አለም አቀፍ ዜናዎች (114)

Friday, 14 November 2014 10:43

የቻይና ኢኮኖሚ የመዳከም አዝማሚያ እንደታየበት ሪፖርቶች አመላከቱ፡፡

ህዳር 05/2007 ዓ.ም

በጥቅምት ወር የቻይና የኢንዱስትሪ ምርቶች በ7.7 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት የችርቻሮ ግብይት ላይ 11.5 በመቶ ያህል ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡

ሆኖም ግን ቀደም ሲል ኢኮኖሚስቶች ተንብየውት ከነበረው የኢንዱስትሪ ምርቶች 0.3 በመቶ ቅናሽ ሲያሳይ የችርቻሮ ንግድ ላይ 0.1 በመቶ መቀዛቀዝ ታይቶበታል ተብሏል፡፡

በተጨማሪ ጠቃሚ እና የኢኮኖሚ ጠቋሚ የሆነው የማይንቀሳቀው የሃብት ኢንቨስትመንት መጠን በመስከረም ወር ከነበረው የ16.1 በመቶ በመውረድ 15.9 በመቶ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

እነዚህ እውነታዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ እ.ኤ.አ በ2014 ሦስተኛው ሩብ ዓመት በአምስት ዓመት ውስጥ ከተመዘገበው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

መንግስት ድጋፉን ማድረግ ከቻለ እየወረደ ያለውን ኢኮኖሚ መታደግ እንደሚቻል የA N Z ባንክ ኢኮኖሚስት የሆኑት ዙሁ ሀኦ ተናግረዋል፡፡

በመስከረም ወር የከተማ የሥራ አጥ ቁጥር መጠን 4.07 መድረሱን ቢቢሲ ዘግቦታል፡፡  

Friday, 14 November 2014 10:39

በሊቢያ የግበጽና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ኤምባሲዎች ለማውደም ታስቦ የተጠመደው ቦምብ የከፋ ጉዳት አለማድረሱ ተነገረ

ህዳር 05/2007 ዓ.ም

ቦምቡ በመኪና ላይ እንደተጠመደ የተነገረ ሲሆን፤ ዒላማው ደግሞ በሊቢያ ዋና ከተማ ላይ የሚገኙትን የግብጽና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE) ኤምባሲዎች ለማውደም እንደነበረ ነው የዜና ምንጮች የተናገሩት፤

የኢስላማዊ ጽንፈኛ ኃይሎች ናቸው በተባሉት ታጣቂዎች አማካኝነት የሃገሪቱ ሁለት ዋነኛ ከተሞች ትሪፖሊ እና ቤንጋዚ በከፍተኛ ሁከት ውስጥ ናቸው የተባለ ሲሆን በርካታ ኤምባሲዎች ቢሮዎቻቸውን ዘግተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሃገሪቱን ለቀው ወጥተው እየተባለ ይገኛል፡፡ የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናገረ እንደተባለው አሁን በሃገሪቱ እየተከሰተ ያለው ክስተት ታሪካዊ የደም መፋሰስ ክስተት ነው፤ የአማጽን ቡድኑ ኃይልን በመጠቀም ፖለቲካዊ ዓላማውን ግብ ለመምታት ይፈልጋል፤ በዚህም የብዘ ንጹሃን ደም በከንቱ ይፈሳል ሲል ተደምጧል፡፡

የሁለቱ ሃገራትን ኤምባሲዎች ለማውደም ታስቦ የተጠመደ ነው የተባለው ቦምብ መጠነኛ ጉዳትን በህንጻው ላይ ከማድረሱ ባለፈ ምንም ያደረሰው ሌላ ጉዳት የለም ተብሏል፡፡

ከትናንት በስቲያ በተመሳሳይ በሃገሪቱ ምስራቃዊ ክፍሎች ቲብሩክ እና ባይዳ ላይ በመኪና በተጠመደ ቦምብ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ፤ 21 ያህል የከፋ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል፡፡

