አገር አቀፍ ዜናዎች

መስከረም 19/2007 ዓ.ም

በድንገተኛ አደጋ (ችግር) ምክንያት ታካሚዎች ወደየሆስፒታል በመሄድ ህክምና ለማግኘት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ የድንገተኛ ህክምና ግብረ-ሃይል የተቋቋመ ሲሆን ግብረ-ሃይሉም ታካሚዎች የሚገጥማቸውን እንግልት መቀነሱ ተገልጧል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ግብረ-ሃይሉ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚከታተል ሲሆን በ24 ሰዓት ውስጥ በአዲስ አበባ የተከናወኑ ጉዳዮች ላይም ሪፖርት እንደሚያቀርብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

የህክምና ተቋሞችም ለታካሚ ተገቢውን ህክምና ማድረግ ካልቻሉ ታካሚዎችን በራሳቸው አምቡላንስ ወደ ሌላ ተቋም ይወስዳሉ፡፡ በዚህም የወላጆችንና የታካሚዎችን እንግልት በመቀነስ ረገድ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ወላጅ እናቶች በቤታቸው ሆነው አገልግሎት በሚፈልጉበት ወቅት የጤና ተቋማትን ማናገር እንዲሁም ታካሚዎች ያላቸውን ቅሬታ ወደ 0937-93-93-93 ወይም ወደ 0937-94-94-94 በመደወል ማቅረብ እና አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም አቶ ግርማ አሸናፊ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

መስከረም 19/2007 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የተመራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጳጳሳትና ምዕመናን የተካተቱበት ቡድን ኮተቤ በሚገኘው መቄዶንያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ተገኝቶ ጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ባስተላለፉት መልዕክት የማዕከሉ ተሞክሮ ለሌሎች አርአያና ምሳሌ የሚሆን ነው ካሉ በኋላ እነዚህ ደጋፊ የሌላቸው ወገኖችን መርዳት የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያን ሊሳተፉበት የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ዘር፣ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይ ማንኛውም የተቸገረ ኢትዮጵያዊ የሚረዳበት እንደመሆኑ ህብረተሰቡ ከማዕከሉ ጎን ይቆም ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንም ለማዕከሉ የ100ሺ ብር ድጋፍ ያደረገች ሲሆን ወደፊትም ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ፓትርያርኩ ቃለ ገብተዋል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

መስከረም 16/2007 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የመስቀል ደመራ በአብያተ ክርስቲያን፣ በየአካባቢው እንዲሁም በመስቀል አደባባይ በድምቀት ይከበራል፡፡

በመስቀል አደባባይ በሚከናወኑ ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያናት ፓትሪያርክ ብፁእ አቡነ ማቲያስ፣ ሊቀ-ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ አንባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የእምነቱ ተከታዮች በስፍራው በመገኘት በድምቀት ያከብራሉ፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የባህልና የትምህርት ድርጅት/ዩኔስኮ/ በቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

መስከረም 15/2007 ዓ.ም

በቅርቡ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO)  ያወጣው መረጃ በዓለማችን በየ 45 ደቂቃው አንድ ሰው  ራስን የማጥፋት እርምጃ እንደሚወስድ አመላክቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገራችን አልፎ አልፎ ከሚታይባቸው ቦታዎች ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ይህን እርምጃ በራሳቸው ላይ የሚወስዱት በውጤት ባለመርካታቸው፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደስታን በማጣትና ድንገት የሚጀምሩት የፍቅር ግንኙነት ባለመሳካቱ እንደሆነ ከአንዳንዶች ህልፈት በኋላ የተቀመጡ መንስኤዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ ጉዳይ ምንም እንኳን በጥናት ባይደገፍም የችግሩ መኖር ሃቅ መሆኑን የሚገልፁት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ናቸው፡፡ እንደርሳቸው ገለፃ ከሆነ በተቋማቱ አካባቢ የሚገኙ ጫት ቤቶችና መጠጥ መሸጫዎች ከሚያስከትሉት የስነ-ምግባር ጉድለት ባሻገር ለዚህ ድርጊት መፈፀም ትልቅ ሚና አላቸው፤ ይህንንም ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ (ቴድሮስ ብርሀኑ)

