አገር አቀፍ ዜናዎች

ጥቅምት 16/2008 ዓ.ም

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች እና አምስት ኩባንያዎች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የተሻሻለውን የጉምሩክ አዋጅ 859/2006ን በመጥቀስ ከ20 በላይ የሚሆኑ ክሶች ሊቋረጡልን ይገባል በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ምስከር የመስማቱ ሂደት ይቀጥል ብሏል።

ቀደም ሲል የተከሳሽ ጠበቆች ክስ ይቋረጥልን በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ አስመልክቶ ከህገ-መንግሰት አጣሪ ጉባኤ የተላከለት ውሳኔ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ዛሬ ቀጠሮ ይዞ ነበር።

ተከሳሾቹ ለዚህ አቤቱታቸው መነሻ ያደረጉት በተሻሻለው አዋጅና በህገ-መንግስቱ ሁለት አንቀጾችን በመጥቀስ አዋጁና ህገ-መንግስቱ ተቃርኖ አላቸው የሚል ነበር።

ችሎቱ ይህንን አስመልክቶ ጉዳዩ ህገ-መንግስታዊ ትርጉም እንዲያገኝ ለህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ልኮ እንደነበርና ጉባኤው አይቃረንም የሚል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ችሎቱ ከጉባኤው የተላከለት ውሳኔ ላይ ዛሬ ብይን በመስጠት ምስክር የመስማቱ ሂደት እንዲቀጥልም ትእዛዝ ሰጥቷል። በዚህም መሰረት እስከ ህዳር ወር መጨረሻ አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ያሉባቸው የመዝገብ ቁጥር 141352 እና 141356 ላይ የወጣውን የጊዜ ሰሌዳ አስታውቋል።

ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሚሰሙ ሲሆን ማክሰኞ እና ሀሙስ በእነዚህ መዝገቦች ውስጥ በተከሳሾች የሚቀርቡ የተለያዩ አቤቱታዎች ብይን ሲሰጥባቸው ቆይተዋል። በመዝገብ ቁጥር 141354 ላይ ብይን ለመስጠትም ቀጠሮ ይዟል፡፡

ጥቅምት 12/2008 ዓ.ም

ከመስከረም 29 ጀምሮ 7 የውጭ ሀገር ዜጎች ከዝሆን ጥርስ የተሰሩ ጌጣጌጦችና ጥርሱን እንዲሁም የነብር ጥርስ እና ጥፍር ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም 63 ህገ-ወጥ የእንስሳት ውጤት አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ ዳንኤል አሰፋ በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የዓለም አቀፍ የዱር እንስሳት ስምምነት ከፍተኛ ባለሞያ ለዛሚ ገልፀዋል፡፡

በትላንትናው እለት በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ከኢትዮጵያ 11 የነብር ጥርሶችን ይዞ ለማለፍ ጥረት ሲያደርግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ግለሰቡ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ሲሰራ እንደነበር ተገልጧል፡፡

የነብር ጥርስ ህልውናቸው አስጊ ደረጃ ላይ የሚገኝ የዱር ህይወት ዝርያዎች ዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነት ወይም (ሳይተስ) ላይ የተመዘገበ በመሆኑ የተነሳ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር እንዲውል እንደተደረገ አቶ ዳንኤል አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

ጥቅምት 12/2008 ዓ.ም

የበረራ ቁጥሩ ETH-500 DUB-IAD 787 ET-ARF ድሪምላይነር አውሮፕላን ዛሬ ማለዳ 2፡41 ደቂቃ ላይ 300 መንገደኞችን አሳፍሮ ከአየርላንድ ዋና ከተማ ደብሊን ወደ አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ መብረር ከጀመረ በኋላ በአትላንቲክ ውቂያኖስ ላይ እንዳለ አንደኛው ሞተሩ ስራ አቁሟል፡፡ ይህንን ተከትሎም ለ1 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ተጉዞ ግማሽ ያህል መንገድ ካገባደደ በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ወደ ተነሳበት እንዲመለስ ግድ ሆኖበታል ተብሏል፡፡

