የሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት በም.ሃረርጌ በተፈፀመው ላይ ለዛሚ የሰጡት ቃለመጠይቅ አንኳር ነጥቦች

Written by on December 19, 2017

 

የሶማሌ ክልል ፕ/ት አቶ አብዲ ኡመር መሃመድ በምእራብ ሃረርጌ በተፈፀመው የጅምላ ግድያ ላይ ለዛሚ ሬድዮ የሰጡት ቃለመጠይቅ አንኳር ነጥቦች

(ቃል በቃል የተፃፈ አይደለም – ሙሉውን ለማድመጥ የድምፅ ፋይል ከታች ያገኛሉ)

 • እኛ እየተፈጠረ ያለውን የሰማነው ታህሳስ 6 ጠዋት ላይ ነው። ወድያውኑም ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጀምሮ የመከላከያ እና የኢህአዴግ አመራር እንዲያውቁ አድርገናል።
 • መከላከያ ከቦታው የ80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የነበረ ሲሆን በፍጥነት ቢንቀሳቀስም በመንገዱ ላይ ተደጋጋሚ የተኩስ ምልልስና የመንገድ መዝጋት እየገጠመው፣ የመንገድ ድልድይ ማፍረስና ጎማ የማያስኬድ የመንገድ መቃጠል ገጥሞት በእግር ጭምር ተጉዞ ለመድረስ አንድ ሰአት የሚፈጀውን መንገድ ሰባት ሰአት እንዲፈጅ ሆኗል።
 • የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከቦታው በ15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሃሩሪቲ እንደደረሰ በመስጊድ ተጠልለው የነበሩ 53 ሰወችን ተረክቧል። ሰወቹ ስለፈሩ ከመቆየት ከመከላከያ ጋር መጓዝን ስለመረጡ በለሊት ይዟቸው ለመጓዝ ተገዷል።
 • መከላከያ በቦታው ሲደርስ ከጭፍጨፋው አምልጦ የተረፈ አንድ ወጣት እንዳገኙና ከአካባቢው በተገኘ መረጃ በመመስረት የተገደሉት ሰወች የተወሰዱበትን ቦታ ፍለጋ አሰሳ እንደጀመረና ሁለት የጅምላ መቃብሮችን እንዳገኘ ተረድተናል።
  ጉርጓዶቹ ተቆፍረው ብዙ ሬሳ እንደተገኘባቸው ለፌዴራል ሪፖርት ተደርጎ በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራ ልኡካን ቡድን በሂሊኮፕተር ደርሰው እንዲያዩ ሆኗል። የልኡካን ቡድኑ ዋና አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ፣ ኮሚሽነር አብዩ አሰፋ፣ ከኦህዴድ ፅ/ቤት አቶ ብርሃኑ የተውጣጣ ቡድን ጥዋት በሂሊኮፕተር ደርሶ ሁኔታውን አረጋግጧል።
  ከሰአት ላይ ቴክኒካል ቡድን ሄዶ በጅምላ የተቀበሩትን ማውጣት ጀምሯል።
 • እስካሁን ባለን መረጃ በቦታው ከነበሩት ከ62ቱ 48 ሰው ተገኝቶ እንደወጣ ነው። በአካባቢው በተደረገ አሰሳም ሌላ 4 ቁስለኛ እንደተገኘ አውቀናል። ፍለጋው እንደቀጠለ ነው።
  እኛ ባለን መረጃ ቶምሳ የተባለ ቀበሌ 24 ሰው እንደተገደለ፣ ሁሉቆ 4 ሰው እንደተገደለ፣ ቆራቴ 18 ሰው እንደተገደለ ሲሆን
  መከላከያ የታደጋቸው ደግሞ በአሮሪቲ 53 ሰው፣ በሳውራ ቀበሌ 100 ሰው፣ በዳሩለማ 300 ሰው እንደሆኑ ነው። እነኚህ የተረፉት አንዳንድ ቦታ በመከላከያ ልዩ ጥረት ሲሆን በተጨማሪም የአካባቢው ህዝብ በቤቱ ደብቆ አቆይቶ ለመከላከያ በማስረከቡም ጭምር ነው።
  የተጣራ ይፋዊ መረጃውን የማጣራት ስራው ሲያልቅ ከፌዴራል መንግስት እንጠብቃለን።
  በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ የምግብና መጠጥ እጥረት ላይ ሲሆኑ ራሽን መንገድ ላይ መሆኑን ተረድተናል።
 • ይሄ ሁኔታ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የጅምላ ጭፍጨፋ ነው። የኦሮሚያ ፕ/ት ክቡር አቶ ለማ መገርሳም በተፈጠረው ማዘናቸውንና ድርጊቱ የኦሮሞን ህዝብ እንደማይወክል በሚድያ ተናግረዋል። ይሄ መልካም ነው።
