አገር አቀፍ ዜናዎች

ኢትዮጲያ የአየር ንብረት ለውጥን ለማቋቋምና ለአረንጎዴ ኢኮኖሚ ልማት የሚውል የአንድ ነጥብ ሰባ አራት ቢሊዮን ብር ድጋፍ ከኖርዌይ ተደርጎላታል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ደን በተራቆተባቸው አከባቢዎች ደን በማልማት የተለያዩ የብዙሃን ህይወት አካላትንና ውሃን ከጥፋት ለመታደግ እንደሚሰራ ተገልጸዋል፡፡በተገኘው ድጋፍ ስድስት መቶ ስልሳ ሺህ ሄክታር መሬት በደን በመሸፈን በደቡብ ክልል ፣በጋንቤላ ፣ኦሮሚያ ክልሎች እስከ 2020 የካርቦንዳኦክሳይድ ልቀትን ለመቀነስ እንድሁም በአማራ እና በትግራይ ክልል ማህበረሰቡን በማሳተፍ 800 ሺህ ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን ታቅዶል፡፡
የሙቀት መጨመር፣ ድርቅ፣ ከባድ ጎርፍ፣ የዝናብ መጠን መቀነስና የወቅት መዛባት የአየር ንብረት ለውጡ ዓበይት ክስተቶች ናቸው፡፡ የበርሃማነት መስፋፋትም እንዲሁም ለግብርና ምርት መቀነስ ብሎም ፍሬ አልባነት መንስኤ እየሆነ ይገኛል፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ ዋና መንስኤነት የሚጠቀሰው ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው በካይ ጋዝ የደን መመናመን እንደሚያስከተል በተደጋጋሚ የዘርፉ ምሁራን እየገለጹ ይገኛሉ ።
በተለይ እንደ ኢትዮጲያ በግብርና ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት የአየር ንብረት መዛባት ለግብርና ምርታማነት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፤ ምክንያቱም ትልቅ ተፅእኖ እያሳደረ ያለው በግብርና ምርታማነት ላይ ነው፡፡ በዚህም አመት ከወጡ ጥናቶች መካከል በታኒክ ጋርደን የተባለ መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው የጥናት ድርጅት በኢትዮጲያ መንግስት ድጋፍ ባደረገው ጥናት የኢትዮጲያ አረቢካ ቡና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወደ ከፍተኛ አከባቢዎች ተወስዶ ማብቀል ካልተጀመረ በ2090 አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ተረጋግጧል፡፡ ለእዚህም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች የአየር ንብረት ለውጡን ለመቋቋምና ለመከላከል የሚያስችል የአረጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ገንዘብ፣ የሰው ኃይልና የአረንጓዴ ልማት ቴክኖሎጂዎች ይጠይቃል፡፡ከዚህ ቀደም ይህንን ችግር ለመፍታት እና የተስተካከለ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲመጣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ለመደገፍ ኖርዌይ፣ሲዊድን፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ ተስማምተው ነበር ፡፡በስምምነቱ መሰረት ኖርዌይ የአንድ ነጥብ ሰባ አራት ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ዘገባው የፍሬህይወት ታደሰ ነው

ኢ ዲ ኤች ኤስ በተባለ አለም አቀፍ የህብረተሰብ እና የጤና ጉዳዩች ጥናት አድራጊ ድርጅት በኢትዩጲያ ስለ ህዝቡ አኗኗር እና ቤቶቻቸው ባደረገው ጥናት ካሳወቃቸው ግኝቶች መካከል ከ4 ቤቶች አንዱ በእማ ወራ እንደሚመራ አመላክቷል፡፡
ጥናቱ በእያንዳንዱ ቤት በአማካይ 4.6 ሰዎች ይኖራሉም ብሏል፡፡ በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ላይ ባደረገው ጥናትም ከኢትዩጲያ ህዝብ 47 በመቶው ከ15 አመት በታች መሆኑን አሳይቷል፡፤
በቤቶች አቅራቢያ የሚገኝ የመጠጥ ውሀ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦትም በከተማ 65 በመቶው ህብረተሰብ በገጠር ደግሞ 57 በመቶው ተጠቃሚ ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ በኢትዩጲያ ያለው የጤና አጠባበቅ 6 በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡
16 በመቶ የሚሆኑት የከተማ ነዋሪዎች የጋራ መጸዳጃ አገልግሎቶችን ሲጠቀሙ ከገጠር ነዋሪዎች ግን 4 በመቶው ብቻ የጋራ መጸዳጃዎች ይጠቀማሉ፡፡ በሀገሪቱም 94 በመቶ የሚሆኑት ቤቶች ዘመናዊ የመጸዳጃ ቤቶች እንደሌሏቸው ተጠቅሷል 9 በመቶ የሚሆኑት ሰዎችም የጋራ መጸዳጃዎችን እንደሚጠቀሙ ተገልጾል፡፡
ከኢትዩጲያ ህዝብ ያልተስተካከሉ የጋራ መጸዳጃ ቤቶች ተጠቃሚዎች 53 በመቶ ሲሆኑ 32 በመቶው ምንም አይነት መጸዳጃ ቤቶች የሏቸውም፡፡
የኤሌክትሪክ ሀይልን በተመለከተ 26 በመቶ የሀገሪቷ ቤቶች አቅርቦቱ ሲደረግላቸው ከዚህ ውስጥ 93 በመቶው አገልግሎት ለከተማዎች የሚቀርብ ነው፡፡ ከገጠሩ ክፍል 8 በመቶው ብቻ የመብራ ሀይል ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
የእቃዎች ባለቤትነትን በተመለከተ 56 በመቶው የሚሆነው የኢትዩጲያ ህዝብ የተንቀሳቃሽ ስልክ፤ 28 በመቶው የሬድዩ እና 14 በመቶ የሚሆነው የቴሌቪዥን ባለቤት ነው፡፡
የኢትዩጲያ መንግስትን ጨምሮ በዩ ኤስ ኤይድ፤ በዩኒ ሴፍ፤ በዩ ኤን ለሴቶች እና በሌሎች አምስት ዋና ዋና አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጥናቶችን እንዲያደርግ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ኢ ዲ ኤች ኤስ ይህንን ጥናት ለማካሄድ በ9 ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በ16ሺህ 650 ቤቶች የሚኖሩ እድሜያቸው ከ15- 49 የሆኑ 15 ሺህ 683 ሴቶችን፤12ሺህ 688 እድሜያቸው ከ15- 59 የሚገኙ ወንዶችን ከተመረጡ የሀገሪቷ ክፍሎች የቤት ባለቤቶች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡
ይህ ጥናትም 95 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችን እና 86 በመቶ የሚሆኑ ወንዶችን ምላሽ ያጠናከረ ነው፡፡

