Super User

Super User

Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ 158 የንግድ ድርጅቶችን ፍቃድ አገደ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ 189‚328 የንግድ ቤቶች ላይ ባደረገው መደበኛ ቁጥጥር 158 የንግድ መደብሮች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ይዘው በመገኘታቸውና በህገ ወጥ ንግድ ላይ ተሳትፈው ስላገኘዋቸው አግጃቸዋለው ብሏል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ከክፍለ ከተማና የወረዳ የፀረ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ ግብረ ሃይል ጋር በመሆን በሰራው ስራ ፍቃዳቸው ከታገደባቸው የንግድ መደብሮች በተጨማሪ 8‚597 የንግድ መደብሮች ታሽገው እንዲቆዩ የተወሰነ ሲሆን 13 ሺህ የንግድ ድርጅቶች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 289 ሺህ የንግድ ፍቃድ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
ዘገባው የምትኬ ቶሌራ ነው፡፡

መንግስት በአዲስ አበባ ከሚገኙ 6 ነዋሪዎች መካከል 1 ሰው በኮንደሚንየም ይኖራል ቢልም፤ ለ40/60 የተመዘገቡ ቅሬታ አቅራቢዎች በበኩላቸው የመንግስት አካላት ህጉን እንደፈለጉት በመቀያየራቸው እምነት አተናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

ሙሉ ክፍያውን ብንከፍልም መንግስት ቃሉን ሳያከብር ከውል ወጪ እጣ ማውጣቱ አግባብ አይደለም ሲሉ በ40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች ቅሬታቸውን ለዛሚ ኤፍ ኤም አሰሙ፡፡ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አቶ ጎህሽ ሀይሌ እንደሚሉት ከሆነ ምዝገባው ከተጀመረ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ሙሉ ክፍያውን ያጠናቀቀ ማንኛውም ግለሰብ ቅድሚያ እንደሚያገኝ ውል ገብተናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የቅሬታ አቅራቢዎቹን ጥያቄ በተመለከተ የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተር ፕራይዝ የኮሚዩንኬሽን የስራ ሂደት መሪ አቶ ዮሀንስ አባይነህ ይህ ጉዳይ እኛን አይመለከትም በማለት ምላሻቸውን ሰተዋል፡፡
ለዓመታት ሙሉ ክፍያውን ከፍለን የቤት ባለቤት ለመሆን በመጠባበቅ ላይ እያለን ሐምሌ 1 2009 የ40/60 የቤቶች እጣ እንደሚወጣ እና በእጣው የሚካተቱት ከምዝገባው ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት የከፈልነው ብቻ ሳንሆን ለአንድ አመት ከስድስት ወር ያህል የቆጠብትንም ያጠቃልላል የሚለውን አስደንጋጭ የዕለተ ሀሙስ መግለጫን ስንሰማ ወደ ሚመለከተው የንግድ ባንክ ሀላፊ በማምራት አካሔዱ ትክክል አለመሆኑን ተነግሮናል ይላሉ ቅሬታ አቅራቢው፡፡

ለቅሬታ አቅራቢዎቹ የተሰጠው ምላሽ ትክክል ስለመሆኑና የቆጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ይመለከተዋል ስላለው ጉዳይ ለማነጋገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሚዮንኬሽን ተቀዳሚ ስራ አስኪያጅ የሆኑትን ሀላፊ ለማነጋገር ብንሞክርም ዛሬ ላይ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ አሳውቀውናል፡፡በየትኛውም አሰራር ቢሆን ህግ ወደ ኋላ አይመለስም እናም በሌለ ህግ ነው የተዳኘነው ሲሉ አቶ ጎህሽ ሀይሌ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ 6 ስዎች መካከል 1 ሰው በኮንደሚንየም ውስጥ መኖር መጀመሩን ሀምሌ 1 2009 ዓ.ም በነበረው የቤቶች ማስተላለፍ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል፡፡