የዚህ ጥቃት ዓላማ የተባለው በህዝብ የተመረጡትን የፓርላማ አባላትና የመንግስት አካላትን ለማጥቃት እንደነበርም ተያይዞ ተዘግቧል፡፡ ዘገባው የአሶሼትድ ፕሬስ ነው፡፡

Thursday, 13 November 2014 11:03

የአሜሪካ ኤምባሲ በሴራሊዮን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኢቦላ ቫይረስ ስርጭት ምክንያት በቂ ጥንቃቄና ቁጥጥር አለመደረጉ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

ህዳር 04/2007 ዓ.ም

በተለይም ኤምባሲው ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ በዚህ ሳምንት እንኳን ጥንቃቄ የጎደላቸውና በባለሞያ ያልታገዘ የቀብር ስነ-ስርዓት እንደሚከናወን ታዝቤያለሁ ብሏል፡፡

ተያይዞ የወጣው ዘገባ እንዳመላከተው በሴራሊዮን ወደ 32 በመቶ የሚጠጉት ዜጎች ያለንኪኪ አስክሬኑ ሳይታጠብ የሚከናወነውን የቀብር ስነ-ስርዓት አይቀበሉትም፡፡

ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት አዲስ ይፋ የሆነው መግለጫ የቫይረሱን መስፋፋት ለመቀነስ እንዲቻል ቫይረሱ መገታቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ በማንኛውን ምክንያት የሚፈጠር ሞት የቀብር ስነ-ስርዓቱ ያለንክኪ እንዲፈፀም የሚያዝ ነው፡፡ ዜናው የቢቢሲ እና የዢንዋ ነው፡፡

በሌላ ዜና በሴራሊዮን የኢቦላ ህሙማንን ለማከም የተመደቡ ከ400 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሞያዎች የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል፡፡ ነርሶችንና የፅዳት ሰራተኞችን ያማከለውና ተቃውሞውን እያሰማ ያለው ቡድን መንግሥት በሳምንት ሊከፍለን ቃል የገባውን 100 ዶላር አላሟላም የሚል ቅሬታንም እያሰሙ ነው፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት አዲስ ባወጣው ሪፖርት በኢቦላ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡት ቁጥር 5,160 መድረሱን አመላክቷል፡፡

በበሽታው የተያዙት ቁጥራቸው አሻቅቧል፤ በምእራብ አፍሪካ ሀገራት ከ14,000 የሚበልጡ መያዛቸውም ተረጋግጧል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

Thursday, 06 November 2014 11:46

በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ግዛት እየተባባሰ በመጣው ጥቃት ምክንያት ወደ 17,000 የሚጠጉ ዜጎች መኖሪያ ቀያቸውን ለመልቀቅ እንደተገደዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

ጥቅምት 27/2007 ዓ.ም

ሪፖርቱ እንዳስነበበው ለሀገሪቱ ስጋት የሆነው ቦኮሃራም በሳምንት ውስጥ በየእለቱ በሚባል ደረጃ ጥቃት ይፈፀማል፡፡ ከተፈናቃዮቹ መካከልም 6,000 የሚሆኑት ህፃናት ናቸው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቀጣይ ግዜያትም መኖሪያ ቀያቸውን ለመልቀቅ የተገደዱትን በመመዝገብ ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ለስደት የተዳረጉም ምዝገባውን እንዲያካሂዱና የሚታደለውን ግብዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ የናይጄሪያ መንግሥትና ታጣቂው ቦኮሃራም የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን የናይጄሪያ መንግስት አስታውቀው ነበር፡፡ ተከትለው የወጡ የዜና ምንጮች ግን ታጣቂ ቡድኑ የተኩስ አቁም ስምምነቱን አለማድረጉንና ይለቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁት ከ200 የሚበልጡ ልጃገረዶችም ከተዋጊዎች ጋር በጋብቻ እንደሚተሳሰሩ ማስታወቁን አስታውሶ የዘገበው ዥንዋ ነው፡፡