ያልፋል አሻግር ዘግቦታል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅ/ቤት በ2009 ባዘጋጀው የህዳሴ ቶምቦላ አገኛለው ካለው ገቢ 40 ሚሊየን ብር ቀነሰበት
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅ/ቤት አንድ ቶምቦላ ቲኬት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚል መሪ ቃል በ2009 በጀት አመት ባዘጋጀው የቶምቦላ ሽልማት አንድ መቶ ሚሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አስቦ አርባ ሚሊየን ብር በማጣት ስልሳ ሚሊየን ብር የተጣራ ገቢ ማሰባሰብ ችሏል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ክብርት ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር በዕቅድ ልክ ገቢው ያልተሰበሰበው በአገሪቱ ያሉት የብሄራዊ ሎተሪ መሸጫ ቢሮዎች አነስተኛ በመሆናቸውና ሎተሪው በሚሸጥበት ወቅት ሌሎች ተደራራቢ ሎተሪዎች መኖራቸው ያሰብንውን ያህል እንዳንሸጥ አድርጎናል ብለዋል፡፡
ፅ/ቤቱ በቀጣይ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያሰበ ሲሆን እስካሁን በቦንድ ግዢው ተሳትፎአቸው አነስተኛ የነበሩትን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አሳትፋለው ከፍተኛ ገቢ አገኝበታለውያልኩትን የዲያስፖራ ሎተሪ ለመጀመር መሬት ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አግኝቼ ለሽልማት የሚሆን ቪላ ቤት ይቀረኛል ብሏል፡፡
የግድቡ ግንባታ 60 ፐርሰንት ላይ የደረሰ ሲሆን እስካሁን ለግድቡ ግንባታ ከህዝቡ ከ10.1 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡
ምትኬ ቶሌራ

የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በስሩ ለሚገኙ ሶስት ድርጅቶች ካፒታል ማስተካከያ ተደረገ፡፡

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሥር የሚገኙ የኢትዮጵያ ማዕድን፣ነዳጅና ባዬፊዩል ኮርፖሬሽን ፣ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ፣የአሰላ ብቅል ፋብሪካ እና የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ካፒታል መጠንን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተጠቀሱትን የልማት ድርጅቶች ካፒታል ፈትሾ እንዲስተካከል የውሳኔ ሀሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ነሐሴ 5 ቀን 2ዐዐ9ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የውሳኔ ሀሳቡን ተቀብሎ አጽድቋል፡፡

በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዩፊዬል ኮርፖሬሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 367/2ዐዐ8 ሲቋቋም የተፈቀደ ካፒታሉ ብር 15.26 ቢሊዬን እና የተከፊለ ካፒታሉ ብር 4 ቢሊዬን መሆኑ የተጠቀሰ ቢሆንም ኮርፖሬሽኑ ወደ ሥራ ሲገባ በተጨባጭ የተከፈለው ካፒታል ብር 419.6 ሚሊዮን ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል ፡፡
ስለሆነም የዚሁ የተከፈለ ካፒታልን መነሻ በማድረግ በአዋጅ ቁጥር 25/84 አንቀጽ 2ዐ (1) መሠረት የተፈቀደ ካፒታሉ ወደ ብር 1ቢሊዩን 678ሚሊዩን 64ዐሺህ ዝቅ እንዲል ተደርጎ ተስተካክሏል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በሚኒስትሮች ቤት ደንብ ቁጥር 22/1985 ሲቋቋም የተከፈለ ካፒታሉ ብር 8.39 ሚሊየን ብር የነበረ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት ቆይቷል፡፡
አሁን የድርጅቱ የተከፈለ ካፒታል ወደ ብር 382ሚሊዩን 177ሺህ እና የተፈቀደ ካፒታሉ ደግሞ ወደ ብር 1ቢሊዩን 528ሚሊዩን 700 ሺኅ ብር እንዲያድግ ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ከሃያ ዓመት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 74/1985 እንደገና ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የተከፈለ ካፒታል ብር ወደ ብር 220ቢሊዩን 985ሚሊዩን 434ሺህ 93 እንዲያድግ በሚኒስቴሩ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
እነዚህ የካፒታል ማሻሻያዎች የልማት ድርጅቶቹ ማቋቋሚያ ደንቦች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እንዲወጡና ተግባራዊ እንዲደረጉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑ ታውቋል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ

