የአሜሪካ ተምች 32 በመቶ የሚሆነውን የኢትዩጲያ የበቆሎ ማሳ በማጥቃቱ የሀገሪቷ የዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ አደረገ፡፡

የአሜሪካ ተምች 32 በመቶ የሚሆነውን የኢትዩጲያ የበቆሎ ማሳ በማጥቃቱ የሀገሪቷ የዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ አደረገ፡፡
ትላንት ባጠናቀቅነው የሀምሌ ወር የሀገሪቷ ወርሀዊ የዋጋ ግሽበት ወደ 9.4 በመቶ ማደጉን የማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የዋጋ ግሽበትን አጠቃላይ የሆነ የዋጋ መጨመር ወይም ደግሞ ብዙ ገንዘብ ትንሽ እቃ ሲፈልግ ማለት ነው ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡
ባለፉት 10 ወራት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት ወር ከነበረበት 5.6 በመቶ አሁን ወደ ሁለት አሀዝ እድገት እጅጉን ተጠግቷል፡፡
የዋጋ ግሽበት ባለሁለት አሀዝ እድገት ማሳየት ያለውን ትርጉም የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ አክሊል ውበት የወጋ ግሽበት እድገት ኢኮኖሚው ሲያድግ ሊፈጠር የሚችል ነገር ቢሆንም ከነጠላ አሀዝ እድገት በአንዴ ወደ ባለሁለት አሀዝ እድገት ከተሸጋገረ በኢኮኖሚው የፍላጎት እና የአቅርቦት አቅም ላይ ክፍተት መኖሩን እንደሚያመላክት ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
ግሽበቱ የተፈጠረው የእህል ዋጋ በተለይም የበቆሎ ዋጋ በመናሩ እንደሆነ ሲጠቀስ የምግብ ዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ከነበረበት 11.2 በመቶ ወደ 12.5 በመቶ አድጓል፡፡
በሀገሪቷ አብዛኛው ክፍሎች አዲስ አበባን ጨምሮ አንድ ኪሎ በቆሎ በ12 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በኪሎ በ7 እና 8 ብር ሲሸጥ የነበረው ምርት አሁን ዋጋው እንዲያሻቅብ ሀገሪቷ ለመሰብሰብ ያቀደችው 30 ሚሊዩን ኩንታል በቆሎ በተከሰተው የአሜሪካ ተምች ምክንያት በበቆሎ ከተሸፈነው 71ሺህ 508 ሄክታር 32.2 በመቶው መውደሙ ግሽበቱ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡
በሀገሪቱ የሰብል ምርት ማሽቆልቆል የጀመረው ከባለፈው አመት ጀምሮ ሲሆን በወቅቱ የተሰበሰበው ምርት ከዚያ ቀደም ከነበረው አመት ማለትም በ2007 ከነበረበት በ4.8 ሚሊዩን ኩንታል ዝቅ ብሏል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች፡፡

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.