Wednesday, 05 November 2014 15:11

በሊቢያ ትሪፖሊ ታዋቂ አውራ ጎዳና ላይ ከጣሊያን ዘመን ጊዜ ጀምሮ የተሰራው ሃውልት ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ ከቦታው ተሰውሯል፡፡

ጥቅምት 26/2007 ዓ.ም

ራቁቷን የሆነች ሴት ግመልን ይዛ የሚያሳየውን ታሪካዊ ሀውልት እስካሁን ድረስ  ማን እንደወሰደው የታወቀ ነገር ባይኖርም ብዙዎች ግን እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑን ተጠያቂ እያደረጉ ነው፡፡ ጣሊያን ሊቢያን ገዝታ ከነበረበት ግዜ ጀምሮ በቦታው ላይ ተቀምጦ የቆየ ሃውልት ነው፡፡

የሊቢያ ባለስልጣናት የሀውልቱን መጥፋት አውግዘውታል፡፡ በሀገሪቱ ያሉ ዜጎችን የምንጠይቀው የሊቢያን አይረሴ ቅርሶች እንዲጠብቁ ወይም ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት ላይ እንዲተባበሩ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይነትም በቦታው ላይ ካሉት ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ወንጀለኞቹን ለመያዝ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Tuesday, 04 November 2014 10:54

ቻይና እና ኳታር ወዳጅነታቸውን በተለያዩ ዘርፎች ለማጠናከር ተስማሙ፡፡

ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም

የኳታር ንጉስ በቻይና ባደረጉት ጉብኝት ነው ሀገራቱ ከስምምነት የደረሱት፡፡ የኳታር ንጉስ በትላንትናው ዕለት ነበር ወደ ቻይና ያቀኑት፡፡ ሁለቱ የሀገር መሪዎች በአጠቃላይ ግንኙነታቸው ዙሪያ ሰፊ ሰዓት ወስደው እንደተነጋገሩ ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ቺን ፒንግ ከኳታር ጋር ያላቸው ግንኘነት ማደጉ ለሁለቱም ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት እና ትስስር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ዘገባው የኤዥያን ታይምስ ነው፡፡

Tuesday, 04 November 2014 10:49

በኢቦላ ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዋል ከተባሉ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ዜጎች ላይ ከበድ ያለ የቪዛ ህግ ማስቀመጧን ሲንጋፖር አስታውቃለች፡፡

ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም

ወደ ሲንጋፖር የሚገቡት ላይ የሚደረገው ይኸው ቁጥጥር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚደረገው ከረቡዕ ጀምሮ መሆኑም ታውቋል፡፡ የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን ዜጎች ላይ የሚደረገው ይኸው ቁጥጥር በተሻለ መልኩ ደህንነቱን ለማስጠበቅ ያለመ ነው፡፡ የሲንጋፖር መገናኛ ብዙሃን 2 በኢቦላ የተጠረጠሩ ሰዎች መኖራቸውን ይፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም ሁለቱም በተደረገላቸው ምርመራ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ዜናው የቢቢሲ ነው፡፡

Friday, 31 October 2014 11:35

የቡርኪናፋሶ ፓርላማ ህንፃ አመፅ ባስነሱ የሀገሪቱ ዜጎች መቃጠሉ ተነገረ፡፡

ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም

ከኡጋዱጉ የተሰማው ዜና የሀገሪቱ ፓርቲዎች ዋነኛ መቀመጫ የሆነውና በመሃል ከተማዋ የሚገኘው ፓርላማ ህንፃ የህዝብ አመፅን ባነስነሱ ሃይሎች የእሳት ቃጠሎ እንደደረሰበት ነው የተነገረው፡፡

የሀገሪቱ ፓርላማ የቀየረው ህገ-መንግሥት ፕሬዝዳንቱን ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል መባሉ አመፁን እንዳስነሳና ፓርላማውንም ለማቃጠላቸው ምክንያት እንደሆነ የዜና ምንጮች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