ሦስት አክስዮን ማኅበራት ከኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ጋር እንዲዋሀዱ ውሳኔተሰጠ፡፡
አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማዘጋጃ አክሲዮን ማኅበር፣ አዋሽ መልካሳ አሉሚኒየም ሰልፌትና ሳልፈሪክ አሲድ አክሲዮን ማኅበር እና ኮስቲክ ሶዳ አክሲዮን ማኅበር ከኢትዮጵያ ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ጋር እንዲዋሀዱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
አክሲዮን ማኅበራቱና ኮርፖሬሽኑ እንዲዋሀዱ ያስፈለገው ተቋማቱ አሁን ባሉበት አቅም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ሊጫወቱ ስለማይችሉ የአመራር፣ የኢንቨስትመንት፣ የሰው ኃይል፣ የግብይት እና የአሠራር አቅማቸውን አቀናጅቶ በአጭሩ ጊዜ በማጎልበት የተጠናከረ የተወዳዳሪነት ቁመና እንዲይዙ ለማድረግ ነው፡፡
አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማዘጋጃ አክሲዮን ማኅበር በ2008 አ.ም የአሁኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቀድሞ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ከሚያስተዳድራቸውና ለሽያጭ አቅርቧቸው ከነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ባሳለፍነው አመት ከአዲስ አበባ በ165 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዝዋይ ከተማ ሀገሪቱ በአመት 5.2 ሚሊዩን ዶላር ታወጣበታለች የተባለውን 2.4. d የተባለ ጸረ አረም ኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካውን ገንብቶ ስራ ጀምሮ ነበር፡፡
በወቅቱ አክሲዩን ማህበሩን ማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹን ለመቀጠል የ5 አመት እቅድ መዘጋጀቱ እና በተጨማሪም ያሉትን የጸረ አረም ምርቶች ቁጥርም ከ 23 ወደ 37 ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
የጸረ-ተባይ ማዘጋጃ ማኅበሩ በ1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በ2000 ዓ.ም. በ40.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ እስከ 2008 አ.ም ድረስም 435 ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን፣ 343ቱ ቋሚ ናቸው፡፡
ማህበሩ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ለማዛወር ሁለት ጊዜ ጨረታ ወጥቶ በግዥ እጦት ሳይዛወር ቀርቷል፡
በአሁን በድርጅቶቹ እና በኮርፖሬሽኑ በተደረገው ውህደት በሚፈጠረው ኮርፓሬሽን አስተዳድራዊ ወጪ የመቀነስ ውጤት ሊኖረው የሚችል ሲሆን፣ በውህደቱ የተጣመሩ ተቋማት እንደየሥራ ባህሪያቸው የተመጣጠነ ውስጣዊ የአመራር ነጻነት ይኖራቸዋል፡፡ የተዋሀዱት ተቋማት ምርቶች ለግብርና፣ ለምግብ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለጤና፣ ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ለጨርቃ ጨርቅ እና ለሌሎች በርካታ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
የተጠቀሱት የኬሚካል ማምረቻ አክስዮን ማኅበራት ከኬሚካል ኮርፖሬሽን ጋር ሲዋሃዱ የኮርፓሬሽኑን ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 280/2005 ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የሦስቱ አክሲዮን ማኅበራት መብትና ግዴታዎች ወደ ኮርፓሬሽኑ ተዛውረው እንዲሻሻል ተደርገጓል፡፡
የኮርፓሬሽኑ የፈቀደ ካፒታልም ብር 21.7 ቢሊዮን የነበረው ወደ ብር 21ቢሊዩን 719 ሚሊዩን 751ሺህ 376 ብር እና የተከፈለ ካፒታል ብር 5.4 ቢሊዮን ብር 5ቢሊዩን 893ሚሊዩን 694ሺህ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተቋቋመው አዲስ የአቪየሽን ቡድን አየር መንገድ በ4 ጉዳዩች ላይ የኤርፖርቶች ድርጅት አስተዳደር ውሳኔውን በቅድሚያ ለአየር መንገዱ ማሳወቅ አለበት አለ፡፡
ለቀድሞው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በላከው የውስጥ ደብዳቤ ድርጅቱ በሰው ሀብት ልማት አስተዳደር፤ በጨረታ፤ በውል አፈጻጸም እና ህጋዊ ጉዳዩች ላይ አስተዳደሩ በቅድሚያ የአየር መንገዱን ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት የኤርፖርቶች ድርጅት ካለ አየር መንገዱ ፈቃድ ማንኛውንም ሰራተኛ እድገት መስጠት፤ ማዘዋወር እና ከደረጃ ዝቅ ማድረግ ወይም መሻር አይችልም፡፡
ጨረታ እና ገንዘብን በተመለከተ ሁሉም ከ150 ሺህ ብር በላይ የሆኑ ወጪዎች በቅድሚያ በአየር መንገዱ መጽደቅ ሲኖርበት ውሎችን እና በአሁን ወቅት ያለተጠናቀቁ ማናቸውንም ህጋዊ ጉዳዩች ለአየር መንገዱ በቅድሚያ እንዲያሳውቅ አዲስ የተመሰረተው የአቪዬሽን ቡድን ለድርጅቱ የላከው ደብዳቤ ይገልጻል፡፡
ሁለቱ የሀገሪቷ አንጋፋ ድርጅቶች የተዋሀዱት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማዋሀድ የቀረበውን ረቂቅ ደንብ ዓርብ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ካጸደቀ በኋላ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ቡድን ባሳለፍነው ወር በአዋጅ ሲቋቋም በሥሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን ያቀፈ ተደርጎ ነው፡፡ ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ ቦርድ የሚተዳደሩ ሲሆን፣ የጋራ መርሐ ግብር ይኖራቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ድርጅቶች የየራሳቸው መለያ ብራንድና የንግድ ምልክት ይዘው ይቀጥላሉ፡፡ ሽግግሩ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በወቅቱ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 86 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤትና 95 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት፡፡ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ብዛት ከ12,000 በላይ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በበኩሉ በርካታ የኤርፖርት ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ በ350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማስፋፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን በክልል በሰመራ፣ በሐዋሳ፣ በሽሬ፣ በባሌ ሮቤ፣ በደምቢዶሎና በነቀምቴ ከተሞች ኤርፖርቶች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ 23 ኤርፖርቶች ሲያስተዳድር፣ አራቱ ዓለም አቀፍ ናቸው፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች

