810 ግራም የኮኬይን እፅ በሆዱ ዉስጥ ይዞ የተያዘዉ ተከሳሽ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ::

810 ግራም የኮኬይን እፅ በሆዱ ዉስጥ ይዞ የተያዘዉ ተከሳሽ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ::
ተከሳሽ ሚስተር መላቼይ አኩቹኩዉ በፈፀመዉ የተከለከሉ ዕጾችን ማዘዋወር ወንጀል በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ የልደታ የወንጀል እና የፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬከቶሬት ዐቃቢ ሕግ በመሰረተዉ ክስ በእስራት እና በገንዘብ መቀጮ መቀጣቱን አስታወቀ::
የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳዉ ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀጽ 525 /1/ለ ስር የተመለከተዉን በመተላለፍ ግንቦት 18 ቀን 2009 አመት ምህረት ከምሽቱ በግምት 3 ሰዓት ሲሆን ከብራዚል ሳኦወፖሎ ወደ ናይጀሪያ ሌጎስ ለመሄድ ቦሌ አየር መንገደ ለትራዚተ ባረፈበት ወቅት እንዳይመረት እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይዉል የታገደ የኮኬይን ዕፅ በሆዱ ዉጦ ለማለፍ ሲሞክር በተደረገ ፍተሻ ሀያ ዘጠኝ ፍሬ እጽ ከሆዱ ዉስጥ የወጣ ሲሆን በፌዴራል ፖሊሲ ኮሚሽን ለምርመራ ከሄደ በኃላ 15 ፍሬ ከሆዱ ወጥቷል ተከሳሽ አጠቃላይ 810 ግራም የኮኬይን እፅ በሆዱ ዉስጥ ይዞ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመዉ መርዛማ እፆችን ማዘዋወር ወንጀል ተከሷል።
ለተከሳሹ ክሱ ደርሶት እና በችሎት ተነቦለት በአስተርጋሚ እየታገዘ እንዲረዳዉ ከተደረገ በኃላ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ የተጠየቀዉ ተከሳሽ ያለምንም መቃወሚያ ድርጊቱን ፈፅሜለሁ ጥፋተኛ ነኝ ብሏል::
የፌዴራል ዐቃቢ ሕግ ለጉዳዩ ያስረዱልኛል ያላቸዉን የሰነድ ማስረጃ ካቀረበ በኋላ ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜለሁ በማለቱ ሌላ ማስረጃ መሰማት ሳያስፈልግ የጥፋተኝነት ዉሳኔ እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን በመመልከት ተከሳሹን በተከሰሰበት ክስ ጥፋተኛ ነህ ብሎታል::
የቅጣት አስተያያት የተጠየቀዉ የፌዴራል ዐቃቢ ህግም የወንጀሉ አፈፃፀምና ይዞ የተገኘዉን የኮኬን ዕፅ መጠኑ ሲታይ ደረጃዉ መካከለኛ ተይዞ ተከሳሹን ሊያስተምር ሌሎችንም ሊያስጠነቅቅ የሚችል ቅጣት እንዲወሰን በማለት ሲያመለክት ተከሳሽ በበኩሉ በተከላካይ ጠበቃዉ አማካኝነት የወንጀል ድርጊቱን ማመኑ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን በመጥቀስ በማቅለያነት እንዲያዝለት በማለት አመልክተዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ ደረጃዉ በመካከለኛ በማለት መነሻ ቅጣት 10 አመት በመያዝ ግንቦት 14 ቀን 2009 አመት ምህረት በዋለዉ ችሎት በ7 አመት ጽኑ እስራትና በ7000 ብር የገንዘብ መቀጮ አንዲቀጣ ሲል ወስኗል::
የመረጃ ምንጭ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነዉ።

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.