1987 እ.ኤ.አ ስልጣን እንደያዙ የተነገረው ፕሬዝዳንቱ አራት የምርጫ ዘመኖችን አሸናፊ በመሆን በስልጣን ላይ መቆየታቸው ተነግሯል፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በቀጣዩ የምርጫ ዘመን እንዲመርጧቸው እና አዲሱ መንግሥት ሀገሪቱን እንዲያስተዳደር ጥሪ እያደረጉ ባለበት ወቅት ይህ አደጋ መከሰቱ ጉዳዩን ወደባሰ ነውጥ ውስጥ ይከተዋል የሚል ስጋት እየፈጠረ ይገኛል ብሏል፡፡

ይህ ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ በወጡ ዜናዎች ፕሬዝዳንት ብሌይስ ኮምፓወሬ ይፋዊ የሆነ ንግግር ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ንግግራቸው 2015 የእኔ ስልጣን ዘመን ማብቂያ ጊዜ ነው፤ ከዛ በፊት ስልጣኔን አለቅም ማለታቸው ተነግሯል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት በምዕራብ ሀገራት ጉብኘት ለማድረግ እየተሰናዱ ባለበት በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የህዝቦች ዓመፅ ለማረጋጋት ልዩ መልዕክተኛ ወደ ቡርኪናፋሶ ተልኳል፡፡ ሞሃመድ አቢን ቻምባስ ዛሬ ማለዳው ላይ ወደ ሀገሪቱ እንዳቀኑ የተነገረ ሲሆን ሰላማዊ ድርድር እንዲካሄድና ህዝቡ በፕሬዝዳንቱ ስልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ ከመግባባት እንዲደርሱ እንደሚያደርጉ ታምኗል፡፡ ዜናው የሮይተርስ ነው፡፡

Friday, 31 October 2014 10:53

የኢራቅ የፔሽመርግ ተዋጊዎች ወደ ኮባኒ ግዛት መግባታቸው ተነገረ፡፡

ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም

በቱርክ ድንበር በማቋረጥ ወደ ኮባኒ የገቡት ተዋጊዎች የአይ ኤስ ፅንፈኛ ቡድን ለመዋጋት ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ነው የተሰማው፡፡ 150 የሚጠጉ የኢራቅ የኩርድ ተዋጊዎች በቱርክ ቆይታ ያደረገ ሲሆን ቱርክ በግዛቷ እንዲተላለፉ ከፈቀደች በኋላ ነው፡፡ ይህም የአይ ኤስ ታጣቂ ቡድን የያዛቸውን ስፍራ እንዲለቅ ያስችለዋል የተባለ ሲሆን የሶሪያ ኩርዶችን ለመደገፍም ያግዛል ተብሏል፡፡

እስካሁንም 200 የሚጠጉ የፔሽመርግ ተዋጊዎች ወደ ስፍራው አቅንተዋል ተብሏል፡፡ ከእሮብ ጀምሮ በአሜሪካ በተፈፀመ የአየር ጥቃት የአይ ኤስ ዋና ፅ/ቤት የሆነውን ህንፃ ዴር ኢዝዞር እና የፀጥታ ቢሮ እንዳወደሙ ተነግሯል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

Thursday, 30 October 2014 10:36

ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሶማሌያዊያን የሰብዓዊ እርዳታን ይፈልጋሉ ተባለ፡፡

ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን ናቸው ይህን የተናገሩት፡፡ በሶማሌያ ጉብኝት በማድረግ ላይ የነበሩት ባንኪሙን በቀጠናው ባለው ጦርነትና የሰላም እጦት መነሾነት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በየዕለቱ የምግብና የንፁህ መጠጥ ውሃ ብሎም የጤና እርዳታን እያገኙ አይደለም ያሉ ሲሆን በተለይም የሶማሌ ህዝብ ለዓመታት ከኖሩበት ሁከትና የአሸባሪዎች መናኸሪያ መሆን መንሻነት ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ህዝቦች የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ባለፈው የፈረንጆቹ መስከረም ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ቡድን ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የምግብ እና መሰረታዊ ፍላጎቶች እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ስጋት እንደሆኑ ያረጋገጡ ሲሆን በ2011 እ.ኤ.አ ከተከሰተውና 260,000 ሰዎችን ለሞት ካበቃው ድርቅ ባልተናነሰ ሁኔታ ጉዳትን እንደሚያስከትልም ጠቁመዋል፡፡ ዘገባው የሮይተርስ ነው፡፡