የብሄራዊ ትምባሆ ድርጅት የአርባ በመቶ ድርሻውን ለግል ድርጅት በአምስት መቶ አስር ሚሊዮን ዶላር በሸጠ ማግስት በግማሽ ዓመቱ ከውጭ በሚያስገባቸው የትምባሆ ምረቶች ማግኘት የነበረበትን 26 ሚሊዮን ብር አጣ፡፡
የብሄራዊ ትንባዎ ድርጅት በፈረንጆቹ 2017 አጋማሽ ወር ላይ ከውጭ አገራት በሚያስገባቸው የሮዝማንና ና የማልቦሮ የሲጋራ ምርቶቹ 29.8 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አስቦ 3.1 ሚሊዮን ብር በማግኘት ከ26 ሚሊየን ብር በላይ አጥቷል፡፡
የድርጅቱ የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌቱ አለማየሁ ለምርቶቹ ሽያጭ መቀነስ የውጪ ምንዛሬ መቀነስን እንደ ምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
ድርጅቱ በተጨማሪም በሀገሪቱ ላሉ አጫሾች የሚሆኑ አምስት የሲጋራ አይነቶችን ማምረት ብችልም በአገሪቱ ውስጥ በተስፋፋው የኮንትሮባንድ ንግድ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻዬ 65 ፐርሰንት ብቻ ሆኗል ብለዋል፡፡
የኢትዮጲያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለ ስልጣን የጅጅጋ ቅርንጫፍ ከሰኔ አንድ እስከ ሰኔ 30/2009 ድረስ ግምታቸው 4 ሚሊየን ብር በላይ ሊያወጡ የሚችሉ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን ሲጋራም ዋነኛ ምርት መሆኑን አስታውቋል ፡፡
ድርጅቱ በጃፓኑ ቶባኮ ኢንተርናሽናል 40 ፐርሰንት በመንግስት 31 እንዲሁም በሼባ ኩባንያ 29 ፐርሰንት ድርሻው የተያዘ ሲሆን
የድርጅቱን ከፍተኛ ድርሻ የያዘው የጃፓኑ ድርጅት ሱዳን ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ጨምሮ በሰባት የአፍሪካ አገራት ግዙፍ ኢኮኖሚን እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ምትኬ ቶሌራ

