አገር አቀፍ ዜናዎች

በዘንድሮው ክረምት ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ከባድ ጉዳት ለመቀነስ ከ1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የመጠባበቂያ ምግብ ተከማችቶ ተዘጋጅቷል::
የትሮፒካ ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከ5ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ የሚሞቅ ከሆነ ኤልኒኖ ፤ ከ0.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች የሚቀዘቅዝ ከሆነ ደግሞ ላሊና ይባላል ሲሉ የዘርፏ ባለሙያዎች ስለ ተፈጥሮ ክስተቶቹ ኤልኒኖና ላሊና ይናገራሉ፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወቅት አብዛኛው የላኒናን ክስተት ተከትሎ ከባድ ጎርፍ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ሊከሰት እንደሚችልም የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የትንበያ ሪፖርት ያመለክታል። ይህም በሰዎች፣ በንብረትና በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያሰከተላል፡፡ ከመደበኛው መጠን በላይ ይዘንባል ተብሎ በሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ምክንያት የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ለችግር ሲል ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሰራው መረጃ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ 700 ወረዳዎች አሉ ከነዚህ መካከል ለአደጋ ተጋላጭ ተብለው 300 ወረዳዎች ላይ በተካሄደ ጥናት በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሚከሰቱት አደጋዎች ጎርፍና ድርቅ መሆናቸው ተለይቷል፡፡
ታዲያ በዚህ ጉዳይ ላይ በሀገሪቱ በባለፈው አመት በአየር መዛባት (ኤልኒኖ) ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቶ ከ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተረጂ እንደሆኑ ይታወሳል፡፡ በኤልኒኖ ምክንያት በተፈጠረው ድርቅ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህል ከኤጀንሲው ወጪ ተደርጓል። ለሴፍቲኔት ፕሮግራም 130 ሺ ሜትሪክ ቶን ፣ ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ 270 ሺ ሜትሪክ ቶን ተሰጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት አስተዳደር ሊከሰት የሚችለውን ከባድ ጉዳት ለመቀነስ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምግብ ክምችት ማዘጋጀቱን ገልïል፡፡
በ2008 በጀት ዓመት 20 ሺ ሜትሪክ ቶን ታዝዞ በጥራት ጉድለት 7 ሺ 500 ሜትሪክ ቶን ተመላሽ መደረጉን ይታወሳል፡፡ በኤጀንሲው መስፈርት መሠረት ከባዕድ ነገር ንጹሕ መሆኑን፣የእርጥበት መጠኑ፣ አቧራማነቱ፣ ጠጠራማነቱ፣ በተባይ አለመያዙና አለመበላቱ እንዲሁም የተሰባበረና የተጨማደደ አለመሆኑ ይረጋገጣል፡፡
ጥራቱን የጠበቀ እህል ማከማቸት ካልተቻለ ለረጅም ጊዜያት በተቀመጠ ቁጥር እህሉን ለማከም የሚወጣው ወጪ እየጨመረ፣ ንጥረ ነገሩን እያጣ ስለሚሄድ ለሰው ልጅ ምግብነት ወደማይውልበት ደረጃ በመድረስ ኪሳራ ሊያስከትል ስለሚችል በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ይመዘናል፡፡
ከ89 ነጥብ5 በላይ ንጹሕ ከሆነ በሁለተኛ ደረጃነት፣ ከ94 በመቶ በላይ አንደኛ ደረጃ ንጹሕ ሆኖ ገቢ እንደሚደረግም ኤጀንሲው በመስፈርትነት አስቀምጧል፡፡
የላኒናን ክስተት ተከትሎ በሚከሰት ከባድ ዝናብ ብቻ ሳይሆን የክረምት ዝናብ በጨመረ ቁጥር አብዛኞቹ የሀገሪቱ ክፍሎች በስጋት ላይ ያሉ መሆናቸው ይታወቃል።በክረምት ወቅት ይዘንባል ተብሎ በተተነበየው ከባድ ዝናብ 486ሺ 10 ሰዎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የበሻሌ አካባቢ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች መንግስት ቃል የገባላቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አላሟላልንም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ በሻሌ ትምህርት ቤት አካባቢ ለልማት ቦታው ይፈለጋል በሚል ምክንያት መንግስት ለዓመታት ከኖርንበት መሬታችን ቢያስነሳንም ቃል የተገባልን የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቆዎቻችን አልተመለሱም ለከፋ ችግርም ተጋልጠናል ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለዛሚ ቅሬታቸውን አቅርበዋል ፡፡
ስሜ አይገለፅ ያሉት የሰባ ዓመት አዛውንት በወቅቱ መንግስት መሬቱን ለልማት እፈልጋለው ሲለኝ 40.000 ካሬ ሜትር የሆነ የእርሻና የመኖሪያ መሬቴን መንግስት ወስዶ አሁን እኔንና መላ ቤተሰቤን ዞር ብሎ አላየም ችግር ላይ ነኝ ብለዋል፡፡
የአካባቢው ኗሪ የሆኑት አርሶ አደር አሰፋ አርሶ አደሩ አርሶ እንዳይበላ እዚህ ግባ በማይባል ካሳ መሬቱን መወሰዱ ሳያንሰው ቃል የተገባልን የመንገድ የመብራት ስራ ባለመሰራቱ ችግር ላይ ወድቀናል ሲሉ ስሜ እንዳይገለፅ ያለው ወጣት እኛ ወጣቶች በመንግስት አካላት ተደራጅታችሁ ስራ ትጀምራላችሁ ተብለን ነበረ አሁን ግን ተታለናል ይላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና መህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የልማት ተነሺ አርሶ አደር የልማት መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኩርኩራ ሙሉ ስማቸው እንዲገለፅ ፈቃደኛ ባይሆኑም ዛሚ ስለጉዳዮ አነጋግሮ ቢሮአችን ከተቋቋመ አንድ ዓመቱ ነው ይህን መረጃም ለመስጠት አንችልም ብለውናል፡፡
የቢሮ አላፊው ይህን ቢሉንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2009 እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ አቅጣጫ ሪፖርቱ ላይ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ከ22 ሺህ በላይ የልማት ተነሺ አርሶ አሰደሮች እና ቤተሰቦች መረጃ መደረጀቱንና ለ396 የአርሶ አደር ልጆች በማዕድን ስራ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ይላል፡፡
ምትኬ ቶሌራ