ሀምሌ 1 2009 ዓ.ም በተላለፉት 972 የ40/60 ቤቶች መካከል ባለ 4 መኝታ ቤቶች ይገኙበታል ከቤት ፈላጊዎች ፍላጎት እና ውል ውጪ ለምን ባለ 4 መኝታ ቤቶች ተገነቡ ለሚለው ጥያቄ አቶ ዩሀንስ አባይነህ የአበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተር ፕራይዝ የኮሚዩንኬሽን የስራ ሂደት መሪ እንደሚሉት ከሆነ የዲዛይን ለውጥ መምጣቱ እና የንግድ ባንክ ዋነኛ የጉዳዩ ባለቤት በመሆኑ ገንቡ ስንባል ገንብተዋል ሲሉ ምላሽ ሰተዋል ፡፡በውሉ መሰረት ባለመስራቱ በመንግስት ላይ እምነት ያሳጣናል ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ከ 972ቱ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የ 320 የንግድ ቤቶቹ በጨረታ እንደሚተላለፉ በዕለተ ቅዳሜ ተነግሯል፡፡ በ 40/60 የቤት ልምት ተጠቃሚ ለመሆን ከ 166 ሺ የቤት ፈላጊዎች ሲመዘገቡ 17 ሺ 644 ተመዝጋቢዎች መቶ ፐርሰንት ክፍያቸውን አጠናቀዋል፡፡41300 የሚሆኑት ደግሞ 40 ፐርሰንት ክፍያቸውን ማገባደዳቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡

ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው

ኢትዮጲያ ብሄራዊ የንባብ ቀን ሊኖራት ነው ፡፡
ከ2006 ዓም ጀምሮ በየዓመቱ ሰኔ ሰላሳ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ የንባብ ቀን ሆኖ እንዲከበር በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ጥረቶች ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ በአገሪቱ ደረጃ ብሄራዊ የንባብ ቀን ሆኖ ሊከበር ነው ተባለ፡፡
የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ለአራት አመታት የዓመቱ ተማሪዎች መደበኛ የትምህርት ሲያልቅ ከንባብ ጋር እንዳይቆራረጡና ይበልጥ ከመጸሀፍት ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ የሰኔ ሰላሳ የንባብ ቀን መከበር መጀመሩን የገለፁት የኢትዪጲያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ሙሴ ያዕቆብ በቅርቡ ይህ የንባብ ቀን ለፓርላማ ቀርቦ ብሄራዊ የንባብ ቀን ይሆናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ላለፉት 57 ዓመታት በኢትዮጲያ የስነ ፅሁፍ የዕውቀትና የንባብ ባህል እድገት እንደተወጡት ሚና ደራሲያኑ ከብዕር ትሩፋቶቻቸው መጠቀም ያለባቸውን ያህል እንዳልተጠቀሙና ቤት ንብረት ያላፈሩ በመሆናቸው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ ደራሲያን ፅሁፎቻቸውን ለማሳተም የገንዘብ አቅም ፈታኝ የነበረ ሲሆን በተዘዋዋሪ የህትመት ፈንድ ስርዓት ቀደም ሲል ከአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ከሩብ ሚሊየን ብር በላይ አጫጭር ታሪኮች መታተማቸውን በኃላም ከብራንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋር በመሆን በሶስት ሚሊየን ብር ድርሰቶቻቸውን ማሳተም ላልቻሉና ማህበተሩ የመረጣቸው ስራዎች መታተማቸውን የገለፁት ደራሲ አይለመለኮት መዋዕል አሁን ላይ ከየካቲት ወረቀት ስራዎች ድርጅት ጋር ውል ተፈራርመዋል፡፡
የኢትዮጲያ ደራሲያን ማህበር ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን ከሐምሌ 1እስከ 5 ድረስ የንባብ ቀኑ ይከበራል፡፡
ምትኬ ቶሌራ