በኦሮሚያ ክልል በህገ ወጥ ማስረጃ ሲሰሩ የነበሩ ከ1ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ተገኙ::
በኦሮሚያ ክልል በሀስተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሰሩ የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች መገኘታቸውን የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
ሰራተኞቹ በክልሉ ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ባሉ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ በሀስተኛ የትምህርት ማስረጃ እየሰሩ የሚገኙ ናቸው።
በዚህም ያለአግባብ የማይገባቸውን ጥቅም እያገኙና በማይመጥናቸው የስራ ደረጃ ላይ በመስራት ላይ ይገኛሉ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን የሚያጋልጡ ሰራተኞችን ይቅርታ ተደርጎላቸው ከዚህ በፊት ባላቸው ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃና በሚመጥናቸው የስራ ቦታ የሚሰሩ ሲሆን
ከነሐሴ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ቢሮው በሚያደርገው ማጣራት ህጋዊ ያልሆነ መረጃ ይዞ በማገልግል ላይ ያሉ ሰራተኞች ከስራው እስከ መጨረሻ ድረስ ይባረራሉ ፤ እስከ አሁን በሀሰተኛ መረጃ ያገኙትን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ይመልሳሉ
ሰራተኞቹ የትምህርት ማስረጃ ያገኙባቸዉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ምርመራ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተነግሯል
በክልሉ ከ470 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ያሉ ሲሆን በክልል ባሉት ተቋማት፣በከተማ አስተዳደሮች፣በዞኖች፣ በወረዳ እና በመንግስት የልማት ድርጅት የሚሰሩ ናቸው።
ከሐምሌ 15 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይሰሩ የነበሩ የመንግስት ሰራተኞቹ እራሳቸውን እንዲያጋልጡ በተሰጣቸው ዕድል መሰረት ሰራተኞቹ ራሳቸውን እያጋጡ ነው ተብሏል።
እጹብ ድንቅ ሀይሉ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ሁለተኛ ምድብ ችሎት በትላንት ውሎው በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ የ 54 ሰዎች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ ፡፡
ፍርድ ቤቱ በቅርቡ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ባለሃብቶችና ደላሎች መካከል በትላንትናው ዕለት የሃያ ሁለቱን ጉዳይ ሲመለከት ማምሸቱ ይታወሳል ፡፡
ፍርድ ቤቱ በትላንት ውሎው ከእሮብ ችሎት ለትላንት በይደር የተላለፉ የ 32 ተጠርሪዎችን እና በዛሬው እለት ከገንዘብና ኢኮኖሚክ ትብብር ሚኒስቴር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የአቶ ሲጀን አባ ጎጃም ጉዳይ መርምሯል፡፡
ፖሊስ ፍርድ ቤቱ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎች መመርመር ይቀረኛል ፤ የሰው ምስክሮች አልሰማውም ፤ አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ ባለ ስልጣናት በመሆናቸው መረጃ ይሸሽጉብኛል፣ ምስክሮቼንም ያባብላሉ በሚል የዋስትና መብታቸው እንዳይከበርና ተጨማሪ የአስራ አራት ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቋ፡፡
የተጠርጣሪዎች ጠበቃ በበኩላቸው አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ከተጠረጠሩበት መስሪያ ቤት ከለቀቁ የቆዩ በመሆናቸው ሰነዶችን መደበቅ አይችሉም ቀደም ሲል ለፖሊስ የተሰጠው የምርመራ ጊዜ በቂ በመሆኑ ፖሊስ ተጨማሪ የተጠየቀው 14 የምርመራ ቀን አላስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ግራ ቀኙን የመረመረው የልደታ ምድብ ችሎት ፖሊስ ጉዳዩን እንዲያጣራ ተጨማሪ 14 ቀን ፈቅዷል፡፡
በዚህም መሰረት በነ አቶ ፀጋዬ ፣በነአቶ ዘነበ ፣በነ አቶ አበበ ፣በአ አቶ ኤፍሬም፣ ስር ያሉ የክስ መዝገቦች ለነሀሴ 17 ሲቀጠሩ
በነ አቶ አብዶ መሀመድ ፣ በነ አቶ ሙሳ ፣ በነ ኢንጂነር ፍቃደ እና ወይዘሮ ሳባ የክስ መዝገቦች ነሀሴ 15 2009 እንዲታዩ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ፍርድ ቤቱ አክሎም በአዲስ አበባ መንገዶች ባለ ስልጣን እና በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮቸክት ላይ ፖሊስ ገና ያልመረመራቸውና ያላደራጃቸው 99 ሰነዶች መኖራቸውን ገልፆ ፖሊስ በአፋጣኝ ምርመራውን እንዲያካሄድ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
ለተጠርጣሪዎች የጤናና የአስተዳደር መብቶች እንዲከበሩ በሳምንት ሁለት ቀን ከጠበቃቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ፈቅደዋል፡፡

የአፍሪካን ልማት ባንክ ለደቡብ ሱዳን ድርቅን እንከላከል በሚባለዉ የአጭር ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ መፍትሄ ሰጭ በሆነዉ ፕሮጀክት በኩል ለደቡብ ሱዳን አርባሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ሰጠ፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከደቡብ ሱዳን እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር ድርቅን እንከላከል በተባለዉ ፕሮጀክት ስር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ይህም ዉል ድርቅን እንከላከል በተባለዉ ፕሮጀክት ስር በአፍሪካ ልማት ባንክ ቦርድ ዳይሬክተሮች አማካኝነት እ.ኤ.አ ጁላይ 21 2017 የፀደቀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ድርጅትም በደቡብ ሱዳን በወኪሉ አማካኝነት ይህን በተግባር ላይ ለማዋል የሚከናወኑ ነገሮችን እየተከታተለ ሪፖርት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡ወኪሉም ከመንግስታት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
የባንኩ አላማም ሶስት መቶ ሺ ለሚደርሱ የደበብ ሱዳን ግለሰቦች ድርቁን በአስቸኳይ ለመቋቋም የሚያስችሏቸዉን መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማለትም ምግብ ፣ ዉሀ እንዲሁም የህክምና አገልግሎቶች ማቅረብ እንደሆነ ተናግሯል፡፡በተጨማሪም በምግብ ለተጎዱ ሌሎች አካላትም እንደሚረዱ ጨምረዉ ገልፀዋል፡፡
የእርዳታዉም ስምምነት በዋነኝነት በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን እጅጉን ለተጎዱ ህዝቦች የምግብ እና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ነዉ፡፡
ይህ ባንክ በድርቅ ለተጎዱ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሀገራት 1.1 ቢሊዮን ብር ለመስጠት አቅዷል፡፡
በፊርማዉ ሰአትም የቦርዱ አባላት እና የተለያዩ ባለስልጣናት እየሆነ ባለዉ ነገር ደስተኛ መሆናቸዉን ገልፀዋል በተጨማሪም ይህ ድጋፍ የደን የግብርና እና ተመሳሳይ የሆኑ የሚኒስተር መስሪያ ቤቶችን እንዲጠነክሩ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ምንጭ ሱዳን ትሪቡን