Thursday, 30 October 2014 10:31

ህንድ ለቬትናም የጦር መርከቦችን ልታቀርብ እንደሆነ ታወቀ፡፡

ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ቬትናምን እየጎበኙ የሚገኙ ሲሆን በጉብኝታቸው ላይ ይህንን እንደተናገሩ ነው የተሰማው፡፡

ከቻይና ጋር በግዛት ይገባኛል ቬትናም ክርክር ውስጥ መግባቷ የሚታወስ ነው፤ ታዲያ ይህንኑ የቻይናን ተፅእኖ ለመከላከል ወታደራዊ አቅሟን ለማጠንከር ሳትወሰን አልቀረችም ተብሎላታል፡፡

ህንድ በቬትናም የሃይል ዘርፍ አቅርቦት ላይ ለመሳተፍም ፍላጎት ያሳየች ሲሆን የጦር መርከቦችን ለማቅረብ ማቀዷ ደግሞ ነገሩን የበለጠ እንዳያከረው ተሰግቷል፡፡ የቬትናሙ ሚኒስትር ኑጉዩን ታን ዱግ እና የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ቻይና በቀጠናው እያሳደረች ያለውን ስጋት በጋራ ለመመከት መስማማታቸው ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ቻይና ምንም ምላሽ አለመሰጠቷን ሮይተርስ ነው የዘገበው፡፡

Wednesday, 29 October 2014 14:10

የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሳታ መሞታቸው ተሰማ፡፡

ጥቅምት 19/2007 ዓ.ም

ዛሬ ማለዳው ላይ ከሀገሪቱ ታማኝ ምንጮች ሰማሁ ብሎ የተናገረው AFP ፕሬዝዳንቱ በእንግሊዝ ለንደን የህክምና ክትትል ያደረጉ በነበረበት ወቅት ነው ህልፈታቸው የተሰማው፡፡

የዛምቢያ ባለስልጣናት ከሉሳካ ምንም ያሉት ነገር የለም የተባለ ሲሆን ዘኢንዲፔንደንት ዛምቢያ  የተባለው የዜና ምንጭ እና የሀገሪቱ የወሬ ምንጮች ትክክለኝነቱን ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱ ፓርላማም መሞታቸውን በይፋ ተናግሯል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳታ ከባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ በኋላ ከህዝብ አይን እርቀው ነበር የተባለ ሲሆን በሀገሪቱ ማድረግ የሚገባቸውን ህዝባዊ ገለፃም እንዳላደረጉ ተነግሯል፡፡

በፈረንጆቹ መስከረም 19 ቀን ላይ ለሀገሪቱ ፓርላማ አልሞትኩም የሚል መልዕክትም ልከዋል የተባሉት ፕሬዝዳንቱ በለንደን ረዘም ያለን ጊዜ በህክምና ክትትል ሲያሳልፉ እንደነበር የዜና ምንጮች ተናግረዋል ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሳታ የ77 ዓመት አዛውንት እንደነበሩም ተነግሯል፡፡ ዘገባው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡

Tuesday, 28 October 2014 10:53

በላይቤሪያ ይኖሩ የነበሩ ኬንያውያን ከኢቦላ ጋር በተያያዘ ሳይያዙ አይቀሩም በሚል ወደ ሀገራቸው እንዲላኩ ተደረገ፡፡

ጥቅምት 18/2007 ዓ.ም

ካፒታል ኒውስ ዛሬ ባወጣው ዜና እንደተናገረው በላይቤሪያ ይኖሩ የነበሩና በእርዳታ መስጫ ተቋም ውስጥ የተሰማሩ የነበሩት 12 ያህል ኬንያውያን ናቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገው፡፡

