በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ አደጋ አራት ተማሪዎች በጭስ የመታፈን አደጋ ሲደርስባቸው፤ አንድ መቶ ሺ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ ተሰማ፡፡

ግንቦት 29/2008 ዓ.ም

እሁድ ምሽት 2፡30 ሰዓት በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪዎች የመኝታ ፍራሽ ማከማቻ በሆነ ክፍል ውስጥ የተነሳው እሳት አራት ተማሪዎች በጭስ እንዲታፈኑ ያደረገ ሲሆን አንድ መቶ ሺ ብር የሚገመት የንብረት ውድመትም አስከትሏል ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡

አደጋ የደረሰባቸው ሁለት ተማሪዎች በሚኒሊክ ሆስፒታል ሁለቱ ደግሞ በየካ ጤና ጣቢያ የህክምና እርዳታን እያገኙ እንደሆነ የተናገሩት ሀላፊው የእሳቱ ትክክለኛ መንስኤም በፖሊስ እየተጣራ እንደሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡

እሳቱን ለማጥፋት 12 ሺ ሊትር ውሀ፣ 14 ባለሙያዎች እና 2 አምቡላንስ እንዲሁም ሁለት የአደጋ መከላከያ መኪናዎች ተሰማርተው እንደነበርም ተገልጧል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.