ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ የአለም አቀፍ የሆቴል ማኔጅመንት የሚያስተዳድረው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በአዳማ ከተማ ስራ ሊጀምር ነው፡፡

Written by on October 22, 2017

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ 1ሺህ175 በላይ ባለ ኮከብ የሆኑ ሆቴሎችን የሚያስተዳድረው ሉቨር ሆቴል ግሩፕ ስር የሚተዳደረው የጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ብራንድ ነው በአዳማ ከተማ ስራ የሚጀምረው፡፡ የሆቴሉ ግንባታ በአሁኑ ወቅት አርባ በመቶ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ የኢንቨስትመንት በጀቱ አራት መቶ ሰባ ሚሊዮን እንደሚፈጅ ተግልጾል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዩሀንስ ጥላሁን እንዳሉት ከሆነ ሀገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ አለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች እንደሚያስፈልግ እና ሆቴሉ በክልል ከተማ መገንባቱ ከተማዋን የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአስመጪና ላኪነት የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት የአሁኑ የአዳማ ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ባለቤት አቶ በዙ በየነ በበኩላቸው ሆቴሉን በአዳማ ለመገንባት ዋነኛ አላማ አዳማ ከተማ የንግድ እና የመዝናኛ ከተማ ከመሆኗ ባሻገር ለአከባቢው ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላችንን ለማበርከት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ሆቴሉ አንድ መቶ ሰላሳ ሰባት ከፕሬዘደንሺያል እስከ እስታንዳርድ የእንግዳ ማረፊያዎች እና አራት ሺ ካሬሜትር ላይ ያረፈ የስብሰባ እንዲሁም ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚሆኑ አዳራሾች እንደሚገነቡ ተግልጾል፡፡

አለም አቀፍ ብራንዱን እና የሆቴሉን ባለቤት በማስማማት ያፈራረመው ኦዚ ሆስፒታሊቲ አማካሪ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ቁምነገር ተከተል እንደሚሉት ከሆነ አለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎች ወደ ክልል ከተሞች መግባታቸው አዲስ አበባ ላይ ብቻ የነበረውን የስብሰባ እና ሌሎች ዝግጅቶች ለክልሎች እድል የሚሰጥ በመሆኑ ፍትሀዊ የገበያ ድርሻ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል፡፡

ሆቴሉ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር በአከባቢው ካሉ ስዎች ጀምሮ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ሀገሪቱ ያላት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ቁጥር ከፍ በማድረግ ለአለም አቀፍ ዝግጅቶች ከተማዋን ተመራጭ እንደሚያደርጋት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የስራ ሀላፊ ተናግረዋል ሲል ነጋሽ በዳዳ ዘግቦታል፡፡


Reader's opinions

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


[There are no radio stations in the database]