አውሮፕላኑ በስራ ላይ የነበረውን ሌላኛውን ሞተር ተጠቅሞም ወደ ደብሊን አውሮፕላን ማረፊያ በመመለስ በሰላም ማረፉንና ችግሩ እስኪስተካከልም ተሳፈሪዎቹን ወደ አሜሪካ የሚያደርስ አውሮፕላን ከጀርመን ፍራንክፈርት ወደ ደብሊን መላኩን አይሪሽ ሚረር ዘግቧል፡፡

ጥቅምት 08/2008 ዓ.ም

በተለያዩ ዘርፎች እየተደረጉ ላሉ ለውጥ አምጭ እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ጉልበት የሆነውን የሰው ሃብት ሀገሪቱ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባና ይበልጥ ማስፋት ያለባት ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ኤልክትሪካልና ኮምፒተር ምህንድስና ትምህርት ቤት በቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ ማስተማር መጀመሩን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተገለጸው በዚህ በቴሌኮም ዘርፍ የላቀ የሰው ሃይል ሀገሪቱ ትፈልጋለች፤ በተለየ ትኩረት ለመስራትም እቅድ ተይዟል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛ ብዙሃን ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገ/ሚካኤል እንዳሉት ከሆነ በዚህ በቴሌኮም ዘርፍ ከውጭ በሚመጡ ባለሞያዎች ብቻ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጣትን ማሰብ የለብንም፤ የራሳችንን የሰው ሃይል በብቃት ማፍራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም በማስተማር ደረጃ የተጀመረው ይህ የቴሌኮም ኢንጅነሪንግ ስልጠና ተጨባጭ ለውጥን እንዲያመጣ ተደርጎ የተቀረፀ እና ለውጡንም በተግባር ለማየት በምንፈልግበት ዘርፍ ነው ሲሉ ተናገረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

የጥቅምት 2-1-08

ከአንድ ዓመት በፊት በ47 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወጭ የተቋቋመው ሽንትስ የጨርቃ ጨርቅ ጋርመንት ፋብሪካ መዳረሻውን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በማድረግ የተለያዩ አልባሳትን እያመረተ ወደ አውሮፓ ሀገራት ይላካል፡፡

ድርጅቱ በኮሪያ ባለሃብቶች የተቋቋመና አፍሪካ ውስጥ የመጀሪያውን ፋብሪካ የከፈተው በአዲስ አበባ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ  ከ1,500 በላይ ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል፡፡ ፋብሪካው የፈጠረው የስራ እድል መልካም ቢሆንም አብዛኞቹ ሰራተኞች ግን የወር ደሞዛቸው አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ደመወዛቸው ወቅቱን ጠብቆ እንደማይከፈላቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የቤት ኪራይን ጨምሮ ጊዜ ለማይሰጡ ወጭዎቻቸው ስለማይደርስ የተስተጓጎለ ህይወት እንድንመራ ተገድርጎናል ነው የሚሉት፡፡

ከደመወዝ መጠን ዝቅተኝነትና በወቅቱ ክፍያ ካለመፈፀሙ በተጨማሪ በየ 6 ወሩ የደሞወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ቢገለፅም በተግባር እየታየ ያለው ግን ወጥ ያልሆነና አንዳንዶች ከ6 ወር በፊት ጭማሪ ሲደረግላቸው አንዳንዶች ደግሞ በ10 ወርም ላይጨመርላቸው እንደሚችል አጨማመሩም ውጤቱን መሰረት ያላደረገ ነው ይላሉ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢንዱስት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ሃይሌ ችግሩ የደመወዝ ማነስ ሳይሆን ከተማው ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ነው ይላሉ፡፡

ይህንን ችግርም ለመቅረፍ ፋብሪካው እንደመፍትሄ እያሰበ ያለው የሰራተኞች መኖሪያ መንደር መገንባት ስለሆነ ለዚህ የሚሆን ቦታ ከመንግሥት ጠይቋልም ብለዋል፡፡ አቶ ታደሰ የደመወዝ በወቅቱ አለመክፈልን በተመለከተ የምናውቀው ነገር አልነበረም ችግሩ ካለ ግን እንከታተላለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የጥቅምት 2-1-08