በአዲስ አበባ የቀን ገቢ ግምት ገማች ባለሞያዎች ስራቸዉን ቢያጠናቅቁም አሁንም ግን ቀን ገቢ ገማች ነን የሚሉ ህገ-ወጦች መኖራቸዉ ታዉቋል፡፡
የቀን ገቢ ገማች ነን እያሉ ባጅ አንጠላጥለዉ የሚዘዋወሩ ሕገ ወጥ ገማቾች ተጭበርብረናል ሲሉ አንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ ቅሬታቸዉን ለዛሚአሰምተዋል፡፡
በጉዳዩም ላይ የኢትዮጲያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ ታክስ ፕሮግራምና ልማት ስራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ነፃነት አበራ እደገለፁት ገማች ባለሞያዎችን ካስዎጣንና ስራዉን ካጠናቀቅን ወር ሆኖናል በመሆኑም ህብረተሰቡበህገወጥ ገማቾች እንዳይታለል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ትብለጽ ተስፋዬ ዘግባዋለች፡፡

በ40/60 የቤት ግንባታ ከውል ውጪ የካሬ ጭማሪና ባለ 4 መኝታ ቤት መገንባቱ አግባብ አይደለም ሲሉ ቀድሞ የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ የቤቱ መገንባት ለተጠቃሚዎች ተጨማሪ እድል ነው ሲል ምላሽ ሰቷል፡፡
በ40/60 የቤት ፕሮግራም ተመዝጋቢዎች እንደሚሉት ከሆነ ቀድመን የከፈልን በመሆናችን እንደቅደም ተከተላችን ልንስተናገድ ሲገባን ይህ አለመደረጉ አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሚዩንኬሽን ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በልሁ ታከለ የተዋዋልነው ውል ምዝገባው በጀመረ ለተከታታይ 18 ወራት የቆጠቡት ጨምሮ በእጣው እነደሚሳተፉ የሚገልፅ ነው ሲሉ ምላሽ ሰተዋል፡፡
ተጠባባቂ ስራ አስኪያጁ ይህን ቢሉም በተመዝጋቢዎች እጅ የሚገኘው ውል ቅድሚያ ለከፈሉ ቅድሚያ እንደሚሰጥ እና በቅደም ተከተል ቤቱ እንደሚተላለፍላቸው ያሰረዳል፡፡ ከ166 ሺ በላይ ግለሰቦች የተዋዋሉበት የግንባታ ውል እያለ አንድም ሰው ያልተዋዋለበትን ግንባታ ለምን አስገነባችሁ ለሚለው ጥያቄ አቶ በልሁ ታከለ ይህ እንደ ተጨማሪ እድል ሊታይ ይገባዋል የሚል ምላሻቸውን ሰተዋል፡፡
ተመዝጋቢዎቹ በበኩላቸው አማራጩ መልካም ቢሆንም ላላሰብነው ውጪ የሚዳርግ አሰራር በመሆኑ መንግስት ተጨማሪ አማራጮችን ሊያስቀምጥልን ይገባል በማለት ቅሬታቸውን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በውላችን መሰረት ልንሰተናገድ ሲገባን ቅድሚያ ከፍለን ከዳር መቆማችን በ40/60 ላይ በባንኩ አሰራር እምነት ያሳጣናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከውል ውጪ ተገንብተዋል በተባሉት የቤት አማራጮች ላይ የተሳተፉት ግለሰቦች ተጨማሪ እድል ነው የሚለው ባንኩ፤ በሌላ በኩል ግለሰቦቹ እንደ እድል ሳይሆን ተጨማሪውን መክፈል እንደ እዳ ቢመለከቱት የባንኩ አሰራር እንዴት ይሆናል ለሚለው ጥያቄ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጁ በቂ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2010 የበጀት አመት 7 ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን እከተላለው አለ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2010 በጀት ዓመት ዋና ዋና የዕቅድ አቅጣጫዎችን በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቀው በ2010 የበጀት ዓመት ዕቅዴን ለማሳካት የምጠቀምበትን 7 የትኩረት አቅጣጫዎቼን ለምክር ቤቱ አባላት እወቁልኝ ብለዋል፡፡
የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ማስቀጠል‚ የስራ አጥነትን ችግር መቅረፍ ‚ለልማት የሚውሉ መሬቶችን መልሶ የማልማት ስራ ‚የትምህርቱንና የጤናውን ዘርፍ ማጠንከር‚የተጀመረውን የቤት ልማት ዘርፍ ማጎልበት ‚የከተማዋን የውሃ አቅርቦት መጨመር ‚በንግድ በኢንዱስትሪና ለኢንቬስትመንት ዘርፍ ትኩረት መስጠት የሚሉት በከተማ አስተዳደሩ ትኩረት የተሰጣቸው 7 ጉዳዮች ሆነዋል፡፡
የፍትህ ዘርፉ አስተማማኝ ማድረግ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ ተቀዳሚ ስራዎቼ ይሆናሉ ብሏል፡፡
ዛሬ የተጀመረው የምክር ቤቱ አራተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ጉባዬ እስከ አምሌ 5 ሲቆይ የከተማ አስተዳደሩን የፍርድቤት እንዲሁም የዋና ኦዲተሩና የቋሚ ኮሚቴዎችን ሪፖርት ያዳምጣል አዋጆችንም ያፀድቃል ተብሏል፡፡
ዘገባው የምትኬ ቶሌራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቆሼ አካባቢ በደረሰ አደጋ ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል አለ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቆሼ አካባቢ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በደረሰ የአፈር ክምር መደርመስ አደጋ ከህብረተሰቡ 98.4 ሚሊዮን ብር እና ከ7.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘቱን ገልፃል፡፡
ከህብረተሰቡ በተገኘ እርዳታም በተሰራው ተጎጂዎችን የማቋቋም ስራ ለ16 ህጋዊ ይዞታ ባለቤቶች ምትክ ቦታና ካርታ ለ13 የህጋዊ ይዞታ ባለቤቶች ልጆች የጋራ ህንፃ መኖሪያ ለ54 ተከራዮች 10/90 ኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤት ሲሰጥ ለ102 ህገ ወጥ ሰፋሪዎች አስተዳደሩ 24 ሚሊዮን ብር ወጪ አደረኩባቸው ያላቸውን ቤቶች አከራይቷቸዋል፡፡
አሁንም ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ 98 ህጋዊ ይዞታ ባለቤቶች ምትክ ቦታና ካሳ አግኝተዋል ተብሏል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለተጎጂዎች 32 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ የተነገረ ሲሆን ቀሪው 66 ሚሊዮን ብር ለቀጣይ ተመሳሳይ ዓላማ ይውላል ተብሏል፡፡
በአደጋው የ118 ዜጎች ህይወት ሲያልፍ 592 ሰዎች በአደጋው ተጎጂዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ዘገባው የምትኬ ቶሌራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ 158 የንግድ ድርጅቶችን ፍቃድ አገደ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ 189‚328 የንግድ ቤቶች ላይ ባደረገው መደበኛ ቁጥጥር 158 የንግድ መደብሮች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ይዘው በመገኘታቸውና በህገ ወጥ ንግድ ላይ ተሳትፈው ስላገኘዋቸው አግጃቸዋለው ብሏል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ከክፍለ ከተማና የወረዳ የፀረ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ ግብረ ሃይል ጋር በመሆን በሰራው ስራ ፍቃዳቸው ከታገደባቸው የንግድ መደብሮች በተጨማሪ 8‚597 የንግድ መደብሮች ታሽገው እንዲቆዩ የተወሰነ ሲሆን 13 ሺህ የንግድ ድርጅቶች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 289 ሺህ የንግድ ፍቃድ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
ዘገባው የምትኬ ቶሌራ ነው፡፡

