የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የአሜሪካ መጤ ተምችን የሚያጠፋ ፀረ ተምች መድሀኒት ማግኘታቸዉን ይፋ አድርገዋል።

በአሁኑ ሰአት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘዉን የአሜሪካ መጤ ተምች ለማጥፋት በዘርፉ ተመራማሪዎች የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ባለበት ወቅት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የአሜሪካ መጤ ተምችን የሚያጠፋ ፀረ ተምች መድሀኒት ማግኘታቸዉን ይፋ አድርገዋል።
ተመራማሪዎቹ ይህ መጤ ተምች ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ምርምር መጀመራቸዉን እና ያገኙትን ጸረ ተምች መድሀኒት በወላይታ ዞን በሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ሙከራ አድርገዉ ጥሩ ዉጤት መገኘቱን በዩኒቨርስቲዉ የምርምር እና ማህበረሰብ ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ኩማ ለዛሚ ተናግረዋል።
በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያገኙትን የጸረ ተምች መድሀኒት የባለቤትነት ማረጋገጫ እስካላገኙ ድረስ ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንደማያዉሉት እየተናገሩ እንደሆነ የሚገልጹ መልእክቶች እየተጻፉ ስለመሆኑ ከዛሚ ለተነሳላቸዉ ጥያቄም
ዶክትር ብርሀኑ መድሀኒቱ ስለተቀመመባቸዉ እጽዋቶች እንዲሁም ስለ ሂደቱ ለመናገር ተመራማሪዎቹ የፈጠራ ባለመብት መሆናቸዉ እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉ መናገራቸዉን እና ለዚህም እንቅስቃሴ መጀመራቸዉን ገልጸዉ
ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት ጋር በመነጋገርም የባለቤትነት ማረጋገጫ ምዝገባዉን ካደረጉበት እለት ጀምሮ ስራቸዉን መቀጠል እንደሚችሉ ስምምነት ላይ መደረሱን ነግረዉናል።
የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ በበኩላቸዉ ምንም እንኳን የፈጠራ ባለመብትነት ሂደቱ ግዜ የሚወስድ ቢሆንም ከጉዳዩ አሳሳቢነት እና ሀገራዊ ፋይዳ አንጻር በልዩ ሁኔታ ታይቶ የምርመራዉ ጊዜ እንዲያጥር ሊደረግ እንደሚችል ለዛሚ ተናግረዋል።
ተመራማሪዎቹ ሀምሌ 24 ቀን ወደ ኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት በማምራት የባለቤትነት ማረጋገጫ ጥያቄያቸዉን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
እጹብድንቅ ሀይሉ

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.