በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተቋቋመው አዲስ የአቪየሽን ቡድን አየር መንገድ በ4 ጉዳዩች ላይ የኤርፖርቶች ድርጅት አስተዳደር ውሳኔውን በቅድሚያ ለአየር መንገዱ ማሳወቅ አለበት አለ፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተቋቋመው አዲስ የአቪየሽን ቡድን አየር መንገድ በ4 ጉዳዩች ላይ የኤርፖርቶች ድርጅት አስተዳደር ውሳኔውን በቅድሚያ ለአየር መንገዱ ማሳወቅ አለበት አለ፡፡
ለቀድሞው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በላከው የውስጥ ደብዳቤ ድርጅቱ በሰው ሀብት ልማት አስተዳደር፤ በጨረታ፤ በውል አፈጻጸም እና ህጋዊ ጉዳዩች ላይ አስተዳደሩ በቅድሚያ የአየር መንገዱን ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት የኤርፖርቶች ድርጅት ካለ አየር መንገዱ ፈቃድ ማንኛውንም ሰራተኛ እድገት መስጠት፤ ማዘዋወር እና ከደረጃ ዝቅ ማድረግ ወይም መሻር አይችልም፡፡
ጨረታ እና ገንዘብን በተመለከተ ሁሉም ከ150 ሺህ ብር በላይ የሆኑ ወጪዎች በቅድሚያ በአየር መንገዱ መጽደቅ ሲኖርበት ውሎችን እና በአሁን ወቅት ያለተጠናቀቁ ማናቸውንም ህጋዊ ጉዳዩች ለአየር መንገዱ በቅድሚያ እንዲያሳውቅ አዲስ የተመሰረተው የአቪዬሽን ቡድን ለድርጅቱ የላከው ደብዳቤ ይገልጻል፡፡
ሁለቱ የሀገሪቷ አንጋፋ ድርጅቶች የተዋሀዱት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማዋሀድ የቀረበውን ረቂቅ ደንብ ዓርብ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ካጸደቀ በኋላ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ቡድን ባሳለፍነው ወር በአዋጅ ሲቋቋም በሥሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን ያቀፈ ተደርጎ ነው፡፡ ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ ቦርድ የሚተዳደሩ ሲሆን፣ የጋራ መርሐ ግብር ይኖራቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ድርጅቶች የየራሳቸው መለያ ብራንድና የንግድ ምልክት ይዘው ይቀጥላሉ፡፡ ሽግግሩ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በወቅቱ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 86 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤትና 95 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት፡፡ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ብዛት ከ12,000 በላይ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በበኩሉ በርካታ የኤርፖርት ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ በ350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማስፋፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን በክልል በሰመራ፣ በሐዋሳ፣ በሽሬ፣ በባሌ ሮቤ፣ በደምቢዶሎና በነቀምቴ ከተሞች ኤርፖርቶች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ 23 ኤርፖርቶች ሲያስተዳድር፣ አራቱ ዓለም አቀፍ ናቸው፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.