Super User

Super User

Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሚያዚያ 11/2008 ዓ.ም

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ድረ-ገጽ እንዳስነበበው ሊቀመንበሯ ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በጋምቤላ ክልል ጃካዋ አካባቢ የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቀው ያወገዙ ሲሆን ኮሚሽኑ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን እንደሚቆምም አመልክተዋል።

ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ የተጠለፉ ህጻናትና ሴቶች እንዲለቀቁ ጽኑ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስታት በጋራ በመሆን ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ እንደሚኖርባቸውና ሕብረቱም ከዚህ ጥረት ጎን እንደሚሰለፍ ተናግረዋል።

ሚያዚያ 11/2008 ዓ.ም

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች ህይወታቸው ያለፈ ንፁሃን ዜጎችን ለማሰብ ከነገ ረቡዕ ጀምሮ የሁለት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን አውጇል፡፡

ምክር ቤቱ ከነገ ጀምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ፅ/ቤቶች ለሁለት ቀናት የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስኗል።

በተመሳሳይ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ የሆኑ መርከቦችም ከነገ ጀምሮ የኢፌዴሪ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ የሚያደርጉ ይሆናል።

ባሳለፍነው አርብ ምሽት በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች በደቡብ ሱዳን በኩል ድንበር ሰብሮ በመግባት በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው ከ208 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

እንዲሁም ቁጥራቸው 108 የሚደርስ ህጻናት በታጠቁት ሀይሎች ታፍነው ተወስደዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም ጥቃት ፈጻሚ ወንበዴዎችን ድንበር በመሻገር እርምጃ እየወሰደባቸው ሲሆን፥ ከ60 የሚበልጡ ጥቃት ፈጻሚዎች ተገድለው የጦር መሳሪያም ተይዟል።

በአሁኑ ጊዜም በታጣቂዎች ታፍነው የተያዙትን የማስለቀቁ ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ምንጭ - የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት

 

ሚያዚያ 06/2008 ዓ.ም

ጊዮርጊስ ከመከላከያ ባደረጉት ተስተካካይ ጨዋታ ላይ አምቡላንስና ቃሬዛ ባለመገኘቱ ጠብታ አምቡላንስ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

የጠብታ አምቡላንስ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አንስቴቲስት ክብረት አበበ “ለተፈጠረው ችግር በይፋ ይቅርታ እንጠይቃለን፤ ፌዴሬሽኑ ተገቢውን መረጃ ቢሰጠንም በጊዜው ለመገኘት ሳንችል ቀርተናል፡፡ መዘግየታችን ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርስ መቅረቱ ግን አስደስቶናል” ሲሉ ለሃገሬ ስፖርት ተናግረዋል፡፡

የስፖርት ቤተሰቡ ግን ከጠብታ አምቡላንስ ውጪ የውድድርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ እና የጨዋታው ኮሚሽነርን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

“የተሟላ መሳሪያ ሳይኖር ጨዋታው መጀመር አልነበረበትም፤ ኮሚሽነሩ እና የውድድሩ አዘጋጆች ተመሳሳይ ስህተት ከመስራት ሊታረሙ ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

መከላከያ እና ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ የጊዮርጊሱ አሉላ ግርማ በደረሰበት ጉዳት ወደ ሜዳ ገብቶ ድጋፍ የሚያደርግለት አምቡላንስ እና ቃሬዛ ባለመኖሩ በክለቡ ተጫዋቾች እርዳታ ከሜዳ እንዲወጣ መደረጉ ይታወቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

ሚያዚያ 03/2008 ዓ.ም

በየሁለት ሰከንድ ልዩነት ደም የሚፈልግ አንድ ሰው ያለ ሲሆን ከአገራችን ነባራዊ የህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አንድ ሚሊዮን ከረጢት ደም በአገራችን ይፈለጋል፡፡ ይሁን እንጂ 128ሺ ከረጢት ደም ብቻ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡

ይህም በተለያየ አደጋ፤ ከእርግዝና ጋር እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት የደም አቅርቦቱ ዝቅተኛ መሆኑን የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ዘለቀ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በየሶስት ወር ልዩነት ደም የሚለግሱ መደበኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ሊበረክት ይገባል፤ ይህም የደም አለጋገስ ሂደት የሰውን ህይወት ከማትረፍ ባሻገር ለጋሹን ጤነኛ የደም ባለቤት ያደርገዋል ተብሏል፡፡

