የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ከማስታወቂያ ጀምሮ ባሉ ከአንድ ሺህ በላይ ጉዳዩች ላይ የሚያወጡትን አላስፈላጊ ወጪ እንዲያቆሙ አስጠነቀቀ፡፡

የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ከማስታወቂያ ጀምሮ ባሉ ከአንድ ሺህ በላይ ጉዳዩች ላይ የሚያወጡትን አላስፈላጊ ወጪ እንዲያቆሙ አስጠነቀቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለ2010 የበጀት አመት 320.8 ቢሊዩን ብር ለኢፌድሪ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አቅርቦ ያጸደቀ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ገንዘብ በማፍሰስ በማስታወቂያ መስሪያ ቤቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፤ አላስፈላጊ የሆነ በሚል ያስቀመጠውን ለስብሰባ የሚወጣ ከፍተኛ አበል ፤ ለተለያዩ ጉዳዩች የሚፈጸሙ የአበል ክፍያዎች እጅግ ከፍተኛ መሆን እና ነዳጅ አጠቃቀሞችንም የሚጨምር ከአንድ ሺህ በላይ ጉዳዩች የተካተቱበት ዝርዝር በማዘጋጀት ለሚኒስትር መስሪያ ቤቶቹ የገንዘብ አጠቃቀማቸውን ወጪ ቆጣቢ እንዲያደርጉ አሳስቦ አሰራጭቷል፡፡
ከእነዚህ መስሪያ ቤቶች መካከል የፌደራል የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለአመራር እና ድጋፍ አገልግሎት ፕሮግራም 6 ሚሊየን 107 ሺህ 172 ብር የተመደበለት ሲሆን ይህ ገንዘብ ለአበል እና ለስልጠና ወጪ የሚደረግ ነው፡፡
የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ለዛሚ እንደተናገሩት መስሪያቤቶቹ እንዲሰሩ የተሰጣቸውን ገንዘብ አላፈላጊ በሆነ ሁኔታ እያባከኑት እንደሆነ እና ከአትራፊ ድርጅት እኩል እራሳቸውን ማስተዋወቅም አላስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ከሆነ መስሪያ ቤቶቹ በሬድዩ እና በቴሌቪዥን የሚያሰራጯቸው ማስታወቂያዎች እና ስፖንሰር የሚያደርጓቸው ፕሮግራሞች በቀጥታ እነሱን የሚመለከቱ ሆነው አልተገኙም ውጤት ተኮርም አይደሉም፡፡
ውጤት ተኮር ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች መካከል የኢትዩጲያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስለ ግብር መክፈል የሚያስተላልፋቸው ዝግጅቶች ውጤት ተኮር የሆነ መስሪያ ቤቱ ገንዘብ አውጥቶ በሌላ መልኩ የሚያገኝበት ነገር ነው ሲሉ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬቱ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
በ2010 የበጀት አመት የኢትዩጲያ መንገዶች ባለስልጣን 50 ቢሊዩን ብር፤ በሁለተኛነት የትምህርት ሚኒስቴር እና በስሩ ያሉት ኤጀንሲዎች እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከ700 ሚሊዩን እስከ 1 ቢሊዩን ብር ድረስ ተመድቦላቸዋል፤ ግብርና እና መከላከያ እንዲሁም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ9 እስከ 12 ቢሊዩን ብር በሚደርስ በጀት ከፍተኛ ገንዘብ ከተመደበላቸው መካከል ናቸው፡፡
አቶ ሀጂ ታዲያ ሁሉንም መስሪያ ቤቶች ትልልቅ በጀት ከተመደበላቸው በተዋረድ እንደየጠቀሜታ ፈርጃቸው በጀት የጸደቀላቸውን መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸው ገንዘብ ለስራ እንጂ አላፈላጊ በሆነ መልኩ መስሪያቤቱን ለማስተዋወቅ እና ገንዘብ ለማውጣት አይደለም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.