ከአንድ ዓመት በፊት በ47 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወጭ የተቋቋመው ሽንትስ የጨርቃ ጨርቅ ጋርመንት ፋብሪካ መዳረሻውን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በማድረግ የተለያዩ አልባሳትን እያመረተ ወደ አውሮፓ ሀገራት ይላካል፡፡

ድርጅቱ በኮሪያ ባለሃብቶች የተቋቋመና አፍሪካ ውስጥ የመጀሪያውን ፋብሪካ የከፈተው በአዲስ አበባ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ  ከ1,500 በላይ ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል፡፡ ፋብሪካው የፈጠረው የስራ እድል መልካም ቢሆንም አብዛኞቹ ሰራተኞች ግን የወር ደሞዛቸው አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ደመወዛቸው ወቅቱን ጠብቆ እንደማይከፈላቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የቤት ኪራይን ጨምሮ ጊዜ ለማይሰጡ ወጭዎቻቸው ስለማይደርስ የተስተጓጎለ ህይወት እንድንመራ ተገድርጎናል ነው የሚሉት፡፡

ከደመወዝ መጠን ዝቅተኝነትና በወቅቱ ክፍያ ካለመፈፀሙ በተጨማሪ በየ 6 ወሩ የደሞወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ቢገለፅም በተግባር እየታየ ያለው ግን ወጥ ያልሆነና አንዳንዶች ከ6 ወር በፊት ጭማሪ ሲደረግላቸው አንዳንዶች ደግሞ በ10 ወርም ላይጨመርላቸው እንደሚችል አጨማመሩም ውጤቱን መሰረት ያላደረገ ነው ይላሉ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢንዱስት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ሃይሌ ችግሩ የደመወዝ ማነስ ሳይሆን ከተማው ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ነው ይላሉ፡፡

ይህንን ችግርም ለመቅረፍ ፋብሪካው እንደመፍትሄ እያሰበ ያለው የሰራተኞች መኖሪያ መንደር መገንባት ስለሆነ ለዚህ የሚሆን ቦታ ከመንግሥት ጠይቋልም ብለዋል፡፡ አቶ ታደሰ የደመወዝ በወቅቱ አለመክፈልን በተመለከተ የምናውቀው ነገር አልነበረም ችግሩ ካለ ግን እንከታተላለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

መስከረም 27/2008 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም ልዩ ስሙ ኦርማ ጋራዥ አካባቢ የተወለዱት አምባሳደር ዘውዴ ትምህርታቸውን በሊሴ ገብረማርያም ለ12 ዓመታት ከተማሩ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ሀገር በመሄድ ተምረው በጋዜጠኝነት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ወደ ሃገር ከተመለሱም በኋላ በተለያየ የጋዜጠኝነትና በዲፕሎማትነት ሙያ አገልግለዋል፡፡  በጊዜውም የወሬ ምንጭ የሚባል የዜና አገልግሎት መስርተው ከዋና ዳይሬክተርነት እስከ ረዳት ሚኒስትርነት ደረጃ ያገለገሉ ሲሆን በፈረንሳይ የአምባሳደር ምክትል፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረዳት ሚኒስትር፣ በሮም የንጉሠ ነገስቱ አምባሳደር እና በቱኒዚያ አምባሳደር ሆነው መስራታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ በደርግ የስልጣን ዘመንም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ መስሪያ ቤት የመንግስታት ግንኙነትና የፖለቲካ ኃላፊ በመሆን ለረጅም አመታት አገልግለዋል::

አምባሳደር ዘውዴ ጡረታ ከወጡ በኋላ በታሪክ ተመራማሪነት እና በጸሐፊነት ጊዜያቸውን ያሳለፉ ሲሆኑ ”የኤርትራ ጉዳይ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት”፣ “ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ” እና “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ታሪክ” ካሳተሟቸው መጻህፍት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ መንግስት ሁለተኛ መጽሀፍንም እያዘጋጁ ነበር፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በተወለዱ በ81 ዓመታቸው ማረፋቸውን ለአምባሳደሩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

