አገር አቀፍ ዜናዎች

ግንቦት 16/2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ እና የድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት ባጋጠማቸው የተወሰኑ (ሚዛን፣ ቴፒ፣ አሶሳ፣ ጅማ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ) ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች ድምፅ ያልሰጡ ተማሪዎች በነገው ዕለት ሙሉ ቀን ድምፅ እንዲሰጡ መወሰኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ግንቦት 16/2007 ዓ.ም

በቀላሉ የሚከናወን የምርጫ ሂደት በመሆኑ ከማጭበርበርም ሆነ የማታለል ስራ የአሰራር ስርዓቱ ነፃ መሆኑን የገለፁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ወርክ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አዳምነሽ አጥናፉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የምታራምደው የምርጫ ሂደት አብዛኛዎቹ ያደጉ አገራት የሚከተሉት ሲሆን ይህም በቀላሉ አሸናፊው የሚለይበት እና የአሰራር ውስብስብነት የሌለው ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ግንቦት 16/2007 ዓ.ም

የዘንድሮው የምርጫ ሂደት በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ መገኘቱ ከበፊቶቹ የምርጫ ሂደቶች ከፍተኛ የሆነ ትምህርት በመወሰዱ ነው ያሉት የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዝደንት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው ሲሆኑ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም እንደገለፁት ህዝቡ በተለያየ ጊዜ የሚፈልገውን ፓርቲ መምረጥ መቻሉ እና መብቱን በአግባቡ መጠቀሙ አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡ የምርጫ ስርዓት ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፤ ይህም ለእድገታችን ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ አለውም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ምርጫ ማለት የሀሳብ ልዩነቶችን ለውድድር የምናቀርብበት እንጂ አላስፈላጊ የሆነ ችግር ውስጥ የምንገባበት ሊሆን አይገባም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ግንቦት 16/2007 ዓ.ም

በዞኑ ሁለት ፓርቲዎች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እና መኢዴፓ ዕጩዎቻቸውን አቅርበዋል ያሉት የዞኑ የምርጫ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ካሚል አህመድ ናቸው፡፡ ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ነው፤ ለመራጭነት የተመዘገበው ህብረተሰብ ከጠዋት ጀምሮ በነቂስ ወጥቶ እየመረጠ ይገኛልም ብለዋል፡፡ በዞኑም በምርጫው ሂደት የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ግንቦት 16/2007 ዓ.ም

በሀገሪቱ የሚገኙ አንድ መቶ አርባ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ህገ-መንግስቱ የሰጣቸውን የመምረጥና መመረጥ መብት ተጠቅመው ድምፅ እየሰጡ እንደሚገኙ ገልፀው፤ ሆኖም ግን በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት መከሰቱን አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ችግሩን ለመፍታት ወደ ስፍራዎቹ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እየተላኩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሁለት ሰዓታት ውስጥም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል ሲሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ተናግረዋል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ግንቦት 14/2007 ዓ.ም

የኢቦላን ወረርሽኝ ለማስቆም ታህሳስ ወር 2007 ዓ.ም ከሄዱት 184 አባላት መካከል 13ቱ የጤና ባለሞያዎች በሴራሊዮን እና በላይቤሪያ እንደሚቆዩ ተጠቁሟል፡፡

ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱት የጤና ባለሞያዎችም በአዳማ ከተማ መለስ ዜናዊ አካዳሚ ውስጥ  በተዘጋጀ ማረፊያ ቦታ ለ21 ቀናት ይቆያሉ፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