ከ5000 በላይ ምዕራብ አፍሪካውያን በኢቦላ ምክንያት ሞተዋል የሚለው ዘገባው ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ላይቤሪያውያን እንደሆኑ ተናግሯል፡፡

ኬንያ የአየር በረራን አለማቋረጧን ተከትሎ የህዝቦቿ ስጋት እያየለ እንደመጣ የተነገረ ቢሆንም እስካሁን በተደረገ ምርመራ አንድም ኬንያዊ ላይ ቫይረሱ እንዳልተገኘ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

የሀገሪቱ የጤና ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ እንደተናገሩት ኬንያ በአሁን ወቅት ከኢቦላ ነፃ ከሆኑ ሀገራት ተርታ የምትመደብ ስትሆን ለቱሪስቶችም አስጊ አይደለምች ብለዋል፡፡

አሁን በላይቤሪያ በቫይረሱ ተይዘዋል የተባሉት 12 ኬንያውያን የተለየ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውና ከህዝብም እንዳይገናኙ እንደሚደረግ ተያይዞ ተነግሯል፡፡ ዘገባው የካፒታል ኒውስ ነው፡፡

Tuesday, 28 October 2014 10:30

ጋና እና ሱዳን ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

ጥቅምት 18/2007 ዓ.ም

በጋና የሱዳን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ባቢኪር ኤልሲደግ ሞሀመድ ኤላሚን የጋና ፖሊስ እና መንግሥት ከሱዳን ፖሊስ እና መንግሥት ጋር በመተባበር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያለውን የመከላከልና አዘዋዋሪዎችንም በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተለይም ከኤርትራ፣ ሱማሊያ እና ኢትዮጵያ የሚገቡ ህገ-ወጥ ስደተኞች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው ያሉት አምባሳደሩ ወደ ጣልያን እና እስራኤል እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ለመግባት ሱዳንና ጋናን መሸጋገሪያ ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ ለሀገራቱ ደህንነት ስጋት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ጋና ለጎብኚዎች ምቹ እና ሰላማዊ ሀገር ከመሆኗ ባሻገር ህገ-ወጥ ስደተኞችንና አዘዋዋሪዎችን ለመቆጣጠርም ተመራጭ ሀገር ነች፡፡ ስለሆነም ትልቅ ሚና መጫወት ይጠበቅባታል ሲሉ አክለዋል፡፡ ዜናው የኦል አፍሪካ ነው፡፡

Thursday, 23 October 2014 09:20

ሰሜን ኮሪያ በቁጥጥ ስር ያዋለቻቸውን አሜሪካዊ መልቀቋን አስታወቀች፡፡

ጥቅምት 13/2007 ዓ.ም

ጂፍሪ ፎል የተለቀቁት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በፕሬዝዳንት ኪም ዩንግ ኡን ትዕዛዝ መሰረት መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የ56 ዓመቱ ፎል አስፈላጊውን የህግ ሂደት ተከትሎ ለአሜሪካ ባለስልጣናት ተላልፎ መሰጠቱን የሰሜን ኮሪያ የዜና ወኪል አስታውቋል፡፡ ፎል ወደ ሰሜን ኮሪያ የገቡት ባለፈው ሚያዝያ ወር ሲሆን የተያዙትም በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ የሃይማኖት መፅሃፍ ትተው ከወጡ በኋላ ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ሃይማኖት ለመስበክ መግባት በወንጀል ድርጊት ያስቀጣል፡፡ የፎል ቤተሰቦች ግን ግለሰቡ ለዚሁ ተግባር ወደ ሰሜን ኮሪያ አለማቅናታቸውን አስተባብለዋለ፡፡ ዘገባው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡

Tuesday, 21 October 2014 10:09

የቻይና መንግሥት በኢቦላ ለተጠቁ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት እርዳታ አደረገች፡፡