መስከረም 20/2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲቲዩት የቀጣይ ጊዜ እቅዴ ናቸው ካላቸው መካከል በአዲስ አበባ ብቻ የነበረውን የካይዘን ተቋም ወደ ክልሎችም ማስፋፋት አንዱ ነው፡፡ በካይዘን ኢንስቲቲዩት የቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሰብለ ወንጌል ሀረገወይን ለዛሚ እንደተናገሩት በተለይም ቀጣዩ 2016 የፈረንጆቹ ዓመት ሲመጣ ክልሎች ላይ የላቀ ስራ መስራት እንፈልጋለን፤ ዝግጅቱም ተጠናቋል ያሉ ሲሆን ይህ ከመንግሥትም የመጣ መመሪያ ነው ብለዋል፡፡

በካይዘን ፍልስፍና መሰረት የክልሎችን አቅም መገንባትና ያላቸውን ሃብት በትክክል ወደ ተግባር ለውጠውት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልም ጭምር ይህ ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡ አማራና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በጥቅሉ አራት ክልሎች ላይ ስራው የሚጀመር ሲሆን ቀስ በቀስም ወደ ሁሉም ክልሎች እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡

መስከረም 20/2008 ዓ.ም

ከፌዴራል የተነሱ 41 አርቲስቶችና 67 የሚዲያ ባለሞያዎች ተካተዋል፡፡ ከክልል የሚቀላቀሉ ሌሎች የታሪካዊው ጉዞ ተሳታፊዎችም ይጠበቃሉ፡፡ መነሻውን ባህር ዳር ያደረገው ይኸው ታሪካዊ ጉዞ መዳረሻውን ሃሙሲት በለሳ ጎንደር እና ዋግ ሁምራ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ይሄው የጥበብ ጉዞ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረው የብአዴን ኢሀዴግ የምስረታ በአል አንዱ አካል ሲሆን በአሉ በድምቀት ህዳር 11 ይከበራል፡፡ የታሪካዊው ጉዞ ተሳታፊዎች ዛሬ ሃሙሲትና በለሳን ከጎበኙ በኋላ በሁለት ምድብ ተከፍለው ግማሹ ወደ ጎንደር እና ሌላኛው ምድብ ደግሞ ወደ ዋግ ሁምራ እንደሚያቀና ይጠበቃል፡፡ ይኸው “ታሪካዊ የጥበብ ጉዞ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጉብኝት ዋነኛ መዳረሻዎቹም የብአዴን ኢሀዴግ የተመሰረተባቸውን እና የትጥቅ ትግል ያከናወነባቸው ቦታዎችን ያከተተ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ ተጓዦቹም ለጉዞ የሚሆኑ የቀደምት ታጋዮች ይለብሷቸው የነበሩ ካኪ ቁምጣና ኮት እንዲሁም ሽርጥ ተሰጥቷቸዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)

መስከረም 18/2008 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ሽልማቱን ያገኘችው የምዕተ ዓመቱን ግቦች በማስፈፀም ረገድ ባስመዘገበችው ውጤት ነው፡፡ የዋንጫ ሽልማቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ተቀብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ኒዮርክ በተዘጋጀው በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ንግግር አድርገዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን ለተሸላሚ ሀገራቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከዓለም ምግብ ድርጅት ዓለም አቀፍ ሽልማት እንደተበረከተላት ይታወሳል፡፡

መስከረም 18/2008 ዓ.ም

በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ የተወለደበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ የሚከናወነው የመታሰቢያ ፕሮግራም ትናንት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በድምቀት ተከብሯል፡፡ ዘንድሮ ከክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ ህልት በኋላ ለ7ኛ ጊዜ የተከበረው ይህ ዓመታዊ በዓል በብሔራዊ ቴአትር አዘጋጅነት ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ ቀደም በጥላሁን ስም የተቋቋመው ኮሚቴ ያዘጋጀው እንደነበር ተነግሯል፡፡

በዕለቱ ጥላሁንን የተመለከቱ የተለያዩ ትውስታዎችና ፁሁፎች እንዲሁም ስራውን የተመለከቱ ንግግሮች የቀረቡ ሲሆን የሙዚቃ ባለሞያና መምህር የሆነው አክሊሉ ዘውዴ ‹‹ጥላሁን በሙዚቀኛ አይን›› በሚል ርዕስ የጥላሁንን የድምፅ አወጣጥና የስራዎቹን ረቂቅነት ተናግሯል፡፡