በየአውራ መንገዱ ተሰምሮ የነበረው እና ከጊዜያት በኋላ የት እንደገባ ያለታወቀው ቢጫ ሳጥን ህግ ወቶለት ዳግም ስራ ሊጀምር ነው፡፡
ቢጫ ሳጥን ወይም የሎው ቦክስ በተለይ የትራፊክ ፍሰቱ ከፍተኛ በሆነባቸው የመስቀለኛ መንገዶች ላይ የመስቀለኛ መንገዶቹን የክልል ቅርፅ እንደ አስፈላጊነቱ የያዘና በየመንገዱ ላይ በግልፅ ሁኔታ ተቀብቶ የትራፊክ ፍሰቱን በቅደም ተከተል ለማስተናገድ የሚረዳ የቢጫ ቀለም ቅብ ማለት ነው፡፡
ከነዚህ ቦታዎች በተጨማሪ በሆስፒታሎች ውስጥ የድንገተኛ እርዳታ ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ለሚሄዱ ተሸከርካሪዎች ሌሎች ተሸከርካሪዎች ቆመው መተላለፊያውን እንዳያውኩ የቢጫ ሳጥንን በመጠቀም አከባቢውን ለተረጂዎች ግልፅ ማድረግ የሚያስችል የትራፊክ መብራት አጋዥ አሰራር ነው፡፡
በወቅቱ ስራ ላይ የነበረው የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በቢሮው የትራንስፖርት ዘርፍ የካቲት 26/2006ዓ.ም ይፋ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ቦታዎች ላይ ተግባራዊ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው መንገዶች ላይ የተቀቡት ቢጫ ሳጥኖች አገልግሎታቸው ሳይታወቅ ተሰውረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የመንገድ ደህንነትና አቅም ግንባታ ዋና የስራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ ሀገሬ ሀይሉ ቀድሞ የትራፊክ ደንብ ላይ ህግ ስላልወጣለት እንዲቋረጥ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለአገልግሎቱ መቋረጥ ቀድሞ በትራፊክ ህግ ውስጥ መግባት ባለመቻሉ ነው የሚሉት ሀላፊው ጠቀሜታው ታምኖበት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ ህጉ ለምን አስቀድሞ አልታሰበበትም ለሚለው ጥያቄ አቶ ሀገሬ ሀይሉ በምላሻቸው ለሙከራ የተጀመረ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ዳግም ይህንን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ አጥፊዎችን መቅጣት የሚያስችል ደንብ ቁጥር 395/2009 ማሻሻያ ተደርጎበት እንደወጣ ሀላፊው ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡ከዚህ በፊት ለአንዱ የከተማችን አደባባይ ብቻ 80 ሺህ ብር ወቶበታል የተባለው የቢጫ ሳጥን አገልግሎት መች እንደሚጀመር ሀላፊው በውል እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡
ወደፊት ይተገበራል በተባለው የቢጫ ሳጥን መስቀለኛ መገጣጠሚያ ላይ ሲደርሱ አሽከርካሪዎች የቢጫ ሳጥን ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ወደሚሄዱበት አቅጣጫ ያለው መንገድ በበቂ መልኩ ለጉዞአቸው ክፍት መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይገባቸዋል፡፡በቢጫ ሳጥን ውስጥ ገብቶ መቆም የትራፊክ ፍሰቱን ከማስተጓጎሉም በላይ ህጉ ተግባራዊ ሲደርግ የደንብ መተላለፍ ቅጣትን ያስከትላል፡፡እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አከባቢ የቢጫ ሳጥን አሰራር እንግሊዝ፣ አየር ላንድ፣ካናዳ፣አውስትራሊያ፣ሰሜን አሜሪካ፣ሆንግ ኮንግ ብራዚል እና ራሺያ ረዘም ላለ ጊዜ በህግ ደረጃ ተቀብለው ከተገበሩት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው::

