Super User

Super User

Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በ3.4 ቢሊዮን ብር ተገንብቶ መስከረም ወር የተመረቀው የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር ከምረቃው በኋላ ባሉት ከ 3 እስከ 6 ወራት ውስጥ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚጀምር መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባቡሩ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ዛሬም ድረስ መደበኛ አገልግሎቱን አልጀመረም፡፡ ለምን ስንል ለኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተፈራን ባነጋገርንበት ወቅት ባቡሩ የሙከራ ስራውን በወቅቱ ባለመጀመሩ የመደበኛ ስራው መዘግየቱን ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
እስከ አሁን መደበኛ የሚባል ስራውን ያልጀመረው ባቡሩ ስራውን መች ይጀምራል ለሚለው ጥያቄ አቶ ደረጄ ተፈራ በምላሻቸው ጊዜውን በትክክል ማስቀመጥ ያስቸግራል ሲሉ ምላሽ ሰተዋል፡፡
መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የኢትዩ ጅቡቲ የምድር ባቡር አስተዳደር 75 ከመቶ ከኢትዮጵያ ቀሪ 25 ከመቶ የሚሆነውን የንግድ ፈቃድ ከጅቡቲ ማግኘት ችሎአል፡፡
ጅቡቲ ላይ ቆመው የሚገኙት የባቡሩ ዋገኖች አገሪቱን ለኪራይ ኪሳራ እየዳረጉ በሀገር ውስጥ የገቡት ሎኮሞቲቮችም ቢሆኑ ለብልሽት መጋለጣቸው ኪሳራው በማን ይታሰባል ለሚለው ጥያቄ አቶ ደረጄ ተፈራ ጅቡቲን በተመለከተ የጋራ ንብረት ስለሆነ ኪራይ አታስከፍልም በሀገር ውስጥ ያሉትም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለብልሽት ስለማይዳረጉ ስጋት የለብንም ሲሉ ምላሽ ሰተዋል፡፡
752 ኪሎ ሜትርን የሚሸፍነው ባቡሩ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ቀናትን ይፈጅ የነበረውን ርቀት ወደ 10 ሰዓታት ዝቅ ያደርገዋል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡
ለሚቀጥሉት 6 ዓመታት ቻይናውያን የሚያስተዳድሩትን ባቡር ለመመረቅ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሀ/ማርያም ደሳለኝ፣የጅቡቲው ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌህ፣የቶጎ ሪፐብሊክ ፕሬዘዳንት ፋዩሪ ኦሲዙማ እና የቻይና ልዩ ልዑክ ተወካይ ዙሻኦሺ በለቡ ባቡር ጣቢያ መገኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

በናይሮቢ በተካሄደው እርዳታውን የማስረከብ ስነስርዓት ላይ በአገሪቱ የቻይና አምባሳደር እንዳሉት እርዳታው ቤጂንግ ለአገሪቱ ለመስጠት ካሰበችው 450000 ከረጢት የእርዳታ ሩዝ ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ነው፡፡ ቻይና በኬኒያ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምትሠጠው እርዳታ 517 ሚሊዮን ብር ያወጣል፡፡
እርዳታውን በመረከብ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የአገሪቱ State department ተቀዳሚ ፀሐፊ ጆሴፍታ ሙኩቤ እንዳሉት ቻይና ለሕዝባችን ያደረገችው ነገር የሚያስመሰግናት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል በድርቅ በተመቱ የአገሪቱ ክፍሎች አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 3.5 ሚሊዮን ዜጎች ይገኛሉ፡፡
አገሪቱ የመታው ድርቅ የመኖ እጥረት እንዲከሰትና የወተት ምርቱም እንዲያሽቆሎቁል አግርጎዋል፡፡ በተጨማሪም የመሰረታዊ ምግብ ዋጋ ጨምሯል፡፡ የተከሰተው ድርቅ በውኃ ግኝት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ምክንያት የሰብል ምርት እንዲያሽቆሎቁል ያደረገ ጭምር ነው፡፡ ከቻይና የተበረከተው እርዳታ ከሞንባሳ ናይሮቢ በተዘረጋው የባቡር መስመር የተጓጓዘ ነው፡፡

