አለም አቀፍ ዜናዎች (114)

Thursday, 09 October 2014 14:54

ከፈረንጆቹ ሚያዚያ ጀምሮ በዩክሬን ቀውስ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3,660 መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

መስከረም 29/2007 ዓ.ም

ከሚያዝያ አጋማሽ እስከ ማክሰኞ በነበረው ጊዜ ህይወታቸውን ካጡት 3,660 በተጨማሪ 8,756 የሚሆኑት ሰዎች በምስራቅ ዩክሬን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትላንትናው ዕለት ባወጣው ወርሃዊ ሪፖርት ነው ጉዳዩን ያስታወቀው፡፡

በአማፂያኑ እና በዩክሬን መንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላም ቢሆን ቀውሱ የተረጋጋ ቢመስልም ግጭቶች ነበሩ ያለው ሪፖርቱ ሰዎች በዚሁ ቀውስ ሂወታቸውን እንዳጡ አትቷል፡፡ ዘገባው የYahoo News ነው፡፡ 

Thursday, 09 October 2014 14:53

በማሊ በተለይ በሀገሪቱ በሰሜን ክፍል ያሉ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወታደሮች እንዲላኩ ተጠይቀዋል፡፡

መስከረም 29/2007 ዓ.ም

የማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብሉላዬ ዲዮብ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በቅርቡ በተ.መ.ድ ሰላም አስከባሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ተወስኗል፡፡

በታጣቂዎቹ ቀደም ባለው ጊዜ ከኒጀር የመጡ 9 ሰላም አስከባሪዎች ተገድለው የነበረ ሲሆን ማክሰኞ እለት ደግሞ አንድ ሴኔጋላዊ ሰላም አስከባሪ ህይወቱን አጥቷል፡፡

የተ.መ.ድ ሰላም ማስከበር ቡድን ሃላፊ እንዳሉት በማሊ ያለው ወታደራዊ ሃይል የፈረንሳይ ወታደሮች በመልቀቃቸው የተፈጠረውን ክፍተት መሸፈን አልቻለም፡፡

ምንጮች እንዳመለከቱት እስካሁን እ.ኤ.አ በ2013 ተልዕኮውን ለማስፈፀም ወታደሮች ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ 31 ሰላም አስከባሪዎች ሞተዋል፤ 91 የሚሆኑት ቆስለዋል፡፡ ዘገባው የBBC ነው፡፡

Tuesday, 07 October 2014 09:14

የላይቤሪያ የህትመት ሚዲያ ህብረት የሀገሪቱ መንግሥት በኦቦላ በሽታ ላይ የሚሰሩ ዘገባዎችን እያገደ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

መስከረም 27/2007 ዓ.ም

በሱዳን በኢቦላ ዙሪያ የሚሰሩ ዘገባዎች ይታገዱ መባሉን የሚያመላከተው ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ፤ የላይቤሪያ የህትመት ሚዲያ ህብረትም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን አመላክቷል፡፡ የህብረቱ አባላት መንግሥት በሽታውን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ከማጠናከር ይልቅ ዘገባዎችን ማገዱ አግባብ አይደለም ሲሉ ወቀሳቸውን እየሰነዘሩ ነው፡፡

የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ በዚህ ዙሪያ የሚተላለፉ ጉዳዮች መስመር እየሳቱ ነው የሚል አስተያየት አለው፡፡ ለማገገሚያነት በተሰሩ የጤና ማዕከላት ውስጥ የሚነሱ ፎቶግራፎች፣ የሚሰሩ ቃለ-መጠይቆችና ተያያዥ ጉዳዮች የህሙማንን መብት መጋፋት እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡ የሚዲያዎችን ነፃነት የሚጋፉ ተግባራት ተመልስው መምጣታቸው የሀገሪቱን ዴሞክሲያዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው መባሉን VOA ዘግቧል፡፡

Tuesday, 07 October 2014 09:14

የእስራኤል ታጣቂ ቡድን የሆነ እና በአንፃሩ አይ ኤስ ተብሎ የሚጠራው ቡድን የሽብር ጥቃቱን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተነገረ፡፡