ጥቅምት 11/2006 ዓ.ም

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እያደረገ ያለውን ስርጭቱ የተዛመተባቸውን እና በርካቶች እየሞቱበት ያለው የኦቦላ ቫይረስ ለመከላከልና አስተማማኝ የጤና ክትትልና ህዝቦችን የመርዳት ተግባሩን ያግዝለታል የተባለለትን የገንዘብ እርዳታ ነው የቻይና መንግሥት አደረገች የተባለው፡፡

ጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን የ6 ሚሊዮን ዶላር እርዳታን ከቻይና መንግሥት ያገኙ ሀገራት ሲሆኑ እኩልም ይካፈላሉ ተብሏል፡፡

ሶስቱ ሀገራት በኢቦላ ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቁና ህዝቦቹም የምግብ እጥረት እያጋጠማቸው በመሆኑ መመረጣቸው ተነግሯል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለአንድ ወር ያህል የሚቆይ ከ300,000 በላይ ህዝቦችን ሊመግብ የሚች ገንዘብ ማግኘታቸውን የተናገሩ ሲሆን ሩዝ እና የመሳሰሉትን የምግብ አይነቶችን እንደሚገዙ ተናግረዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምዕራብ አፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር ዴኒስ ብራውን የቻይናን መንግሥት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦችን እናመሰግናለን፤ በአስቸጋሪ ጊዜ ላይ በነበርንበት ወቅት ላይ ነው ይህን እርዳታ ያደረጉልን ብለዋል ሲል የቻይና ዴይሊ ድረ-ገፅ አስነብቧል፡፡

Monday, 20 October 2014 13:06

ኬንያን ከሶማሊያ በሚያገናኛት ድንበር ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ የኬንያን ፖሊስ ሃይል መሪ መግደሉ ተነገረ፡፡

ጥቅምት 10/2007 ዓ.ም

በሊቦይ ድንበር መሪው በተደጋጋሚ በጥይት መደብደቡ የተገለፀ ሲሆን ወደቤቱ እያቀና ባለበት ሰዓት መሆኑም ታውቋል፡፡

አንዳንድ እማኞችን ይዘናል የሚሉ ምንጮች እንደሚሉት፤ ጥቃት አድራሾቹ ተኩስ ከመክፈታቸው በፊት አራት ሆነው የፖሊስ መሪውን ይከታተሉ ነበር፡፡

ከሶማሊያ 18 ኪ.ሜ በምዕራብ በኩል ርቆ የሚገኘው ሊቦይ በእጅጉ የተጨናነቀ የገበያ ማዕከል ነው፡፡ ከሌሎች ከተሞች አንፃር ሲታይም ብዙ ጥቃትና ሽብር የማይከሰትበት ነው፡፡ የታጣቂዎቹ ማንነት እስካሁን በውል ባይታወቅም ክትትል እንደሚደረግባቸውና ለፍርድ እንደሚቀርቡም የኬንያ የፀጥታ ሃይል ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡ ዘገባው የደይሊ ኔሽን ነው፡፡

Friday, 17 October 2014 11:51

ቻይና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመጣመር ፅንፈኝነትን እና አሸባሪነትን ለመግታት ተስማማች፡፡

ጥቅምት 07/2007 ዓ.ም

የትብብር ስምምነቱ የተጠናከረ ህብረት በመፍጠር ታጣቂ ቡድኖችን ለማዳከም ያለመ ነው ተብሏል፡፡ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር  ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ከሆኑ ማኑኤል ባሩሶ እና ከአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቫን ሮምፑይ ጋር መወያየታቸው ነው የተነገረው፡፡ በጣሊያኗ ሚላን እየተካሄደው ባለው በዚሁ ውይይት የመካከለኛው ምስራቅ እና ወቅታዊ ሁኔታዎች በዋናነት ተነስተዋል፡፡ በተጨማሪም ዩክሬንን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርህ መሰረት ወደ መረጋጋት መምጣት እንድትችል የአውሮፓ ህብረት መሪዎች እና የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስት የትብብር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