ሦስት አክስዮን ማኅበራት ከኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ጋር እንዲዋሀዱ ውሳኔተሰጠ፡፡

ሦስት አክስዮን ማኅበራት ከኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ጋር እንዲዋሀዱ ውሳኔተሰጠ፡፡
አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማዘጋጃ አክሲዮን ማኅበር፣ አዋሽ መልካሳ አሉሚኒየም ሰልፌትና ሳልፈሪክ አሲድ አክሲዮን ማኅበር እና ኮስቲክ ሶዳ አክሲዮን ማኅበር ከኢትዮጵያ ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ጋር እንዲዋሀዱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
አክሲዮን ማኅበራቱና ኮርፖሬሽኑ እንዲዋሀዱ ያስፈለገው ተቋማቱ አሁን ባሉበት አቅም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ሊጫወቱ ስለማይችሉ የአመራር፣ የኢንቨስትመንት፣ የሰው ኃይል፣ የግብይት እና የአሠራር አቅማቸውን አቀናጅቶ በአጭሩ ጊዜ በማጎልበት የተጠናከረ የተወዳዳሪነት ቁመና እንዲይዙ ለማድረግ ነው፡፡
አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማዘጋጃ አክሲዮን ማኅበር በ2008 አ.ም የአሁኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቀድሞ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ከሚያስተዳድራቸውና ለሽያጭ አቅርቧቸው ከነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ባሳለፍነው አመት ከአዲስ አበባ በ165 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዝዋይ ከተማ ሀገሪቱ በአመት 5.2 ሚሊዩን ዶላር ታወጣበታለች የተባለውን 2.4. d የተባለ ጸረ አረም ኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካውን ገንብቶ ስራ ጀምሮ ነበር፡፡
በወቅቱ አክሲዩን ማህበሩን ማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹን ለመቀጠል የ5 አመት እቅድ መዘጋጀቱ እና በተጨማሪም ያሉትን የጸረ አረም ምርቶች ቁጥርም ከ 23 ወደ 37 ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
የጸረ-ተባይ ማዘጋጃ ማኅበሩ በ1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በ2000 ዓ.ም. በ40.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ እስከ 2008 አ.ም ድረስም 435 ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን፣ 343ቱ ቋሚ ናቸው፡፡
ማህበሩ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ለማዛወር ሁለት ጊዜ ጨረታ ወጥቶ በግዥ እጦት ሳይዛወር ቀርቷል፡
በአሁን በድርጅቶቹ እና በኮርፖሬሽኑ በተደረገው ውህደት በሚፈጠረው ኮርፓሬሽን አስተዳድራዊ ወጪ የመቀነስ ውጤት ሊኖረው የሚችል ሲሆን፣ በውህደቱ የተጣመሩ ተቋማት እንደየሥራ ባህሪያቸው የተመጣጠነ ውስጣዊ የአመራር ነጻነት ይኖራቸዋል፡፡ የተዋሀዱት ተቋማት ምርቶች ለግብርና፣ ለምግብ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለጤና፣ ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ለጨርቃ ጨርቅ እና ለሌሎች በርካታ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
የተጠቀሱት የኬሚካል ማምረቻ አክስዮን ማኅበራት ከኬሚካል ኮርፖሬሽን ጋር ሲዋሃዱ የኮርፓሬሽኑን ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 280/2005 ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የሦስቱ አክሲዮን ማኅበራት መብትና ግዴታዎች ወደ ኮርፓሬሽኑ ተዛውረው እንዲሻሻል ተደርገጓል፡፡
የኮርፓሬሽኑ የፈቀደ ካፒታልም ብር 21.7 ቢሊዮን የነበረው ወደ ብር 21ቢሊዩን 719 ሚሊዩን 751ሺህ 376 ብር እና የተከፈለ ካፒታል ብር 5.4 ቢሊዮን ብር 5ቢሊዩን 893ሚሊዩን 694ሺህ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.