ግንቦት 14/2007 ዓ.ም

በአየር ድብደባው ሌሎች ሁለት ኢትዮጵያዊያንም ላይ ከባድና ቀላል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን መንግስት አስታውቋል። ከፅህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በሰሜን የመን ሀራድ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የስደተኞች ካምፕ ላይ በደረሰው የአየር ድብደባ የኢትዮጵያዊያኑ ህይወት ማለፉ መንግስት ከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን ፈጥሮበታል። የኢትዮጵያ መንግስት ሰንአ በሚገኘው የሚሲዮኑ ፅህፈት ቤት አማካኝነት ጉዳዩን በመከታተል ላይ ሲሆን አደጋውን በተመለከተ አዲስ አበባ የሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ የተሟላና አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲያቀርብ በመንግስት መጠየቁን በመግለጫ አስታውቋል። በቅርቡ በየመንና በአካባቢው በተፈጠረው ግጭትና ቀውስ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን መንግስት ወደ ሀገራቸው የመለሰ መሆኑን መግለጫው አስታውሷል። ቀሪ ዜጎቻችንንም ከየመን ለማስወጣት ከሳኡዲ መንግስት ጋር በመተባበር የተጠናከረ ጥረት በማድረግ ላይ ባለበት ወቅት ይሄ አደጋ መከሰቱ መንግስትን እጅግ ያሳዘነው መሆኑን አስታውቋል። መንግስት በደረሰው አሰቃቂና አሳዛኝ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ መፅናናትን ተመኝቷል።

ግንቦት 14/2007 ዓ.ም

-    የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሐሙስ ግንባት 13 ቀን 2007 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡

-    እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ይካሄዳል፡፡ የምርጫ ሂደቱ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር በጭራሽ አይቋረጥም፡፡

-    በየምርጫ ጣቢያው የተመደቡ የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ የሕዝብ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎችና የፀጥታ ሃይሎች ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡

-    እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ ወኪል ማስቀመጥ ይችላል፡፡ ወኪሎቹ  በድምፅ መስጫው ቀን ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት እንዲገኙ ጥሪ ይደረጋል፡፡

-    ይሁን እንጂ በራሳቸው ምክንያት መገኘት ባይችሉ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን እንደማያስተጓጉለው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተቀማጭ ወኪሎች በእያንዳንዱ የምርጫ ሂደት በሚገኙ ቃለ-ጉባዔዎች ላይ እንዲፈርሙ ቢጠበቅም ፍቃኛ ሳይሆኑ በሚቀሩበት ጊዜ የምርጫ ሂደቱ አይስተጓጎልም፡፡

-    መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲመጡ ለመምረጥ ከሚያስፈልጋቸው ሰነዶች፤ ማለትም የመራጮች ካርድና መታወቂያ በስተቀር ምንም አይነት ነገር ይዞ መምጣት የለባቸውም፡፡ በተለይም የጦር መሳሪያና ተዛማጅ ነገሮች እንዲሁም ሞባይል ስልኮችን ይዞ መግባት አይፈቀድም፡፡

-    መራጮች በሚስጥር ድምፅ መስጫው ሲገቡ እስክሪፕቶና የጣት አሻራ ለማድረግ የሚያገልግል መርገጫ ያገኛሉ፡፡ ስለሆነም እስክሪፕቶ ይዞ መግባት አስፈላጊ አይደለም፡፡

-    ማንኛውም መራጭ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲመጣ፣ በምርጫው እለት ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለ በመሆኑ የተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ቲሸርት፣ ኮፍያ፣ ባጅና የመሳሰሉትን እና ከፖለቲካ ፓርቲ አርማ ወይም ምልክት ጋር ግንኙነት ያለው ቁሳቁስ/ነገር መያዝ ወይም በሰውነት አካላት እንቅስቃሴ ለማሳየት መሞከር የለበትም፡፡

-    መራጮች ድምፅ ከሰጡ በኋላ በምርጫ ጣቢያ አካባቢ ተሰብስቦ መቆም አይቻልም፡፡

-    ከምርጫ ጣቢያው ጀምሮ በየደረጃው የምርጫ ውጤት የመግለፅ ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለሆነ ማንኛውም ሌላ ግለሰብ/ድርጅት በምንም መልኩ የምርጫ ትንበያ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡ ትንበያ ፈፅሞ የተገኘ ግለሰብ/ድርጅት በሕግ ይቀጣል፡፡

-    በምርጫ ሂደቱ ቅሬታ ያለው አካል በተቀመጠው የቅሬታ አቀራረብ ስርዓት ብቻ መጠቀም እንደሚገባ እና ከዚህ ውጭ የቦርዱን ውሳኔ በፀጋ መቀበልና ማክበር ይገባል፡፡

