አገር አቀፍ ዜናዎች

ሰኔ 10/2007 ዓ.ም

በዛሬው እለት በልደታ የህፃናት ፀባይ ማረሚያ ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 60 ሚሊዮን ብር በተበጀተ በጀት የህፃናት ታራሚዎችን ማስተናገድ የሚችል ህንፃ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡

በሀገራችን በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ የሚገኙ የህፃናት ፀባይ ማረሚያ ማዕከላት ምቹ ባለመሆናቸው ለህፃናቱና ለአገልግሎቱ አመቺ እንዲሆን በዘመናዊ መልክ ለመገንባት ታቅዶ መሆኑን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም የገለፁት የአዲስ አበባ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ ሀብታሙ መብራቴ ናቸው፡፡

ከ150 በላይ ታራሚ ህፃናት በማቆያው በመልካም ስነ-ምግባር ታንፀውና በተለያዩ እውቀት ተገንብተው የሚወጡበት ማዕከል እንደሚገነባም ተናግረዋል፡፡ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ዝግጅት ላይም የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

ሰኔ 10/2007 ዓ.ም

ከ2005 ዓ.ም በጀት ዓመት በፊት ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች ከአየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ መጋዘን እንዲሁም ወደ ክልል ያሰራጩ የነበሩት በሁለት የማቀዝቀዣ ሰንሰለት ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ነበር ያለው የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አሁን ላይ ቁጥራቸውን ማሳደግ መቻሉን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በፊት በሁለት ተሽከርካሪዎችና በተለያዩ ማቀዝቀዣ ሳጥኖች አማካኝነት መድኃኒቶች ከአዲስ አበባ መጋዘን ወደ ክልል ይሰራጩ ነበር ያሉት በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የግዥ ትንበያ እና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሬድ ገዙ ናቸው፡፡

እያንዳንዱ ክልል መድኃኒቶችን ከአዲስ አበባ መጋዘን እና ከሌሎች ስፍራውን ማጓጓዝ የሚችልበት የቀዝቃዛ ሰንሰለት ተሽከርካሪዎች አሏቸው፡፡

ይህ መፈጠሩ መድኃኒቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለተጠቃሚው በፍጥነት እንዲደርስ ትልቅ እገዛን ያበረከተ ነው ተብሏል፡፡ (ሰላም ተሾመ)

ሰኔ 09/2007 ዓ.ም

የ35 ዓመቱ አስመላሽ ዘፈሩ ከአልሙኒየም፣ ከጣውላና ከብረት የሰራውን አውሮፕላን የሙከራ በረራ ሰኔ 4 ቀን አድርጎ የነበረ ሲሆን፤ የአየር መቅዘፊያ ብሎኑ በመጥበቁ የተነሳ በረራው እክል ገጥሞታል፡፡ አስመላሽ እንደተናገረው ከሆነ ምንም አይነት ችግር በአውሮፕላኑ ላይ የለም ነገር ግን ትንሽ እክል አጋጥሟል ብሏል፡፡

የትኛውም የፈጠራ ስራ የዚህ አይነቱ ክፍተት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ በእኔ በኩል ስኬታማ ነበር ሲል ገልጧል፡፡

አየር መቅዘፊያውን በተለያዩ ቁሳቁሶች በማስተካከል ዳግመኛ በረራውን እንደሚያከናውን የገፀ ሲሆን የገንዘብ እጥረት በፈጠራ ስራው ላይ መስተጓጎል እንደፈጠረበት ለጣቢያችን አስታውቋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች የአውሮፕላን በረራው ከሸፈ በማለት የገለፁበት መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ገልፆ ሙከራው 95 በመቶ ስኬታማ ነው 5 በመቶውን አስተካክዬ በቅርቡ ሙከራዬን አደርጋለሁ በማለት ተናግሯል፡፡ (ሰላም ተሾመ)