መስከረም 27/2007 ዓ.ም

የአሸባሪ ቡድኑ አባላት የሆኑ ኮማንዶዎቹን በስደተኞች ስም ወደ ምዕራብ አውሮፓ በመላክ የሽብር ጥቃት ለማድረስ እያሴረ መሆኑን ጀርመን የተናገረች ነው፡፡ አራት አባላት ያሉት የሽብር ቡድን በሶሪያና ቱርክ ድንበር ሰርጎ በመግባት እና በተጭበረበረ የጉዞ ሰነድ ወደተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ለመግባት ማቀዱ ነው የታወቀው፡፡ የሽብር ቡድኑም ጀርመን ለኩርድ ወታደሮች ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር አስቧል፡፡ ምንም እንኳን ጀርመን እንዲህ ብትልም የአሜሪካ የደህንነት አባላት እንዳስታወቁት ከሆነ በአየር ማረፊያዎች እጅግ ጥብቅ ቁጥጥር በመኖሩ አሸባሪዎች አውሮፕላኖችን እንደማይጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

የተረጋገጠ የሽብር ጥቃት ፍንጭ ባይኖርም ጀርመን የአሸባሪዎች ቀጣይ የጥቃት ኢላማ ናት ሲሉ የጀርመን የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡ ዘገባው የሮይተርስ ነው፡፡

Thursday, 02 October 2014 12:23

የቻይናዋ ከፊል ራስ ገዝ መስተዳድር ከተማ የሆንግ ኮንግ ህዝብ የከተማይቱን አስተዳደር በመቃወም የጀመረውን ሰልፍ እንደቀጠለ ነው፡

መስከረም 22/2007 ዓ.ም

የከተማው ህዝብ ባለፈው እሁድ የጀመረውን የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያበቃ የከተማው አስተዳደርና የቻይና ማዕከላዊ መንግሥት ቢጠይቁም ሰልፉ አለመቋረጡን ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች አስለቃሽ ጋዝ በመጠቀም ሰልፈኛውን ለመበተን ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካም መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ የሰልፈኞቹ መልዕክት በሀገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሆንግ ኮንግ  ዋና አስተዳዳሪ በነፃነት መምረጥ በሚችሉበት ዙሪያ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ምንም እንኳን ሰልፈኞችን ለመበተን የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች እንዳሉት የሆንግ ኮንግ ዝናባማና ነፋሻማ አየርን በመቋቋም በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የከተማይቱ አደባባይ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ሰልፉ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ስልጣን ከያዘበት 65 ዓመት ክብረ በዓል ጋር መገጣጠሙን ሮይተርስ ነው የዘገበው፡፡

Thursday, 02 October 2014 12:19

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀድሞ ተዋጊዎች በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለከፋ ረሀብ እየተጋለጡ ነው ተባለ፡፡

መስከረም 22/2007 ዓ.ም

ከ100 በላይ የሚሆኑና ቀድመው በውጊያ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወታደሮች በዚሁ በገጠማቸው ረሀብ ምክንያት ህይወታቸውን እያጡ ነው፤ ቤተሰቦቻቸውም ተመሳሳዩ እጣ ደርሷቸዋል፡፡

የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እንዳመላከተው ባለፈው ዓመት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምዕራብ ክፍል በሚገኘው ብዙ ትኩረት በማይሰጠው ካምፕ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ ይህም የተደረገው እጅ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የሚላክላቸው ምግብ ሊዳረስ የሚችል አይደለም የተባለ ሲሆን የጤና አገልግሎቱንም በበቂ ሁኔታ ማግኘት አልቻሉም፡፡ አንዳንዶቹም በአካባቢው ካሉ ገበሬዎች እህል መስረቅ ጀምረዋል፡፡ የሀገሪቱ ወታደራዊ ሃይል ጉዳዩን አጣራዋለሁ ያለ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡ ዜናው የቢቢሲ ነው፡፡

Tuesday, 30 September 2014 09:12

በአልጄሪያ ፈረንሳያዊው ቱሪስት መገደሉን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ ሊጎዳ እንደሚችል ተነገረ፡፡

መስከረም 20/2007 ዓ.ም

ባለፈው ሳምንት በሀገር ውስጥ ታጣቂዎች በፈረንሳዩ ቱሪስት ላይ የተደረገው አፈና እና ግድያ ከአይ ኤስ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡

ይህም የሰሜን አፍሪካ ሀገራትን ያሰጋ ሲሆን የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም ተቀዛቅዟል፡፡

በአልጄሪያ ደቡብ ክፍል ያሉት በርካታ የቱሪዝም ኤጀንሲዎች ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት በርካታ ጎብኚዎች ወደ ሰሀራ በረሀ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሰርዘዋል፡፡ ኤጀንሲዎቹ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ማምጣት የሚችለውን ቱሪዝምን ለማጠናከር ሀገሪቱ ምቹና ሰላማዊ መሆኗ በስፋት ሊቀሰቀስ ይገባል እያሉ ነው፡፡