በ6ክልልሎች የሚገኙ 8.5 ሚሊየን ህዝቦች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል 3.67 ሚሊየን ተጎጂዎችን በመያዝ ከፍተገኛዉን ቁጥር ይዟል፡፡ ለአጠቃላ ተጎጅዎችም እርዳታ 487.7 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል፡፡
በበልግ አብቃይና በአርብቶ አደር አከባቢዎች በተደረገ የምግብ ዋስትና የዳሰሳ ጥናት ለቀጣይ አምስት ወራት ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊየን ህዝብ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገዉ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገልጻዋል፡፡
የተረጂዎች ቁጥርም ባለፈዉ አመት ከነበረዉ ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ወደ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊየን የጨመረ ሲሆን ለዚህም ምክንያት ናቸዉ የተባሉት
የበልግ ዝናብ መዛባት፤ የመኖና ግጦሽ ማነስ፤ የምርት መቀነስና የዉሀ እጥረት ተጠቅሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚለየን ተጎጂ በመያዝ በተጎጂ ቁጥር ቀዳሚ ሆናለች፡፡
ለተጎጂዎች እርዳታ አራት መቶ ሰማንያ ሰባት ሚሊየን ሚሊየን ነጥብ ሰባት የአሜርካን ዶላር እንደሚያስፈልግ የገለፀዉ ኮሚሽኑ የኢትዮጲያ መንግስት ለዚህ እርዳታ ከስድስት መቶ ሰባ ሁለት ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ የእህል ግዥ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቴር የሆኑት አቶ ደበበ ዘዉዴ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
ትብለጽ ተስፋዬ ዘግባዋለች፡፡

ንፋስ የቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ ተከስቶ የወደቀ ዛፍ ሁለት መኪኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡
በአዲስ አበባ በተለምዶ ፍልውሃ እየተባለ በሚጠራው አከባቢ ከፍተኛ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለ ዝናብ ምክንያት 96907 ታርጋ ቁጥር አ.አ የተመዘገበ ሀይሎክስ መኪና ላይ ዛፍ ወድቆበት ከጥቅም ውጪ ሆኖል፡፡
በተጨማሪም እዛው የቆመ የቤት መኪና ታርጋ ቁጥር 974220 የተመዘገበ የሆላ መስታወቱ ሙሉ በሙሉ ረግፎል ፡፡
አደጋው የተከሰተው ሀይለኛ ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት እና ከፍተኛ ዝናብ በመኖሩ እንደሆነም በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች ገልጸውልናል፡፡
ግዙፉ ዛፍ ከስሩ ተነቅሎ መኪናው ላይ በመውደቁ መኪናው ከአገልግሎት ውጪ እንደሆነም መመልከት ችለናል ፡፡
በቦታው የትራፊክ ፖሊሶች እንዲሁም የከተማው ፖሊሶች የነበሩ ቢሆንም አደጋውን መከላከል አልተቻለም ፡፡
ዛፉ የመኪና አሰፋልት ላይ በመውደቁ መንገዱ በጣም ተጨናንቆ የነበረ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች በመተባበር ዛፉን ከወደቀበት ለማንሳት ጥረት እያደረጉ እንደነበር በቦታው ተገኝታ ፍሬህይወት ታደሰ ዘግባዋለች፡፡

ከ59ሺህ በላይ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዩች ውስጥ በቀን ገቢ ግምቱ ዙሪያ 24 በመቶው ብቻ ቅሬታ ቢያቀርቡም ባለስልጣኑ የክፍያው ሂደት በዚህ ምክንያት ተጓቷል ሲል የመክፈያ ቀነ ገደቡን ለ10 ቀናት አራዘመ፡፡
የኢትዮጲያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀን ገቢ ግምትን አስመልክቶ ከማህበረሰቡ ያሰባሰባቸዉን የህዝብ ቅሬታና አስተያየት መሰረት በማድረግ ሀምሌ 18 ቀን 2009 አ.ም በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ቅሬታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ እንደተፈታና ከ 59ሺ 275 የደረጃ ሐ የግብር ከፋዮች መካከል ቅሬታ ያቀረበዉ 24በመቶዉ የሚሆነዉ ብቻ መሆኑን የገለጸዉ ባለስልጣኑ ቅሬታቸዉንም 99.2በመቶ ፈትቻለሁሲል አሳውቆ ነበር፡፡
ታዲያ የ2009 ግብር ማሳወቂያ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. መጠናቀቅ ቢኖርበትም በቀን ገቢ ግምት መረጃ አሰባበሰቡ ዘግይቶ በመጀመሩ በርካታ ግብር ከፋዮች ጊዜው እንዲራዘም ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ባለስልጣኑም ግብርን አሳውቆ የመክፈያ ጊዜው እስከ ነሃሴ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ለ 10 ቀናት አራዝሟል፡፡ በተለያየ ጊዜ ከህዝቡ የተነሱ ቅሬታዎችንና የባለስልጣኑን ምላሽ በምሽት የዛሚ 24 አቅርቦ እንደነበር የሚታወስ ነዉ፡፡
ትብለፅ ተስፋዬ ዘግባዋለች፡፡

ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ 573/2000 ላይ በሚያደርጉት ድርድር የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሲሳተፉ የሚያስፈልጋቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፊርማ ብዛት ከፍ እንዲል ተስማሙ፡፡
በዛሬው እለት በአዋጁ ላይ መጨመር እና መቀነስ እንዲሁም መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የተወያዩት የፓለቲካ ፓርቲዎች ለእለቱ ካነሷቸው ጉዳዩች መካከል የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድምጽ ብዛት ላይ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሲሳተፉ የሚያስፈልጋቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፊርማ ብዛት በሀገር አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚፈልግ ፓርቲ ያስፈልገው የነበረው የ1ሺህ500 ሰዎች ፊርማ ወደ 3000 እንዲሁም በክልል ደረጃ 750 የነበረው ወደ 1ሺህ500 እንዲያድግ ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የድርድሩ የሚዲያና ኮሚዩንኬሽን ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባለፉት ሁለት መድረኮች ባደረጉት ድርድር ከአዋጁ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን 31 አንቀፆች ተወያይተውባቸዋል፡፡
በአዋጁ ላይ የሚደረገው ውይይት ሲጠናቀቅ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ነጥቦች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
የፓለቲካ ፓርቲዎቹ ለመደራደር የሚሆኑ ጉዳዩች እና ቅደምተከተላቸው ላይ ሲደራደሩ ከስድስት ወራት በላይ ከፈጀ በኋላ ይህ ድርድር በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ

የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ከማስታወቂያ ጀምሮ ባሉ ከአንድ ሺህ በላይ ጉዳዩች ላይ የሚያወጡትን አላስፈላጊ ወጪ እንዲያቆሙ አስጠነቀቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለ2010 የበጀት አመት 320.8 ቢሊዩን ብር ለኢፌድሪ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አቅርቦ ያጸደቀ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ገንዘብ በማፍሰስ በማስታወቂያ መስሪያ ቤቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፤ አላስፈላጊ የሆነ በሚል ያስቀመጠውን ለስብሰባ የሚወጣ ከፍተኛ አበል ፤ ለተለያዩ ጉዳዩች የሚፈጸሙ የአበል ክፍያዎች እጅግ ከፍተኛ መሆን እና ነዳጅ አጠቃቀሞችንም የሚጨምር ከአንድ ሺህ በላይ ጉዳዩች የተካተቱበት ዝርዝር በማዘጋጀት ለሚኒስትር መስሪያ ቤቶቹ የገንዘብ አጠቃቀማቸውን ወጪ ቆጣቢ እንዲያደርጉ አሳስቦ አሰራጭቷል፡፡
ከእነዚህ መስሪያ ቤቶች መካከል የፌደራል የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለአመራር እና ድጋፍ አገልግሎት ፕሮግራም 6 ሚሊየን 107 ሺህ 172 ብር የተመደበለት ሲሆን ይህ ገንዘብ ለአበል እና ለስልጠና ወጪ የሚደረግ ነው፡፡
የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ለዛሚ እንደተናገሩት መስሪያቤቶቹ እንዲሰሩ የተሰጣቸውን ገንዘብ አላፈላጊ በሆነ ሁኔታ እያባከኑት እንደሆነ እና ከአትራፊ ድርጅት እኩል እራሳቸውን ማስተዋወቅም አላስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ከሆነ መስሪያ ቤቶቹ በሬድዩ እና በቴሌቪዥን የሚያሰራጯቸው ማስታወቂያዎች እና ስፖንሰር የሚያደርጓቸው ፕሮግራሞች በቀጥታ እነሱን የሚመለከቱ ሆነው አልተገኙም ውጤት ተኮርም አይደሉም፡፡
ውጤት ተኮር ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች መካከል የኢትዩጲያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስለ ግብር መክፈል የሚያስተላልፋቸው ዝግጅቶች ውጤት ተኮር የሆነ መስሪያ ቤቱ ገንዘብ አውጥቶ በሌላ መልኩ የሚያገኝበት ነገር ነው ሲሉ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬቱ ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
በ2010 የበጀት አመት የኢትዩጲያ መንገዶች ባለስልጣን 50 ቢሊዩን ብር፤ በሁለተኛነት የትምህርት ሚኒስቴር እና በስሩ ያሉት ኤጀንሲዎች እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከ700 ሚሊዩን እስከ 1 ቢሊዩን ብር ድረስ ተመድቦላቸዋል፤ ግብርና እና መከላከያ እንዲሁም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ9 እስከ 12 ቢሊዩን ብር በሚደርስ በጀት ከፍተኛ ገንዘብ ከተመደበላቸው መካከል ናቸው፡፡
አቶ ሀጂ ታዲያ ሁሉንም መስሪያ ቤቶች ትልልቅ በጀት ከተመደበላቸው በተዋረድ እንደየጠቀሜታ ፈርጃቸው በጀት የጸደቀላቸውን መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸው ገንዘብ ለስራ እንጂ አላፈላጊ በሆነ መልኩ መስሪያቤቱን ለማስተዋወቅ እና ገንዘብ ለማውጣት አይደለም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች

የአሜሪካ ተምች 32 በመቶ የሚሆነውን የኢትዩጲያ የበቆሎ ማሳ በማጥቃቱ የሀገሪቷ የዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ አደረገ፡፡
ትላንት ባጠናቀቅነው የሀምሌ ወር የሀገሪቷ ወርሀዊ የዋጋ ግሽበት ወደ 9.4 በመቶ ማደጉን የማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የዋጋ ግሽበትን አጠቃላይ የሆነ የዋጋ መጨመር ወይም ደግሞ ብዙ ገንዘብ ትንሽ እቃ ሲፈልግ ማለት ነው ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡
ባለፉት 10 ወራት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት ወር ከነበረበት 5.6 በመቶ አሁን ወደ ሁለት አሀዝ እድገት እጅጉን ተጠግቷል፡፡
የዋጋ ግሽበት ባለሁለት አሀዝ እድገት ማሳየት ያለውን ትርጉም የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ አክሊል ውበት የወጋ ግሽበት እድገት ኢኮኖሚው ሲያድግ ሊፈጠር የሚችል ነገር ቢሆንም ከነጠላ አሀዝ እድገት በአንዴ ወደ ባለሁለት አሀዝ እድገት ከተሸጋገረ በኢኮኖሚው የፍላጎት እና የአቅርቦት አቅም ላይ ክፍተት መኖሩን እንደሚያመላክት ለዛሚ ተናግረዋል፡፡
ግሽበቱ የተፈጠረው የእህል ዋጋ በተለይም የበቆሎ ዋጋ በመናሩ እንደሆነ ሲጠቀስ የምግብ ዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ከነበረበት 11.2 በመቶ ወደ 12.5 በመቶ አድጓል፡፡
በሀገሪቷ አብዛኛው ክፍሎች አዲስ አበባን ጨምሮ አንድ ኪሎ በቆሎ በ12 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በኪሎ በ7 እና 8 ብር ሲሸጥ የነበረው ምርት አሁን ዋጋው እንዲያሻቅብ ሀገሪቷ ለመሰብሰብ ያቀደችው 30 ሚሊዩን ኩንታል በቆሎ በተከሰተው የአሜሪካ ተምች ምክንያት በበቆሎ ከተሸፈነው 71ሺህ 508 ሄክታር 32.2 በመቶው መውደሙ ግሽበቱ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡
በሀገሪቱ የሰብል ምርት ማሽቆልቆል የጀመረው ከባለፈው አመት ጀምሮ ሲሆን በወቅቱ የተሰበሰበው ምርት ከዚያ ቀደም ከነበረው አመት ማለትም በ2007 ከነበረበት በ4.8 ሚሊዩን ኩንታል ዝቅ ብሏል፡፡
ናርዶስ ዩሴፍ ዘግባዋለች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከ200 በላይ የአሳንሰር ግዢ ጨረታ የተጫራቾች አቅም ከደረጃ በታች መሆን አዘገየ
በተለያዩ አካባቢዎች በከተማ አስተዳደሩ የአሳንሰር የይገዛልን ጥያቄ የቀረበባቸው ከሁለት መቶ በላይ አሳንሰሮች ወይም ሊፍቶች ግዢ ጨረታ ሲያካሂድ የነበረው የፌደራል ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንስ ጨረታው በወቅቱ ውድቅ የተደረገበትን ምክንያ ተጫራቾች በቴክኒክና በፋይናንስ ያሳዩት ብቃት ከደረጃ በታች በመሆኑ ነው ፡፡
ሜሪት እና ኮምፕሪናስ ቤዝድ የተጫቾቹ ቴክኒክ አቅም እና በፋይናንስ የተጫራቾቹ አቅም ቢፈተሸም በሁለቱም ዘርፍ ተጫራቾቹ ማሟላት ባለ መቻላቸው ጨረታው ውድቅ ተደርጓል፡፡
የንብረት ጊዢ አዋጅ ቁጥር 649 /2001 የፌደራል ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንሲ የፌደራል ባለ በጀት መስሪያቤቶች አቅም ይገነባል የመንግስት ንብረቶችን ያስተዳድራል በሻጭና በገዢ መካከል ያሉ አቤቱታዎችን ይፈታል ከክልሎች የሚመጡለትን የዕቃ ግዢዎች እንደሚያስተናግድ በግልፅ ተቀምጠዋል፡፡
አሁን ላይ የ202 አሳንሰሮችን የግዢ ጨረታ ከፌደራል ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንሲ ተረክቦ እየሰራ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንብረት ግዢና ማስወገድ ኤጀንሲ ሲሆን አሳንሰሮቹ የጨረታ ግዢ ሂደት ላይ መሆኑንና በመስከረም አሊያም ጥቅምት ወር ላይ ግዢያቸው ይፈፃማል ተብሏል፡፡

በአፋር ክልል በደረሰ ከፍተኛ ጎርፍ ሳቢያ 63 ሺህ ሰዎች አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡
በአፋር ክልል መጋሌ ወረዳ ዞን ሁለት በደረሰው የጎርፍ አደጋ 204 የሚደርሱ ቤቶች፣ትምህርት ቤቶች እና የህክምና ጣቢያዎች ችግር ገጥሞቸዋል፡፡ በክልሉ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ነዋሪዎቹ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ፣ የምግብ እጥረትም አጋጥሞቸዋል በተጨማሪም በዚህ ክረምት ብቻ 44 ሺህ አንድ መቶ ዜጎች ከቤታቸው እንደሚፈናቀሉ ተተንብዮል፡፡ ይህንን ችግር ተመልክቶ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለክልሉ በተለይም በወረዳዉ በድርቁ የከፍ ጉዳት በደረሰባቸው 15 ቀበሌዎች ለሚገኙ አንድ ሺ ያህል ነዋሪዎች 5ሺ ፍየሎች አከፋፍሎል፡፡ በባለፈው አመትም ከ2 ሺህ 3 መቶ በላይ የወረዳዉ ነዋሪዎች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጎል፡፡ አፋር ክልል በከፍተኛ መጠን ጎርፍ ከሚያጠቃቸው ክልሎች ቀዳሚውን ስፍራ ስትይዝ እንደ ዋና ምክንያት ደግሞ የሚቀመጠው የአዋሽ ወንዝ በከፍተኛ መጠን መሙላት ነው፡፡ ሌላው ከፍተኛ ዝናብ ከከፍታማ የሀገሪቱ ክፍሎች ማለትም በአማራ እና በትግራይ ክልል መከሰት ለአፋር ክልል በጎርፍ መጥለቅለቅ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው ስትል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ
ፍሬህይወት ታደሰ ዘግባዋለች ፡፡