1933 ዓ.ም ላይ የተወለደው ክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ 2001 ዓ.ም ላይ ህልፈቱ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ (ያልፋል አሻግር)

መስከረም 11/2008 ዓ.ም

ብሩክ ዘአብ ይባላል፤ የ15 ዓመት ታዳጊ ነው፡፡ የተወለደው በጎንደር ከተማ ቀበሌ 02 ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ፈጣን አዕምሮ እንዳለው በቅርበት የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ በጎንደር አካባቢ እና በሌሎች ስፍራዎች ያገኛቸውን መረጃዎች በቀዳሚነት ያሰራጫል፡፡

የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ጎንደር ከተማ ሲገቡ ታሪካዊ ቦታዎችን ያስጎበኛል፤ የእንግዳ ማረፊያዎችንም ይጠቁማል፡፡ በዚህ በሚያገኘው ገቢ ትምህርቱን ይከታተላል፡፡ አሳዳጊ አያቱንም ይጦራል፡፡

በጎንደር አካባቢ ለመረጃ ካለው ቅርበት እና ፍጥነት ቢቢሲ የተሰኘውን ቅፅል ስም አግኝቷል፡፡ ለጎንደር ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብም የህዝብ ግንኙነት ስራ ይሰራል፡፡ ሁሉም የጎንደር አካባቢ ነዋሪዎች ብሩክ ከማለት ይልቅ ቢቢሲ በማለት ሲጠሩት ይስተዋላል፡፡

በቅርቡ ወደ ጎንደር ተጉዘው የነበሩት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ብሩክን ያገኙት ሲሆን በፍጥነቱና ለመረጃ ባለው ቅርበት ተደምመዋል፡፡ በቀጣይም መጥተው እንደሚያገኙት እና ልዩ ዘገባ እንደሚሰሩለት ቃል ገብተውለታል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

መስከረም 07/2008 ዓ.ም

በትናንትናው እለት በሸራተን አዲስ ሆቴል የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ለፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ለኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታደሰ ሃይሌ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ደዋኖ ከድር እንዲሁም ለንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ከበደ ጫኔ በአማካሪያቸው በአቶ አየነ ፈረደ በኩል ከምክር ቤቱ ጎን በመቆም የግሉ ዘርፍ ለሚያጋጥመው ችግር መፍትሄ በመስጠታቸው የውጪውን ባለሃብት ከሀገር ውስጥ ባለሃብት ጋር ለማገናኘት ባደረጉት ጥረት ከወርቅ የተሰራ የምክር ቤቱ አርማ እና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ለኩላሊት እጥበት ማህበር የ100,000ሺ ብር ቼክ ስጦታ ለመስጠት አስተባባሪ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ከፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለመቀበል ወደ መድረክ የቀረበ ቢሆንም ቼኩ በመረሳቱ ለሌላ ቀን በፕሬዝዳንቱ በኩል እንደሚደርስ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ገልፀው አስተባባሪው ወደ መቀመጫው ተመልሷል፡፡ (ታሪክ አዱኛ) 

መስከረም 06/2008 ዓ.ም

ባለስልጣኑ አዳዲስ መንገዶችን ተከትለው የሚገነቡትን የህንፃ ባለቤቶች ህንፃቸውን ለመገንባት አሸዋና ጠጠሮች በእግረኛ መንገድ ላይ በማድረግ ችግር ስለፈጠሩ መንገዴን ሰርቃችኋል በማለት ቀጥቷቸዋል፡፡ በተሽከርካሪ መንገድ ላይ ለረጅም ጊዜ መኪና ማቆም፣ የጎዳና ላይ ንግድ እና ሌሎችም መንገዴን ተሰርቆብኛል እንድል ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ብሏል፡፡ በመሰል ተግባር መንገዶቼን የሚሰርቁትን አሁንም ተከታትዬ መቅጣቴን እቀጥላለሁ ብሏል፡፡ (ነጋሽ በዳዳ)