የ55 ዓመቱ ፈረንሳያዊ ጎብኚ ጉዳይ ግን በእቅዱ ላይ ከፍተኛ የሆነ እንቅፋት ሆኗል፡፡

አልጄሪያ መሰል ተግባራትን ለመከላከል ተጨማሪ ወታደራዊ ሀይል ያሰማራች ሲሆን ቱሪስቶችም መረጃዎችን አሟልተው የሚገኙበትና እነርሱም በግልፅ ያሉበትን ሁኔታ የሚናሩበት መንገድ ምቹ ሆኗል፡፡ ዜናው የኦል አፍሪካ ነው፡፡

Monday, 29 September 2014 09:51

ደቡብ አፍሪካ ለኩባ 31 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በእርዳታ ለመስጠት ተስማምታለች፡፡

መስከረም 19/2007 ዓ.ም

ይህንን እርዳታ ለመስጠት ከስምምነት የደረሱት በሶስት ጊዜ ክፍያ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍያ ለኩባ የግብርናው ዘርፍ የዘር እርዳታ የሚውል 3.57 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

ሁለተኛው 8.93 ሚሊዮን ዶላር የተለያዩ ግብአቶችን ከደቡብ አፍሪካ ለመግዛት የመጨረሻው ደግሞ 18.75 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን እርዳታ እንደሆነ ተገልጧል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡ ህግ አውጪዎች ስምምነቱን እየተቃወሙት ነው፡፡

የህዝብን ገንዘብ ያለአግባብ የመጠቀም አካሄድ ነው የሚል አስተያየትም ተሰጥቶበታል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የዚህን እርዳታ በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2010 ቃል ገብተው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ዘገባው የዴይሊ ኒውስ ነው፡፡

Thursday, 25 September 2014 09:37

በኒውዮርክ በተዘጋጀው የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ ጉባኤ ቻይና ችግሩን ለመቅረፍ እንደምትሰራ አስታወቀች፡፡

መስከረም 15/2007 ዓ.ም

ቻይና በከፍተኛ መጠን የካርቦን ልቀት ወደ ከባቢ አየር እንደምትለቅም ይታወቃል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተዘጋጀው በዚሁ ጉባዔ ላይ የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዘሀንግ ጋኦሊ ሀገራቸው የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው ሀገራቸው አሜሪካ እና ቻይና ልቀትን በመቀነስ በኩል ሌሎች ሀገራትን በማስተባበር ቀዳሚ መሆን እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡ የአሁኑ ጉባዔ የ20 አባል ሀገራት በቀጣይ ዓመት ፓሪስ ላይ በሚካሄደው ጉባዔ ላይ በተዘጋጀው የአየር ንብረት ስምምነት ላይ እንዲፈርሙ የሚያስችል እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን ገልፀዋል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Thursday, 25 September 2014 09:29

በናይጄሪያ ቦርኖ ግዛት 50 የቦኮሃራም ታጣቂ ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ፡፡

መስከረም 15/2007 ዓ.ም

ይህ የሆነው በትናንትናው ዕለት ሲሆን መረጃውን ማንነታቸውን የደበቁ አካላት ይፋ አድርገውታል፡፡ ወደ ሌላኛው ሰሜናዊ ግዛት ጎምቤ በመሸጋገር ላይ እያሉ መያዛቸውንም ምንጮች አመላክተዋል፡፡ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ታጣቂዎች እድሜያወች ከ18-25 ዓመት ውስጥ ባለው ነው፡፡ መሪያቸው በተኩስ ልውውጥ መገደሉን ተከትሎ በወቅቱ እየሸሹ ነበር፡፡

የጥበቃና ፀጥታን የማስከበር ስራን ህብረተሰቡ በንቃት ተግባራዊ እያደረገ ነው የተባለ ሲሆን እስካሁን ከታየው በተሻለ መልኩ ናይጄሪያ ሽብርተኝነትን መዋጋት የቻለችበት ጊዜ መሆኑም ተዘግቧል፡፡ ዜናው የዢንዋ ነው፡፡

Friday, 19 September 2014 12:25

የአፍሪካ ህብረትና ሩሲያ ጥምረታቸውን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል፡፡

መስከረም 9/2006

የህብረቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ሊኮሳዛና ዲላሚኒንዙማ እና የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበራቸውን አሰራር ለማጠናከር የሚያስችሉ ስርአቶችን ዘርግተዋል፡፡ ዲላሚኒንዙማ የሁለቱን ምክክር ተከትሎ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በተለይ በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመሰረተ ልማትና በግብርና ዘርፍ መተጋገዛቸው መሳኝ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