-    ድምፅ ከተቆጠረ በኋላ ውጤቱ ግንቦት 17 ቀን ጠዋት በየምርጫ ጣቢያው ይለጠፋል፡፡

(ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተወሰደ)

ግንቦት 14/2007 ዓ.ም

ዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ቀን በብዝሀ ህይወት ላይ ያለውን እውቀትና ግንዛቤ ለማሳደግና ብዝሀ ሕይወትን እስካሁን ጠብቀው ላቆዩልን ማህበረሰቦች እውቅና ለመስጠት በሚል አላማ በብዝሀ ህይወት ዓለም አቀፍ ስምምነት አባል ሀገራት ዘንድ በየዓመቱ ግንቦት 14 (May 22) ተከብሮ ይውላል፡፡

ኢትዮጵያም ዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ስምምነትን ካፀደቁ ሀገራት አንዷ እንደመሆኗ በብዝሀ ህይወት ሀብታችን ላይ ያለውን ግንዛቤና እውቀት ለማሳደግ በዓሉን በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ስታከብር ቆይታለች፡፡ በዚህም መሰረት በዚህ ዓመት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ “Biodiversity for Sustainable Development” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን በአገራችን ደግሞ “ብዝሀ ሕይወት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል ለ14ኛ ጊዜ ይከበራል ሲል የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገልጧል፡፡

ግንቦት 13/2007 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በዛሬው እለት ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምርጫ ስርዓቱ ለተቃዋሚዎችም ሆነ ለኢህአዴግ ለዚህ በር የሚከፍት አይደለም ብለዋል፡፡ ድምፅ መስጫ ወረቀት ሊዘጋጅ የሚችልበት ሁኔታ አለመኖሩንም ለምክር ቤቱ ገልፀዋል፡፡ እያንዳንዷ በምርጫ ጣቢያ የምትሰጥ የድምፅ መስጫ ወረቀት የእነርሱም ታዛቢዎች ጭምር የፈረሙባት የድምፅ መስጫ ወረቀት ናት ብለዋል፡፡

በምን መልኩ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ወይም ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጨማሪ ያልተፈረመባቸው የድምፅ መስጫዎች ሊያመጡ እንደሚችሉ ግልፅ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንደነዚህ አይነት ነገሮች የሚያመለክቱት አንድም ከራስ ግል ቆዳ ጭምር ጋር የተያያዘ እኔ ከተሸነፍኩ የተሸነፍኩት ህዝቡ ስለወሰነ ሳይሆን ኢህአዴግ ስላጭበረበረ ነው ብሎ ሽንፈትን በፀጋ ላለመቀበል የሚደረግ መፍጨርጨር የሚመስል፤ በሌላ በኩል ለምርጫ ህጋችንና ስርዓታችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሸነፉባቸው ወቅቶችም ቢሆን የስራ ምርጥ የሚባል የምርጫ ማስፈፀሚያ ስርዓቶች ያሉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ይህን እያወቁና እየተረዱ ነው የሚናገሩት ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በውስን ቦታዎችና በአንዳንድ አካባቢዎች በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የሚደረጉ ቅስቀሳዎች ወደ አላስፈላጊ ሂደት ውስጥ ደጋፊዎቻቸው እንዲገቡ የማድረግ ነገር እንደሚታይ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ ለሰላም ዘብ በመቆም እንዲህ አይነት እኩይ ቅስቀሳዎች ህዝቡ የሰጠው ድምፅ ተቆጥሮ እስኪነገር ድረስ የሚመለከታቸው አካላት የሚወስኑትን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ግንቦት 12/2007 ዓ.ም

ትናንት ምሽት በተካሄደው የሽልማትና የእውቅና አሰጣጥ ዝግጅት ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ፅ/ቤት ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ እንደገለፁት ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረውና አሁን ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው የሽልማት ስነ-ስርዓቱ በ5 ዘርፎች፤ ማለትም በላቀ አገልግሎት፣ በማስተማርና በእውቀት ሽግግር እንዲሁም በምርምር ስራዎች ሀገርና ህዝብ የጠቀሙና የላቁ ወጣት ሙህራንና በስራዎቻቸው ልዩነት የፈጠሩ ተብለው 35 ሰዎች ለሽልማት በቅተዋል፡፡

በእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢና የፌዴሬሽን ም/ቤት  አፈ-ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለብርሃን በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል፡፡

ይህ የሽልማትና የእውቅና ስነ-ስርዓት ባለፈው ዓመት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ከዚህ በኋላ በየዓመቱ መደበኛ የሽልማት ፕሮግራም ሆኖ እንደሚቀጥል አቶ አሰማኸኝ ገልፀዋል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ግንቦት 12/2007 ዓ.ም

በከተማችን የሚገኙ የጤና ጣቢያዎችን እንዲሁም ሆስፒታሎችን ለህብረተሰቡ በቀላሉ ለማዳረስና የአገልግሎት አድማሳቸውን ለማስፋት እየተሰራ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም ከ86 በላይ ሲሆኑ በቅርቡም ቁጥራቸው ወደ 101 ከፍ እንደሚል ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም አዳዲስ ሆስፒታሎችን ከመገንባት ጎን ለጎን እድሳት የማድረግ ስራም እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በቅርቡም በ3 ክ/ከተሞች፤ ማለትም በቦሌ፣ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ኮልፌ ቀራኒዮ የሆስፒታል ግንባታ ሊካሄድ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊ ልዩ አማካሪ አቶ አንተነህ ምትኩ ተናግረዋል፡፡ ግንባታውም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሁሉንም አይነት ህክምና ህብረተሰቡ በአንድ ቦታ እንዲያገኝ የሚያስችል እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

ከከተማችን ስፋት ጋር በተያያዘ ሰው በብዛት ያለበትን ቦታ በመምረጥ ግንባዎች የሚካሄዱ ሲሆን የ3ቱ ሆስፒታሎች ግንባታም በ2008 ዓ.ም የሚጀመር ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ አገልግሎት ለሚሰጡ የጤና ባለሞያዎችም ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አቶ አንተነህ ምትኩ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

ግንቦት 10/2007 ዓ.ም

በዘንድሮው የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከፈተና ዝግጅት ጀምሮ እስከ ውጤት ማሳወቅ ድረስ ያለውን ሂደት በተመለከተ አዳዲስ እና ዘመናዊ አሰራር መዘርጋቱ ተገልጧል፡፡

በተለይም የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ይሄድላቸዋል ያሉት የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገ/እግዚአብሔር፤ ተፈታኞች በፎርማቸው ላይ የሞባይል ቁጥራቸውን ይሞላሉ በዚህም መሰረት ተፈታኞች ፈተናው ታርሞ እንደተጠናቀቀ የፈተና ውጤታቸው በፅሁፍ መልዕክት ይላክላቸዋል ብለዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ግንቦት 10/2007 ዓ.ም

በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር ከሚተዳደሩት ከ16 በላይ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ በሆነው በኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ በፖሊ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ትብብር ለስራ የበቃው የትራንስፎርመር ማምረቻ ፍብሪካ ግንባታ በ2006 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የ350,000,000 ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡

ይህ ፍብሪካ በዓመት አስር ሺህ ያህል ትራንስፎርመር እንደሚያመርት የገለፁት የኢንዱስትሪው ዋና ስራ አስኪያጅ ሻምበል አሰፋ ዩሃንስ ናቸው፡፡

በዚህ ፍብሪካ ምረቃ ዝግጅት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፤ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ላይ ፋን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የብረታብረት የኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሃላፊዎችና ሰራተኞች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡

ፋብሪካው ለተለያዩ ጥቅሞች የሚውሉ ከ10KVA እስከ 31,500KVA ሬቲንግ ያላቸው ትራንስፎርመሮችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል ተብሏል፡፡ (መሰረት ሙሉ)