በ 2050 ይኖራል ተብሎ በተገመተው የሕዝብ ቁጥር መሰረት ህንድ ከቻይና እንደምትበልጥና በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በቀዳሚነት የተሰለፈችው ናይጄሪያ 2050 ከመግባቱ ጥቂት ግዜ ቀደም ብሎ አሜሪካን በመብለጥ በአለም ሶስተኛ የሕዝብ ብዛት እንደሚኖራት ተገምቷል፡፡
የአፍሪካ 26 አገራት የሕዝብ ቁጥራቸው በእጥፍ እንደሚያድግና በ 2050 የአለም 47 አገሮች ደግሞ 33 በመቶ ወይንም አሁን ካላቸው 1 ቢሊዮን ዜጎች ወደ 1.9 ቢሊዮን እንደሚጨምር የተባበሩት መንግስታት በትላትናው ዕለት ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በዚህ ሪፖርት መሰረት በአለማችን አነስተኛ ወሊድ ያለባቸው አገራት ቻይና፣ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ራሺያ፣ ጃፓን እና ሌሎችም ሆነውዋል፡፡ 60 እና ከ 60 አመት በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር አሁን ካለበት 962 ሚሊዮን በእጥፍ በማደግ 2.1 ቢሊዮን እንደሚሆንም ሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡
ዘገባው የ News 24 ነው፡፡

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አላባዲ እራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን በሞሱል ከተማ የሚገኘውን ጥንታዊ መስኪድ ማውደሙ በጦርነቱ ድል እንዳልቀናውና እየተሸነፈ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አይ ኤስ (IS) የኢራቅ መንግስት ኃይሎች የሚያደርጉትን ግስጋሴ ለማስቆም ውጊያ ባደረገበት ወቅት ነው አል ኑሪ የተሰኘውን ጥንታዊ መስኪድ እንዳወደመውም የተነገረው፡፡ አይ ኤስ (IS) በበኩሉ ጥንታዊ መስኪዱ የወደመው የአሜሪካ አየር ኃይል በሰነዘረው የአየር ጥቃት እንደሆነ ተናግሮዋል፡፡ ከስምንት መቶ አመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት ይህ ጥንታዊ መስኪድ ከአየር ላይ በተነሳ ፎቶግራፍ መሰረት በስፋት ወድሞዋል፡፡
በኢራቅ የአሜሪካን ኮማንደር ሜጀር ጀነራል ጆሴፍ ማርቲን እንዳሉት አይ ኤስ (IS) ያወደመው የኢራቅ እና ሞሱል ታላቁን ሐብት ነው፡፡ አክለውም ይህ ድርጊት በኢራቅ እና ሞሱል ህዝብ ላይ የተፈፀመ ወንጀል እንደሆነ ነው ተናግረዋል፡፡
ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በተጀመረው ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢራቅ ኃይሎች፣ የኩርዲሽ ተዋጊዎች፣ የሱኒ አረቦች እና የሺአ ሚሊሻዎች በአሜሪካ በሚመራው የአየር ላይ ጥቃትና ወታደራዊ ምክር እየታገዙ ቁልፍ ከተማዎችን በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ውጊያ ላይ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አይ ኤስ (IS) ቢያንስ አንድ መቶ ሺህ ሰዎችን በሞሱል በመያዝ እራሱን ለመከላከል እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
ዘገባው የ BBC ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒት እና ጤና እንክብካቤ ባለሥልጣን የህክምና አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ከሚመለከት ክፍል የሚመጡ የተለያዩ ጉዳዮችንና መረጃዎችን በማሰባሰብ እና ዶክተሮች ስራቸውን በሚከውኑበት ወቅት ሊያጋጥም የሚችል ስጋትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዶችተሮችና የህክምና ባለሙያዎች ኢንሹራንስ መክፈቱን ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንሽ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስተላለፈው የመጨረሻ ውሳኔ መሰረት በህክምና ወቅት ለተፈፀመ ስዕተት 4 ሚሊዮን ብር በካሳ መልክ ተጠይቆ ከ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ፍትሃ ብሄር ህግ በህክምና ወቅት ለሚደርስ ስዕተት የህክምና ተቋሙን እና ሠራተኞቹን ተጠያቂ በማድረግ ካሳ እንዲከፈል ያደርጋል፡፡ የተለያዩ አገራትም በህክምና ወቅት ለሚደርስ ስዕተት ካሳ እንዲከፈል እና አስፈላጊ ወጪዎችም እንዲሸፈኑ ያስገድዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሜዲካል አሶሴሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የኔነህ ጌታቸው እንዳሉት በኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንሽ የተጀመረው የኢንሹራንስ አይነት ለረጅም ግዜ ይጠብቁት የነበረ እና በሙያ ውስጥ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን የሚጠቅም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በእንግሊዝ ሜዲካል ኢንደሚኒቲ ኢንሹራንስ የሌላቸው የህክምና ባለሙያዎች የንግድ ፍቃድ አይሰጣቸውም፡፡

ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስት የብድር ስምምነት አዋጆችን መርምሮ ማጽደቁን ባልደረባችን ናርዶስ ዮሴፍ ዘግባለች።
ምክር ቤቱ በሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን በ42ኛ መደበኛ ጉባኤው ከቀረቡለት 15 የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች በብድር ስምምነት ላይ ያተኮሩ ስድስት ረቂቅ አዋጆችን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የስምምነት አዋጆቹ ለሁለተኛው የከተሞች የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን 236 ሚሊዮን 400 ሺህ ኤስ.ዲ.አር እና 125 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት አዋጅ ጸድቋል።
ኤስ ዲ አር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለአባል አገራት እንደ አማራጭ መገበያያ የፈጠረው የገንዘብ መለኪያ ሲሆን የአንድ ኤስ ዲ አር ዋጋ ምንዛሬ 1 ነጥብ 4 የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ነው።
ለንግድና ሎጂስቲክስ 110 ሚሊዮን 400 ሺህ ኤስ.ዲ.አር፣ ለጥራት ማረጋገጫ መሰረተ ልማት ማሻሻያ 37 ሚሊዮን 200 ሺህ ኤስ.ዲ.አር፣ ለጤና መሰረተ ልማት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ 110 ሚሊዮን 600 ሺህ ኤስ.ዲ.አር ከአለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ጸድቀዋል።
ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ድርጅት ጋር ለሴቶች ንግድ ስራ ፈጠራ ብቃት ማሻሻያ ማሳደጊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚሆን 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን የጃፓን የን የብድር ስምምነት አዋጅ ጸድቋል።
ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሆኑ የጤና ተቋማት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የጸደቀው የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት አዋጅ በኢትዮጵያና በኢጣልያ መንግስት መካከል የተደረገ ነው።
የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ገነት ታደሰ እንዳሉት፤ የብድር ስምምነት አዋጆቹ አገሪቱ የጀመረችውን ልማት ለማስቀጠል የሚያግዙ ናቸው።
ከስምምነቱ የሚገኘው ገንዘብ የብድር ጫናው ያልበዛና ከአገሪቱ የብድር ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም የባቡር ትራንስፖርት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝና የግብጽ አቻቸው " የሞት ሽረት " ተብሎ የሚጠበቀውን የአባይ ተፋሰስ አገራት ስብሰባ ለመሳተፍ ወደ ኡጋንዳ ኢንቴቤ አምርተዋል ፡፡ግብጽ በጉባኤው አዲስ አማራጭ ዶክመንት ይዛ እንደምትቀርብ ይጠበቃል ፡፡
ከሰባት አመታት ምልልስ በኋላ ስምምነት ላይ ያለመድረስ ፍጥጫ የነገው ስብሰባ በኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴ ቪኒ ካለፈው አንድ ወር በፊት በቀረበ ጉትጎታ የተሳካ ሲሆን በነዚህ ወራት ለ3 ጊዜ ያህል ቀኖቹ ተቀይረዋል ፡፡ቀነ ቀጠሮው የተቀየረውም ኢትዮጵያ ግብጽ እንደ አማራጭ ያመጣችውን የኢንቴቤውን ስምምነት ማሻሻያ የያዘ ዶክመንት ለማጥና በጠየቀችው መሰረት ነበር፡፡
የኢንቴቤው ስምምነት ላለፉት አመታት በወንዙ 11 ተፋሳሽ አገራት እንዲፈረም የተጠየቀ ሲሆን ብሩንዲ፤ ሩዋንዳ ፤ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ፤ ኡጋንዳ ፤ ኬኒያ ፤ ተንዛኒያ ሁለቱ ሱዳኖች ፤ ኤርትራ ፤ እና የነገው ዋነኛ ተዋናይ ተብለው የተጠበቁትና በመሪዎቻቸው የተመሬት ኢትዮጵያና ግብጽ ናቸው፡፡
ከሁለቱ አገራት መሪዎች ውጭ የነገው ስብሰባ ቡድን በምክትል ሚንስትሮችና የውሀ ሀብት ሚንስትሮቻቸው እንደሚመራም ታውቋል ፡፡
የኢንቴቤው ስምምነት ዛሬ ላይ ተለዋጭ ሀሳብ አለኝ ያለችው ግብጽ ፤ እንዲሁም ሱዳን ከጅምሩ ሙሉ በሙሉ ላለመቀበል ወስነው ለአመታት የተጓዙ መሆናቸው ይታወሳል ፡፡