አፍሪካ በአጭር ጊዜ ውስጥ የበለፀገች አህጉር መሆኗን ለማረጋገጥና ዜጎቿንም ከድህነት ለማውጣት ህብረቱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው የተባለ ሲሆን ሰርጌ ላቭሮቭም ሀገራቸው በተጠቀሱት ዘርች ላይ ውጤታማ የሆነ እንቅስቃሴ እንዳላት ማረጋገጣቸውን ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል፡፡

Friday, 19 September 2014 12:25

ለጋዛ መልሶ ግንባታ ሳዒዱ አረቢያ ግማሽ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለመስጠት ቃል ገባች፡፡

መስከረም 9/2006

በፍልስጤም እና በእስራኤል መሃከል ተከስቶ በነበረው ደም አፋሳሽ እልቂት ብዙዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ በርካታ መኖሪያ ቤቶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፤ የመሰረተ ልማት አውታሮችም በጋዛ ተናግረው ይገኛሉ፡፡ በጋዛ ሰርጥ የደረሰውን መፈራረስ መልሶ ለመገንባት በቀጣይ ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ራሚ አል አምደላህ ተናግረዋል፡፡ በግብፅ ሸምጋይነት በካይሮ በሚደረገው የጋዛ መልሶ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትን ጨምሮ ኳታር እና ቱርክ እንደሚገኙ እና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ሳኡዲ ቀደም ካለ ድጋፉን ለማድረግ ቃል መግባቷ ለፍልስጤም ያላትን አጋርነት ያሳየ ነው ተብሏል፡፡

እስራኤል በበኩሏ ለጋዛ ዳግም ግንባታ የሚውል ቁሳቁሶች እንዲገቡ መፍቀዷ ይታወሳል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪነት በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ ጋዛ ሰርጥ ለሚገቡ የግንባታ እቃዎች እስራኤል ይሁንታ ሰጥታለች፡፡ ዘገባው የሮይተርስ ነው፡፡

Friday, 19 September 2014 12:23

የሊቢያ የቀድሞው የአየር ሃይል መሪ በቤንጋዚ መገደላቸው ተሰማ፡፡

መስከረም 9/2006

አህመድ ሀቢብ አል ማስማሪ ምሽት ላይ ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥይት በተደጋጋሚ የተተኮሰባቸው ሲሆን የቤንጋዚ የህክምና ማዕከልም ህይወታቸው ወዲያው ማለፉንና በበርካታ ጥይቶች መደብደባቸውን አመላክቷል፡፡የዜናው ምንጭ ዢንዋ ነው፡፡

Friday, 19 September 2014 12:22

ጊኒ በኢቦላ በሽታ /ቫይረስ/ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት በሚል በተለያዩ መንደሮች ውስጥ ገብተው የጠፉትን የጤና ባለሞያዎች የሚፈልግ ቡድን አሰማርታለች፡፡

መስከረም 9/2006

ከሁለት ቀናት በፊት በየመንደሩ ሲዞሩ ጥቃት የደረሰባቸውና አሁንም ያሉበት ያልታወቁት ባለሞያዎች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ግን ታግተው ወይም ተገድለው እንደሆነ እያመላከቱ ነው፡፡

እማኞች እንደሚሉት በጤና ቡድኑ ላይ ከአካባቢው ነዋሪ ድንጋይ ሲወረወር ነበር፡፤

በቅርቡ እየወጡ ያሉ መረጃዎች በሚያመላክቱት መሰረት ደግሞ ግንዛቤውን ለመስጠት በጊኒ የሚንቀሳቀሱት ልዑካን መልካም አቀባበር እያገኙ አይደለም ከዚህ ቀደምም ይፋ ያልሆኑ ጥቃቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

ከጠቱት ሰዎች ውስጥ ጋዜጠኞችና የሀገር ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚገኙም ምንጮች እየተናገሩ ነው፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Friday, 19 September 2014 12:21

በግብፅ ለእዕምሮ ህመም የሚያጋልጥ ነው የተባለ ህገ-ወጥ መድሀኒትን ይዞ ለመግባት የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥ ስር ዋለ፡፡

መስከረም 9/2006

ግለሰቡ በግብፅ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ 420 ያህል ለአዕምሮ ህመም የሚያጋልጡ የተባሉና በግለሰብ ደረጃም ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ይዞ መገኘት የማይፈቀዱ መድሀኒቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ይዞ ለመግት ሲሞክር ነው በደህንነት ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡

በፍተሸ ወቅት በቦርሳው የያዛቸው እቃዎች በ x-ray ሲፈተሸ መድሀኒቶቹ እንደተገኙ ተነግሯል፡፡

የግብፅ መንግስት የግለሰቡን ስም መግለፅ ሳይፈልግ ቀርቷል ነገር ግን ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቀው ተነግሯል፡፡

ዜናውን ኦል አፍሪካን ድረገፅ ዘግቦታል፡፡

Thursday, 18 September 2014 14:42

ስኮትላንዳውያን ከእንግሊዝ ለመገንጠል ህዝበ ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡

መስከረም 8/2006

የስኮትላንድን መገንጠል በሚደግፉና የሀገሪቱን መገንጠል በሚቃወሙ ሁለት ወገኖች መካከል በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ፣ የስኮትላንድን መገንጠል በሚቃወሙ ወገኖች ድምፅ የበላይነት እንደቀጠለ ነው፡፡

የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስትር አሌክስ ሳልሞንድ ለመራጮች እንዳሉት ሀገሪቱ እንድትገነጠል ይሁኝታቸውን በድምፃቸው እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ የሀገሪቱን መገንጠል የሚቃወሙ በበኩላቸው ድምፅ ሰጪዎች ለስኮትላንድ መገንጠል አሉታዊ ድምፃቸውን እንዲሰጡ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛል፡፡ ዛሬ በሚደረገው የህዝብ ውሳኔ ድምፅ የ307 ዓመት ጥምረታቸው ያበቃለታል ወይስ ይቀጥላል የሚለው ይታወቃል፡፡ ከ4 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን ከ2006 በላይ ድምፅ መስጫ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ዘገባው የሮይተርስ ነው፡፡

Thursday, 18 September 2014 14:42

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ጉደላክ ጆናታን በሀገሪቱ አሁን ላይ ምንም አይነት የተመዘገበ የ ኢቦላ የቫይረስ ተጠቂ እንደሌለ አስታወቁ፡፡

መስከረም 8/2006

በበሽታው ተይዘው ከነበሩ 19 ሰዎች መካከል 7ቱ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ድነዋል ተብሏል፡፡

አሁንም እየተመለከትናቸውና ተከልለው የተቀመጡ ሰዎች አሉ ነገር ግን ሀገሪቱ ከቫይሰሩ ነፃ መሆኗን አረጋግጠናል ሲሉ በአቡጃ ተገኝተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም በሀገሪቱ ት/ቤቶች እንዲዘጉ መወሰናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሌላ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን እርምጃው የተወሰነው ወጥነት ያለውን የመከላከል ስራ ተግባራዊ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ በርካታ ናይጄሪያውያን በሽታውን ይዘው ይመጣሉ በሚል ግምት ከፍተኛ የሆነ መገለል እየደረሰባቸው እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ገፅታውን መቀየር አስፈላጊ እንደሆነም ጆናታን አሳስበዋል፡፡

ዘገባው የዥንዋ ነው፡፡ 

Wednesday, 17 September 2014 12:16

በካቡል በደረሰው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 3 የኔቶ (NATO) ወታደሮች ተገደሉ፡፡

መስከረም 07/2007

ጥቃቱ የደረሰው በታሊባኑ ታጣቂዎች መሆኑ ታውቋል፡፡ ከሞቱት ወታደሮች በተጨማሪ 16 ንፁሃን ዜጎች መጎዳታቸውን መንግሥት አስታውቋል፡፡ 4ቱ የኔቶ ወታደሮች ሲሆኑ ጉዳታቸው የከፋ ነው፡፡ አደጋው የተከሰተው የትራፊክ መጨናን በበዛበት መንገድ ላይ በመኪና በተጠመደ ቦንብ ነው፡፡ መንገዱ ለአሜሪከ ኤምባሲ ቅርብ ነው ተብሏል፡፡

ፍንዳታው የአካባቢው ያሉትን ህንፃዎች አናግቷል፡፡ በጥቃቱ የሞቱት የኔቶ ወታደሮ ዜግነት አልተነገረም፡፡ በአፍጋኒስታን የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ በሁለቱ ተፎካካሪዎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፤ ይህም ለታሊባን ተመችቷታል ሲል AFP ገልጧል፡፡

ሁለቱ ተፎካካሪዎች ስልጣን ለመጋራት ወደ ስምምነት እየመጡ ነው እየተባለ ይገኛል፡፡ ዘገባው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