የንግድ ሚንስቴር ከኤክስፖርት ዘርፍ 4.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ቢጠብቅም ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰብ አልቻለም፡፡

የንግድ ሚንስቴር ከኤክስፖርት ዘርፍ 4.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ቢጠብቅም ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰብ አልቻለም፡፡
የውጪ ምንዛሬን በከፍተኛ ደረጃ ያስገኛል የተባለው የኤክስፖርት ዕቅድ ግቡን መምታት አለመቻሉን ነው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት የሚያመላክተው፡፡ከሁሉም ዘርፎች ለውጪ ገበያ በማቅረብ 4.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት የታሰበ ቢሆንም የእቅዱ 59 ከመቶ 2.53 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ እንደተገኘ ተነግሯል፡፡ ከገቢ ድርሻ አንፃር 77.5 በመቶ ከግብርና ምርቶች፣14.3 በመቶ ከኢንዱስትሪ ውጤቶች፣7.1 በመቶ ከማዕድን ቀሪው 1.1 በመቶ የሌሎች ዘርፎች እንደሆነ መረጃው ያመላክታል፡፡ የሀገሪቱን የቀጣይ የኢኮኖሚ ሸክም ይሸከማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የኢንዱስትሪው ውጤቶች በአገልግሎት ካረጀው ግብርና ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ በታች ውጤት አስመዝግቧል፡፡
የግብርና ምርቶችን በተመለከተ በዓለም ገበያ ላይ ያለው የግብርና ምርቶች ዋጋ መቀዛቀዝና ተወዳዳሪ መሆን አለመቻል ለጉድለቱ ቀዳሚ ምክንያት ተብሎ በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ተቀምጧል፡፡የግብርና ምርቶችን አቅርቦት በጥራትና በመጠን ያለማሳደግ፣በአምራች ኢንዱስትሪው የግብአት አቅርቦትና የጥራት ችግር መኖር ተከታይ ችግሮች ተብለው ተለይተው ተነግረዋል፡፡በዚህ ችግር ብቻ ያልተገታው ኤክስፖርቱ የሀገር ውስጥ ዋጋ ሳቢ በመሆኑ ፋብሪካዎች ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መምረጣቸው፣በአንዳንድ ክልሎች የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት እና የግብይት ስርዓቱ ውስጥ የሚሰተዋሉ ክፍተቶች ተደማምረው ለሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ እንዳይገባ አድርገዋል ሲል የንግድ ሚንስቴር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ11 ወራት ሪፖርቱን ሲያስደምጥ አብራርቷል፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው፡፡

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.