መንግስት በአዲስ አበባ ከሚገኙ 6 ነዋሪዎች መካከል 1 ሰው በኮንደሚንየም ይኖራል ቢልም፤ ለ40/60 የተመዘገቡ ቅሬታ አቅራቢዎች በበኩላቸው የመንግስት አካላት ህጉን እንደፈለጉት በመቀያየራቸው እምነት አተናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

ሙሉ ክፍያውን ብንከፍልም መንግስት ቃሉን ሳያከብር ከውል ወጪ እጣ ማውጣቱ አግባብ አይደለም ሲሉ በ40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች ቅሬታቸውን ለዛሚ ኤፍ ኤም አሰሙ፡፡ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አቶ ጎህሽ ሀይሌ እንደሚሉት ከሆነ ምዝገባው ከተጀመረ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ሙሉ ክፍያውን ያጠናቀቀ ማንኛውም ግለሰብ ቅድሚያ እንደሚያገኝ ውል ገብተናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የቅሬታ አቅራቢዎቹን ጥያቄ በተመለከተ የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተር ፕራይዝ የኮሚዩንኬሽን የስራ ሂደት መሪ አቶ ዮሀንስ አባይነህ ይህ ጉዳይ እኛን አይመለከትም በማለት ምላሻቸውን ሰተዋል፡፡
ለዓመታት ሙሉ ክፍያውን ከፍለን የቤት ባለቤት ለመሆን በመጠባበቅ ላይ እያለን ሐምሌ 1 2009 የ40/60 የቤቶች እጣ እንደሚወጣ እና በእጣው የሚካተቱት ከምዝገባው ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት የከፈልነው ብቻ ሳንሆን ለአንድ አመት ከስድስት ወር ያህል የቆጠብትንም ያጠቃልላል የሚለውን አስደንጋጭ የዕለተ ሀሙስ መግለጫን ስንሰማ ወደ ሚመለከተው የንግድ ባንክ ሀላፊ በማምራት አካሔዱ ትክክል አለመሆኑን ተነግሮናል ይላሉ ቅሬታ አቅራቢው፡፡

ለቅሬታ አቅራቢዎቹ የተሰጠው ምላሽ ትክክል ስለመሆኑና የቆጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ይመለከተዋል ስላለው ጉዳይ ለማነጋገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሚዮንኬሽን ተቀዳሚ ስራ አስኪያጅ የሆኑትን ሀላፊ ለማነጋገር ብንሞክርም ዛሬ ላይ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ አሳውቀውናል፡፡በየትኛውም አሰራር ቢሆን ህግ ወደ ኋላ አይመለስም እናም በሌለ ህግ ነው የተዳኘነው ሲሉ አቶ ጎህሽ ሀይሌ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ 6 ስዎች መካከል 1 ሰው በኮንደሚንየም ውስጥ መኖር መጀመሩን ሀምሌ 1 2009 ዓ.ም በነበረው የቤቶች ማስተላለፍ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል፡፡

ሀምሌ 1 2009 ዓ.ም በተላለፉት 972 የ40/60 ቤቶች መካከል ባለ 4 መኝታ ቤቶች ይገኙበታል ከቤት ፈላጊዎች ፍላጎት እና ውል ውጪ ለምን ባለ 4 መኝታ ቤቶች ተገነቡ ለሚለው ጥያቄ አቶ ዩሀንስ አባይነህ የአበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተር ፕራይዝ የኮሚዩንኬሽን የስራ ሂደት መሪ እንደሚሉት ከሆነ የዲዛይን ለውጥ መምጣቱ እና የንግድ ባንክ ዋነኛ የጉዳዩ ባለቤት በመሆኑ ገንቡ ስንባል ገንብተዋል ሲሉ ምላሽ ሰተዋል ፡፡በውሉ መሰረት ባለመስራቱ በመንግስት ላይ እምነት ያሳጣናል ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ከ 972ቱ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የ 320 የንግድ ቤቶቹ በጨረታ እንደሚተላለፉ በዕለተ ቅዳሜ ተነግሯል፡፡ በ 40/60 የቤት ልምት ተጠቃሚ ለመሆን ከ 166 ሺ የቤት ፈላጊዎች ሲመዘገቡ 17 ሺ 644 ተመዝጋቢዎች መቶ ፐርሰንት ክፍያቸውን አጠናቀዋል፡፡41300 የሚሆኑት ደግሞ 40 ፐርሰንት ክፍያቸውን ማገባደዳቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡

ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

ኢትዮጲያ ብሄራዊ የንባብ ቀን ሊኖራት ነው ፡፡
ከ2006 ዓም ጀምሮ በየዓመቱ ሰኔ ሰላሳ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ የንባብ ቀን ሆኖ እንዲከበር በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ጥረቶች ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ በአገሪቱ ደረጃ ብሄራዊ የንባብ ቀን ሆኖ ሊከበር ነው ተባለ፡፡
የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ለአራት አመታት የዓመቱ ተማሪዎች መደበኛ የትምህርት ሲያልቅ ከንባብ ጋር እንዳይቆራረጡና ይበልጥ ከመጸሀፍት ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ የሰኔ ሰላሳ የንባብ ቀን መከበር መጀመሩን የገለፁት የኢትዪጲያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ሙሴ ያዕቆብ በቅርቡ ይህ የንባብ ቀን ለፓርላማ ቀርቦ ብሄራዊ የንባብ ቀን ይሆናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ላለፉት 57 ዓመታት በኢትዮጲያ የስነ ፅሁፍ የዕውቀትና የንባብ ባህል እድገት እንደተወጡት ሚና ደራሲያኑ ከብዕር ትሩፋቶቻቸው መጠቀም ያለባቸውን ያህል እንዳልተጠቀሙና ቤት ንብረት ያላፈሩ በመሆናቸው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ ደራሲያን ፅሁፎቻቸውን ለማሳተም የገንዘብ አቅም ፈታኝ የነበረ ሲሆን በተዘዋዋሪ የህትመት ፈንድ ስርዓት ቀደም ሲል ከአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ከሩብ ሚሊየን ብር በላይ አጫጭር ታሪኮች መታተማቸውን በኃላም ከብራንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋር በመሆን በሶስት ሚሊየን ብር ድርሰቶቻቸውን ማሳተም ላልቻሉና ማህበተሩ የመረጣቸው ስራዎች መታተማቸውን የገለፁት ደራሲ አይለመለኮት መዋዕል አሁን ላይ ከየካቲት ወረቀት ስራዎች ድርጅት ጋር ውል ተፈራርመዋል፡፡
የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን ከሐምሌ 1እስከ 5 ድረስ የንባብ ቀኑ ይከበራል፡፡
ምትኬ ቶሌራ

በየአውራ መንገዱ ተሰምሮ የነበረው እና ከጊዜያት በኋላ የት እንደገባ ያለታወቀው ቢጫ ሳጥን ህግ ወቶለት ዳግም ስራ ሊጀምር ነው፡፡
ቢጫ ሳጥን ወይም የሎው ቦክስ በተለይ የትራፊክ ፍሰቱ ከፍተኛ በሆነባቸው የመስቀለኛ መንገዶች ላይ የመስቀለኛ መንገዶቹን የክልል ቅርፅ እንደ አስፈላጊነቱ የያዘና በየመንገዱ ላይ በግልፅ ሁኔታ ተቀብቶ የትራፊክ ፍሰቱን በቅደም ተከተል ለማስተናገድ የሚረዳ የቢጫ ቀለም ቅብ ማለት ነው፡፡
ከነዚህ ቦታዎች በተጨማሪ በሆስፒታሎች ውስጥ የድንገተኛ እርዳታ ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ለሚሄዱ ተሸከርካሪዎች ሌሎች ተሸከርካሪዎች ቆመው መተላለፊያውን እንዳያውኩ የቢጫ ሳጥንን በመጠቀም አከባቢውን ለተረጂዎች ግልፅ ማድረግ የሚያስችል የትራፊክ መብራት አጋዥ አሰራር ነው፡፡
በወቅቱ ስራ ላይ የነበረው የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በቢሮው የትራንስፖርት ዘርፍ የካቲት 26/2006ዓ.ም ይፋ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ቦታዎች ላይ ተግባራዊ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው መንገዶች ላይ የተቀቡት ቢጫ ሳጥኖች አገልግሎታቸው ሳይታወቅ ተሰውረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የመንገድ ደህንነትና አቅም ግንባታ ዋና የስራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ ሀገሬ ሀይሉ ቀድሞ የትራፊክ ደንብ ላይ ህግ ስላልወጣለት እንዲቋረጥ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለአገልግሎቱ መቋረጥ ቀድሞ በትራፊክ ህግ ውስጥ መግባት ባለመቻሉ ነው የሚሉት ሀላፊው ጠቀሜታው ታምኖበት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ ህጉ ለምን አስቀድሞ አልታሰበበትም ለሚለው ጥያቄ አቶ ሀገሬ ሀይሉ በምላሻቸው ለሙከራ የተጀመረ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ዳግም ይህንን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ አጥፊዎችን መቅጣት የሚያስችል ደንብ ቁጥር 395/2009 ማሻሻያ ተደርጎበት እንደወጣ ሀላፊው ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ከዚህ በፊት ለአንዱ የከተማችን አደባባይ ብቻ 80 ሺህ ብር ወቶበታል የተባለው የቢጫ ሳጥን አገልግሎት መች እንደሚጀመር ሀላፊው በውል እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡
ወደፊት ይተገበራል በተባለው የቢጫ ሳጥን መስቀለኛ መገጣጠሚያ ላይ ሲደርሱ አሽከርካሪዎች የቢጫ ሳጥን ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ወደሚሄዱበት አቅጣጫ ያለው መንገድ በበቂ መልኩ ለጉዞአቸው ክፍት መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይገባቸዋል፡፡በቢጫ ሳጥን ውስጥ ገብቶ መቆም የትራፊክ ፍሰቱን ከማስተጓጎሉም በላይ ህጉ ተግባራዊ ሲደርግ የደንብ መተላለፍ ቅጣትን ያስከትላል፡፡እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አከባቢ የቢጫ ሳጥን አሰራር እንግሊዝ፣ አየር ላንድ፣ካናዳ፣አውስትራሊያ፣ሰሜን አሜሪካ፣ሆንግ ኮንግ ብራዚል እና ራሺያ ረዘም ላለ ጊዜ በህግ ደረጃ ተቀብለው ከተገበሩት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው::