መስከረም 06/2008 ዓ.ም

በየካ ሀያት ቁጥር 2 ኮንደሚኒየም አካባቢ እዮብ እንግዱ የተባለው የ3 ዓመት ህፃን አባቱን ጁስ ግዛልኝ ብሎ ይጠይቀዋል፤ አባትም ልጁ እዛው እንዲጠብቀው እና ገዝቶለት እንደሚመጣ ትዕዛዝ ሰጥቶ ጁሱን ሊገዛ አቅራቢያው ወዳለ ሱቅ ይሄዳል፡፡ ህፃን እዮብ አባቱን ከኋላ በመከተል ድንገት በአካባቢው በነበረና ተቆፍሮ ባልተደፈነ የውሀ ጉድጓድ ውስጥ ይገባል፣ አባትም ጁሱን ገዝቶ ሲመጣ ልጁን ከስፍራው ያጣዋል፡፡ ከ5 ደቂቃዎች በላይ በተደረገ አሰሳም ህፃን እዮብ እንግዱ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ተገኝቷል፡፡ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ በነበረበት ሰዓትም ህይወቱ አልፏል፡፡ 

መስከረም 06/2008 ዓ.ም

ሰሎሜ ጉልላት የተባለችው የ20 ዓመት ወጣት ከአንድ ሴት ከጓደኛዋ ጋር በመሆን በለቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ በሚገኝ መዝናኛ ቤት በመዝናናት ላይ እያሉ በጥበቃ ስራ ላይ የነበረ የፌዴራል ፖሊስ አባል ከጓደኛዋ ጋር የመዝናኛው መፀዳጃ ቤት ሲገቡ ተከትሎ በመግባት የዋና ክፍሉን በር ቆልፎ በክፍሉ ውስጥ እንዳለች የተኩስ ድምፅ የተሰማ ሲሆን ወዲያው ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ተጠርጣሪው የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ራሱን ለማጥፋት ቢሞክርም ሕይወቱ ባለማለፉ የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገለት እንደሚገኝና ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለዛሚ 90.7 ገልጧል፡፡

መስከረም 04/2007 ዓ.ም

አቶ ሞላ አስገዶም የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር እና ከመሰረቱ ነባር አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ንቅናቄው በወቅቱ ስለተመሰረተበት እንዲሁም ስለተቋረጠበት ሁኔታ፤ በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ውስጥ ስላለው እንቅስቃሴ በተጨማሪም በቅርቡ አሸባሪው ግንቦት ሰባት እና አርበኞች ግንባርን ጨምሮ ስላካሄዱት ጥምረት ዛሬ በግዮን ሆቴል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ከግንቦት ሰባቱ መሪ ዶ/ር ብሀኑ ነጋ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት እንዲሁም አቶ ሞላ የጥምረቱ ምክትል ሊቀመንበር በቅርቡ መደረጋቸውን ተከትሎ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በቃላቸው የማይገኙ ውሸታም ናቸው ሲሉ ገልፀዋቸዋል፡፡

ትግላቸውን ለማቋረጥ የተገደዱትም ኢትዮጵያ እያደገች በመምጣቷ በልማት መገስገሷ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለአንድ ዓመት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲሰሩ እንደቆዩ የገለፁት አቶ ሞላ አስገዶም ባደረጉት እንቅስቃሴም የኤርትራ ወታደሮችን በመደምሰስ ወደ ሱዳንና ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ (ሱራፌል ዘላለም)

መስከረም 04/2008 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት ከቀረቡት 3000 ያህል መስፈርቶች 40 ያህል ብቻ እንደቀረውና በተሰጠው ውስን ጊዜ ውስጥ ቀሪ መስፈርቶቹን አሟልቶ ሰርተፍኬቱን እንደሚያገኝ ተነግሯል፡፡ ዝቅተኛው የባቡር መስመር ዋጋ 2 ብር ሲሆን 4 ኪ.ሜ ወይም የ2 ብር መንገድን ሳይከፍል ለመጓዝ የሚሞክር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ተጠቃሚም የዋጋውን 10 እጥፍ እንደሚከፍል ተገልጧል፡፡