“አንተ ማነህ ከተባልኩ መጀመሪያ ኢትዩጲያዊ ነኝ። የትኛው ብሄረሰብ ስባል ነው ሶማሌ የምለው“ – ፕ/ት አብዲ መሃመድ

Written by on December 27, 2017

“አንተ ማነህ ከተባልኩ መጀመሪያ ኢትዩጲያዊ ነኝ። የትኛው ብሄረሰብ ስባል ነው ሶማሌ የምለው“ – ፕ/ት አብዲ መሃመድ

/////////////////////

ትምህርት ሚኒስቴር የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች የሆኑ እና በኢትዩጲያ ሶማሌ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ፤እንዲሁም የኢትዩጲያ ሶማሌ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ሆነው በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን ከየሚገኙበት ዩኒቨርስቲዎች በጊዜያዊነት ለቀው በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው እንዲማሩ ከሁለት ወራት በፊት ወስኖ ነበር፡፡ በክልሎቹ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችም ይህ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
በኢትዩጲያ ሶማሌ ክልል የሚገኙት የጅግጅጋ እና የቀብሪድሀር ዩኒቨርስቲዎች የዘንድሮ የትምህርት ዘመናቸውን ጥቅምት አንድ ቀን ጀምረዋል፡፡ በዩኒቨርስቲዎቹ ይማሩ ከነበሩ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች አብዛኞቹ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጥሪ ተቀብለው ሄደዋል፡፡የተወሰኑት ግን አንሄድም ብለው ቀርተዋል፡፡

በአሁን ወቅት በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ስላለው የጸጥታ እና የመማር ማስተማር ስርአት ዛሚ በቦታው ተገኝቶ ተማሪዎችን እና የዩኒቨርስቲው ሰራተኞችን እንዲሁም አስተዳደሩን አነጋግሯል፡፡
#መምህር አብዱሎ ከኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ ነው የመጣው፡፡ በዩኒቨርስቲው የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በዚሁ ትምህርት ክፍል ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ በመምህርነት እንዲሁም በግቢ ጥበቃ እና ደህንነት አስተባባሪነት እያገለገለ ይገኛል፡፡

አሁን ስላለው የጸጥታ እና የመማር ማስተማር ሂደት ነግሮናል፡፡ለመምህር አብዱሎ ከዩኒቨርስቲው የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ኢትዩጲያውያን ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር ትእዛዝ ወደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ሲሄዱ እርሶ ለምን ቆዩ የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦለት ነበር፡፡
መምህሩ ተማሪዎቹ እና አንዳንድ መምህራን ግቢውን ለቀው በሄዱበት ወቅት ያልሄድኩት በግቢው ምንም አይነት ግጭት ስላልነበረ ነው፡፡ እነሱም የሄዱት በማህበራዊ ድረ-ገጽ ይለጠፉ የነበሩት መረጃዎች እንዲረበሹ ስላደረጋቸው ነው፡፡ብዙ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ የሆኑ መምህራን ያልሄዱም አሉ፡፡

ከተማሪዎችም መማር እንፈልጋለን ብለው መጥተው ተማሩ ተብለው አሁንም ድረስ ምንም እንኳን ከትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ ቢቀርብም መሄድ አንፈልግም ብለው የቀሩ አሉ ብለውናል፡፡ ክረምት ወራት ላይም ተማሪዎችም መምህራንም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ ተደርጎላቸው እንደነበር፤ ነገር ግን ከሚያውቋቸው የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ የሆኑ መምህራን ሶስቱ መሄዳቸውንም ተናግረዋል፡፡
ስጋት ገብቷቸው ሄደዋል ስለተባሉት መምህራን ዛሚ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ኡመር በጉዳዩ ላይ ለዛሚ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

#ምክትል ፕሬዚዳንቱ እነዚህን መምህራን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ተጠርተው ሄደው ውይይት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚያ በኋላም የተመለሱ መምህራን ያሉ ቢሆንም አሁንም ያልተመለሱም እንዳሉ አልካዱም፡፡
በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የአምስተኛ አመት የምህንድስና #ተማሪ የሆነው አንዱአለም አሰፋ ከደቡብ ብሄርብሄረሰቦች እና ህዝቦች ብሄራዊ ክልል ዳውሮ መጥቶ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በትምህርት ተቋሙ ያለውን የደህንነት ሁኔታ እንደተባለው አይደለም ሲል ይገልጸዋል፡፡ ተማሪው ከሌላ ቦታ የምንሰማቸው ወሬዎች ቢኖሩም እዚህ ጋር የምናየው ሁኔታ ሰላም መሆኑን ነው ብሏል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴርን ውሳኔ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች የተቋሙን ቅጥር ግቢ ለቀው በሄዱበት ወቅት የነበረውን ሁኔታም እንዲህ ገልጾታል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተማሪዎቹ እንዲመለሱ እና በጊዜያዊነት በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከመጥራቱ በፊት የክልሉ የሀይማኖት አባቶች፤ በዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ሀላፊነት ላይ ያሉ ዶክተሮች እና የተማሪ ህብረት ተወካዩች በከፍተኛ የትምህርት ተቋሙ በሚኖራቸው ቆይታ ከአንድ ክልል በመምጣታቸው ብቻ ምንም አይነት መጥፎ ነገር እንደማይደርስባቸው በመንገር አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር፡፡