በአገሪቱ ከሚገኙ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ውስጥ 373ቱ ከደረጃ በታች መስራታቸው ተገለፀ፡፡
በኢትዮጲያ ውስጥ ከሚገኙ 1371 በጥቃቅንና አነስተኛ ዘፍር የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ውስጥ 373 በተቀመጠላቸው መመዘኛ መሰረት ከስልሳ እጅ በላይ ውጤት ባለማስመዝገባቸው ከደረጃ በታች መስራታቸው ተገልፃል፡፡
የፌደራል የከተሞች የስራ ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ባለሙያ አቶ አብይ ጌታሁን ለዛሚ እንደተናገሩት የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሲቀር በሁሉም ክልሎችና በአዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር በአፈፃጸማቸው ከስልሳ እጅ በታች ያስመዘገቡ ተቋማት ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
ተቋማቱን ለመለየት መመዘኛ መስፈርቱ ስራ አጦችን ከመመዝገብ መለየት አንስቶ ስልጠና እንዲያገኙ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ያላቸው ግኑኝነት ቁጣባ ሚቆጥቡና ብድርና የወሰዱት ብድራቸውን እንዲመልሱ ያደረጉት ክትትል እንደ መስፈርትነት ተይዟል ብለዋል፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ለሚደራጁ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ከመስፈርቶቹ 90 እጅ በላይ በማምጣት በአንደኝነት ደረጃ ላይ የተቀመጡት 88 ቱ ሲሆኑ ከአንድ እስከ አራት በወጣው ደረጃ የኦረሚያ ክልል 605 ተቋማቱን ሲያስመርጥ ጋምቤላ ክልል ሶስት ብቻ ማስመረጡ ተገልፃል፡፡
ለተቋማቱ ከስልሳ እጅ በታች አፈፃፀም ማስመዝገብ የሰው ሀብት ሃይል ችግር ቁሳቁስ በአግባቡ አለመደራጀት የአቅም ውሱንነት እንደ ምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
በምትኬ ቶሌራ

ኢትዮጲያዊው ጆኒ ግርማ በአለማቀፍ ደረጃ ከቀረቡ 338 ፕሮጀክቶች ውስጥ ፕሮጀክቱ ምርጥ አስር ውስጥ ገባ፡፡
ኢትዮጲያዊው ጆኒ ግርማ በአለም አቀፍ ደረጃ 338 ፕሮጀክቶች ለውድድር በቀረቡበት ዓለማቀፍ ውድድር ከተወዳደሩ ውስጥ የመጨረሻ ዙር የተመረጡ 10 እጩዎች ውስጥ መግባት ችሏል፡፡
ጆኒ ግርማ በደቡብ ምዕራብ አከባቢ የገጠር ሥራ አጥ ወጣቶችን ያሳተፈ ዘላቂ ኦርጋኒክ የማር ምርት ለማምረትና ኤክስፖርት ለማድረግ እየሰራ ይገኛልም ተብሏል፡፡
ቀን በቀን እየጨመረ ከሚገኘው የአለም ህዝብ ጋር ተያይዞ የግብርና ስራ የአለምን ስነ ምህዳር እና በውስጧ የሚገኙት ህይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ የህይወት ጉዞ የተመቻቸ እንዲሆን ያግዛል የተባለ ሲሆን ፡፡
ፕሮጀክቶቹም የሰው ልጅ ለምግብ ለዕለት ተዕለት ፍጆታቸው የሚጠቀሙበበት ከመጠን የዘለለ የግብርና ምርቶች ተጠቃሚነት የአለምን ገፅታ እንዴት እንደቀየሩ የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል፡፡
ሽልማቶቹ የሚደረጉት በአራት ቡድኖች ተከፋፍሎ ሲሆን ጥናቶቹ በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድሩት ተፅህኖ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አሊያም በስነ ምግብ ዙሪያ ያለው ተፅህኖ በባዮ ዳይቬርሲቲ እና በውሀ ዙሪያ የግብርና ውጤቶች ያላቸው ተፅህኖ ከግምት ውስጥ ይገባል ተብሏል፡፡
ጆኒ ግርማ በመጪው ህዳር ወር በጀርመን ሀገር ተገኝቶ ፕሮጀክቱን እንደሚያቀርብ እንዲያቀርብ መጋበዙ የታወቀ ሲሆን ፡፡
አሸናፊዎችን ለመለየት ቀጥታ የህዝብ ምርጫ የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጲያዊውን ጆኒ ግርማን ለመምረጥ Apis Agribusiness" የሚለው ሥር vote ማድረግ ይቻላል ተብሏል፡፡
እሰከ አርብ ሰኔ 30 ድረስ ድምፅ መስጠት ይቻላሉ፡፡ እባክዎን ያለችው አጭር (አራት ቀናት) ስለሆነ ፈጥነው ይምረጡ፡፡
መረጃውን ከሶሻል ሰርች ላይ ያገኘን ሲሆን ምትኬ ቶሌራ ዘግባዋለች ፡፡