ሰኔ 05/2007 ዓ.ም

ተከሳሹ መሀመድ ከማል ጥር 18 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ በልደታ ክ/ከተማ በወረዳ 3 ቀበሌ 47 ክልል ልዩ ቦታው አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ካለው መኖሪያ ቤት ውስጥ በእርሱ ጥገኝነት ወይም ቁጥጥር ስር የምትገኘውን የባለቤቱን የእህት ልጅ የሆነችውን እና የ12 ዓመት እድሜ ያላትን የግል ተበዳይ አስገድዶ የደፈረ በመሆኑና በድጋሚ የካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም  ከጠዋቱ 2፡30 ሲሆን በተጠቀሰው ቦታ የግል ተበዳይ ላይ የወሲብ ጥቃት ሊፈፅም ሲል እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 627(1) እና 4(ሀ) ላይ የተመከተውን በመተላለፍ በፈፀመው በህፃናት ልጆች ላይ የሚፈፀም የወሲብ ጥቃት ወንጀል ተከሷል፡፡

ክሱን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎትም የአቃቤ ህግ የሰነድና የሰው ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው በማለት በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

ሰኔ 04/2007 ዓ.ም

ሙሀሙድ ጋአሰ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ እንደሉት በዩኔስኮ የጣና ሀይቅ መካተቱ ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ እና በስፍራውም ተጨማሪ ጥናት ለማካሄድ ያግዛል ብለዋል፡፡ በሰሜን ምዕራባዊ የአማራ ክልል የሚገኘው ጣና ሀይቅ 84 ኪ.ሜ ርዝመት እና 66 ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ 15 ሜትር ጥልቀት ያለው ሐይቅ የበርካታ ደሴቶች መገኛም ነው፡፡ በ2156 ኪ.ሜ2 ያረፈው ሀይቁ በፓርቹጋል የሚሽነሪ ሰራተኛ ማኑኤል ዲ አልሳዲያ በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንኳን 21 ደሴቶች እንደነበሩት ገልጧል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ በስም የተዘረዘሩ 37 ደሴቶች የሚገኙ ሲሆን 19ኙ ገዳማት እና አብያተ-ክርስቲያናት ናቸው፡፡ (ስምኦን ደረጄ)

ሰኔ 03/2007 ዓ.ም

ከ70 አመት በላይ እድሜ ያላቸው የጨርቃጨርቅ፣ የቀለም እና የቆዳ ማምረቻ ፋብሪካዎች በሀገራችን  የሚገኙ ሲሆን በፌዴራል የአካባቢ ብክለት አዋጅ ቁጥር 300/2002 በአንቀጽ 20  እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት  በወጣው ደንብ መሰረት ፋብሪካዎቹ ተረፈ ምርታቸውን የሚያስወግዱበት ስርአት ኋላ ቀር በመሆኑ ለማስተካከያ ለ5 አመት  የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን የእፎይታ ጊዜያቸውን ከጨረሱ በኋላ የተረፈ ምርት አወጋገዳቸውን ያላስተካከሉ አምራቾች ወደ ህግ መወሰዳቸውን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም የገለጹት የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የህግ ጉዳዮች ኦፊሰር አቶ አሳምነው ተክለዮሀንስ ናቸው፡፡ ወደ ህግ ከተወሰዱት መካከል የቆዳ ምርት ላይ ያሉ 7 ፋብሪካዎች እና 5 የጨርቃጨርቅ ነባር አምራቾች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻን ከህግ ውጪ ወደ ወንዝ በመልቀቃቸውና የአካባቢው ነዋሪዎችን ጤና በመበከሉ ምክንያት ተጠያቂ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ በብርሃን መንጸባረቅ ምክንያት ተጽኖ ይፈጥራሉ የተባሉ ህንጻዎች እንዲስተካከሉ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)

