በሜቴክ የሚገነባው ጣና በለስ ቁጥር ሁለት አፈፃፀሙ ከ25 በመቶ በታች በመሆኑ ውል ለማቋረጥ ከጫፍ መደረሱ ተነግሯል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የልማት ድርጅቶቹን የ2009 ዓ.ም የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የስኳር ፕሮጀክቶቹ በመርሃ ግብሩ መሰረት ካልተጠናቀቁ የሚመለከታቸው አካላት ከተጠያቂነት አይድኑም ማለቱን ተከትሎ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ በከፊል የስኳር ምርት ማምረት መጀመሩ ተነግሯል፡፡ ፋብሪካው ምርቱን መጀመሩ ለምክር ቤቱ ማሳሰቢያ ምሳሽ ለመስጠት የታሰበ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ የስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጋሻው አይችሉም እውነት ነው ሲሉ ምላሽ ሰተዋል፡፤
የአዋጭነት ጥናት አንስቶ ዝርዝር ዲዛይንን ጨምሮ የግንባታ ምርትና አቅርቦት፣ የሲቪል ስራዎች እንዲሁም የኢሬክሽን አና የዝርጋታ ስራዎች በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ተሰርተዋል የሚሉት የብረታብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ ናቸው እንደ ጀነራሉ ገለፃ ከሆነ የሙከራ ስራውን የጀመረው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ በቀን 12 ሺ ቶን አገዳ መፍጨት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ባሻገር የጣና በለስ ቁጥር አንድና ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ለሜቴክ የተሰጡ መሆናቸውም የሚታወስ ነው፡፡የጣና በለስ ቁጥር ሁለት ፕሮጀክት አፈጻጻም 25 በመቶ ብቻ በመሆኑ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የተደረገው ውል እንዲቋረጥ እርምጃ መውሰድ ጀምረናል ሲሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት የጣና በለስ ቁጥር አንድ ፕሮጀክት ግንባታን አጠናቆ ወደ ሙከራ ስራ መግባት የነበረበት ቢሆንም እስካሁን ያለውን አፈፃፀም በመቶኛ የሚያስቀምጥበት ጊዜ ላይ አለመድረሱን በተናገሩበት በዚህ ወቅት ነው የኩራዝ ፋብሪካ ወደ ምርት የገባው
የፋብሪካው ግንባታ በሚያዝያ ወር ተጠናቆ የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት የስኳር ምርት ስራ መጀመር እንደነበረበት ነው ሚኒስቴሩ ባሳለፍነው ሳምንት ያመለከቱት።
ይህ በእንዲህ እያለ የስኳር ኮርፖሮሽን የኮርፖሬት ስራ አስፈፃሚው አቶ ጋሻው አይችሉም የኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ስራ መጀመር ስኬት ነው ሲሉ ተናገረዋል፡፡
ከ3 ዓመታት በፊት ስራ ይጀምራል የተባለው ፕሮጀክቱ ዛረም ድረስ ወደ መደበኛ የማምረት ስራ መግባት አልቻለም፡፡ ፋብሪካው በ 3 ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ምርት ማምርት እንደሚጀምር ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ ተናግረዋል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ በ235 ሚሊዩን ዶላር እንደተገነባ ከሜቴክ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ የጣና በለስ ቁጥር አንድና ሁለት፣ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ሙሉ በሙሉ ፕሮጀክቶችን በተከለሰው መርሃ ግብር መሰረት በ2010 ዓ.ም ለማጠናቀቅ መታቀዱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መነገሩ ሲታወስ ለፋብሪካዎቹ የተተከሉት አገዳዎች እየደረሱ በመሆናቸው የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በፍጥነት እንዲካሔድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ክትትል ማድረግ አለበት በአፅንኦት የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡

ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው፡፡

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.