መስከረም 15/2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደም ባንክ በማዕከላዊና ተንቀሳቃሽ ቡድን ተደራጅቶ ባከናወነው ተግባር ከ80,180 ከረጢት በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉ ተገልጧል፡፡

ተቋሙ በተለያዩ ስልጠናዎች፣ ስብሰባዎች እንዲሁም ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ደም የመሰብሰብ ስራ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና በመውሰድ ላይ ከሚገኙ ተማሪዎች ደም በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህም ከ180 በላይ ከረጢት ደም መሰብሰብ መቻሉን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የተንቀሳቃሽ ቡድን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሚኪያስ ማሞ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም አምና በወር ውስጥ ከሚለገሰውና ከዚያም በላይ በመንቀሳቀስ ይሰበሰብ የነበረውን ደም በአሁኑ ወቅት በ1 ወር ጊዜ ውስጥ መሰብሰብ መቻሉን አቶ ሚኪያስ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ደም ለመሰብሰብ በሚንቀሳቀሰው ቡድን ውስጥ ከ5-7 የሚደርሱ አባላት እንዳሉት ገልፀው በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስልጠና ከመጡ ተማሪዎች እንዲሁም አስተባባሪዎች ጋር በመነጋገር በቀጣይ ቀናቶች ውስጥ የሚኖረው ስልጠና ላይ በመገኘት የሚሰበስቡ ሲሆን ከምንግዜውም በላይ በደም ልገሳ ዙሪያ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲሁም ፈቃደኝነት ላይ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

መስከረም 14/2007

በ2006 ዓ.ም በከተማዋ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ በ20/80 እና በ10/90 እንዲሁም 40/በ60 የጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ መከናወኑ ይታወሳል፡፡ ለነባር ተመዝጋቢዎች 73 ሺ የቤት ግንባታዎች በተያዘው ዓመት የሚጠናቀቁ ሲሆን በ2006 ዓ.ም መጨረሻ የተጀመሩ 50ሺ ቤት ግንባታቸው እየከተናወኑ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል እጣ የወጣባቸው ወደ 22ሺ አምስት መቶ አስራ ሁለት ቤቶች የቁልፍ ርክክብ እየተከናወነ የሚገኝ እና በአሁን ሰዓትም 15ሺ መድረሱም ተገልጧል፡፡ በአሁኑ ሰዓት 30ሺ ቤቶች 90 ከመቶ መድረሳቸውን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ ናቸው፡፡ ለአዲስ ተመዝጋቢዎች የተጀመረው የ10 በ90 24ሺ አምስት መቶ ቤት ግንባታ 80 ከመቶ ድረሱንም ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ከተመዝጋቢ ቁጥር በላይ ቤት ተገንብቷል ብለዋል ፡፡ በዚሁ በያዝነው ዓመት የቤቱ ዕጣ እደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ 20 በ80ን በተመለከተ ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በፈጣን ሁኔታ እየተሰሩ መሆናቸወንም ተናግረዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

መስከረም 14/2007

የትራኮማ በሽታ በአገራችን ሰፊ በሆነ መልኩ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ከ1-9 ዓመት በሆናቸው ህፃናት ላይ ይስተዋላል፡፡

በሽታውም በተገቢው ሰዓት ህክምና ካልተደረገለት አይነ-ስውርነትን ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጧል፡፡ በአሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ሰዎች በበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቁ ሲሆን ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህዝቦች የዚትሮማክስ መድኃኒት ለተከታታይ 5 ዓመታት እንደሚያስፈልግ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ቡድን አስተባባሪ አቶ ኡመር ሻፊ ተናግረዋል፡፡