ሰኔ 03/2007 ዓ.ም

በ10ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ የወጣላቸው ቀድሞ የመንግሥት ሰራተኞች የነበሩ አሁን ወደ ግል ስራ የቀየሩ ከቴሌ፣ ከመብራት ሃይልና ከሌሎችም መስሪያ ቤቶች የተቀነሱና በጡረታ የተገለሉ አካላት የቅድመ ክፍያ ውል ለመፈፀም ባቀኑባቸው በሁሉም ክ/ከተሞች ውሉን መፈፀም እንደማይችሉ ከሚያዝያ 28/2007 ዓ.ም ጀምሮ እንደተገለፀላቸው ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ገልፀው የነበረ ሲሆን በወቅቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ለዛሚ 90.7 የተሰጠው ምላሽ በጉዳዩ ዙሪያ መፍትሄ ለመስጠት ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ኤጀንሲው ከትናንትናው እለት ጀምሮ ባለእድለኞቹ ውሉን እንዲፈፅሙ መወሰኑን ለዛሚ 90.7 የገለፁት የአዲስ አበባ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃሊማ ባልገባ ናቸው፡፡ የቤት ባለእድለኞች በቂ ማስረጃ ሳይጣራ በዕጣው እንዲካተቱ መደረጉ ስህተት እንደነበረም ተናግረዋል፤ በቀጣይ የሚወጣው የ11ኛ ዙር የቤት ባለቤት እጣ አወጣጥ ግን መረጃዎች ተጣርተው ካለቁ በኋላ እንደሚከናወን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም አሳውቀዋል፡፡ (ታሪክ አዱኛ) 

ሰኔ 03/2007 ዓ.ም

ዝግጅቱ በሀገራችን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሀገር ውስጥ የሚታዩ ኢንዱስትሪ ነክ ጉዳዮችን ለመዳሰስ እና አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎችን ለማካፈል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገልጧል፡፡ የኦዚ ቢዝነስ እና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ መስራችና ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል እንዳሉት ከሆነ 3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ በዋናነት ተሳታፊ ድርጅቶች እና ተቋማት ከእለት ተዕለት ክንውኖቻቸው በተጨማሪ ክህሎትና ስኬት የሚያገኙበት ከመሆኑም በላይ በሀገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ በጎ ተፅእኖ እንደሚያሳርፍ አቶ ቁምነገር ተከተል ተናግረዋል፡፡ ዝግጅቱ በነገው እለት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቶ ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

ሰኔ 02/2007 ዓ.ም

በ60 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው ኤሌምቱ ኢንትግሬትድ ወተት ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ጥራቱን የጠበቀ የወተት ምርትን ለህብረተሰቡ እያቀረበ እንደሚገኝና በዘርፉ ህጋዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር እንደሚጠር አስታውቋል፡፡ የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በላቸው ሁሪሳ እንደተናገሩት ከሆነ በሀገሪቱ የወተት ግብይት የህግ ማዕቀፍ እየተደረገለት አይደለም፡፡ ተዋንያኑን የሚዳኝ ደንብና መመሪያ አልወጣለትም፤ በዚህም የተነሳ በወተት ግብይት ውስጥ ፍቃድ የሌላቸው ግለሰቦች እንደፈለጉ ወደ ንግዱ ሲገቡና ሲወጡ ይስተዋላል፡፡ ከገበሬው በዱቤ በመግዛት ሳይከፍሉ ቀርተው ሀብታቸውን የተቀሙ ገበሬዋች በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የጥራት ቁጥጥር ባለመኖሩ ትክክለኛ ወተት ለተጠቃሚዎች ስለማቅረባቸው ማረጋገጫ የለም ሲሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በላቸው ሁሪሳ ገልፀዋል፡፡ ኤሌምቱ ስራ ሲጀምር 100 ለሚደርሱ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ወተት ፣ እርጎ እና አይብን ለተጠቃሚዎች ያከፋፍላል፡፡ (ሰላም ተሾመ)

ሰኔ 01/2007 ዓ.ም

ሀገራችን የተባበሩት መንግስታት የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) አገሪቱ ረሃብን በመቀነስ ለሰራችው አመርቂ ስራ እውቅና ሰጥቷታል፡፡