ጥቅምት አንድ ትምህርት ከጀመረው ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት ተማሪዎች በጊዜያዊነት በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች እንዲማሩ መመደባቸው ሲነገራቸው ግን ብዙም አልቆየም፡፡ጥሪውን የተቀበሉት አብዛኞቹ ስለመሄዳቸው ተማሪ አንዷለም እኔ በግሌ ቅር ብሎኛል ሲል ምክንያቱንም አስረድቷል፡፡
‹‹አንድ ኢትዩጲያዊ እንደመሆናቸው ከአንድ ክልል በመምጣታቸው ምክንያት ብቻ ከእኛ ተለይተው ተነጥለው ሲሄዱ ይሰማናል፡፡ እንደ እኔ እምነት መሄድ አልነበረባቸውም፡፡ ይህ ዩኒቨርስቲ የኢትዩጲያ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ፌደራላዊ አወቃቀር ነው፡፡ እዚህ መማር ነበረባቸው፡፡ እዚህ ለየት ያለ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር፡፡ ግን አንድ ሰው እሄዳለሁ ካለ መብቱ ነው፡፡እዛም ሄደው ሰላማዊ የመማር ሂደት እንደቀጠሉና እንዳልቀጠሉ እናውቀዋለን፤ እየሰማን ነው እዛም ችግር እንዳለ፡፡›› የምህንድስና ተማሪው ስሜቱን የገለጸበት ቃላቶች ናቸው፡፡

ሌላው የጀግጅጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው እና የኢትዩጲያ ሶማሌ ክልል ተወላጅ የሆነው አህመድ መሀመድ የሶስተኛ አመት የግብርና ትምህርት ክፍል ተማሪ ሲሆነ በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ደህንነት የተጠበቀ መሆኑን በስፍራው ለተገኘው የጋዜጠኞች ቡድን ተናግሯል።በአሁን ወቅት በዩኒቨርስቲው እየተማሩ ያሉት ተማሪዎች የመጀመሪያው የትምህርት መንፈቅ አመት ተጠናቆ የማጠቃለያ ፈተና እየጠበቁ ነው።

የትምህርት ተቋሙን ለመማር ማስተማር ደህንነቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ኡመር አረጋግጠው ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ከዚህ ዩኒቨርስቲ ይውጡ የሚለውን አልደግፍም፥ ይህ ታሪካዊ ስህተት ነው ብለዋል።

የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀመድ ኡመር ታህሳስ 15ቀን በወቅታዊ ጉዳዩች ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ከክልሉ ዩኒቨርስቲዎች በጊዜያዊነት ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ርእሰ መስተዳደሩ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የአንዱን ባህል በማማር አንድነት ኢትዩጲያዊነት የሚፈጠርባቸው እና የሚጠናከርባቸው ቦታዎች ናቸው። ግን የሶማሌ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች በክልሉ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ የሚማሩ ከሆነ ይህ አይኖርም፡፡ ህብረ – ብሄራዊ ያልሆኑ ዩኒቨርስቲዎች ትውልዱን አንድነት አያስተምሩም:: ስለዚህ በዚህ ሁኔታ አላምንበትም ብለዋል፡፡

እኔ አንተ ማነህ ከተባልኩ መጀመሪያ ኢትዩጲያዊ ነኝ። የትኛው ብሄረሰብ ስባል ነው ሶማሌ የምለው ብለዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በጊዜያዊነት ክልሎቹ ሰላም እና መረጋጋት እስኪሰፍንባቸው ነው በሚል በሁለቱ ክልልሎች ዩኒቨርስቲዎች የነበሩትን እና ሌላ ዩኒቨርስቲዎች እየተማሩ ያሉትን ተማሪዎች መቼ እንዲመለሱ እንደሚያደርግ አላስታወቀም፡፡


Reader's opinions

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


[There are no radio stations in the database]