በአገሪቱ ከሚገኙ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ውስጥ 373ቱ ከደረጃ በታች መስራታቸው ተገለፀ፡፡
በኢትዮጲያ ውስጥ ከሚገኙ 1371 በጥቃቅንና አነስተኛ ዘፍር የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ውስጥ 373 በተቀመጠላቸው መመዘኛ መሰረት ከስልሳ እጅ በላይ ውጤት ባለማስመዝገባቸው ከደረጃ በታች መስራታቸው ተገልፃል፡፡
የፌደራል የከተሞች የስራ ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ባለሙያ አቶ አብይ ጌታሁን ለዛሚ እንደተናገሩት የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሲቀር በሁሉም ክልሎችና በአዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር በአፈፃጸማቸው ከስልሳ እጅ በታች ያስመዘገቡ ተቋማት ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
ተቋማቱን ለመለየት መመዘኛ መስፈርቱ ስራ አጦችን ከመመዝገብ መለየት አንስቶ ስልጠና እንዲያገኙ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ያላቸው ግኑኝነት ቁጣባ ሚቆጥቡና ብድርና የወሰዱት ብድራቸውን እንዲመልሱ ያደረጉት ክትትል እንደ መስፈርትነት ተይዟል ብለዋል፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ለሚደራጁ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ከመስፈርቶቹ 90 እጅ በላይ በማምጣት በአንደኝነት ደረጃ ላይ የተቀመጡት 88 ቱ ሲሆኑ ከአንድ እስከ አራት በወጣው ደረጃ የኦረሚያ ክልል 605 ተቋማቱን ሲያስመርጥ ጋምቤላ ክልል ሶስት ብቻ ማስመረጡ ተገልፃል፡፡
ለተቋማቱ ከስልሳ እጅ በታች አፈፃፀም ማስመዝገብ የሰው ሀብት ሃይል ችግር ቁሳቁስ በአግባቡ አለመደራጀት የአቅም ውሱንነት እንደ ምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
በምትኬ ቶሌራ

የኮሌራ በሽታ በየመን በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ ፡፡
የተባበሩት መንግስታት እንዳመለከተው፤ በዓለም ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትለዉ የየመን ውሃ ወለድ ኮሌራ በመቀስቀሱ ከ220ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸዉንና ከ1ሺ 300 በላይ የመናዊያን በበሽታው ህይወታቸው ማለፉን አክለዉ ገልፀዋል ፡፡
ከሟቾቹም መካከል ገሚሶቹ ህጻናት መሆናቸውን ድርጅቱ አስታዉቋል፡፡ በሽታው ጦርነቱ በተፋፋመባቸው ከተሞች በተለይም ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በከፍተኛ በፍጥነት እየተዛመተ ነው ያለው ድርጅቱ በቀን እስከ 5ሺ የሀገሪቱ ሰዎች በኮሌራ እየተያዙ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታትና ዩኒሴፍ በጋራ በሽታውን ለመግታት የተቻላቸውን እያደረጉ ቢሆንም ጦርነቱ የሽታውን መዛመት ለመቆጣር አስቸጋሪ እንዳደረገባቸዉም ገልፃዋል ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የየመን ጤና ተቁማት ፣ውሃና ፍሳሽ ከሁለት ዓመት በፊት መዘጋታቸው ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ድርጅቱ አስረድተዋል ፡፡
ሲኤንኤን ጠቅሳ ትብለፅ ተስፋዬ ዘግባዋለች

ኢትዮጲያዊው ጆኒ ግርማ በአለማቀፍ ደረጃ ከቀረቡ 338 ፕሮጀክቶች ውስጥ ፕሮጀክቱ ምርጥ አስር ውስጥ ገባ፡፡
ኢትዮጲያዊው ጆኒ ግርማ በአለም አቀፍ ደረጃ 338 ፕሮጀክቶች ለውድድር በቀረቡበት ዓለማቀፍ ውድድር ከተወዳደሩ ውስጥ የመጨረሻ ዙር የተመረጡ 10 እጩዎች ውስጥ መግባት ችሏል፡፡
ጆኒ ግርማ በደቡብ ምዕራብ አከባቢ የገጠር ሥራ አጥ ወጣቶችን ያሳተፈ ዘላቂ ኦርጋኒክ የማር ምርት ለማምረትና ኤክስፖርት ለማድረግ እየሰራ ይገኛልም ተብሏል፡፡
ቀን በቀን እየጨመረ ከሚገኘው የአለም ህዝብ ጋር ተያይዞ የግብርና ስራ የአለምን ስነ ምህዳር እና በውስጧ የሚገኙት ህይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ የህይወት ጉዞ የተመቻቸ እንዲሆን ያግዛል የተባለ ሲሆን ፡፡
ፕሮጀክቶቹም የሰው ልጅ ለምግብ ለዕለት ተዕለት ፍጆታቸው የሚጠቀሙበበት ከመጠን የዘለለ የግብርና ምርቶች ተጠቃሚነት የአለምን ገፅታ እንዴት እንደቀየሩ የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል፡፡
ሽልማቶቹ የሚደረጉት በአራት ቡድኖች ተከፋፍሎ ሲሆን ጥናቶቹ በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድሩት ተፅህኖ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አሊያም በስነ ምግብ ዙሪያ ያለው ተፅህኖ በባዮ ዳይቬርሲቲ እና በውሀ ዙሪያ የግብርና ውጤቶች ያላቸው ተፅህኖ ከግምት ውስጥ ይገባል ተብሏል፡፡
ጆኒ ግርማ በመጪው ህዳር ወር በጀርመን ሀገር ተገኝቶ ፕሮጀክቱን እንደሚያቀርብ እንዲያቀርብ መጋበዙ የታወቀ ሲሆን ፡፡
አሸናፊዎችን ለመለየት ቀጥታ የህዝብ ምርጫ የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጲያዊውን ጆኒ ግርማን ለመምረጥ Apis Agribusiness" የሚለው ሥር vote ማድረግ ይቻላል ተብሏል፡፡
እሰከ አርብ ሰኔ 30 ድረስ ድምፅ መስጠት ይቻላሉ፡፡ እባክዎን ያለችው አጭር (አራት ቀናት) ስለሆነ ፈጥነው ይምረጡ፡፡
መረጃውን ከሶሻል ሰርች ላይ ያገኘን ሲሆን ምትኬ ቶሌራ ዘግባዋለች ፡፡

የሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ያላቸው ሁሉ በቀጣይ በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ላይ ጣልቃ እንዳይገቡ አስጠነቀቁ፡፡
በአገሪቱ ያለው የዲፕሎማሲ ተልዕኮ አላማው የአገሪቱን የምርጫ ኮሚሽን የሚተካ ወይም ሊተካ የሚችል መሆን የለበትም ብለዋል፡፡ አክለውም ባደረግነው ምርጫ ሌሎች ጣልቃ ገብተውብናል እያሉ የሚያለቅሱት ሰዎች እራሳቸው በሌሎች ምርጫ ላይ ጣልቃ ይገባሉ ብለዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ ይህንን ያሉት የአውሮጳ ሕብረት የምርጫ ኮሚሽን በአገሪቱ በሚደረገው ምርጫ ላይ ተወካይ ለመላክ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኃላ ነበር፡፡ ካጋሜ እንዳሉት የፈለጉት ዕጩ ተወዳዳሪ እንዲያሸንፍ ለማድረግ ቢችሉ ከማድረግ ወደ ኃላ አይሉም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ከምዕራብያውያን የሚደረግ ጫናን በጽኑ ለመከላከል በሚል ከተለያዩ አገራት የሚገቡ የተለበሱ ልብሶችን ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ውሳኔ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፖል ካጋሜ በቀጣይ በአገሪቱ የሚደረገው ምርጫ ላይ ለሶስተኛ ግዜ እንደሚወዳደሩ ይታወቃል፡፡ በምርጫውም ግሪን ዲሞክራቲክ የተሰኘው ፓርቲ መሪ የሆኑትን ፍራንክ ሃቤኔዛ ይገጥማሉ ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

ደቡብ ሱዳን የስዋሂሊ ቋንቋ የአገሪቱ ይፋዊ መግባቢያ እንዲሆን ልታደርግ ነው፡፡
የስዋሂሊ ቋንቋ በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (EAC) አባል በሆኑ አገራት ይተገበራል:: ደቡብ ሱዳንም የዚህ ማህበረሰብ አባል ለመሆን ከሚጠበቅባት ነገሮች መካከል አንዱ ቋንቋውን መጠቀም ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብን መስራች ከሆኑት አገራት መካከል ኬንያ፣ ዩንጋዳ እና ታንዛኒያ ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ጎን ለጎን የስዋሂሊ ቋንቋን ይፋዊ ቋንቋቸው አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
ሩዋንዳ ከብሔራዊ መግባቢያዋ ኪንያሩዋንዳ፣ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዘኛ ቀጥሎ በአራተኝነት መግባቢያዋ እንዲሆን ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ነች፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት የስዋሂሊ ቋንቋን እንዲያስተምሩለት በማሰብ ከታንዛኒያ መምህሮች እንዲመጡ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ጥያቄውን ያቀረቡት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝደንት ታባን ዴንግ ሲሆኑ ጥያቄውንም ያቀረቡት የአፍሪካ ሕብረት ከተጠናቀቀ በኃላ እንደሆነ የታንዛኒያው ምክትል ፕሬዝደንት ሳሚያ ሃሰን ለሲቲዝን ለተባለው የዜና አውታር ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የጤና፣ የግብርና እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ታባን ዴንግ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
ዘገባው የአፍሪካ ኒውስ ነው፡፡