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ በሚፈለገው መጠን ብድርን የሚደፍር ትውልድ መገንባት አልተቻለም ሲል በሌላ በኩል ከአጠቃላይ ተጠቃሚዎቹ 80 በመቶ ለመበደር አላማ የሚመጡ ሆነዋል፡፡
የዜጎች ቀጣይ እድገት ሊመዘገብበት የሚችለው ቅደመ ቁጠባን በማዳበር ለሚፈልጉት ዓላማ ማስፈፀሚያ ብድር መወሰድ ነው ሲሉ የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ስሩር ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በቅድሚያ ቆጥቦ መበደርን ይፈራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት የህብረት ስራ ማህበራት መካከል አዋጭ የገንዘብ እና ብድር ተቋም አንዱ ሲሆን ተቋሙ እስከ መጋቢት 30/ 2009 ዓ.ም ድረስ 4893 አባላትን ማሰባሰብ ችሎአል፡፡ከዚህም ውስጥ 457 አባላት ለቤት መግዣ እና 338 ያህሉ ደግሞ ተሸከርካሪ ለመግዛት የተበደሩ ናቸው፡፡ የቁጠባ ባህሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይፋ ቢደረግም የተናጠል ቁጠባው አሁንም እድገት ማሳየት አለመቻሉን የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የፋይናንስ ህብረት ስራ ማህበራት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሀኑ ዱፌራ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
የተበዳሪውን ማህበረሰብ ስጋት እና ፍራቻ ለመቀነስ አዳዲስ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው የሚሉት አቶ ዑስማን ስሩር በርካታ ገንዘብን ሰብስቦ በባንክ ማስቀመጥ ሳይሆን ለብድር አቅርቦት በማቅረብ ላይ ችግር በመኖሩ በሌላ በኩል የተበዳሪውን ፍላጎት ማርካት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመሰረታዊና ዩኒየን የገንዘብ ቁጠባና ህብረት ስራ ማህበራት እስከ አሁን 8.8 ቢሊዩን ብር ሲሰበሰብ 3.2 ቢሊዩን ብር ደግሞ ካፒታል ያስመዘገቡት ተቋማቱ አጠቃላይ ድምር 12 ቢሊዩን ብር በነዚህ የህብረት ስራ ተቋማት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የብድር አገልግሎት ለማግኘት ግለሰቦች በቅድሚያ የሚፈልጉትን የብድር መጠን 25 በመቶ ለተከታታይ 6 ወራት መቆጠብ እንዳለባቸው ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የተበዳሪዎችን መጠን በተመለከተ ከሚቆጥብት በላይ ለብድር የሚጠይቁት ገንዘብ ይልቃል የሚሉት ሀላፊው የብድር መጠኑ ከቆጣቢው ጋር ሲነፃፀር ተበዳሪው እንደሚልቅ ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ዘመናዊ የህብረት ስራ ከተጀመረ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን የህግ ድጋፍ አግኝቶ የተጀመረውም በንጉሱ ዘመን ነው፡፡ለመጀመሪያ ጊዜ የገበሬዎች የእርሻ ኅብረት ስራ ድንጋጌ ቁጥር 44/1953 ወጥቶ ስራ ላይ ውሏል፡፡ ለዚህ ድንጋጌ መውጣት ምክንያት የሆነው በከተማና በገጠር የነበረው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ሲሆን በከተማ የነበረውን ስራ አጥነትን ለመቅረፍ፣ከገጠር ወደ ከተማ የነበረውን ፍልሰት ለማስቀረት፣ በወቅቱ በመሬት ይዞታ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ለመፍታት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

ኢትዮጲያ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን ጥሩ መንገዶችን ተከትላለች ተብሏል፡፡
ኢትዮጲያ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን የተለያዩ የግብርና ጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ስነ ምህዳሩ እና ዘመናዊ ተክኖሎጂዎችን መጠቀሟ ሴክተሩን ለማዘመን ያግዛል ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጲያን ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ለማዘመን የኤክስቴንሽን ሰራተኞች መሳተፋቸው የጥናትና ምርምር ተቋማት በባለሙያ የታገዘው ግብርናዋ እንዲዘምን አግዞታል ተብሏል፡፡
የግብርና እና የተፈጥሮ አብት ሚኒስተር በ2016-2017 የምርት ዘመን ከአገሪቱ አጠቃላይ ዕድገት ኢትዮጲያ 13.8 ሚሊዮን ኤክታር መሬት በተለያዩ አዝእርቶች እንዲሸፈኑ በማድረግ ከ348 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በሚመጣው የመኧር ወቅት ታገኛለች ብለዋል፡፡
10.7 ሚሊዮን ኤክታር የሚሆነው መሬት እየለማ መሆኑንና ከዛ ውስጥ ደግሞ 3.5 ሚሊየን የሚሆነው ሄክታር መሬት ዘር ተዘርቶባቸዋል ከዚህም 14 ሚሊየን ኤክታር ምርት ይገኛል ተብሏል፡፡
ባሁኑ ወቅት ገበያ ተኮር የሆነ ግብርናን ለመምራት በአገሪቱ በተመረጡ 239 ወረዳዎች በምርጥ ዘር የታገዙ የአትክልትና ፍራፍሬ የእንስሳት ማርባት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአማራ እና ኦረሚያ ክልሎች የሚገኙ ገበሬዎች በኤክታር ከ66 እስከ 70 ኩንታል የሚደርስ ምርት እያገኙ ነው ተብለዋል፡፡
ምርቱን ከዚህ የላቀ እንዳይሆን በሴክተሩ ላይ ያለው የአቅም ውስንነት የገበያ ትስስሩ የላላ መሆን ተፅህኖ አሳድሮብናል ብሏል፡፡
ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጅማሮ ላይ ምርታማ የሚያደርጉ እና የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ ምርቶች ላይ ትኩረት አድረገን ለመስራት የያዝንውን አቅጣጫ እንቀጥልበታል ብለዋል፡፡
All African.com ጥቅሳ ምትኬ ቶሌራ ዘግባዋለች፡፡

በወርልድ ባንክ ግሩፕ በየአመቱ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው ዱዊንግ ቢዝነስ (Doing Business) የተሰኘ ሪፖርት ኢትዮጵያን ከ 190 አገራት 159ኛ ደረጃ ላይ አስቀመጠ፡፡
ይህ ሪፖርት በዋነኝነት በአንድ አገር የንግድና ኢንቨስትመንት ተግባርን ለማከናወን የተቀመጡ ደንቦችና በንግድና ኢንቨስትመንት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን የሚቃኝ ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ በአንድ አገር የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥራ ለማከናወንና ሂደቱን ለመጀመር ወሳኝ ናቸው ተብለው የተቀመጡ አስራ አንድ ያህል መስፈርቶች አሉ፡፡ በእነዚህ መስፈርቶች መሰረት አገሪቱ ያገኘችውን ደረጃ ምክንያት በማድረግ ከሪፖርቱ ኢትዮጵያ ምን ልትማርና ልታሻሽል ትችላለች ብለን ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አምርተን ነበር፡፡
በኮሚሽኑ የኢንቨስትመንት ክላይሜት ማሻሻያ እና የኤክስፖርት ተወዳዳሪነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ለማ ፈይሳ በሰጡን ምላሽ የኢትዮጵያን ደረጃ የማሻሻል ሥራ ብቻ ሳይሆን በአለም ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ትልቅ ደረጃ ማድረስ አላማቸው እንደሆነና በዚህ ሪፖርት ግን ከኢትዮጵያ በላይ ካሉት ዩጋንዳና ኬኒያ ትምህርት መውሰድ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
ሚካኤል ጌታሠጠኝ

