በየአውራ መንገዱ ተሰምሮ የነበረው እና ከጊዜያት በኋላ የት እንደገባ ያለታወቀው ቢጫ ሳጥን ህግ ወቶለት ዳግም ስራ ሊጀምር ነው፡፡

በየአውራ መንገዱ ተሰምሮ የነበረው እና ከጊዜያት በኋላ የት እንደገባ ያለታወቀው ቢጫ ሳጥን ህግ ወቶለት ዳግም ስራ ሊጀምር ነው፡፡
ቢጫ ሳጥን ወይም የሎው ቦክስ በተለይ የትራፊክ ፍሰቱ ከፍተኛ በሆነባቸው የመስቀለኛ መንገዶች ላይ የመስቀለኛ መንገዶቹን የክልል ቅርፅ እንደ አስፈላጊነቱ የያዘና በየመንገዱ ላይ በግልፅ ሁኔታ ተቀብቶ የትራፊክ ፍሰቱን በቅደም ተከተል ለማስተናገድ የሚረዳ የቢጫ ቀለም ቅብ ማለት ነው፡፡
ከነዚህ ቦታዎች በተጨማሪ በሆስፒታሎች ውስጥ የድንገተኛ እርዳታ ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ለሚሄዱ ተሸከርካሪዎች ሌሎች ተሸከርካሪዎች ቆመው መተላለፊያውን እንዳያውኩ የቢጫ ሳጥንን በመጠቀም አከባቢውን ለተረጂዎች ግልፅ ማድረግ የሚያስችል የትራፊክ መብራት አጋዥ አሰራር ነው፡፡
በወቅቱ ስራ ላይ የነበረው የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በቢሮው የትራንስፖርት ዘርፍ የካቲት 26/2006ዓ.ም ይፋ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ቦታዎች ላይ ተግባራዊ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው መንገዶች ላይ የተቀቡት ቢጫ ሳጥኖች አገልግሎታቸው ሳይታወቅ ተሰውረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የመንገድ ደህንነትና አቅም ግንባታ ዋና የስራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ ሀገሬ ሀይሉ ቀድሞ የትራፊክ ደንብ ላይ ህግ ስላልወጣለት እንዲቋረጥ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለአገልግሎቱ መቋረጥ ቀድሞ በትራፊክ ህግ ውስጥ መግባት ባለመቻሉ ነው የሚሉት ሀላፊው ጠቀሜታው ታምኖበት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ ህጉ ለምን አስቀድሞ አልታሰበበትም ለሚለው ጥያቄ አቶ ሀገሬ ሀይሉ በምላሻቸው ለሙከራ የተጀመረ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ዳግም ይህንን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ አጥፊዎችን መቅጣት የሚያስችል ደንብ ቁጥር 395/2009 ማሻሻያ ተደርጎበት እንደወጣ ሀላፊው ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ከዚህ በፊት ለአንዱ የከተማችን አደባባይ ብቻ 80 ሺህ ብር ወቶበታል የተባለው የቢጫ ሳጥን አገልግሎት መች እንደሚጀመር ሀላፊው በውል እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡
ወደፊት ይተገበራል በተባለው የቢጫ ሳጥን መስቀለኛ መገጣጠሚያ ላይ ሲደርሱ አሽከርካሪዎች የቢጫ ሳጥን ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ወደሚሄዱበት አቅጣጫ ያለው መንገድ በበቂ መልኩ ለጉዞአቸው ክፍት መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይገባቸዋል፡፡በቢጫ ሳጥን ውስጥ ገብቶ መቆም የትራፊክ ፍሰቱን ከማስተጓጎሉም በላይ ህጉ ተግባራዊ ሲደርግ የደንብ መተላለፍ ቅጣትን ያስከትላል፡፡እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አከባቢ የቢጫ ሳጥን አሰራር እንግሊዝ፣ አየር ላንድ፣ካናዳ፣አውስትራሊያ፣ሰሜን አሜሪካ፣ሆንግ ኮንግ ብራዚል እና ራሺያ ረዘም ላለ ጊዜ በህግ ደረጃ ተቀብለው ከተገበሩት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው::

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.