በሽታውን ለመከላከል በአማራ ክልል ከ6 ዓመት በላይ የዚትሮማክስ መድኃኒት ሲከፋፈል የቆየ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ መከላከል አለመቻሉን አስታውቀዋል፡፡

አያይዘውም በሽታውን ለመከላከል ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢ ንፅህና ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓትም በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ላይ የትራኮማ መድኃኒት የሆነውን ዚትሮማክስን በማከፋፈል ላይ እንደሚገኙ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ቡድን አስተባባሪ አቶ ኡመር ሻፊ ገልፀዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

መስከረም 13/2007

በሀገሪቷ የማርና ሰም አምራቾችና ላኪዎች መኖራቸው ይታወቃል፤ ሆኖም አምራቾቹ በዋናነት ከሚያነሱት ጥያቄዎች መካከል የላብራቶሪ ፍተሻ መሳሪያ አለመኖር ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ መሳሪያ ባለመኖሩም ወደ አውሮፓ በማቅናት ለአንድ ናሙና 50 ዩሮ ለማውጣት መገደዳቸውን ገለፀዋል፡፡

በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተውን በጉዳዩ ዙሪያ አናግረናቸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃም የላብራቶሪ መፈተሻ መሳሪያውን ለሟሟላት በመንግሥት በኩል ብዙ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ ወደፊትም ጥያቄያቸው መልስ እንደሚያገኝ ገልፀዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

መስከረም 13/2007

በአርሲ ዞን ዝዋይ ዱግዳ ወረዳ ቡርካ ለመፋ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ይኸው ጀማል ሙሀመድ የተባለው ግለሰብ ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ከነበረው ህጋዊ ያልሆኑት ሚስቱ ባፈራው ልጅ ላይ ነው ይህንን ድርጊት የፈፀመው፡፡ ለ5 ዓመት በድብቅ ሲፈፀም የነበረውን ግንኙነት የአካባቢው ነዋሪ በማወቁ በተሰማው መሸማቀቅ እንደሆነ ይህንን ድርጊት የፈፀመው ከዞኑ ፖሊስ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

በባለቤቱ ጥቆማ እና በቤተሰብ ግፊት በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለው ይኸው ግለሰብ ለጊዜው ድርጊቱን አልፈፀምኩም ብሎ ቢክድም እያደር በተሰማው ፀፀት ግን ድርጊቱን መፈፀሙን ሊያምን ችሏል፡፡ በፖሊስ የሰውና የሰነድ ማስረጃ የቀረበለት የወረዳ አቃቤ ህግም ከዞኑ ፍትህ ፅ/ቤት ጋር በአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ ተመስርቶበታል፡፡ ክሱን የተመለከተው ፍ/ቤትም ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ የ18 ዓመት ፅኑ እስራት ወስኖበታል፡፡ (ቴድሮስ ብርሀኑ)

መስከረም 12/2007

ተከሳሽ ሙዘይን ሰይድ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ልዩ ቦታው ጉርጂ በመባል የሚታወቅ አካባቢ ነዋ ነበር፡፡

ታህሳስ 18/2006 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ሲሆን ታድያ በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ አረቄ መሸጫ ጎራ በማለት አንድ ሁለት ሲል ያመሻል፡፡

ጉዳዩን ጨርሶ ወደ መኖሪያው ሲመለስ ሟች አቢግዴለው በእርሻ ስራው ላይ ተጠምዶ ያገኘዋል፡፡ ወትሮም በማሳና በሰብል ነክተህብኛል አልነካሁም የተነሳው ክርክር ላይ የነበሩት እነዚህ ግለሰቦች ወደ አልተገባ ጭቅጭቅ መግባታቸው ለአቶ አቢ በጩቤ መሞት ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ 

ወዲያውም አረቄውን ስትሸጥለት የቆየችውና ሁኔታው አላምር ብሏት ለማረጋጋት የሞከረችው ሻጭም ተከትላው ነበርና ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ለፖሊስ በሰጡትም ጥቆማ በቁጥጥር ስር ሊው ችሏል፡፡