በአዲስ አበባ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ዘንቦ የኮቢል ነዳጅ ማደያን ከጥቅም ውጪ አድርጓል፡፡
አዲስ አበባ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የቤት ቁጥር 052 የተመዘገበ በተለምዶ እራስ መኮንን ድልድይ አለፍ ብሎ የሚገኝ የነዳጅ ማደያ እሁድ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ጣሪያው ተደርምሶ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርጎታል፡፡
ታድያ በቦታው ተገኝተን የነዳጅ ማደያውን ስራ አሰኪያጅ አነጋግረናቸው የሰጡን ምላሽ አደጋው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የነዳጅ መቅጃዎችን ጨምሮ ምንም አለመቅረፍን ተናግረዋል፡፡
ስራአስኪያጁም አክለው በሰው ህይወት ላይ ምንም የገጠመ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ይሄ የተፈጥሮ ጉዳይ ስለሆነ ማንም ተጠያቂ የሚሆንበት ጉዳይ እንዳልሆነም አስረግጠው ተናግረዋል፡
በሀገሪቱ የነዳጅ ጣቢያዎችን በተመለከተ ከወጡ ጥናቶች መካከል 700 ያህል የነዳጅ ጣቢያዎችን አሎት ነገር ግን በቂ አይደለም፡፡ 700የነዳጅ ማደያ ለ100 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ 103 የነዳጅ ማደያ ብቻ እንዳለ ተገልጾዋል፡፡
ዘገባው የፍሬህይወት ታደሰ ነው

ግዮን ሆቴል እና ፍል ውሀ ንብረትነታቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆኖ በማእከላዊ ፓርክነት እንዲያገለግሉ ተወሰነ፡፡
በአዲሱ አስረኛው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መሰረት የኢዮቤልዩ ቤመንግስትና ዋናው የመከላከያ ሚኒስቴር ህንፃ ወደ ሙዝየምነት እንዲቀየሩ የሚደረግ ሲሆን ግዮን ሆቴል በአንፃሩ ወደ ህዝብ ፓርክነት የሚቀየር ይሆናል በሚል ተነግሮ እንደነበር ይታወሳል።
ለሽያጭ ከሚቀርቡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ግዮን ሆቴል ይገኝ የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚም ጨረታ ሲወጣበት ቆይቷል፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ታዲያ ግዮን ሆቴል ከዚህ መሰሉ የጨረታ ሂደት እንዲወጣ ትዕዛዙን ሰጠ፤ በዚህም መሰረት የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ግዮን ሆቴልን ከሽያጭ ውጪ አድርጐታል፡፡
ይህ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ታዲያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግዮንንም ሆነ ፍልውሀን እኔ ማስተዳደር እችላለሁ በሚል ሙሉ ለሙሉ ወደ እርሱ እንዲተላለፍ ሲጠይቅ የቆየ ሲሆን አሁን ላይ ይህ ጥያቄ እልባት ማግኘቱን ከከንቲባው ሰምተናል፤
የእነዚህ ቦታዎች ለከተማ መስረዳድሩ መሰጠቱ አካባቢውን የከተማ ማዕከል ለማድረግ የታሰበው ስራ ላይ የሚጨምረው ነገርም አለ ይላሉ ከንቲባው
ይህን ጉዳይ ሰምታችኋል ወይ ብለን ወደ ፕራይቬታይዜሽን እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ደውለን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ደብዳቤ እንደተፃፈላቸውና ግልባጩም ለከተማ መስረዳድሩ እንደተሰጠ አረጋግጠውልናል፤
በግዮን ሆቴል አካባቢ የሚካሄደውን የማልማትና አካባቢውን የመለወጥ ስራ ጋር ተያይዞ ሆቴሉ የህዝብ ፓርክ መሆኑ ተመጋጋቢ ያደርገዋልም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በወቅቱ ተናግሮ ነበር፤ ከተማ መስረዳድሩ ደግሞ ይህን እውን ለማድረግ ውሳኔ ይረዳኛል ብሏል፡፡
አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ሊዝናኑበት በሚችል መልኩ ፍልውሃን ጨምሮ የግዮንን አካባቢ በዘመናዊ የህዝብ ፓርክነት ለማልማት በአዲሱ ማስተር ፕላን ታቅዷል ከተማ መስተዳድሩም ይህን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፤ሆቴሉ ወደ ፓርክነት ሲቀየር በአደረጃጀቱም ሆነ ልህዝብ በሚኖረው የአገልግሎት ተደራሽነት የአሰራር ለውጥ የሚያደርግ ይሆናል።
አካባቢውን የከተማዋን ዋና የመዝናኛ ማዕከል ለማድረግ በተያዘው እቅድ መሰረት ከእስጢፋኖስና ከኢሲኤ ጀርባ አንድ ፓርክ በግንባታ ላይ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በሂልተን ሆቴልና በቤተመንግስት መካከል ያለውና አልፎ አልፎ ለህዝብ ክፍት የሚሆነው አፍሪካ ፓርክም የዚሁ ሰፊ የከተማዋ ማዕከላዊ ፓርክ አካል ነው።
በ1950 ዓ.ም. የተመሠረተው ግዮን ሆቴል በ123 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ነው፡፡