በአሜሪካ ምእራባዊ ክፍል አሪዞና በተከሰተ ከባድ ሙቀት ምክንያት ፎኒክስ ስካይ ሀርበር የተባለ አየር መንገድ 40 በረራዎችን ሰርዟል፡፡
ከፍተኛ ሙቀት አየሩ እንዲወፍር እና አውሮፕላኖችን ለመነሳት እና ለማረፍ ከባድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል፡፡ የአውሮፕላኖችን የተለያዩ ክፍሎችንምያበላሻል፡፡
ዛሬ እና ነገ እስከ 48 ዲግሪ ሴሊሺየስ ድረስ ይደርሳል ተብሎ የተገመተው ሙቀት አየር መንገዱ በትላንትናው እለት ከ 6 ሰአት እስከ 9 ሰአት ባለው ጊዜ ሎስአንጀለስን ጨምሮ ወደ 4 የአሜሪካ ከተማዎችየሚያደርገውን በረራ ሰርዟል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሀገሪቱ ፓርላማ ለ2018 ባወጣው በጀት ላይ የሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ቀድሞ ከነበረው 8.2 ቢሊየን ዶላር ላይ 31 ፐርሰንቱን ሲቀንስ ከኤጀንሲው 15ሺህ ሰራተኞች 3500 ይባረራሉ፡፡
ኤጀንሲው ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለአካባቢ ጥናት እና ልማት ከሚውል 483 ሚሊየን ዶላር በግማሽ ተቀንሶበታል፡፡
የአሜሪካው ትራምፕ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትም ሀገራቸውን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አስወጥተዋል፡፡
በወቅቱ ፕሬዙዳንቱ ከነጩ ቤተመንግስታቸው የጽጌሬዳ የአትክልት ቦታ ሆነው አሜሪካንን እና ዜጎቿን ለመጠበቅ የገባሁትን የማይሻር ቃል ለመጠበቅ አሜሪካን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ አስወጥቼያታለሁ ብለው ነበር፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ እየተጎዳች ያለችው አሜሪካ ብቻ አይደለችም በሀዋይ ዩኒቨርስቲ ፕፌሰር የሆኑት ካሚሎ ሞር ለአርጀዚራ በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ የአለም 30 ፐርሰንት ህዝብ በየአመቱ ቢያንስ ለ20 ቀን ከአየር ንብረት ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች ተጋላጭ ነው ብለዋል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ችግሮቹን ለመፍታት ተግባራዊ እርምጃ ካልተወሰደም ችግሩ የአለም 50 ፐርሰንት ሰዎችን ወደ ማዳረስ ከፍ ይላል፡፡
በኢትዩጲያ ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ የተባለው የደን ተክሎች እና እጽዋት ጥናት ድርጅት ተሰርቶ በኔቸር ፕላንትስ የታተመ ጥናት በያዝነው ክፍለዘመን መጨረሻ ላይ ኢትዩጲያ መሬቷ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቡና ለማብቀል ተስማሚ እንደ ማይሆን አብራርቷል፡፡
ጥናቱ የሀገሪቱ ሙቀት በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን እና በተቃራኒው እያሽቆለቆለ መሆኑን ገልጾል፡፡
በአሜሪካ ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ዜጎቾን ሲያስተጓጉል እና ጥፋት ሲያደርስ የመጀመሪያው አይደለም፡፡
ከ5 አመታት በፊት በሀገሪቷ ቨርጂኒያን እና ኦሀዮን ጨምሮ በስተምስራቅ በሚገኙ ስድስት ክልሎች በነበረ ሀይለኛ ሙቀት 42 ሰዎች ሞተው ነበር፡፡