  ባለፈው አወዳይ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ተፈፅሞ በክልሉም በፌዴራልም ይወገዝ ተብሎ ተስማምተን አልተፈጸመም። የአሁኑን የሚለየው ግን የክልሉ ፕሬዚደንትም ጠ/ሚኒስትሩም ሃዘናቸውን ገልፀዋል አውግዘዋል። ይሄ ለሱማሌም ለኢትዮጵያ ህዝብም መፅናናት ነው የሚሆነው።
 • ይሄ ለምን ተደረገ ለሚለው ጥያቄ መልሱ የፌዴራል ስርአቱን ለማፍረስና ኢትዮጲያዊነትን ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ትግል አካል ነው ነው የምለው።
  እነዚህ ሰወች ለምእተ አመት ያህል እዛ የኖሩ ሶማልኛ የማይናገሩ ቢሆኑም የአባት አባት ሱማሌ ነው በሚል ነው የተገደሉት። ይሄ ኦሮሚያንም የኢትዮጲያንም ህዝብ አይወክልም። ቢሆንም ሃቁን መናገር አለብን እንጂ መረጃ ማሳሳት የቁጥር ጨዋታ ጥሩ አይደለም ሁለቱንም ህዝብ አያቀራርብም።
 • እኛም ጉዳዩን ስንሰማ የኛ ብቻ አይደሉም የሞቱት ጉዳዩን ለኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ እንስጠው እንተወው ብለን ወስነናል።
 • ከአሁን በኋላ ወንጀለኞቹን ለህግ ለማቅረብ ጥረት ማድረግ እንጂ ሌላ ማለቂያ የሌለው ነገር ውስጥ መግባት አያስፈልግም ብለን ለህዝባችን ነግረናል።
  ባህር ማዶ ሆነው በሶሻል ሚድያ ሶማሊ ተጠቃ በሚል የማይገባ ነገር የሚቀሰቅሱትንም ሌላ ፖለቲካ አለውና ህዝባችን እንዳይሰማ እንመክራለን።
 • እጅግ ብዙ ኦሮሞዎች ሶማሊ ውስጥ እጅግ ብዙ ሶማሊዎች ኦሮሚያ ውስጥ ይኖራሉ። ይሄንን መለያየት የማይችል ህዝብ በጥቂቶች ስራ በመነሳት ነዳጅ መጨመር አያስፈልግም ብለን መክረን ምንም አይነት ምላሽ እንዳይኖር እየሰራን ነው።
 • በክልላችን ያሉ ኦሮሞዎች ከእኛ እኩል ነው ዜናውን የሰሙት። ምንም አያውቁም። ወንጀሉን የፈፀሙት እነሱንም አማክረው አይደለም ይሄን የሰሩት። በሁኔታው ያዘኑትም ከእኛ በላይ ነው። ድርጊቱ አይመለከታቸውም።
  የክልሉና የፌዴራል መንግስት በወሰዱት ጠንካራ አቋምም ይሄ ጉዳይ የኛ ሳይሆን የሃገር ጉዳይ ነው በሚል ህዝባችን ተረጋግቷል ክልላችንም ሰላም ነው።
 • ይሄ ተፈናቃዮችን በመመለስ ስራ ላይ ምን ኢምፓክት ይኖረዋል ለሚለው መልሴ እንደውም ይበልጥ ጠንክረን እንሰራለን የሚል ነው።
  ዛሬ ብዙ ኦሮሞ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ወደ ጅግጅጋ ተመልሰው ንግዳቸውን ተረክበው ስራ ጀምረዋል። ወደ ቤታቸውም እየተመለሱ ነው።
 • አሁንም ከክልላችን የተፈናቀሉ እንዲመለሱና ንብረታቸውንም እንዲረከቡ ለደህንነታቸውም እኛ ሃላፊነቱን እንደምንወስድ በማሳወቅ ኑ አብረን እንኑር ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ።
 • ለክልሉና ለፌዴራል መንግስት
  እኛ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ያደረጉትን መልእክት ሙሉ ለሙሉ ተቀብለናል እንዲሁም ጥፋተኛ ግለሰቦችና ከጀርባቸው ያሉት ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን።
  ፨፨፨፨፨፨፨፨፨
  የኦሮሚያ ፕሬዚደንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መልስ እንዲሰጡን ጥያቄ አቅርበን እየተጠባበቅን በመሆኑ መልስ እንዳገኘን ለአድማጮቻችን የምናቀርብ መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን።


Reader's opinions

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


[There are no radio stations in the database]