ኢትዮጵያ እቅዱን አንድ ዓመት ቀድማ ማሳካት መቻሏም ተገልጧል፡፡ በዚህም መሰረት ረሃብን በግማሽ በመቀነሷ ከአለም አቀፍ የምግብና የእርሻ ድርጅት የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡

የሽልማት ስነ-ስርዓቱ በትላንትናው ዕለት በጣሊያን ሮም ተካሂዷል፡፡ ከ72 አገራትም 29 የሚሆኑት ረሀብን በግማሽ ለመቀነስ የሚቻላቸው ናቸው የተባሉ ሲሆን 12 አገራት ደግሞ አጠቃላይ የረሀብተኛ ህዝባቸውን ቁጥር ከ5 በመቶ በታች ማድረግ ይቻላሉ ተብለው እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

እቅዱ እየተተገበረባቸው ከሚገኙ 129 የአለም አገራት መካከል 72ቱ ረሃብን መቀነስ ችለዋል፡፡ በ35ኛው የፋኦ ጉባኤ ተገኝተው የዕውቅና ምስክር ወረቀቱን የተቀበሉት የኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ (ሰላም ተሾመ)

ሰኔ 01/2007 ዓ.ም

ከአራት አመታት በፊት በሀገራችን መድሃኒት የማከማቸት አቅም 46ሺ ሜትር ኪውብ ነበር፡፡ አቅሙን ወደ 580ሺ ኪውብ እንዲድግ 17 መጋዘኖች በሁሉም ዋና ዋና ከተማውች እየተገነቡ መሆኑን በመዳኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የግዥ ትንበያ እና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሬድ ይገዙ ገልፀዋለል፡፡ አዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፤ ድሬዳዋ፤ ነገሌ ቦረና፤ ባህርዳር ፤ጎንደር፤ ደሴ ፤ መቀሌ ፤ጅማ ፤ ቀባሪ ደሀር ፤ነቀምቴ ፤ጋንቤላ ፤አሶሳ ፤ጅጅጋ ፤ አፋር ፤ሽሬ  ፤ግንባታው ካሉባቸው መካከል  ይጠቀሳሉ፡፡ እየተገነቡ ካሉት መካከል 8 የመድሀኒት ማከማቻ ግንባታዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አቶ ያሬድ ገልጸዋል ፡፡ መጋዘኖቹ መድሃኒት የማከማቸት አቅም እንዲያድግ ከማድረጉ በላይ በፍጥነት በሀገሪቱ ባሉ ጤና ተቋማት  እንዲዳረስ ያደርጋል ብለዋል፡፡ (ሰላም ተሾመ)

ግንቦት 28/2007 ዓ.ም

በአሁኑ ሰዓትም እሳቱን ለማጥፋት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን፣ ህብረተሰቡና የፖሊስ አካላት ርብርብ እየደረጉ መሆናቸውን አቶ ንጋቱ ማሞ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አስታውቀዋል፡፡

ግንቦት 28/2007 ዓ.ም

አስመላሽ ዘፈሩ ይባላል፡፡ የ35 ዓመት ወጣትና የሰንዳፋ ነዋሪ ነው፡፡ ከአልሙኒየም፣ ከጣውላና ከብረት ይህን አውሮፕላን ሰርቷል፡፡ ታህሳስ 1/2006 ዓ.ም ስራውን በመጀመር ከአንድ አመት ከሰባት ወር በኋላ አጠናቋል፡፡ አውሮፕላኗ እስከ 3 ሺ ጫማ ከፍታ እና 182 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ እንደምትችል ነግሮናል፡፡ የሙከራ በረራውን ሰኔ 4/2007 ዓ.ም በሰንዳፋ ከተማ ያካሂዳል፡፡

ግንቦት 28/2007 ዓ.ም

በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል፤ መንግሥት በሀገሪቱ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለማስፋፋት ሲያከናውናቸው ከቆየው ግንባታዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የICT መንደር በመጪው እሁድ ተመርቆ ስራ እንደሚጀምር ያስታወቁት በትላንትናው እለት ነው፡፡

