ጥር 12/2008 ዓ.ም

ይህ ሩዋንዳ ኪጋሊ ውስጥ የሚገኝ የኢትዬጵያ ሬስቶራንት ነው፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ የባህል ምግቦች አሉት፤ በባህላዊ ምስሎችም አጊጧል ፣በሬስቶራንቱ የሚከፈተው ሙዚቃም የአማርኛ ነው ነገር ግን አንድም አማርኛ ተናጋሪ ሰው በቤቱ የለም፡፡

ሩዋንዳውያን አብዛኛው ነገራቸው በመልክ ለሀበሻ ስለሚቀርብ አስተናጋጆቹን አማርኛ ተናጋሪ አስመስሏቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባለቤቱን ጨምሮ ሁሉም ሩዋንዳውያን ናቸው፤ ምግብ አብሳዮቹም እንደዛው፡፡

ቤቱ ስራውን ሲጀምር አንድ መስፍን የተባለ ኢትዮጵያዊ ምግብ አብሳይ እንደነበር እና ከአራት ወር በፊት ህይወቱ እንዳለፈ አሁን ላሉት ምግብ አብሳዮች ደግሞ የሀበሻን ምግብ አሰራር እንዳስተማራቸው ሰምተናል፡፡ የምግብ መምረጫው ፅሁፍ ላይም አንድ የምግብ አይነት በስሙ ሰፍሯል "መስፍን የአዋዜ ጥብስ" የሚል…………. ሀገር ማስተዋወቅ እንዲህ ነው።

 

ታህሳስ 03/2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ባህልና ሙዚቃን ለማሳደግና ለሌሎችም ለማስተዋወቅ የሚሰራው የሰላም ኢትዮጵያ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው ይህን የሙዚቃ ፌስቲቫል ለአራተኛ ጊዜ ሰላም ፌስቲቫል አዲስ በሚል ያዘጋጀው፡፡

የሰላም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወንድሙ እንደተናገሩት የሀገሪቱን የሙዚቃ ዕድገት እና የሙዚቃ ሰዎች ከሌሎች ሀገራት የሙዚቃ ሰዎች ጋር እያጣመሩ እንዲሰሩ ማስቻል፣ ስለ ባህልና ሙዚቃ የሚያትቱ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችንና የፓናል ውይይቶችን ማድረግ ብሎም ህብረተሰቡ ስለ ሀገሩ ባህልና ሙዚቃ የጠለቀ እውቀትን መስጠት የፌስቲቫሉ ዋነኛ ዓላማ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በፌስቲቫሉ ሳውንድ ኢንጂነሪንግን ጨምሮ ሙዚቃ ላይ እና መሳሪያቸው ላይ ያተኮሩ ወርክሾፖች፣ የባህል ልውውጥ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች፣ የሙዚቃ ዶክመንታሪ፣ ሴሚናሮችና ሌሎችም መሰል ዝግጅቶች ይቀርቡበታል ተብሏል፡፡

ከጥር 9-10/2007 ዓ.ም ድረስ በትሮፒካል ጋርደን በሚካሄደው በዚህ የሙዚቃ ፌስቲቫል ሚካኤል በላይነህን ጨምሮ ከ25 በላይ ድምፃዊያን እና ከአራቱም የሀገሪቱ ክልሎች የሚመጡ የባህል ተጫዋቾች ይገኛሉ የተባለ ሲሆን ከኬንያ፣ ኮንጎ እና ኡጋንዳ እንዲሁም ከስዊድን ጭምር የሚመጡ እውቅ ድምፃዊያን ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡

ሰላም ኢትዮጵያ ይህን ፌስቲቫል ከይሳቃል ኢንተርቴይመንት ጋር በመተባበር ያዘጋጀ ሲሆን የስዊድን ኤምባሲም ለዝግጅቱ መቃናት አስተዋፅኦ አበርክቷል ሲሉ አቶ ተሾመ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡ (ያልፋል አሻግር)

ህዳር 23/2007 ዓ.ም

ከህዳር 22-28 ቀን 2007 ዓ.ም የሚቆየውና በአፍሪካ ቀዳሚ ሰፍራ ከሚሰጣቸው የፎቶ ግራፍ ፌስቲቫሎች አንዱ የሆነው አዲስ ፎቶ ፌስት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ተመርቆ ተከፈቷል፡፡

ትናንት እኩለ ቀን ላይ በሸራተን አዲስ የተጀመረው ታላቅ የፎቶግራፍ ፌስቲቫል በመላው ዓለም ከሚገኙ 32 ሀገራት የተውጣጡ የ95 ፎቶ አንሺዎችና ባለሞያዎች ስራዎች ለእይታ ይበቁበታል ተብሏል፡፡

የፌስቲቫሉ መስራችና ዳይሬክተር የሆነችው የፎቶ ባለሞያ አይዳ ሙሉነህ እንዳለችው ፌስቲቫሉ ከዓለም አቀፍ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ አዘጋጆችና ፎቶግራፍ አንሺዎች ጋር በጋራ የመስራት አጋጣሚዎችን ይፈጥራል፡፡

አዲስ ፎቶ ፌስት ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ አንድ ጊዜ ይዘጋጃል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)

ህዳር 16/2007 ዓ.ም

በቅድስት ይልማ ተፅፎ ዳይሬክት የተደረገው ረቡኒ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ሽልማት ከየትኛውም ፊልም በላቀ ሁኔታ 6 ዋንጫዎችን ወስዷል፡፡ ረቡኒ የዓመቱ ምርጥ ፊልምና የዓመቱ ምርጥ የተመልካች ምርጫን ከማሸነፉም በተጨማሪ በዓመቱ ምርጥ የሴት ተዋናይት ሩታ መንግስተአብን፤ በዓመቱ ምርጥ ታዳጊዎች ተዋናይ ህፃን የአብስራ ተክሉን፤ በዓመቱ ምርጥ የፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ደግሞ ቅድስት ይልማን አስመርጧል፡፡

በተጨማሪም በዓመቱ ምርጥ የወንድ ተዋናይ ተዘራ ለማ ከበኩር ልጅ ፊልም፤ በዓመቱ ምርጥ የወንድ ረዳት ተዋናይ ቴዎድሮስ ፍቃዱ ከትመጣለህ ብዬ፤ የዓመቱ ምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይት እድለወርቅ ጣሰው ከስር ሚዜዋ እንዲሁም በዓመቱ ምርጥ ሲኒማቶግራፈር ሰው መሆን ይሰማውና ታሪኩ ደሳለኝ አሸንፈዋል፡፡

በሊንኬጅ ማስታወቂያና ጋዜጣ ስራ የተዘጋጀው 9ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ለአንድ ሳምንት ከተካሄደ በኋላ ትናንት ምሽት በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽልማት ስነ-ስርዓት በድምቀት ተጠናቋል፡፡ (እንደገና ደሳለኝ)