመሪያ ተጎዦች የሽኝት ፕሮግራም ተደርጎል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

ጳጉሜ 05/2006

September 15 ሰኞ ቀን ላይ የሚውል እንደሆነ የሚጠበቀው ይኸው ስብሰባ ዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ኃ/የተ/የግ/ማ እና በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጥምረት አዘጋጅተውታል፡፡

ከ September 15-18 ባለው ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ለዚሁ ታላቅ የተባለ ስብሰባ በዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመራ ልዑክ ይላካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፎረሙ ኢትዮጵያ የንግድ ትስስሯን ከካናዳ ጋር እንድታጠናክር አጋዥ ነው፤ በካናዳ ፌርሞንት ሮያል ዮርክ ቶሮንቶ ሆቴልም ይዘጋጃል እንደ Yarnsandfibers.com ዘገባ፡፡

ጳጉሜ 05/2006

ጉብኝታቸው ለሶስት ቀናት ያህል እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጥምረት ለማጠንከርም ያለመ ነው፡፡

Indrawati ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝንና ሌሎች የካቢኔው ዋና አባላትን ያገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሀገሪቱ ፈታኝ የሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክርም የተነገረ ሲሆን ከግሉ ዘርፍ፣ ማህበራዊ ተቋማትና የግል ድርጅቶች፣ ከብዙሃን መገናኛ አካላትና ከሌሎችም ወሳኝ ተቋማት ተወካዮች ጋርም ይመክራሉ ተብሏል፡፡

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ስራ ፈጣሪነትን ማበረታታት እና ድህነትን መቀነስ ላይም ዋና ትኩረታቸውን እንደሚያደርጉ World bank.org አስነብቧል፡፡

ጳጉሜ 04/2006

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር, የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን, ሱር ኮንስትራክሽን፣ የቻይና CGGC ካምፓኒ እና ሲኖ ሃይድሮ በትላንትናው እለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ለገባ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ፕሮጀክት ግምባታ የስምምነት ፊርማቸውን አስቀምጠዋል፡፡ የገባ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ፕሮጀክት የሚከናወነው በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ 540 ኪ/ሜትር ላይ በሚገኘው በኢሉ አባቦራ እና በጅማ ዞን አዋሳኝ ላይ ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ሞዴል በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰራ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ሙሁራኖችም የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡

ለፕሮጀክቱ 583.06 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግ ሲሆን 80 ከመቶው ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር እንዲሁም 20 ከመቶ ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተገኘ ነው በማለት የገለፁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱም በ4 ዓመት ከግማሽ ይጠናቀቃል ተብሏል፤ በዚህ ፕሮጀክት ግምባታ 25 ከመቶ የኮንስትራክሽን ስራው በሱር ኮንስትራክሽን የሚከናወን ነው ተብሏል፡፡

(ታሪክ አዱኛ)

ጳጉሜ 04/2006- የባህል ምሽት ቤቶች የሀገራችንን ባህል በማንፀባረቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን ቱሪስቶች ወደ ሌላ የሀገሪቱ ክፍል ከመጓዛቸው በፊት በምሽት ቤቶች ስለ ባህላችን አልባሳት፣ አመጋገብና ጭፈራዎች የተወሰነ ግንዛቤ የሚገኝበት ቦታ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በአንዳንድ የባህል ምሽት ቤቶች ውስጥ የሚካሄዱ ድርጊቶች የኢትዮጵያን በጎ ባህል ከማንፀባረቅ ይልቅ አሉታዊ በሆነ መልኩ ሲያንፀባርቁ እየታየ ይገኛል፡፡

ስለሆነም የህብረተሰቡን የብሄር ብሄረሰቦችን መቻቻል የሚሸረሽሩ ነገሮችን በቃላትም ይሁን በዜማ መቅረብ እንደሌለበትና እንደነዚህ አይነት ድርጊቶችን የሚያካሂዱ የባህል ቤቶች እርምት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