ክሱን ሲመለከት የቆየው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መስከረም 8/2007 በዋለው ችሎት በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተስኖበታል፡፡ (ቴድሮስ ብርሀኑ)

መስከረም 12/2007

ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው የሚገኙና ኢንቨስት ለማድረግ አሁንም እየገቡ ያሉ መኖራቸው ይታወቃል፤ ይህም ለሀገር እድገት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ሆኖም ግን ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ከተፈቀደላቸው ዘርፍ ውጪ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለመከታተልና ቁጥጥር ለማድረግ የክትትል ቡድን ማቋቋሙ ተገልጧል፡፡

ይህ ቡድን ፕሮጀክቶችን በመከታተል ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ የሚያደርግ እና ከተፈቀደላቸው ውጪ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ተከታትሎ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ለዛሚ 90.7 የገለፁት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሰይድ ናቸው፡፡ በቅርቡ በአማራ ክልል በፍቼ ገነት አካባቢ አርማታ ብረት ለማምረት ፍቃድ ወስዶ የነበረ ባለሃብት ምርቱን በማቆም ያለቀለት አርማታ ብረት እያስገባ በማሸጥ ላይ የነበረ በመሆኑ ሰሞኑን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንሰጡት ተናግርዋል፡፡በአዲስ አበባ ከተማም በተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጡ ተናግረዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

Haymanot alemu

መስከረም 09/2007

ተዋናይ፣የፊልም ዳይሬክተር፣ መምህር፣ የዳንስ ጥበብ ባለሙያ፣ የማስታወቂያ ባለሙያና አማካሪ የነበረው ሀይማኖት በአሜሪካ ሚኔሶታ ዩኒቨርስቲ ነው የትወና ትምህርት 2ኛ ዲግሪ ያገኘው፡፡ በብሉ ናይል የፊልምና ቴሌቪንዥን አካዳሚ መምህር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግሏል፡፡

ፊት ለፊት በተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ፣ ግርዶሽ እና ጉዲፈቻ በተሰኙት የፊልሞች ላይም በመተወንና በሌሎች ስራዎቹ እውቅናን አትርፏል፡፡

በፊልምና ተያየዥ ጉዳዮች ላይም የማማከር አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ 

መስከረም 9/2006

በጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልል ደረጃና በዞን እንዲሁም በወረዳ የሚገኙ ከ9 በላይ የሆኑ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ከትናንት በስቲያ እና በትናንትናው ዕለትም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ የዚህ መንስኤ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች በክልሉ ነዋሪዎችና ከሌሎች ክልሎች የሰፈሩ የማህበረሰብ አካላት ጋር በተፈጠረው ግጭት ነው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገው፡፡ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ናቸው ተብለው በመጠርጠራቸው መሆኑን በተለይ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም የገለፁት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቡን ዊዩ ሲሆኑ የግጭቱ መነሻ በመሬት ይዞታ ግጭት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት የፖሊስና የመከላከያ አባላት የማረጋጋት ስራ መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው የችግሩ መንስኤ እየተጣራ መሆኑንና በጉዳዩ ላይ እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩትን አካላት ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ለማዋል ምርመራ መጀመሩን ገልፀው በተፈጠረው ግጭትም ከይዞታቸው የተፈናቀሉ ግለሰቦችን በየቦታቸው የመመለስ ስራ መሰራቱንም ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ገልፀዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

መስከረም 8/2006

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1980 የተመሰረተው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መስከረም 27 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 17 ቀን የተመሰረተ በመሆኑ በየዓመቱ በመላው ዓለም ታስቦ ይውላል፡፡ ይህ አጋጣሚ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በድምቀት ከሚከበረው ከመስቀል በዓል ጋር መገጣጠሙ ሀገራችን ያላትን የቱሪስት መስህብ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ይጠቅማል ሲሉ የገለፁት በኤ.ፌ.ዴ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት  ባለሞያው አቶ መላኩ አላምረው ናቸው፡፡