የደም ለጋሾች ቁጥር አሁን ላይ ከ8 ሺ በታች በመሆኑ በአገራችን የደም ፈላጊው ቁጥርና አቅርቦት ላይ አለመመጣጠን በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን የገለፁት አቶ አብርሀም ዘለቀ፤ የህክምና እርዳታ የሚሰጡ ከ300 በላይ ተቋማትን ፍላጎት ማርካት ባለመቻሉ በደም እጥረት የሚሞተው ሰው ቁጥር ከፍ ብሏል ሲሉም ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ (ርብቃ ታያቸው)

መጋቢት 28/2008 ዓ.ም

ዓለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (ዋዳ) አምስት አገራትን አስጠንቅቋል፡፡

ኤጀንሲው ይፋ ባደረገው መረጃ ምርመራውን ሰፋ አድርገው እንዲጀምሩ፣ የየሀገራቸውን የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ እንዲያጠናክሩ እና ሌሎች ከልካይ ህጎችን እንዲያወጡ እስከ ህዳር 2009 ድረስ ቀነ ገደብ የሰጣቸው አምስት አገራት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሮኮ፣ ዩክሬን እና ቤላሩስ ናቸው፡፡

አምስቱም ሃገራት ይህን ካላደረጉ ከህዳር 2009 በኋላ እንደሚያግዳቸው ያስጠነቀቀው ዋዳ የታዘዙትን ተግባራዊ ያደርጋሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ተስፋውን ገልጧል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

መጋቢት 28/2008 ዓ.ም

የ6ቱ ኢንስትራክተሮች ጉዳይ ተቃውሞ እና ድጋፍ እያስተናገደ ባለበት በአሁኑ ወቅት የቴክኒክ ክፍሉ አባል የሆነው ዳንኤል ገ/ማርያም 7ኛው ኢንስትራክተር ሊሆን ከጫፍ ደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ልማት ክፍል የአሰልጣኞች ስልጠና ዴስክ ሃላፊ የሆነው አቶ ዳንኤል በካሜሩን ያውንዴ ለ5 ቀናት የተሰጠውን የኢንስትራክተርነት ስልጠና ወስዶ ተመልሷል፡፡

ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገሮች የመጡ 24 ባለሙያዎች ስልጠናውን የወሰዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡

6ቱ የካፍ ኢንስትራክተሮች አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ ዶ/ር ጌታቸው አበበ፣ አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ሃይማኖት እና አብርሃም መብራቱ፣ አቶ አንተነህ እሸቴ እና አቶ መኮንን ኩሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት) 

መጋቢት 28/2008 ዓ.ም

ዛሬ ላይ 1.8 ቢሊዮን ያህል ፎቶዎች በየቀኑ በፌስ ቡክ በትዊተርና በኢንስታግራም ገጾች ላይ ይለጠፋሉ፡፡ የእይታ ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ፌስ ቡክ ላይ የሚለጠፉ ምስሎችን ለማየት እድል ሳይኖራቸው ቆይቷል፡፡ በርግጥ ኮምፒዩተር ላይ በሚጫን ስክሪን ሪደር በሚባል ሶፍትዌር ጽሁፎችን ሲያነቡ ቢቆዩም ምስሎችን ለመረዳት ግን አልቻሉም ነበር፡፡ አሁን ደሞ ፌስ ቡክ አንድ መልካም የፈጠራ ውጤት ይዞ ብቅ ብሏል፡፡

ይህ የፈጠራ ውጤት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አማካኝነት ፌስቡክና ኢንስታግራም ላይ የሚለጠፉ ምስሎችን በማንበብ የእይታ ብርሃናቸውን ያጡ ተጠቃሚዎች እንዲረዱ ያስችላል ብሏል፡፡ አዲሱ ሶፍትዌር ከሰማኒያ በላይ የምስል ሁኔታዎችን ይተረጉማል፡፡

1- በትራንስፖርት ላይ የመኪና፣ የጀልባ፣ የአውሮፕላን፣ የብስክሌት፣ የባቡር፣ የደረቅ መንገድ፣ የሞተርሳይክል እና የአውቶብስ ምስሎችን በንባብ ያቀርባል፡፡

2- በአካባቢ ሁኔታ ላይ የተራራ፣ ዛፍ፣ በረዶ፣ ሰማይ፣ ውቅያኖስ፣ የውሃ፣ የባህር ዳርቻ፣ የማእበል፣ የጸሃይ እና የሳር ምስሎችን ያነባል

3- ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የቴኒስ፣ ዋና፣ ስታዲየም፣ ቅርጫት ኳስ ፣ቤዝቦል እና የጎልፍ ስፖርቶችን ምስል ይተረጉማል

4- ከምግብ ምስሎች ደግሞ አይስክሬም፣ ሱሺ፣ ፒዛ፣ ፍራፍሬዎች እና የቡና ምስሎች ይተረጎማሉ

5- ከአካላዊ መገለጫዎች ደግሞ የህጻናት፣ የጺም፣ የፈገግታ፣ የጌጣጌጥ አቀማመጥ እንዲሁም ራስን በራስ በማንሳት የተለጠፉ ምስሎችን እያነበበ ለተጠቃሚዎች ይናገራል ተብሏል፡፡