አልጀዚራ እና ቢቢሲን ዋቢ አድርገን ላጠናከርነው ዘገባ ናርዶስ ዩሴፍ፡፡

የኩዌቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር Sheikh Sabah Al-Ahmad Al-Jaber Al-Sabah የእስር ጊዜያቸውን ላላጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን ምህረት መደረጉን ተናግረዋል፤
ምህረትን ያደረጉትም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለያየ ወንጀሎች ተከሰው በእስር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምህረት እንዲያደርጉ ለኩዌት አሚር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፤
ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከአሚሩ ጋር በአህጉራዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ በጋራ መክረዋል በኳታርና ባህረ ሰላጤ ሀገሮች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታም ኢትዮጵያውያ ፅኑ ፍላጎት እንዳላትም ተወያይተዋል፤
ኩዌት በሁለትዮሽ ለመደራደር የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ኢትዮጵያውያ እንደምትደግፍ ጠቁመው ጥረቱም ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት አብራርተዋል፤
በኩዌት ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አሚሩ ለኢትዮጵያውያን ላደረጉት ምህረት በራሳቸውና በመንግስታቸው ስም አመስግነዋል፤
ኢትዮጵያውያ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ለምታደርገው ጥረት አድናቆታቸውን የገለፁት አሚሩ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር ኩዌት ፍላጎት እንዳላት አሚሩ አስታውቀዋል፤
ኩዌት በሳዳም ሁሴን አስተዳደር በተወረረችበት ወቅት የኢትዮጵያውያ መንግስትና ህዝብ ያደረጉትን ድጋፍ ያስታወሱት ሼህ ሳባህ ካሊድ ኢትዮጵያውያ ባለውለታችን ነች ብለዋል፡፡ ከኩዬት ተመላሾች ቁጥራቸው እንደማይታወቅና ምህረት የተደረገላቸው ተመላሾች ከኢትዮጵያ መንግስት እንደ ሳውዲ ተመላሾች ሁሉ ምንም ሊያደርግላቸው እንደማይችል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለምን በስልክ በጠየቅናቸው ወቅት ገልፀውልናል፡፡
ትብለፅ ተስፋዬ ዘግባዋለች

ከጠዋቱ 12፡52 ደቂቃ በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ ሰባት በተለምዶ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ አደጋ አምስት መቶ አርባ አንድ ሺ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፤
በቃጠሎው ስድስት ንግድ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎች፣የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች የተለያዩ እቃዎች መጋዘን የተቃጠሎ ሲሆን አደጋውን ለመቆጣጠር አራት የእሳት አደጋ ሰራተኞች እንዲሁም ሃያ አንድ ሺ ሊትር ውሀ ጥቅም ላይ ውሏል፤
በሰው ህይወት ላይም ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ሲሉ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ ተናግዋል፡፡
ዘገባው የፍሬህይወት ታደሰ ነው፡፡