የዓለም ቱሪዝም ቀን የፊታችን መስከረም 17 ቀን 2007 ዓ.ም ‹‹ቱሪዝም ለማህበረሰብ ልማት›› በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ35ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ27ኛ ጊዜ በአፋር ብሔራዊ ክልል ይከበራል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት በሀገራችን ከማይዳሰሱ ቅርሶች ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኔስኮ የተመዘገበው የመስቀል በዓል አከባበርም በድምቀት ተከብሮ እንደሚውል ተገልጧል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

መስከረም 8/2006

በጋምቤላ ክልል የሚገኘውና የጊኒ ዋር በመባል የሚታወቀው በሽታ ንፅህናው ያልተጠበቀ ወይም የተበከለ ውሃ ለመጠጥ አገልግሎት በሚውልበት ጊዜ ይከሰታል፡፡

በሽታውም ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የሚታወቅ ሲሆን ከተጠቂው እግር እስከ 1 ሜትር የሚሆን ትል እንደሚወጣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትኩርት የሚሹ ትሮፒካል በሽታዎች ቡድን መሪ የሆኑት ሁመር ሻፊ ተናግረዋል፡፡

በጊኒ ዋርም የተጠቃ ሰው እግሩ ላይ በሚፈጠርበት ከፍተኛ የሆነ የማቃጠል ስሜት ወደ ወንዝ በመሄድ እግሩን በሚነክርበት ጊዜ የጊኒ ዋርም ከእግሩ ወጥቶ ወደ ወንዝ በመግባት ጤነኛውን ሰው እንደሚያጠቃ አቶ ሁመር ሻፊ ገልፀዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

መስከረም 8/2006

የጉብኝታቸውም አላማ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት ለማጠናከር ነው ተብሏል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከዶክተር ኒኮሳዛ ዲላሚኒ ዙማ  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በቆይታቸው ተገናኝተው በተለያዩ የሰላምና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ጉብኝታቸውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታውቀዋል፡፡ (ቴድሮስ ብርሀኑ)

መስከረም 8/2006

በክልሉ ከዚህ ቀደም በሽፍቶች አማካኝነት በተለያዩ ቦታዎች የስርቆት ወንጀል ይከሰት እንደነበር ይታወቃል፤ በአሁኑ ሰዓት ግን የስርቆት ወንጀል መቀነሱን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም የገለፁት የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽፈራው ጩሊር ናቸው፡፡

ከወራት በፊት በተደረገ እንቅስቃሴ ከአማራ፣ ከትግራይ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል እና ከቤንሻንጉል የተደራጁ አምስት (5) ዋና ዋና በስርቆት ወንጀል የተሰማሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የአካባቢ ሰላም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በአሁኑ ሰዓት 350 (ሶስት መቶ ሃምሳ) የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ አባላትን በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

መስከረም 07/2007

በየዓመቱ የኦፔክስ ሽልማት ይካሄዳል፤ በቅርቡም በፈረንጆቹ ከመስከረም 15-18/2014 በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ተካሂዷል፡፡

በአስራ ሶስት ቋንቋዎች ደንበኞች ድምፅ እንዲሰጡ የተደረገ ሲሆን በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ አንደኛ ሆኖ ተመርጧል፡፡

ሽልማቱ አየር መንገዶች በደንበኞች አገልግሎት ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ ሲሆን በውጤታቸው መሰረት በሚያገኙት ምላሽ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዲያውቁ የሚጠቁም መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም መስከረም 15 በተካሔደው ስነ-ስርዓት ዓለም አቀፍ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡

አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሽልማቶችን መቀናጀቱ የሚታወስ ነው፡፡

(ሱራፌል ዘላለም)