በቀድሞ የፕራይቬታይዜሽን እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ አማካኝነት ወደ ግል ለማዞር በተደጋጋሚ ለጨረታ የቀረበው ግዮን ሆቴል ወደ ህዝብ ፓርክነት ሊቀየር ነው።
በአዲሱ አስረኛው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መሰረት የኢዮቤልዩ ቤመንግስትና ዋናው የመከላከያ ሚኒስቴር ህንፃ ወደ ሙዝየምነት እንዲቀየሩ የሚደረግ ሲሆን ግዮን ሆቴል በአንፃሩ ወደ ህዝብ ፓርክነት የሚቀየር ይሆናል። እንደ አዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አስፋው ገለፃ ከሆነ ሆቴሉን ወደ ፓርክነት የመቀየሩ ስራ በአካባቢው ከሚካሄዱት ለውጦች ጋር ተመጋጋቢ ሆኖ የሚሄድ ነው።
አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ሊዝናኑበት በሚችል መልኩ ፍልውሃን ጨምሮ የግዮንን አካባቢ በዘመናዊ የህዝብ ፓርክነት ለማልማት በአዲሱ ማስተር ፕላን የታቀደ መሆኑን የገለፁት አቶ ማቴዎስ፤ ይህንን አካባቢ ዋነኛ የከተማዋ የመዝናኛ እምብርት ለማድረግ የታሰበ መሆኑን አመልክተዋል።
ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ስለጉዳዩ ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ ሆቴሉን ወደ ግል ይዞታነት ለማዘዋወር በግልፅ ጨረታ እንደዚሁም በድርድር በተደጋጋሚ ተሞክሮ ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ሂደቱ እንዲቆም የተደረገ መሆኑ ተገልፆልናል። ሆቴሉን ወደ ፓርክነት ለመቀየር በዙሪያው ከሚካሄዱት አካባቢያዊ ልማቶች ጋር በተጣጣመ ተጨማሪ ልማቶች የሚካሄዱበት መሆኑ ታውቋል። በአዲሱ ማስተር ፕላን መሰረት
አካባቢውን የከተማዋን ዋና የመዝናኛ ማዕከል ለማድረግ በተያዘው እቅድ መሰረት ከእስጢፋኖስና ከኢሲኤ ጀርባ አንድ ፓርክ በግንባታ ላይ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በሂልተን ሆቴልና በቤተመንግስት መካከል ያለውና አልፎ አልፎ ለህዝብ ክፍት የሚሆነው አፍሪካ ፓርክም የዚሁ ሰፊ የከተማዋ ማዕከላዊ ፓርክ አካል ነው።

ይህ የህዝብ መዝናኛ እስከ ኢትዮጵያ ሆቴልና ብሄራዊ ቴአትር ድረስ የሚደርስ ይሆናል። ከለገሀር እስከ ብሄራዊ ቴአትር ድረስ ያለው መንገድ ሙሉ በሙሉ ለተሸከርካሪዎች ዝግ ሆኖ ለእግረኞች ብቻ እንዲያገለግል የሚደረግ መሆኑን አቶ ማቴዎስ አመልክተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የልማት ድርጅቶቹን የ2009 ዓ.ም የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የስኳር ፕሮጀክቶቹ በመርሃ ግብሩ መሰረት ካልተጠናቀቁ የሚመለከታቸው አካላት ከተጠያቂነት አይድኑም ማለቱን ተከትሎ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ በከፊል የስኳር ምርት ማምረት መጀመሩ ተነግሯል፡፡ ፋብሪካው ምርቱን መጀመሩ ለምክር ቤቱ ማሳሰቢያ ምሳሽ ለመስጠት የታሰበ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ የስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጋሻው አይችሉም እውነት ነው ሲሉ ምላሽ ሰተዋል፡፤
የአዋጭነት ጥናት አንስቶ ዝርዝር ዲዛይንን ጨምሮ የግንባታ ምርትና አቅርቦት፣ የሲቪል ስራዎች እንዲሁም የኢሬክሽን አና የዝርጋታ ስራዎች በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ተሰርተዋል የሚሉት የብረታብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ ናቸው እንደ ጀነራሉ ገለፃ ከሆነ የሙከራ ስራውን የጀመረው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ በቀን 12 ሺ ቶን አገዳ መፍጨት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ባሻገር የጣና በለስ ቁጥር አንድና ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ለሜቴክ የተሰጡ መሆናቸውም የሚታወስ ነው፡፡የጣና በለስ ቁጥር ሁለት ፕሮጀክት አፈጻጻም 25 በመቶ ብቻ በመሆኑ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የተደረገው ውል እንዲቋረጥ እርምጃ መውሰድ ጀምረናል ሲሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት የጣና በለስ ቁጥር አንድ ፕሮጀክት ግንባታን አጠናቆ ወደ ሙከራ ስራ መግባት የነበረበት ቢሆንም እስካሁን ያለውን አፈፃፀም በመቶኛ የሚያስቀምጥበት ጊዜ ላይ አለመድረሱን በተናገሩበት በዚህ ወቅት ነው የኩራዝ ፋብሪካ ወደ ምርት የገባው
የፋብሪካው ግንባታ በሚያዝያ ወር ተጠናቆ የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት የስኳር ምርት ስራ መጀመር እንደነበረበት ነው ሚኒስቴሩ ባሳለፍነው ሳምንት ያመለከቱት።
ይህ በእንዲህ እያለ የስኳር ኮርፖሮሽን የኮርፖሬት ስራ አስፈፃሚው አቶ ጋሻው አይችሉም የኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ስራ መጀመር ስኬት ነው ሲሉ ተናገረዋል፡፡
ከ3 ዓመታት በፊት ስራ ይጀምራል የተባለው ፕሮጀክቱ ዛረም ድረስ ወደ መደበኛ የማምረት ስራ መግባት አልቻለም፡፡ ፋብሪካው በ 3 ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ምርት ማምርት እንደሚጀምር ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ ተናግረዋል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ በ235 ሚሊዩን ዶላር እንደተገነባ ከሜቴክ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ የጣና በለስ ቁጥር አንድና ሁለት፣ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ሙሉ በሙሉ ፕሮጀክቶችን በተከለሰው መርሃ ግብር መሰረት በ2010 ዓ.ም ለማጠናቀቅ መታቀዱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መነገሩ ሲታወስ ለፋብሪካዎቹ የተተከሉት አገዳዎች እየደረሱ በመሆናቸው የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በፍጥነት እንዲካሔድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ክትትል ማድረግ አለበት በአፅንኦት የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡

ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው፡፡