እነዚህንና መሰል ችግሮችን መቅረፍ እንዲቻል ለሁሉም የምሽት ባህል ቤቶች የሚያገለግልና በምን አይነት መልኩ የኢትዮጵያን ባህል ማንፀባረቅ እንዳለባቸው የሚገልፅ የስነ-ምግባር መመሪያ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ሙልጌታ ሰኢድ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም የምሽት ቤቶች የባህል አምባሳደሮች መሆናቸውንና የሀገር ገፅታን በመገንባቱ ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን አውቀው ዝግጁ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸውን ስነ-ምግባር እንዲያሟሉ ለማድረግ የክትትልና የቁጥጥር ስራን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አቶ ሙልጌታ ሰይድ ተናግረዋል፡፡

(ርብቃ ታያቸው)

ጳጉሜ 01/2006- ከዋሽንግተን ዲሲ እና ለንደን ቀጥሎ በርካታ ቆንፅላዎች መቀመጪያ በመሆን የአፍሪካ  የዲፕሎማሲ ከተማ የምትባለው አዲስ አበባ በየአመቱ በሚሊዮን ሚቆጠሩ ጎቢኚዎችን ታስተናግዳለች ፡፡

አዲስ አበባ ሙዚየም ለዚህ ሲባል እድሳት ያስፈልገዋል፡፡

በዋናነት ዘመናዊ ሙዚየም ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ገብረፃዲቅ  ሀጎስ ተናግረዋል፡፡

የሚገነባው ሙዚየም ከሀገራችን ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ከተለያዩ ሀገራት ልምድ ተወስዷል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ጳጉሜ 01/2006

ከ2002ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ በወርሀ ህዳር ሲከበር የቆየው የከተሞች ሳምንት በ2007 ዓ.ም በድሬደዋ ከተማ ሲከበር የከተሞች ፎረም የሚል መጠሪያን ይይዛል ፡፡ ፎረሙ እስከ ዛሬ በተከበረበት ወቅት እህት ከተሞችን ማሳተፍ አልተቻለም፡፡ ይህ ባለመሆኑ ከሌሎች ሀገራት ይገኝ የነበረውን ልምድና እውቀት መውሰድ ባለመቻሉ የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት በመጪው በዓል ላይ እንዲካፈሉ ይደረጋል ያሉት የድሬደዋ ከተማ የኮንስትራክሽንና ማዘጋጃ ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሒም የሱፍ ናቸው፡፡ ከተማዋ የማስተናገድ አቅሟን ሙሉ በሙሉ እንድትጠቀም እና የሀረር ከተማን ለእንገዶች ማረፊያ ለማድረግ መታቀዱን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡

የድሬደዋ ከተማን የቀድሞ ስልጣኔን የሚያሳዩ የውበትና መናፈሻ ስራ እንዲሁም ሌሎች ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገልጹት ሀላፊው በከተማው ውስጥ ያሉ የመንገድ ኣካፋዮች በተለየ ዲዛይን የማሰዋብ እና የባቡር ጉዞ እንግዶች እንዲያደረጉ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ሀላፊው አሳውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ከተማዋን በስም ብቻ የሚያወቁ እንግዶች ሲመጡ የሚፈልጉትን ቦታ የሚያሳዩ የመረጃ ሰጪ ባለሙያዎችና ከጸጥታ ጋር ተያይዞ ያሉትን ስራዎች ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አቶ ኢብራሒም የሱፍ ተናግረዋል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

ነሐሴ 28/2006- በኢትዮጵያ ልዩ የፈጠራ ስራ ባለቤቶች ስራቸውን የማስተዋወቁ እንቅስቃሴ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የፈጠራ ውጤታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣት ከአእምሮአዊ ንብረት ፅ/ቤት ተገቢውን እውቅና ይወስዳሉ፡፡

የፈጠራ ስራው አዲስነት፣ ለህብረተሰቡ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እንዲሁም ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችል መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የፋይናንስ ችግር የሚገጥማቸው የፈጠራ ባለሞያዎችን በቁሳቁስና በገንዘብ የመደገፍ ስራ እንደሚሰራ በኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ፅ/ቤት የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማማከር ድጋፍ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ተስፋዬ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