ግንቦት 10/2007 ዓ.ም

የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዳማ ከተማ የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ በዛሬው እለት ቦኮ ናዳቤ በሚባል ስፍራ የመሰረት ድንጋይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠ/ሚኒስትሩ ተቀምጧል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የክልሉ ባለሃብቶች ተሳትፎ እንዲያደርጉ የጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ ለዚህም መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፉን ያደርጋል ብለዋል፡፡ በሌላ ዜናም የአዲስ አበባ ሰበታ ጅቡቲ የሜኤሶ ፕሮጀክት የሀዲድ ማንጠፍ ስራ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ይህንንም አስመልክቶ የሙከራ ጎዞ አድርጓ፡፡ በስነ-ስርዓቱም ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠ/ሚኒስትርና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡ ፕሮጀክቱም 4ቱንም አቅጣጫዎች የሚያገናኝ በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ተብሏል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ግንቦት 05/2007 ዓ.ም

ከውጭ ሀገራት ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የህብረተሰቡን የጤና ችግር በአስተማማኝ ሁኔታ ይፈታሉ ተብሎላቸው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት የህክምና መሳሪያዎች ላለፉት ወራት በባለሞያ እጦት ምክንያት ያለ ስራ ተቀምጠው ጥያቄ ሲነሳባቸው ቆይተው ነበር፡፡

ታዲያ አሁን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተሰማው መሰረት ከነርሶች ጀምሮ ያሉ ባለሞያዎች እየሰለጠኑ ከመሳሪያዎቹ ጋር እንዲግባቡ የተደረገና ወደ ስራም የተሰማሩ ሲሆን ስራውንም በተገቢውም ሁኔታ እየከወነ ነው ተብሏል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ አሚኖ ለዛሚ 90.7 እንደተናገሩት በብልሽት ላይ የነበሩ መሳሪያዎች የጥገና ስራ እንዲያገኙ ተደርጓል፤ ጥቃቅን የተባሉ ችግሮችም ተፈተዋል ያሉ ሲሆን ከመሳሪያዎቹ እክሎች ብዛት መነሾነት ግን የሁሉም መሳሪያዎች ችግር ተፈቷል ማለት አይደለም፤ ይህ ደግሞ አርኪ ነው ሊያስብል አይችልም ብለዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ሚያዚያ 30/2007 ዓ.ም

ለ80ኛ ዓመታት ያህል የሰብዓዊ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የ80ኛ ዓመት ክብረ-በዓሉን እያከበረ ይገኛል፡፡ ይህ ማህበር ኢትዮጵያ ዳግም በኢጣሊያን ከተወረረችበት ጊዜ ጀምሮ ለዘመናት ለተከሰቱ የድንገተኛ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ፈጥኖ በመድረስ የሰብዓዊ አገልግሎቱን ሲሰጥ መቆየቱን የገለፁት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ናቸው፡፡

በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የ80ኛ ዓመት ክብረ-በዓል ላይ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር መህመድ ረጃ እና ሌሎች የቀይ መስቀል ማህበር የቦርድ አባላት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት ተከብሯል፡፡ ዶ/ር አህመደም ከዛሬ ሚያዝያ 30 ጀምሮ ለአንድ ሰዓት ያህል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 80ኛ ዓመት ይከበራል ለዚህም ሁሉም ተባባሪ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ግብዣቸውን አቅርበዋል፡፡ በቅርቡም የሀገር አቀፍ የቀይ መስቀል ወጣቶች ም/ቤት ሊመሰረት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሚያዚያ 30/2007 ዓ.ም

የከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን በዘንድሮው በጀት ዓመት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀትን መድቦ እየሰራቸው የሚገኙ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ መንገዶች መልካም ፍፃሜን እያሳዩ ነው ሲል ነው የተናገረው፡፡  በየካ አባዶ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ቦሌ ሰሚት እና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉት 5 ያህል የመንገድ ፕሮጀክቶች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘላቸው ሲሆን ከእቅድ በላይ በሆነ ትግበራ ሂደትም እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጧል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ ሲሳይ ወርቅነህ በዘንድሮው ዓመት 100 ኪ.ሜ ያህል የሚሸፍን የመንገድ ስራ እቅዶችን ይዘናል ያሉ ሲሆን 17% የነበረውን የመንገድ ሽፋን ስራ እቅድም ወደ 19% ለማሳደግ አቅደን አሁን 18% ያህሉ ላይ ደርሰናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