ሚካኤል ጌታሠጠኝ

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ በሚፈለገው መጠን ብድርን የሚደፍር ትውልድ መገንባት አልተቻለም ሲል በሌላ በኩል ከአጠቃላይ ተጠቃሚዎቹ 80 በመቶ ለመበደር አላማ የሚመጡ ሆነዋል፡፡
የዜጎች ቀጣይ እድገት ሊመዘገብበት የሚችለው ቅደመ ቁጠባን በማዳበር ለሚፈልጉት ዓላማ ማስፈፀሚያ ብድር መወሰድ ነው ሲሉ የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ስሩር ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በቅድሚያ ቆጥቦ መበደርን ይፈራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት የህብረት ስራ ማህበራት መካከል አዋጭ የገንዘብ እና ብድር ተቋም አንዱ ሲሆን ተቋሙ እስከ መጋቢት 30/ 2009 ዓ.ም ድረስ 4893 አባላትን ማሰባሰብ ችሎአል፡፡ከዚህም ውስጥ 457 አባላት ለቤት መግዣ እና 338 ያህሉ ደግሞ ተሸከርካሪ ለመግዛት የተበደሩ ናቸው፡፡ የቁጠባ ባህሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይፋ ቢደረግም የተናጠል ቁጠባው አሁንም እድገት ማሳየት አለመቻሉን የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የፋይናንስ ህብረት ስራ ማህበራት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሀኑ ዱፌራ ለዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
የተበዳሪውን ማህበረሰብ ስጋት እና ፍራቻ ለመቀነስ አዳዲስ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው የሚሉት አቶ ዑስማን ስሩር በርካታ ገንዘብን ሰብስቦ በባንክ ማስቀመጥ ሳይሆን ለብድር አቅርቦት በማቅረብ ላይ ችግር በመኖሩ በሌላ በኩል የተበዳሪውን ፍላጎት ማርካት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመሰረታዊና ዩኒየን የገንዘብ ቁጠባና ህብረት ስራ ማህበራት እስከ አሁን 8.8 ቢሊዩን ብር ሲሰበሰብ 3.2 ቢሊዩን ብር ደግሞ ካፒታል ያስመዘገቡት ተቋማቱ አጠቃላይ ድምር 12 ቢሊዩን ብር በነዚህ የህብረት ስራ ተቋማት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የብድር አገልግሎት ለማግኘት ግለሰቦች በቅድሚያ የሚፈልጉትን የብድር መጠን 25 በመቶ ለተከታታይ 6 ወራት መቆጠብ እንዳለባቸው ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የተበዳሪዎችን መጠን በተመለከተ ከሚቆጥብት በላይ ለብድር የሚጠይቁት ገንዘብ ይልቃል የሚሉት ሀላፊው የብድር መጠኑ ከቆጣቢው ጋር ሲነፃፀር ተበዳሪው እንደሚልቅ ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ዘመናዊ የህብረት ስራ ከተጀመረ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን የህግ ድጋፍ አግኝቶ የተጀመረውም በንጉሱ ዘመን ነው፡፡ለመጀመሪያ ጊዜ የገበሬዎች የእርሻ ኅብረት ስራ ድንጋጌ ቁጥር 44/1953 ወጥቶ ስራ ላይ ውሏል፡፡ ለዚህ ድንጋጌ መውጣት ምክንያት የሆነው በከተማና በገጠር የነበረው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ሲሆን በከተማ የነበረውን ስራ አጥነትን ለመቅረፍ፣ከገጠር ወደ ከተማ የነበረውን ፍልሰት ለማስቀረት፣ በወቅቱ በመሬት ይዞታ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ለመፍታት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ዘገባው የነጋሽ በዳዳ ነው