ዘርፉ የሌሎች ሴክተሮች ብቻም ሳይሆን እራሱን ችሎ እንደ አንድ ተቋም መንቀሳቀስ እንደሚችል የሚያሳይ ግንባታ እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል በፓርኩ ውስጥ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ድርጅቶች ስራ ጀምረው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሌሎች የምርምር፣ የስልጠናና የቢዝነስ ተቋማት ተከፍተው ስራ ሲጀምሩ ዘርፉ ለሀገሪቱ አንድ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ተናግረዋል፡፡ (ቴድሮስ ብርሀኑ)

ግንቦት 28/2007 ዓ.ም

የምስክር ወረቀቱን የሚሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማይንቀሳቀስ ንብረት መረጃ ኤጀንሲ ነው፡፡

ኤጀንሲው በአስሩም ክ/ከተሞች ባሉት ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በባለይዞታዎች የይረጋገጥልኝ ጥያቄ የይዞታ ማረጋገጫ ፕሮጀክት ፅ/ቤቱን በማቋቋም የማረጋገጥ ስራ እየሰራ መሆኑ ተገልጧል፡፡

ኤጀንሲው ከተቀበለው ከ65ሺ በላይ የይዞታ ይረጋገጥልኝ ጥያቄ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 9 ወራት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ይዞታዎችን ወሰን ያካለለ ሲሆን የ 7ሺ 699 ይዞታዎች የቅየሳ ስራ መጠናቀቁን የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋወሰን ዴሲሳ ናቸው፡፡

ህጋዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ስርዓት ደግሞ የይዞታ ዋስትና በመስጠት ውጤታማ የሆነ የከተማ መሬት ግብይት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

ግንቦት 27/2007 ዓ.ም

ክብደት ላይ የተመሰረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፍቃድ ማደሻ ክፍያ ታሪፉ እንደሚከተለው ተዘርዝሯል፡-

1. ለአውቶሞቢሎች እና ለህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች     የዓመታዊ ክፍያ መጠን

   • እስከ 5 መቀመጫ ያላቸው                            125 ብር
   • ከ6 - 13 መቀመጫ ያላቸው                           50 ብር
   • ከ13 - 29 መቀመጫ ያላቸው                         200 ብር
   • 30 - 44 መቀመጫ ያላቸው                          250 ብር
   • 44  መቀመጫ ያላቸው                                800 ብር

2. ለደረቅ ጭነት ማመላለሻ

   • እስከ 15 ኩንታል                                      300 ብር
   • ከ16 - 35 ኩንታል                                    550 ብር
   • ከ36 - 70 ኩንታል                                   1,000 ብር
   • ከ71 - 120 ኩንታል                                  1,500 ብር
   • ከ121 - 180 ኩንታል                                2,000 ብር
   • ከ180 በላይ ኩንታል                                  2,500 ብር

3. ለሞተር ሳይክል                                                  50 ብር

4. ለምትክ ተለጣፊ ለመስጠት                                      100 ብር ናቸው፡፡

(ስምኦን ደረጄ)

ግንቦት 27/2007 ዓ.ም

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው የበጀቱ 22 ነጥብ 6 በመቶ ለመደበኛ፣ 37 ነጥብ 4 በመቶ ለካፒታል በጀት፤ ለክልሎች ድጋፍ 34 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም የበጀቱ አጠቃላይ 5 ነጥብ 4 በመቶ ደግሞ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

ግንቦት 27/2007 ዓ.ም

ምርጫ 2007ን በተመለከተ የቦርዱ ሃላፊዋች መግለጫ ሰጥተዋል። በምርጫው ህጋዊ የሆነ የቅሬታ አፈታት ስነ-ሰርዓት መዘርጋቱን የቦርዱ ም/ሰብሳቢ ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ለቦርዱ የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩን አስታውቀዋል። የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በበኩላቸው የምርጫ አስፈፃሚዎችንና ታዛቢዎችን ማክበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)