የዚህ ቴክኖሎጂ ፈጣሪ ለፌስ ቡክ ከሚሰሩ ኢንጅነሮች አንዱ የሆነውና የእይታ ብርሃኑን ያጣው ኢንጅነር ማት ኪንግ የተባለ ሰው መሆኑም ታውቋል፡፡ ይሄው ሰው ሲናገር "ፌስ ቡክ ላይ የሚለጠፉ ብዙዎቹ ጉዳዮች በምስል የተደገፉ ናቸው፤ የእይታ ብርሃኑን ያጣ ሰው ደግሞ ብዙ ጉዳዮች እያለፉት እንደሆነ ሊያስብ ይችላል" ሲል ተደምጧል፡፡ እኛም መልካም ዜና ብለን አቅርበንላችኋል፡፡ (source BBC)

መጋቢት 26/2008 ዓ.ም

ኢትዮጲያዊያን አትሌቶችን ለዶፒንግ ተጠቃሚነት የሚዳረጉ ናቸው የተባሉ ምክንያቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡ ስለ ዶፒንግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መረሀ ግብር ላይ ለመገናኛ ብዙሀኑ መረጃውን የሰጡት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የህክምና ማዕከል ሀላፊ ዶክተር አያሌው ጥላሁን “እናመልጣለን፤ ምንም አንሆንም ወይም አንያዝም” የሚሉ አትሌቶች በመኖራቸው እራሳቸውን ሊያርሙ ይገባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

በቂ እውቀት ሳይኖር ደፋር መሆናቸው፣ በወሬ ስለሚፈቱ፣ ስለማይጠራጠሩ፣ አጉል እምነት፣ ማማከር ነውር ስለሚመስላቸው እና ስለሚፈሩ እንዲሁም ነጭ አምላኪ መሆናቸው ለዶፒንግ ተጠቃሚነት አጋልጧቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የአትሌቶቹ ማህበር፣ ሚዲያው፣ የአሰልጣኞች ማህበር፣ አትሌቲክስ ፌደሬሽን፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር የቀድሞ ጀግኖች አትሌቶች የመፍትሄው አካል በመሆን የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉ ዶ/ር አያሌው ጠይቀዋል፡፡

ሰኔ 30/1999 በአዋጅ ቁጥር 554/1999 ህጉ ጻድቆ ዶፒንግ መውሰድ በወንጀል፣ በፍትሃ ብሄር እና በአስተዳደር ክስ የሚያስመሰርት መሆኑም ይታወቃል፡፡

(የሃገሬ ስፖርት)

መጋቢት 26/2008 ዓ.ም

ላብራቶሪዎቹን ለመጎብኘት የሀገራቱ መሪዎች መፍቀድ እንዳለባቸውም ተገልጧል፡፡

በብሄራዊ ሆቴል በተካሄደው የሚዲያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን እንደተናገሩት በየአመቱ ከ12-17 ሚሊየን ዩሮ በጀት የሚያዝላቸው ላብራቶሪዎች 24 የነበሩ ሲሆን የደቡብ አፍካው በመዘጋቱ አሁን 23 ብቻ ቀርተዋል፡፡

“የላብራቶሪዎቹ መሳሪያዎች በየአመቱ ይቀየራሉ፤ ቦታዎቹንም ሆነ ባለሞያዎቹን ሰው አያውቃቸውም” ያሉት ዶ/ር አያሌው ላብራቶሪዎቹን ለመጎብኘት የየሀገራቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ወይም ፕሬዝዳንቶች ፍቃድ የግድ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“የሲድኒ ኦሎምፒክ የሃይሌ ገ/ስላሴ የሽንት ናሙና አሁንም አለ፤ የሽንትና የደም ናሙናዎች ደግሞ እስከ 8 ዓመት ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ” ያሉት ዶ/ር አያሌው ጥላሁን “በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ተወስደው የተቀመጡ የሽንት ናሙናዎች እንደገና እንዲመረመሩ ተወስኗል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
(የሃገሬ ስፖርት)

መጋቢት 27/2008 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ቫይበርና ዋትስአፕ ያሉ የጥሪ አገልግሎት የሚሰጡ አፕሊኬሽኖች ላይ ተጨማሪ ክፍያ ሊጠይቅ ነው የሚለው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነና ይሄን ጉዳይ ይፋ ያደረገው ጋዜጣም ማስተባበያ እንዲሰጥ መጠየቁን የኢትዮ-ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡ (እንየው ቢሆነኝ)