መብት ያገኙ የፈጠራ ስራዎች  ሁሉ በፅ/ቤቱ አይደገፉም የሚሉት አቶ ያሬድ ፅ/ቤቱ ባለው መመዘኛ መሰረት የሚሰጥ መሆኑን ገልፀው፤ አዲስ ተብለው የሚመጡ የፈጠራ ስራዎች ጥቂት መሆናውን አስታውቀዋል፡፡

እውቅና የሚያገኙ የስራ ፈጠሪዎች ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ስራዎቻቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

(ነጋሽ በዳዳ)

ነሐሴ 27/2006- በኢትዮጵያ ከ66 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች አነስተኛ የእርሻ መሬቶችን በመጠቀም ልዩ ልዩ ሰብሎችን ያመርታሉ፡፡ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ያለምንም ቴክኖሎጂ በባህላዊ ኋላቀር የአሰራር ዘዴ ሲከናወን የነበረው ይህ የእርሻ ስራ ለረጅም ጊዜ ለውጥ ሳያሳይ ቆይቷል፡፡ መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ ግን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ወደ ተሻለ የእድገት አቅጣጫ ማስገባት የቻለ ዘርፍ ነው ተብሏል፡፡ ያም ሆኖ ካለው የሀገሪቱ ሰፊ የእርሻ መሬት እንዲሁም አመቺ የአየር ንብረትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች አንፃር ሲታይ በዘርፉ እጅግ አነስተኛ ባለሀብቶች ብቻ ስለመኖራቸውና ገና ያልተሰራበት ነው የሚሉት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ጥናት ያቀረቡት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ናቸው፡፡

እንደሳቸው ገለፃ ሀገሪቱ ከሌላው ዓለም በተለየ ሁኔታ ዝቅተኛ የሰው ሃይልና የኤሌክትሪክ ዋጋ ስላላት ወደፊት ለባለሃብቶች ትክክለኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ትሆናለች ብለዋል፡፡

(በእንደገና ደሳለኝ)

ነሐሴ 27/2006- ፎረሙ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የግል ባለሃብቶችን እና ወጣቶችን እያሳተፈ የሚገኝ ሲሆን ከወሳኝ ሁነቶች ባሻገር ሁሉን ያካተተ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ አዲስ ራዕይ እና ስትራቴጂ የሚል መሪ ቃልን ይዟል፡፡ በመክፈቻው ፕሮግራም ላይ የናይጄሪያ የግብርና የገጠር ልማት ሚኒስትር ዶክተር ኢክዊኒ ኢዲሼኒ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የልማት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የጥናት ፁሑፋቸውን አቅርበዋል፤ ውይይትም ተደርጎበታል፡፡

የአፍሪካ አረንጓዴ መድረክ አፍሪካ በ2017 ዓ.ም የግብርና ምርት በእጥፍ እንዲጨምር ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡

የመነሻ ጥናት ፅሁፋቸውን ያቀረቡት ዶክተር ኢክዊኒ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ዘርፍ አፍሪካ ያሰበችውን ያህል ለውጥ እንዳታመጣ ማነቆ ሆኖባታል፡፡ የአፍሪካ ሙቀት በ2050 ከ1.5s ወደ 2.5s ከፍ ይላል ተብሎም ይጠበቃል፤ በዚህም ምክንያት አሁን ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የምግብ እጥረት ውስጥ የገቡት 225 ሚሊዮን አፍሪካውያን ቁጥር በ2050 እ.ኤ.አ ወደ 355 ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአፍሪካ አረንጓዴ መድረክ ነገም ቀጥሎ ይውላል፡፡

(በሰላም ተሾመ)

ነሐሴ 23/2006

ይህን ተግባር የሚያከናውነው የውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ይህንን አስታውቋል፡፡ በኤጀንሲው ስር ከሚተዳደሩ 16 ዘላቂ ማረፊያዎች በተጨማሪ በእምነት ተቋማት ስር ያሉ ከ70 በላይ ዘላቂ ማረፊያዎች ወይም የመቃብር ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡

ቁጥራቸው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ እነዚህ በእምነት ተቋማት የሚተዳደሩ ዘላቂ ማረፊያዎች ከተማ ውስጥ ሰፊ ቦታ ይይዛሉ፡፡ በኤጀንሲው የዘላቂ ማረፊያ ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ አጃኢብ ኩምሳ እንዳሉት ከእምነት ተቋማቱ ጋር በመተባበር ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከፊታችን የ2007 ዓ.ም ጀምሮ በየክፍለ ከተማው የሚገኙ የእምነት ተቋማት ዘላቂ ማረፊያዎችን የማሻሻል ስራውን አጠናክረው በመቀጠል የሚታይ ለውጥ ለማምጣት ማቀዳቸውን ሃላፊው ገልፀዋል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ነሐሴ 21/2006- ስነ-ምግባር ከጎደለው አለባበስና የቋንቋ አጠቃቀም ጀምሮ ራቁት ዳንስ ቤቶችና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እስከ መመስረት የሚዘልቁ የራሳችን ያልሆኑ እና ከሀገራችን ባህል ታሪክና ሞራል ጋር የሚጣረሱ ድርጊቶች ይፈፀማሉ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ ችግሩ መሰረተ-ሰፊ ብቻም ሳይሆን ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ከቴክኖሎጂና ከግል ስነ-ምግባርም ጭምር የተያያዘ ስለሆነ በኛ አቅም ብቻ ሊፈታ አይችልም ብሏል፡፡ የቢሮው ሃላፊ አቶ ገብረ-ፃድቅ ሀጎስ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም እንደገለፁት ከአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ከህግ አካላት እና በዋነኝነት  ከነዋሪው ህብረተሰብ ጋር ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ ቢሮአቸው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ላይ በተለይም ከባህል ለውጥ ጋር በተገናኘ ከህብረተሰቡ ጋር መድረኮችን እየፈጠረ እያወያየ ነው ሲሉ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የተጠና ጥናት ተጠናቆ እነዚህ ቤት ያላቸው መጤ ባህሎችን ማስቀረት የሚቻልበትን የተቀናጀ አሰራር ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንገኛለን ሲሉ አቶ ገብረ-ፃድቅ አስታውቀዋል፡፡

ነሐሴ 20/2006- ወጣት ደረጀ ለማና ወ/ሪት ደስታ ሙልጌታ የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ታድያ ወ/ሪት ደስታ ለጊዜው መቼ እንደሆነ ባልታወቀ ቀን ደብረዘይት ሄዳ ለመዝናናት እንቅስቃሴዋንም በፎቶ ማስቀረት ትፈልጋለች፡፡ ግና የፈለገችውን የፎቶግራፍ ማንሻ ባለማግኘቷ 8ሺ ብር የሚያወጣውን የወጣት ደረጀን ሞባይል ተውሳ ትሄዳለች፡፡

ጉዳይዋን ጨርሳ ስትመጣ ከሁለት ጓደኞቿ ጋር በመሆን አመስግና ንብረቱን ትመልሳለች፡፡ ከቀናት በኋላ ግን የተነሳሁት ፎቶ ታጥቦ ይደርስልኛል ብላ ስታስብ በምትኩ የፖሊስ መጥሪያ ይሰጣታል፡፡ ጉዳዩንም ስትመለከት ወጣት ደረጀ በእምነት ማጉደል ወንጀል እንደከሰሳትና የሰጣትን ሞባይል እንዳልመለሰችለት መግለፁን ትመለከታለች፡፡ ወዲያውም ፖሊስ ጣቢያ ቀርባ ንብረቱን መመለሷን ትናገራለች፡፡

ፖሊስም ጉዳዩን ከፌዴራል አቃቤ ህግ ጋር በመሆን መመርመር ይጀምራል፤ ምርመራውን እንዳጠናቀቀም አስፈላጊውን የሰነድ ማስረጃ አጠናቅሮ የወንጀሉን ክስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ፈጣን ምድብ ችሎት ያቀርባል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ክስና ማስረጃ መርምሮ ከሳሽ የነበረውን ወጣት ደረጄ ለምን በሀሰት ሰውን በመወንጀል አንቀፅ 447 ንዑስ /ሀ/ መሰረት ጥፋተኛ ነው በማለት በአንድ ዓመት ፅኑ እስራት እና አንድ ሺ ብር እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡ተሀ